የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እየጨመረ የመጣውን የሲሚንቶ ምርት ዋጋ ለማስተካከል በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሚሆን አዲስ የዋጋ ተመን ማውጣቱን ከወራት በፊት አስታውቆ ነበር። የዋጋ ተመኑ የወጣው በግብይት ሰንሰለቱ ወጥ የሆነ የንግድ ስርዓት እንዲኖር ታስቦ ሲሆን፣ ይህም ከመስከረም 5 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ወራት የሚቆይ መሆኑ በወቅቱ ተነግሯል።
አዲስ በወጣው የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ መሰረት አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዝቅተኛ ዋጋ 510 ብር ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 683 ብር ከ44 ሳንቲም ሆኖ መወሰኑም ይታወቃል። ይሁንና የወጣው የዋጋ ተመን ከነበረው ዋጋ በኩንታል በአማካይ 92 ብር ዝቅ የሚያደርገው በመሆኑ የሲሚንቶ አምራቾች ሚኒስቴሩ ያወጣውን ሲሚንቶ የፋብሪካ መሸጫ ዋጋ ውሳኔ ተቃውሞ ማሰማታቸው ይታወሳል።
መንግስት በሲሚንቶ አቅርቦትና ዋጋ ላይ ያለውን ችግር ለመቆጣጠርና በተለያየ ጊዜ የተለያየ መፍትሄ ለማስቀመጥ ቢጥርም እስካሁን የሲሚንቶ ዋጋ ሊረጋጋ አልቻለም። እንዳውም ከገበያ ላይ በመጥፈት የኮንትሮባንድ ንግድ ጭምር ሆኗል። የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋም ከአንድ ሺህ ስምንት መቶ እስከ ሁለት ሺህ ብር ድረስ በድብቅ የሚቸበቸብበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይሄ ለምን ሆነ ቀጣይ ገበያውን ለማረጋጋት መፍትሄ መሆን ያለበት ምንድነው በሚሉ እና ከዚህ ጋር ተያያዢ በሆኑት ጉዳዮች ዙሪያ ያነጋገርናቸው የቢዚነስ ባለሙያ ኢንጂነር ደሳለኝ ከበደ እንደሚናገሩት፤ የአገራችን ሲሚንቶ ችግር አሁን የመጣ አይደለም። ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ያለ እና እየተንከባለለ እዚህ የደረሰ ነው። ለዚህ አንዱ ምክንያት ላለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት አዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እየተገነቡ አይደለም፤ ፋብሪካዎች አለመቋቋማቸው አንዱ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም እንዲፈጠር ሰበብ ሆኗል።
የአገራችን የህዝብ ቁጥር እየጨመረ በመጣ ቁጥር ቤት ሰሪውም የዚያኑ ያህል እየጨመረ መጥቷል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የመንግስትም ፕሮጀክቶች እየጨመሩ መጥተዋል። ስለዚህ ይህ ሁሉ ተጠራቅሞ የሲሚንቶ እጥረት እንዲፈጠር እያደረገ ነው። ይህም ሆኖ ችግሩ በአንድ ጊዜ የመጣ አይደለም ሲሉ ይናገራሉ።
ዋናው የእጥረቱ ምክንያት የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ሲሆን ፍላጎትን ያጣጣመ የሲሚንቶ ምርት ወደ ገበያ እንዲገባ አለመደረጉ ነው። አሁን ባለው የኮንስትራክሽን ሂደት ባሉት ፋብሪካዎች ብቻ ፍላጎትን ማሟላት አዳጋች ነው። በቀጣይ አዳዲስ ፋብሪካዎች የማይቋቋሙ ካልሆነ መፍትሄ ማምጣትም አይቻልም ሲሉ ያስረዳሉ።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ከዚህ ሌላ ያሉት ፋብሪካዎች ከመቆየታቸው የተነሳ በዛው ልክ ምርታማነታቸው እየቀነሰ ይሄዳል። ያሉትም ፋብሪካዎች ማስፋፊያዎችን ሲሰሩ አይታዩም። ይህ በራሱ የሚፈለገውን ያህል ምርት ተመርቶ ለገበያ እንዳይቀርብ ስለሚያደርገው የሲሚንቶ እጥረት እንዲፈጠር ያደርጋል።
