በደቡብ አፍሪካ የሰሜኑ ጦርነት በሠላም መቋጨት የሚያስችል የሠላም ሥምምነት ተፈርሟል። ያውም በአፍሪካውያን አደራዳሪዎች (ድርድሩን ከአፍሪካ እጅ ለማስወጣት ብዙ ጥረት ቢደረግም፤ አፍሪካዊ ሃሳብ ማሸነፍ ችሏል)። ይህም ስምምነት በብዙ መልኩ ታሪካዊ ያደርገዋል፤ በተለይ ለኢትዮጵያውያን።
በእርግጥም የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ የጦርነት የታሪክ ምዕራፎችን አልፏል። በነዚህ የታሪክ ምዕራፎች ያለፈ ሕዝብ የሠላም አማራጮች ቀርበውለት ተራምዶ ይሄዳል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። የሆነውም ይኸው ነው። እውነተኛ ሠላምን የመሻቱ ፍላጎት ሲመጣ ለመቀበል አሻፈረኝ አላለም።
የኢትዮጵያ መንግሥትም የሕዝቡን ፍላጎት ባዳመጠ መንገድ በደቡብ አፍሪካ ለሰላም ድርድር ወንበር ስቧል። የአገርን ሉዓላዊነት ያከበረ ሥምምነት ፈርሟል። የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያዊነት መልክ የሆነው የትግራይ ሕዝብ አንገቱን ቀና እንዲያደርግ ያለውን ፍላጎት በተግባር አረጋግጧል።
ስምምነቱን ተከትሎ በአገሪቱ አራቱም ማዕዘናት ስለስምምነቱ የታየው እና እየተሰማ ያለው እውነታ፤ ሕዝባችን ስለሰላም ያለውን የጸና እምነት ከማሳየት ባለፈ ጦርነት የቱን ያህል አውዳሚ እንደሆነ መገንዘብ መቻሉን በተጨባጭ ያመላከተ ነው። ሠላም ሲመጣ አየሩን የደስታ መንፈስ መሙላቱም የሠላም ዋጋን ጠንቅቆ ከሚያውቅ ሕዝብ የሚጠበቅ ነው ፤ ያዝልቅልን እንጂ !።
ስምምነቱን ወደ ተሟላ እርቅ ለመቀየር በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው ውይይት እንደቀጠለ ነው። የሕወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት ሂደቱን (በሰላም ስምምነቱ የተደረሰበትን) ለማሳለጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የትግራይ ታጣቂዎች አዛዦች ናይሮቢ ላይ ተገናኝተው እየተወያዩ ነው።
ውይይቱን አስመልክተው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፤ «ፕሪቶሪያ ጀምረናል፤ እየተጠጋን እንገኛለን፤ እናም አሁን ናይሮቢ ነን። በሚቀጥለው ጊዜ መቀሌ ተገኝተን ለስብሰባችን ማሳረጊያ አዲስ አበባ ላይ አብረን እንደምንደሰት ትልቅ ተስፋ አለን። ጸሎት እና ተስፋችን ይህ እንዲሆን ነው» ሲሉ፤ የሰላም ድርድሩ ከስምምነት ተሻግሮ ወደመሬት እየወረደ መሆኑን ጠቁመውናል።
የኡሁሩ ንግግር የሰላም ስምምነቱ በሚፈለገው መልኩ እየሄደ ከመሆኑ ባሻገር በተጨባጭ ከጦርነት አዙሪት የምንወጣበት ጊዜ ሩቅ አለመሆኑን አመላክቶናል፤ ያድርግልን!። በምድራችን ዛሬ እንዲነግስ የምንሻው ሠላም ፋይዳው ተሻጋሪ፤ ለልጆቻችን ነገ የምናወርሳትን አገራዊ ቁመና የሚወስን ነውና።
ለመጪው ትውልድ ልናወርሳት የምንፈልጋት አገር በጦርነት የጥላቻ አዳፋ የጠቆረች ሳይሆን በአብሮነት ክንፍ በመብረር፤ በእድገት የተመሰገነች አገር ነው። ለዚህ ደግሞ የሰላም ስምምነቱ ውጤታማ መሆን አልፋና ኦሜጋ ነው።
