ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ በተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ውስጥ አልፋለች፡፡ በተለይም ዓለምን ጭንቅ ውስጥ ያስገባው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ማስከተሉ አልቀረም፡፡ የጤና ዘርፍ ደግሞ ከወረርሽኙ መከሰት በተጨማሪ በሰሜኑ ኢትዮጵያ ተፈጥሮ በነበረው ጦርነትና በሌሎች አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት እጅጉን ተፈትኗል፡፡
እነዚህን ችግሮች ተቋቁሞ ለማለፍ ብሎም ህብረተሰቡ የሚጠብቀውን አገልግሎት ሳይቆራረጥበት ለማግኘት ይችል ዘንድም በጤና ሚኒስቴር እንዲሁም በመንግስት በኩል የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት ልዩ ልዩ ተግባራትን ማከናወኑን አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩልም የኢትዮጵያ መንግስት ከሚሰራቸው ቀዳሚ ተግባራት መካከል የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ዜጎች ማድረስ አንደኛው ሲሆን በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስትም እያንዳንዱ ዜጋ የጤና አገልግሎት የማግኘት መብቱን በግልጽ ተጠቅሷል። ስለሆነም ዜጎች የጤና አገልግሎት በፍትኃዊነት የማግኘት መብት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ተካተዋል፡፡ ከዚህ አኳያ በአገራችን በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ዜጎች የጤና አገልግሎቶችን የማግኘት ሰብዓዊና ህገ መንግስታዊ መብቶች እንዳይስተጓጎሉ የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ከአለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለጤና አገልግሎት አስላፈጊ የሆኑ ድጋፎችን የማድረስ ተግበራትን አከናውኗል፣ እያከናወነም ይገኛል፡፡
በተለይም በጦርነት ምክንያት የተጎዱ የህከምና መስጫ ሆስፒታሎች ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም ጤና ኬላዎች በተቻለ መጠን ወደቀድሞ አገልግሎታቸው እንዲመለሱ ሰፋፊ ጥረቶች ተደርገው ውጤቶችም መጥተዋል። በሌላ በኩልም የህክምና መሳሪያዎችና መድሃኒቶች በተገቢው ሁኔታ ይሟሉ ዘንድ ከለጋሽ አካላት እንዲሁም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ድጋፎች ተሰብስበው አገልግሎታቸውን እንዲሰጡ ሆኗል ። አሁንም እነዚህ ተቋማት በሚገባ ተሟልተው የማስፋፊያ ስራ ሁሉ ተጨምሮባቸው አገልግሎታቸውን በተሻለ ሁኔታ ይሰጡ ዘንድ ለማስቻል ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛል፡፡
የጤና ተቋማት ለማቋቋምና መልሶ ሥራ ለማስጀመር ሁሉን-አቀፍ የድጋፍ ጥሪ ከቀረበም ዋል አደር ብሏል። ይህንን የድጋፍ ጥሪም በመቀበል አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ሆስፒታሎች ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ በመገኘት ሀኪም ቤቶቹን ለዳግም አገልግሎት የሚበቁበትንና ኅብረተሰቡም የተቋረጠውን አገልግሎት እንዲያገኝ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ መልሶ በመገንባት የጽዳት ስራ በመስራት መድሀኒትና የህከምና መሳሪያዎችን በማሟላት ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ማለት ይቻላል።
ስለጦርነት አውዳሚነት በየጊዜው ይነገራል፤ ይህ አውዳሚ ክስተት ደግሞ ወትሮውንም የተዳከመ የጤና አገልግሎት ባለባት ኢትዮጵያ ላይ ባሉ የጤና ተቋማት ላይ ሲሆን ችግሩን ግዙፍ ያደርገዋል። ለኅብረተሰቡ የጤና አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ላይ የሚደርስ ጉዳት፣ ውድመት ደግሞ በቀላሉ ሊፈታ ሊስተካከል የሚችልም ላይሆን ይችላል።