ኢንጂነር ደሳለኝ እንዳሉት ፣ ሌላው ለሲሚንቶ ምርት እጥረት ምክንያት ከተባለው ውስጥ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያህል በአገራችን የተፈጠረው ጦርነት ነው ይላሉ፤ ለአብነትም መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ የማምረት አቅሙ ትልቅ ነው። ስለዚህ የዚህ ፋብሪካ አለማምረት የሚፈጥረው ክፍተት አለ። ሌላው ደግሞ በተለያየ ምክንያት አንዳንድ የሰላም መደፍርስ በሚኖርበት አካባቢ ፋብሪካዎች ሀብታቸውን በአግባቡ መጠቀም አልቻሉም። ከዚህ የተነሳ ምርታማነታቸው ይቀንሳል። የእነዚህ ድምር ውጤት ለሲሚንቶ እጥረት ምክንያት እንደሚሆን ያመለክታሉ።
ከዚህ የተነሳ መንግስት ለሲሚንቶ እጥረት የተለያየ መፍትሔዎችን ሲሰጥ እናያለን። የሚሰጠው መፍትሄ ከተፈጠረው ችግር አንጻር የሚጠበቅ ነው። ይሁን እንጂ መፍትሔዎቹ አለመስራታቸው የሚታወቀው በየጊዜው አዳዲስ መፍትሔ በማምጣታቸው ነው። ሁሌ አዳዲስ መፍትሔ የምንሰማ ከሆነ የመጀመሪያው መፍትሔ አልሰራም ማለት ነው ይላሉ።
መንግስት መፍትሔ ብሎ አምጥቶ ያልሰራ ነው ያሉትን ኢንጂነር ደሳለኝ ሲጠቅሱ፤ አንዱ የሲሚንቶ ምርት በውስን ኤጀንቶች እንዲከፋፈል መደረጉን ነው። ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ሸማቾች ከፋብሪካ በር ላይ እንዲገዙ የሚል ነው ፤ እሱም እንዲሁ መስራት አልቻለም። ከዚያም ቀጥሎ የቅዳሜና እሁድ ገበያ ተባለ፤ እሱም እንደተፈለገው ያህል መስራት አልቻለም በማለት ያስረዳሉ።
አሁን ደግሞ ቸርቻሪዎቹ ከገበያ ወጥተው በጅንአድ በኩል ማለትም በመንግስት አካላት በኩል እንዲከፋፈል ተደረገ፤ ይኸኛውም እየሰራ አይደለም የሚል እምነት አላቸው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አንደኛ ብዙ ፕሮጀክቶች ቆመዋል። ሁለተኛ ደግሞ ሲሚንቶ የሚከፋፈልበት መንገድ ለምሳሌ 15 ኩንታል ይሰጣሉ፤ ይህ የሚሰጠው አንድ ሰው እንዳለው የቤተሰብ ብዛት ነው፤ ይህ መሆን የለበትም፤ አንድ ሰው በሚሰራው ፕሮጀክት ልክ እንጂ በቤተሰብ ልክ መሆን አልነበረበትም።
ለምሳሌ የወጣው መስፈርት በቤተሰብ ደረጃ 15 ኩንታል ይላል፤ ይህ አግባብ አይደለም። ምክንያቱም ትንሽዬ ቤትም የሚሰራ 15 ኩንታል ትልቅ ፕሮጀክትም የሚሰራ 15 ኩንታል መሆን አልነበረበትም። ይህ አይነት አሰራር በሙያ የተደገፈ ቢሆንና የሚሰራውንም ፕሮጀክት አገራዊ ፋይዳ ከግምት ውስጥ የሚያስገባ ቢሆን መልካም ነበር። በአሁኑ ወቅት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተለይ በከተማ አካባቢ ያሉ ቆመዋል ማለት እንደሚያስደፍርም ነው ያስረዱት።
የሲሚንቶ የዋጋ ተመን መውጣቱ ይታወቃል፤ የዋጋ ተመኑ ለአንድ ወገን ብቻ ነው መፍትሔ የሚሆነው፤ አምራቾችን ከተቀመጠው ዋጋ በላይ አትሽጡ የሚል ነው። ነገር ግን እንደዛ ይቀርባል ወይ የሚለው በራሱ አጠያያቂ ነው ሲሉ ይናገራሉ። ለምሳሌ የሲሚንቶ ዋጋ ገበያ ላይ ሱቆቹ ባይኖሩም በኮንትሮባንድ አንድ ኩንታል እስከ 1 ሺ 500 እና 1 ሺ 600 ብር በድለላ እየተሸጡ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ወይዘሮ ሳራ መኮንን የኬቲ ሮብሰን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ማርኬቲንግ ኦፊሰር ሲሆኑ፣ ድርጅታቸው ከሚሰራቸው ተግባራት አንዱ ማዕድን ላይ መሆኑን ይናገራሉ። በቅርቡ በማዕድን ሚኒስቴር አመቻችነት በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው ኤክስፖ ድርጅቱ ይዞ የቀረበውም የድንጋይ ከሰል ነው። የድንጋይ ከሰሉን በአገር ውስጥ ላሉ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚያቀርቡ ሲሆን፣ እስካሁንም ለዳንጎቴ፣ ለሙገርና ለሀበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማቅረብ መቻሉንም ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንዳሉት፤ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ የሚያቀርቡት የድንጋይ ከሰል አንዋሽ ነው፤ ምርቱንም የሚያገኙት ከአርጆና ከካማሼ ነው፤ በቀጣይ ግን እሴት ጨምረው ለማቅረብና የራሳቸው የማጣሪያ ፋብሪካውም እንዲኖራቸው በመስራት ላይ ይገኛሉ። አገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት እንደመሆኗ በቀጣይ ለፋብሪካዎቹ የተሟላ የድንጋይ ከሰል ለማቅረብ ዝግጁ ናቸው። በአገራችን ደረጃ የድንጋይ ከሰል ፍላጎት ከፍ ያለ ነው። በአሁኑ ወቅት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚፈልጉት ደረጃውን የጠበቀ የድንጋይ ከሰል ነው።
ከሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ የጥራት ቁጥጥር ክፍል ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ለሲሚንቶ ምርት ዋና ግብዓት የሚባሉት የኖራ ድንጋይ፣ የሸክላ አፈርና የአሸዋ ድንጋይ ናቸው። የድንጋይ ከሰል ደግሞ በማቃጠያነት የሚያገለግል ነው። የከሰል ድንጋይ የማይገኝ ከሆነ ደግሞ ከባድ ጥቁር ናፍጣ የሚባለውን ለማቃጠያነት የሚያገለግል ይሆናል። አሁን ላይ የሙገር ፋብሪካ እየተጠቀመ ያለው የድንጋይ ከሰልን ነው።
በፋብሪካው በኩል በግብዓትነት የሚጠቀመው የኖራ ድንጋይ፣ የሸክላ አፈርና የአሸዋ ድንጋይ እጥረት የለም። አንድ የሲሚንቶ ፋብሪካ በመጀመሪያም ቢሆን የሚቋቋመው ሶስቱ ግብዓት በፋብሪካው አካባቢ በትክክልና በብዛት መኖሩ ሲረጋገጥ ነው።
ሙገር እስከ 80 በመቶ የአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ከሁለት ዓመት ወዲህ መጠቀም የጀመረ ሲሆን፣ ከሃያ እስከ አርባ በመቶ አካባቢ ደግሞ ከውጭ የሚያስገባ መሆኑን መረጃ ያመለክታል። ነገር ግን የውጭ ምንዛሬ ችግር እንደዚህ እንደ አሁኑ በሚኖርበት ጊዜ የሚበረታታው የአገር ውስጡን መጠቀም ነው። ይሁንና በአገር ደረጃ የማጣሪያ ፋብሪካውም ገና ስላልተከፈተ በጅምርና በማስተዋወቅ ደረጃ ላይ ናቸው ይላል። እንደመረጃው ከሆነ፤ የድንጋይ ከሰል አቅራቢዎች ባቀረቡት ልክ ሙገር መቀበል ይችላል፤ እጥረቱም ጥራቱም ሲኖር ደግሞ ከውጭ ያስገባል። በአገራችን ነዳጅ በጨመረ ቁጥር የድንጋይ ከሰሉን ዋጋ ይጨምራል።
ከሙገር የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ለሲሚንቶ እጥረት የሚለው ለሲሚንቶ ማምረቻ ከፍተኛ የሆኑ ማሽነሪ ያስፈልጋል። ማሽኖችን ወደአገር ውስጥ ለማስገባት ደግሞ የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል። የውጭ ምንዛሬ ባጋጠመ ቁጥር ደግሞ ትልቁ ተጎጂ የሚሆኑት አምራች ፋብሪካዎች ናቸው። ምንም እንኳ ፋብሪካዎቹ ቀደም ተብለው የተቋቋሙ ቢሆኑም መለዋወጫ ስለሚፈልጉ ነው። ሌላው ደግሞ ሲሚንቶ ገበያ ላይ እንዲያጥር ከሚያደርገው መካከል ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ያለመስራት ችግር ነው።
ለሲሚንቶ እጥረትና ለዋጋው መወደድ የተለያዩ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል። ሆኖም ግን መፍትሄው ምን መሆን አለበት በሚል ለተነሳው ሀሳብ ኢንጂነር ደሳለኝ ይህን ብለዋል፣ ‹‹እንደመፍትሔ የሚታየኝ ፋብሪካዎቹን ማበረታታትና በተቻለ መጠን ብዙ እንዲያመርቱ ማድረግ ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም ፋብሪካዎቹ ማስፋፊያ እንዲያደርጉ ማበረታታት ይጠቅማል። ከዚህ ውጭ ግን መፍትሄ ተብሎ የተቀመጠው የዋጋ ተመን ማውጣት ትክክለኛ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም ››ብለዋል።
