ዘንድሮ ለ22ኛ ጊዜ የሚካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ብቻ ይቀሩታል። በየዓመቱ ከ10 በላይ ውድድሮችን የሚያካሂደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፤ የውድድር ዕድልን ከመፍጠር ባለፈ ታዋቂ አትሌቶችን፣ የውጭ ዜጎችንና ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት እየሳበ ይገኛል። ይህ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ከስፖርታዊ ኩነትነቱ ባሻገር የሀገርን መልካም ገጽታ ከመገንባት አንጻር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተም ነው።
በአፍሪካ በትልቅነቱ ቀዳሚ የሆነውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅ ከሆኑ ምርጥ 10 የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች አንዱ የሆነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫ ማህበር አባልም ነው። በ10ሺ ተሳታፊዎች የተጀመረው ይህ ውድድር በአሁኑ ወቅት 40ሺ ተሳታፊዎችን ለማግኘት ችሏል። ይህ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚካሄዱ ትልልቅ የማራቶንና ሌሎች የጎዳና ላይ ውድድሮች ጋር ተፎካካሪ አድርጎታል። ይህም ኢትዮጵያውያን ታዋቂ አትሌቶች እንዲሁም የሌሎች አገራት ዝነኛ ሯጮች በተጋባዥነት በውድድሩ ላይ እንዲካፈሉ አስችሏል። በዚህም ምክንያት ውድድሩ ይበልጥ ትኩረት እያገኘ ከመምጣቱ ባለፈ በስፖርት ቱሪዝምን ከማስፋፋት አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ውድድሩ ሲካሄድ የክብር እንግዳ በመሆን ኬንያዊቷ አትሌት ፔሬስ ጄፕቺርችር አዲስ አበባ እንደምትገኝ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሳውቋል። የ29 አመቷ ፔሬስ እአአ በ2021 የኒውዮርክ ማራቶንን እና የቶኪዮ ኦሊምፒክ የማራቶን ቻምፒዮን የሆነች አትሌት ናት። በዚህ ዓመት ደግሞ በግሩም ብቃት የቦስተን ማራቶንን አሸንፋለች። ፔሬስ እአአ የ2016 እና የ2020 የሁለት ጊዜ የዓለም ግማሽ ማራቶን አሸናፊም ናት፤ ፈጣን የማራቶን ሰዓቷ የሆነውን 2 ሰዓት ከ17 ደቂቃ ከ16 ሰከንድም ከሁለት ዓመት በፊት ነበር በቫሌንሲያ ማራቶን ያስመዘገበችው።
አትሌቷ ከታዋቂ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጋርም በመፎካከር የምትታወቅ ሲሆን፤ አብራቸው በውድድር ላይ ከተሳተፈቻቸው አትሌቶች ውስጥ ያለምዘርፍ የኋላው፤ ደጊቱ አዝመራው፤ ነፃነት ጉደታ እና ዘይነባ ይመር ተጠቃሽ ናቸው። ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ የመጀመሪያዋ የሚሆነው ፔሬስ ውድድሩ ከመካሄዱ አንድ ቀን አስቀድማ ከባለቤቷ እና ልጇ ጋር በመምጣት እስከ ውድድሩ ቀን የምትቆይም ይሆናል።
ከፔሬስ ጄፕቺርችር ባለፈ ከኬንያ በዘንድሮው ውድድር ለመሳተፍ ከኬንያ የሚመጡ አትሌቶች መኖራቸውንም ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። ከእነዚህም መካከል ከአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ጋር እአአ በ1993 የስቱትጋርት የዓለም ቻምፒዮና ላይ ታሪካዊ የ10ሺ ሜትር ውድድር ያደረገው ኬንያዊው አትሌት ሞሰስ ታኑይም የሚገኝ ይሆናል። ሞሰስ ታኑይ የኤልዶሬት ከተማ ማራቶን ውድድር ዋና አዘጋጅ መሆኑ ይታወቃል። በተጨማሪም ከተለያዩ የኬንያ መገናኛ ብዙሃን የሚመጡ ጋዜጠኞችም እንደሚኖሩ ይጠበቃል።
በአካል በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ተገኝተው ከሚሮጡት ባለፈም ባሉበት አገር ሆነው በኢንተርኔት አማካይነት በሩጫው ላይ የሚሳተፉ የውጭ አገር ሯጮች መኖራቸውም አገርን በበጎ ከማስተዋወቅ ረገድ የሚኖረው ድርሻ ቀላል የሚባል አይደለም። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለአትሌቶች የውድድር መድረክን የሚፈጥር ከመሆኑ ባለፈ በርካታ አትሌቶች ከዚህ ውድድር በመነሳት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ሊሆኑ ችለዋል። ታዋቂና በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሆኑ እንደ እነ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣… የመሳሰሉ አትሌቶችም ከዚህ ቀደም በውድድሩ ተካፍለዋል።
ከጊዜ ወደጊዜ በዚህ ውድድር ላይ በርካታ አትሌቶች ተካፋይ እየሆኑ ሲሆን፤ ቁጥሩን ከመቀነስና ጥራቱን ከመጠበቅ አንጻር አስቀድሞ የማጣሪያ ውድድር ተካሂዷል። ለተሳታፊዎችም በተለያዩ ጊዜያት የልምምድና የስልጠና መርሃ ግብሮች ተካሂደዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኀዳር 5 ቀን 2015 ዓ.ም