በጥበብና በቅኔ ሥራዎቻቸው አንቱ የተባሉትን ያህል በአንድ ነገር ደግሞ ይታማሉ፡፡ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ቆራጥ ተቆርቋሪ አልነበሩም፤ ኧረ እንዲያውም መረር አድርገው የሚወቅሷቸው ሰዎች ‹‹ለጣሊያን ያደረ ባንዳ›› ሁሉ ይሏቸዋል፡፡ ታሪክ ነውና ይህም አብሮ ከስማቸው ጋር ይነሳል፡፡
ያም ሆኖ ግን የጥበብ ሥራዎቻቸው ያንን አሸንፈው ወጥተዋል፡፡ የግጥም ሥራዎቻቸው ከመማሪያ መጻሕፍት እስከ መድረኮችና የመገናኛ ብዙኃን የሃሳብ ማጠናከሪያ እና የውስጥን ስሜት መግለጫ ሆነዋል፡፡
ጽድቅ እና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም
ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም!
ይቺ የከበደ ሚካኤል ግጥም በብዙ ጨዋታዎች ውስጥ ሰዎች ደጋግመው የሚጠቅሷት ናት፡፡ ‹‹ፋኖስ እና ብርጭቆ›› የሚለው የከበደ ሚካኤል ግጥም ከመማሪያ መጻሕፍት ጀምሮ በብዙ አጋጣሚዎች የሚጠቀስ ነው፡፡ ‹‹ጃፓን እንደምን ሰለጠነች?›› የሚለው ደግሞ ከኪነ ጥበብ ባለፈ በታሪክ፣ ፖለቲካና ሥልጣኔ አጋጣሚዎች ሁሉ የሚጠቀስ ነው፡፡
ለመሆኑ የእነዚህ ሁሉ የጥበብና ፍልስፍና ሥራዎች ባለቤት የሆኑት ከበደ ሚካኤል ማን ናቸው? ከ24 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ህዳር 3 ቀን 1991 ዓ.ም ከዚህ ዓመት በሞት የተለዩበትን ምክንያት በማድረግ በሳምንቱ በታሪክ እናስታውሳቸዋለን፡፡
ከበደ ሚካኤል የተወለዱት በኅዳር ወር 1907 ዓ.ም እንደሆነ በሕይወት ታሪካቸው እና ስራዎቻቸው ላይ በመመሥረት በ1976 ዓ.ም የመመረቂያ ፅሑፉን የጻፈው ደራሲ አስፋው አፅምአት አስፍሯል፡፡ በየካቲት መጽሔት ላይ እንደተገለጸው ደግሞ 1908 ዓ.ም የሚል አለ፡፡
ደራሲ ከበደ ሚካኤል ከ1907 እስከ 1908 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከአባታቸው ከአቶ አይታገድ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አፀደ ሚካኤል ሰሜን ሸዋ በጥንታዊቷ መናገሻ አንኮበር ከተማ ተወለዱ።
በተወለዱበት ዘመን አባታቸው አካባቢውን ለቀው በመሄዳቸውና ሳይመለሱም በመቅረታቸው ከበደ በእናታቸው አባት ስም (ሚካኤል) መጠራት ቀጠሉ፡፡ በነገራችን ላይ እርሳቸው ታዋቂ ስለሆኑ የመጠቀስ ዕድል አገኘ እንጂ በአያታቸው የሚጠሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡
ከበደ ሚካኤል የአራት ዓመት ልጅ እንደሆኑ ወይዘሮ ወለተገብርኤል ከተባሉት የሴት አያታቸው ጋር ተቀምጠው ገርብ ገብርኤል በተሰኘው ቤተ ክርስቲያን ትምህርታቸውን ጀመሩ፡፡
በ1917 ዓ.ም አካባቢ የከበደ ሚካኤል እናትና አያታቸው ወደ አርሲ ለኑሮ ሲሄዱ ከበደ አዲስ አበባ በሚገኘው የካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት በአዳሪነት ገቡ፡፡
በ1922 ዓ.ም እናታቸው ከአርሲ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት በመቻላቸው የ14 ዓመቱ ከበደ ከአናታቸው ጋር እየኖሩ ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡
በመሃሉ በአሊያንስ ፍራንሲስ ትምህርት ቤት የነበሩ መምህራን መማታት ያበዙ ስለነበር በዚህ ተማርረው ወደ ላዘሪስት ሚሲዮን ትምህርት ቤት ተዛወሩ፡፡
ቆይቶ ግን ሁኔታዎች በመሻሻላቸው ወደ ቀድሞ ትምህርት ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ወደ አሊያንስ ፍራንሲስ ትምህርት ቤት እንደገና ተመልሰው ሶስት ዓመታትን ያህል እንደቆዩ የሥነ ጽሑፍ ሙያን በትምህርት ቤቱ ዳይሬክትር አማካኝነት የመማር እድል አጋጠማቸው፡፡
የሊባኖስ ዜግነት ያላቸው ማልሃቢ የተባሉት የትምህርት ቤቱ ርዕሠ መምህር እራሳቸው የልቦለድ ድርሰት ፀሐፊ ስለነበሩ ይህንኑ ሙያ ለመረጧቸው ስድስት ተማሪዎቻቸው ለማሳወቅ በግል መኖሪያቸው ማስተማር በጀመሩ ጊዜ ከበደ ሚካኤል አንደኛው የዕድሉ ተጠቃሚ ሆኑ፡፡