የሠላም ስምምነቱ አሁንም በሆነው አገራዊ አውድም፤ የሚኖረው ትርጉምም በጦርነቱ ምክንያት ለህልፈት ሊዳረጉ የሚችሉ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ፣ በጦርነት የተጎዱትን ወገኖቻችንን መልሶ ለማቋቋም፣ የፈረሱ መሠረተ ልማቶችን እንደገና ለመገንባት ያስችላል። ለጦርነት ሲውል የነበረውን በጀት ወደልማት በማዞር ኢኮኖሚው እንዲያገግም ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በተጨማሪም የውጭ ኢንቨስትመንትን በስፋት ወደ አገር ውስጥ በመሳብ ባለሀብቶች ያለ ስጋት እንዲተሙ ያደርጋል።
ለዚህና ከዚህም በላይ ሊሆኑ በሚችሉ ምክንያቶች ነው በአገር ውስጥ ሆነ ከአገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሠላም ስምምነቱ የተሰማቸውን ደስታና እፎይታቸውን ሲገልጹ ማየታችን። ከሰሞኑ የአሜሪካ ድምጽ (ቪኦኤ) የመቀሌ ነዋሪዎችን አነጋግሮ የሠራው ዘገባ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው።
በተቃራኒው ደግሞ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ያንዣበበውን ሠላም ለማደፍረስ ደፋ ቀና የሚሉ እየተመለከትን ነው። በተለይ ደግሞ በትግራይ ሕዝብ ስም የትግራይን ሕዝብ ልባዊ የሠላም ፍላጎት ለማዳፈን የሚጥሩ፤ ይህንኑ አላማቸውን በአደባባይ ሳይቀር ሲያስተጋቡ መስማታችን ከፍ ያለ የልብ በስብራት እየፈጠረብን ነው።
እነዚህ ኃይሎች የትግራይ ሕዝብ በጦርነቱ ምክንያት የከፈለው አላስፈላጊ ዋጋ አስፈላጊ ነው ብለው፤ ከሕዝቡ ማሓበረሰባዊ ስብዕና ባፈነገጠ መንገድ የሚያስቡ፤ በሕዝቡ ሞት፣ መከራና ስቃይ የፖለቲካ ትርፍ የሚሹ ስለመሆናቸው ሥራቸው በራሱ የሚናገረው ነው። ቀደም ባለውም ጊዜ ከግጭቱ ጀርባ በመሆን ግጭቱ ላይ ከጀርባ ሆነው ቤንዚን ሲያርከፈክፉ የነበሩ ክፉ የሞት ነጋዴዎች ናቸው።
ቀደም ባለው ጊዜ አውሮፓና አሜሪካ ላይ ቁጭ ብለው ድሃውን የትግራይ ሕዝብ ግፋ በለው ሲሉ የነበሩ፤ ጦርነቱን በሚፈልጉት ልኬት እየለኩ ሲጮሁና ሲያጯጩሁ የነበሩ ናቸው። አሁን ደግሞ የትግራይ ሕዝብን ልባዊ የሠላም ፍላጎት ለማዳፈን ነጠላ ዘቅዝቀው አደባባይ እየወጡ ናቸው።
የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር ሕዝብ አብሮ እንዳይኖር ‘እንዴት ሰላም፤ ጦርነት ይሻልሀል !’ እያሉ በሰለጠነው ዓለም አደባባዮች እያደረጉት ያለው የጦርነት ስብከት ሁላችንንም አንገት የሚያስደፋ አሳፋሪ ተግባር ነው። ትናንት የትግራይ ሕዝብ ተራበ ፣ ሞተ ፣ ተሰቃየ …. በሚል ያሰሙት የነበረው ጩኸት ‘እውነት ለትግራይ ሕዝብ ከማዘን የመነጨ ነበርን ‘ የሚል ጤናማ ጥያቄ እንድንጠይቅም ያስገድደናል።
በተመሳሳይ ባህር ማዶ ተቀጥረው በጋዜጠኝት ካባ፣ በፖለቲከኛ ጭንብል እና በብሔርተኝነት ጫካ ውስጥ ተደብቀው «ሰላም ይሻላል» በሚል ሲያደነቁሩን የነበሩት እነዚህ ኃይሎች ጨዋታ ቀይረው ጦርነት ሰባኪ መሆናቸው «እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል» እንደሚባለው እውነተኛ ማንነታቸውን ለአደባባይ አብቅቶታል።
እነዚህን ኃይሎች የተፈጠረውን ሰላም ለማደብዘዝ በአንድነት ተሰባስበው ዘመቻ ላይ እንዳሉ ሁሉ፤ እኛም (ኢትዮጵያውያን) በአንድነት ሆነን ስለሠላማችን ዘብ መቆም ይጠበቅብናል። በተለይ የትግራይ ሕዝብ እነዚህ ኃይሎች በቃችሁ በማለት ሠላሙን መጠበቅ ይኖርበታል። ዘላቂ ሠላም ለአገራችን፤ ለኢትዮጵያችን !።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኀዳር 5 ቀን 2015 ዓ.ም