ከዚህ አንጻር በጦርነቱ ምክንያት በጣም ብዙ ሆስፒታሎች እና የጤና ተቋማት ጉዳት ደርሶባቸዋል። እነሱን ሥራ ለማስጀመር የጤና ሚኒስቴር ለተለያዩ ሆስፒታሎች ኃላፊነት እየሰጠ ሲሆን ሁሉም ሆስፒታሎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት የጤና ተቋማቱን ወደነበሩበት ከመመለስ ጀምሮ ቀድሞ ከነበሩበት አንድ ደረጃ ከፍ ብለው አገልግሎት መስጠት እስከሚችሉበት ደረጃ ድረስ ያደረሱም ስለመኖራቸው ይነገራል።
ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ ወሎ ሐይቅ ከተማ የተጓዘው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የባለሙያዎች ቡድን በሆስፒታሉ አስፈላጊውን የጽዳት እና የማስተካከል ሥራ ካከናወነ በኋላ ዳግም ወደ ቀድሞ አገልግሎቱ እንዲገባ ለማድረግ ችሏል። በዚህም የድንገተኛ ክፍል፣ የተመላላሽ ህክምና ክፍል፣ የማዋለድ አገልግሎት እንዲሁም የአስቸኳይ ቀዶ ህክምና፣ የላቦራቶሪ እና የመድኃኒት ቤት አገልግሎቶች በሆስፒታሉ ለመጀመርም ተችሏል ።
ይህ የመልሶ ማቋቋም እርዳታ ሲደረግ ሆስፒታሎቹ ወደቀደመ አገልግሎታቸው ከመመለሳቸውም በላይ ባለሙያዎቹም ወደስራ ገበታቸው ተመልሰው ለህብረተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ የማድረግ ስራንም እንዲጀምሩ ማስቻሉ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
በጦርነቱ ጉዳት ወደ ደረሰባቸው የተለያዩ ከተሞች ሀኪም ቤቶች እና የጤና ተቋማት ለተመሳሳይ ሥራ የተሰማሩ የየሆስፒታሉ ቡድኖችም በተሠማሩባቸው አካባቢዎች ሆነ በሌሎች ቦታዎች የተለያዩ የሆስፒታል ኃላፊዎች ከህክምና ቡድኖቻቸው ጋር ለመልሶ ግንባታው መሰማራታቸው ውጤታማ ስራን ለመስራትም አስችሏል።
የተፈጸመውን ብቻ ከመናገር ተባብሮ ለማስተካከል ጊዜ መባከን የለበትም ለዚህም ነው መንግስት በተለያዩ ምክንያቶች ከውጭ ወደ አገር ቤት የሚመጡ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች በህክምና ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት ተገንዝበው የበኩላቸውን ለመደገፍ እንዲችሉም ሁኔታዎች ሲያመቻች የቆየው። በዚህም በርካታ ዜጎች እንዲሁም ወዳጆቻችን የተለያዩ የህክምና። የጽዳት እቃዎችን። መድሃኒት እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በሙሉ ይዘው በመምጣት አጋርነታቸውን ያሳዩት።
በተመሳሳይ ዘርፉን ከገባበት ችግር ለማውጣት መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር ድርጅቶች በስራው ላይ ለመሳተፍ ወደኋላ አላሉም ። ከብዙዎቹ መካከል ፓዝ ፋይንደር የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ለአማራ ክልል ጤና ቢሮ 79 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የህክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉም የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የገዛቸውን የህክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች ችግር ለደረሰባቸው ሆስፒታሎች ጤና ኬላዎችና ጤና ጣቢያዎች መልሶ ግንባታ ይውል ዘንድም ማበርከቱ በወቅቱ የተነገረ ነበር።
ይህ ድጋፍም ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ከበፊቱ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል መልሶ የማቋቋም ስራ እየተሰራበት ሲሆን በህክምና መሳሪያ፣ በመድሃኒትና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዲሁም በሰው ሀይል መልሶ በማደራጀት በተለይም የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር አስተዋጾ ያለው መሆኑም እሙን ነው።