ትምህርቱ ይሰጥ የነበረው በፈረንሣይኛ ቋንቋ ሲሆን ከበደ እጅግ ሲበዛ ጎበዝና ታታሪ ሆነው ተገኙ፡ ፡ በዚህም የተነሳ የትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ከበደ ወደ ፈረንሳይ አገር ሄደው የከፍተኛ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ይደረግ ዘንድ ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጥያቄ አቀረቡ፡፡
ያን ጊዜ የተወሰኑ ተማሪዎች ከኢትዮጵያ እየወጡ ትምህርታችውን በውጭ አገር የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መማር የጀመሩበት ጊዜ ስለነበር ንጉሠ ነገሥቱ ከበደ ሚካኤልን በተመለከተ የቀረበላቸውን ጥያቄ ያለማቅማማት ተቀበሉት፡፡
ከእርሳቸው ጋር የተመረጡት ተማሪዎች ወደ ውጭ እንዲሄዱ በተዘጋጀበት ጊዜ ግን እንደ አጋጣሚ ሆነና ከበደ በጠና ታመው ቀሩ፡፡ ጤናቸው መሻሻል እንዳሳየ ሁለት መምህራን ወጣቱን ልዑል መኮንን ኃይለሥላሴን ለማስተማር ከፈረንሣይ አገር መጡ፡፡
በቤተ መንግሥት ኃላፊዎች መካከል ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሶስተኛ መምህር መጨመር እንዳለበት ስምምነት ላይ በመደረሉ ከህመማቸው እያገገሙ የመጡት ከበደ ሚካኤል ለዚህ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ተመረጡ፡፡
ከበደ የልዑል መኮንን ሶስተኛ መምህር ሆነው የተመረጡት ወደ ውጭ አገር ለትምህርት እስኪሄዱ ጊዜ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን 1928 ዓ.ም ደረሰና የማይጨው ዘመቻ ታወጀ፡፡ ሁሉም ነገር የጣሊያንን ወረራ በመመከት ላይ በማተኮሩ የከበደ ሚካኤል ወደ ውጭ አገር ሄዶ የመማር ዕድል በዚያው ተሰናክሎ ቀረ፡፡
በአምስት ዓመታቱ የጣሊያን የአገዛዝ ዘመን ግን ከበደ ልዑል መኮንንን ለማስተማር ከመጡት መምህራን አንደኛው ሚስተር ሊሞይን የተባለ አቋቁመውት በነበረው ቤተ መፃህፍት ውስጥ እየተቀመጡ ብዙ የማንበብ ዕድል ስላጋጠማቸው ያ ዘመን በተደጋጋሚ አነበቧቸው ተበለው ከተጠቀሱት መጻሕፍት አንደኛው ናፖሊዮን የተባለው መፅሐፍ ነው፡፡
ከንባቡ ጐን ለጐንም የጣለያንኛ ቋንቋን በሚገባ ተማሩ፡፡ ቋንቋን በተመለከተ ከበደ ሚካኤል ልሣነ ብዙ ከሚባሉ ደራሲዎች አንዱ ናቸው፡፡ ከአገራቸው አማርኛና ግዕዝ ቋንቋዎችን ከውጭ ደግሞ ፈረንሣይኛን፣ ጣሊያንኛንና አንግሊዝኛ ቋንቋዎችን ጠንቅቆው ያውቁ እንደነበር የተረጋገጠ ነው፡፡
በሁሉም ቋንቋዎች የሚያገኙትን መፅሐፍት ታዲያ ለማንበብ አይቦዝኑም፡፡ ለከበደ ሚካኤል እንደ እጅ ማሟሻና እንደመጀመሪያ የሚቆጠረው ድርሰታቸው ብርሃነ ህሊና የተባለው ሲሆን የተጻፈው በጣሊያን ዘመን ነው፡፡
በኋላ የቅኔ ውበት በተባለው መፅሐፋቸው ከተካተቱት ስብስቦች አንደኛው በመሆን በተደጋጋሚ ታትሟል፡፡ ከበደ ሚካኤል ጠላት ከተባረረም በኋላ የድርሰት ሙያን አላቋረጡም፡፡
ከ1933 እስከ 1966 ዓ.ም በጋዜጠኝነት፣ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ በኢንስፔክተርነትና በምክትል ጻይሬክተርነት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በተርጓሚነትና በፀሐፊነት፣ በብሔራዊ ቤተ መፅሀፍት (ወመዘክር) በዳሬክተርነት፣ እንደገና በትምህርት ሚኒስቴር በዳሬክተርነት፣ በንጉሠ ነገሥቱ ካቢኔ ከምክትል ሚኒስትርነት ማዕረግ የዜና ማደራጃ ኃላፊ እና በኋላም ሚኒስትር ሆነው ባገለገሉባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የድርሰት ሙያን አላቋረጡም። በጠቅላላው 20 መጻሕፍትን አሳትመዋል፡፡ አንዳንዶቹም የተውኔት ሥራዎች ናቸው፡፡ እንግሊዛዊውን የተውኔት ደራሲ ሼክስፒርን ለኢትዮጵያ ተደራሲ ያስተዋወቁ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/ 2015 ዓ.ም