ሲሚንቶ በግብዓት እጥረት ምክንያት ሊቆም የሚችል ምርት አይደለም፤ ምክንያቱ ግብዓቱ ሁሉም እዚህ ከመሆኑ በተጨማሪ በበቂ ሁኔታ ምርቱ መኖሩ ተረጋግጦ እዛው ግብዓቱ ባለበት አካባቢ የሚቋቋም ስለሆነ በዚህ ስጋት አይኖርም፤ ነገር ግን ማቀጣጠያ የሚሆነው የድንጋይ ከሰል ወይም ጥቁር ከባድ ነዳጅን መንግስት ከውጭ ከማምጣቱ በስተቀር ሌላው በሀገር ውስጥ አለ ሲሉ ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንዳብራሩት፤ የሲሚንቶ እጥረቱን ለመቀነስ መፍትሔው ፋብሪካዎች እንዲበረታቱና እንዲስፋፉ ማድረግ ነው። ለምሳሌ የዛሬ 10 ዓመት አካባቢ የሲሚንቶ ችግር እንዲፈታ ተብለው የተተከሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ነበሩ። በስድስት ወር ውስጥ አነስተኛ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ሊተከሉ ይችላሉ፤ ለምሳሌ ደጀን በዚያን ጊዜ ችግሩን ለመቋቋም ተብሎ ሁለት የዳንጎቴ የመጀመሪያዎቹ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ተተክለው ነበር፤ አሁን ይህ ችግር እያለ እንኳን አገልግሎት የሚሰጡ አይደሉም፤ ቆመዋል። ከዚህ ሌላ ሙከ ጡሪ አካባቢም እንዲሁም ቆቃ አካባቢም አለ፤ እነዚህ አነስተኛ ፋብሪካዎች ናቸው፤ አሁን ግን አይሰሩም፤ ቆመዋል። ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ባላውቅም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እነዚህ አነስተኛ የሆኑ ፋብሪካዎች እንዲሰሩ ቢደረግ ፤ እንዲሁም እንደእነሱ አይነት አነስተኛ የሆኑ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በየቦታው ቢኖሩ ሲሚንቶን ከአንዱ ወደሌላ ቦታ ከማጓጓዝም ጭምር የሚያድኑ ይሆኑ ነበር።
ሌላ መፍትሔ ነው ብለው የተናገሩት፤ ለምሳሌ ኮንክሪት የተባለውን አርማታ ለመሙላት ሰው በየቦታው ጠጠር ዘርግፎ አሸዋ እያደረገ ነው የሚያመርተው፤ ነገር ግን ኮንክሪት (አርማታ) የሚያምርቱና የሚሸጡ ድርጅቶች አሉ። እነሱ በተፈለገ ሰዓት ማምጣት ይችላሉና አንድ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሚንቶን የግድ መግዛት አይጠበቅበትም፤ ስለዚህ ይህንንም አማራጭ ማየቱ ተገቢ ነው። ሰሞኑን እንዲያውም የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ባለድርሻዎችን በማሰባሰብ እነርሱን ሲያበረታታ ነበር። እነርሱን ማበረታት ከኮንትሮባንድ ያድናል።
አሁን ያሉት ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ ነው ማለት አንችልም፤ ምክንያቱም ለምሳሌ ሙገር ለተወሰነ ጊዜ እያመረተ የነበረው በጣም በጥቂቱ ነበር። ጥሬ እቃውን የሚያገኝበት ቦታ ስላልነበር ከዛ ጋር በተያያዘ ችግር ነበር፤ ነገር ግን ሰላሙ ሲመለስ ወደማምረት ገብቷል። ይሁንና ችግሩ ሲሚንቶ ፈላጊው ብዙ በመሆኑ አሁንም ቢሆን በተፈለገው ልክ ማግኘት እየተቻለ አይደለም ብለዋል።
የመጨረሻ መፍትሄ ነው የምለው ይላሉ ኢንጂነሩ፣ ብዙ ሲሚንቶ ማምረት ነው። ያሉት ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ላይ ብቻ ከተወሰንን ምርት አይኖረንም፤ ስለዚህ በአገራችን ትልልቅ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ሊኖሩን የግድ ነው። አሁን መሰረት የተጣለባቸው የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አሉ። ለምሳሌ አንድ ድሬዳዋ ሌላው ለሚ አካባቢም የናሽናል ሲሚንቶ ተጀምሯል። ይህኛው የሶስት ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ያህል ሊያመርት የሚችል ነው።
መንግስት ለግብርናው በተለይም ለስንዴ ትኩረት እንደተሰጠው ሁሉ ብዙ ሲሚንቶ እንዲመረት ለዘርፉ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። ባለሀብቶችን እየደገፉ ወደማምረት እንዲመጡ ማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ ያግዛል። አሁን በመንግስት የተቀመጠው የዋጋ ተመን ብቻውን መፍትሄ አይሆንም። ስለዚህ ጎን ለጎን ስራዎች መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 6/ 2015 ዓ.ም