በጦርነቱ ወቅት በህክምና እጦት በእናቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰው ሞት፣ በንጹሃን ላይ የሚደርስ የስነ ልቦና፣ የአካልና የአእምሮ ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የሁሉንም አካላት ርብርብ የሚጠበቅ መሆኑን አሁንም አያጠያይቅም። የወደሙ የጤና ተቋማትን በፊት አገልግሎት ይሰጡበት ከነበረው በተሻለ ለህብረተሰቡ እንዲያገለግሉ ለማስቻል እየተደረገ ባለው ጥረት ሁሉም በሚችለው የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም የሚያስገድዱ ናቸው።
ባለፈው ሳምንትም የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ በጦርነትና ግጭት በተጎዱ አካባቢዎች የጤና ተቋማትን ጠግኖ አገልግሎት ለማስጀመር የሚውል የ 31ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ማድረጉ ተጠቃሽ ነው።
ኅብረቱ የገንዘብ ድጋፉ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነትና በሌሎች ግጭቶች ለተጎዱ ሴቶችና ሕጻናት ማገገሚያ እንዲውል የሰጠው ለተመድ የሕጻናት ድርጅት (ዩኒሴፍ) ነው። ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ከ 3 ሺ በላይ ጤና ተቋማት እንደወደሙ ወይም ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚታወቅ ሲሆን እነዚህ ተቋማት ለዳግም አገልግሎት ይበቁ ዘንድ ብሎም ህብረተሰቡ ተገቢውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻልም ድጋፉ ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን በድጋፍ አሰጣጡ ወቅት ተገልጿል ።
ገንዘቡ በተለይ በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በሴቶችና ሕጻናት በተቀረጹ ፕሮጀክቶች ላይ የሚውል መሆኑ ደግሞ እንደ አገር የተያዘውን የጤና ዘርፍ የማጠናከር ላቅ ወዳለ ደረጃ የማድረስ ስራ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያግዝ ስለመሆኑም ጥርጥር የለውም።
በእርዳታ አሰጣጡ ወቅት በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ አምባሳደር ሮላንድ ኮያ እንዳሉት ጦርነቱ በጤና አገልግሎት አሰጣጣ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል። አሁን በተገኘው የሰላም ስምምነት አማካይነት ደግሞ የተጎዱ ሆስፒታሎችን ለዳግም አገልግሎት ለማዘጋጀት ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ ድጋፉ ሆስፒታሎቹን ለዳግም አገልግሎት ለማብቃት ብሎም ከነበሩበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚውል ሲሆን በተለይም ሴቶችና ህጻናትን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የጤና ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንደሚውልም ጨምረው ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው ህብረቱ ለጤናው ዘርፍ ያደረገው ድጋፍ ወቅቱን የዋጀ አጅግ በጣም አስፈላጊ በሆነበት ሰዓት የመጣ በመሆኑ የጤናውን ሴክተር ዳግም ወደስራ ለማስገባት እንደሚውልም ነው ያብራሩት።
እንደ ዶክተር ደረጄ ገለጻ ድጋፉ በጦርነት የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለከፍተኛ የስነ ልቦና የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍ ብሎም ሴቶችና ህጻናት ተገቢውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ሽፋኑን ለማስፋት እንደሚውል ተናግረዋል።
አዎ እንደ አገር ከገባንበት ችግር ሊያወጣን የሚችለው ይህ መሰሉ ድፍጋፍና አብሮ የመቆም ሁኔታ ነው። እንደ ዜጋም ሆነ አጋሮቻችን በዚህ መልኩ የሚያደርጉልን ድጋፍ ደግሞ የጤናውን ዘርፍ ከገባበት ችግር ለማውጣት ብቻ ሳይሆን ዘርፉ ከነበረበት ደረጃም ከፍ ለማድረግ የሚኖረው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/ 2015 ዓ.ም