እኛ ቤት የእህቴ ልጅ አለ፡፡ የአንደኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ በትምህርቱ ደህና የሚባል ልጅ ቢሆንም እንደ ማንኛውም ልጅ ጨዋታ ያታልለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የቤት ሥራውን በተደጋጋሚ ይዘነጋል፡፡ በቀደምም የሆነው ይሄው ነው፡፡ እናቱ በተደጋጋሚ የቤት ሥራ ያለው እንደሆነ ስትጠይቀው መልሱ የለኝም
ነበር፡፡ እሷም በሰጣት መልስ መሠረት የቤት ሥራ ከሌለው በጊዜ እንዲተኛ ነግራው ሥራዎቿን መሥራት ቀጠለች፡፡ ሥራዎቿን ጨራርሳ ቴሌቪዥን ልታይ ቁጭ ስትል ግን ልጅ የቤት ሥራ እንዳለው ትዝ አለው፡፡ የቤት ሥራ አለኝ አላት፡፡ ተናደደች፣ ተቆጣች፡፡ አማራጭ ስላልነበራት ግን በመኝታ ሰዓት እንደገና የእሱን ደብተር መፈለግ እና የቤት ሥራ ማሠራት ያዘች፡፡ ሰዓቱ በጣም መሽቶ ስለነበር ልጅም እንቅልፍ እየተጫጫነው ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙውን የቤት ሥራውን ክፍል የሠራችው እሷ ናት ማለት ይቻላል፡፡ እንደምንም ተሰርቶ ሲያልቅ ልጅ ወደ መኝታው ሄደ፡፡ የቤት ሥራውን የሠራው የተማረው ምን ያህል እንደገባው ለመገንዘብ ሳይሆን በቀጣይ ቀን ከሚጠብቀው የመምህሩ ዱላ ለማምለጥ ነው፡፡ እናትም የቤት ሥራውን ያሠራችው ልጇ ምን ያህል የተማረው እንደገባው ለማየት ሳይሆን ልጇን በቀጣዩ ቀን ከሚጠብቀው ተጠያቂነት ለማዳን ነው፡፡
ይህ ዓይነቱ ነገር በየቤቱ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ልጅ ካለ እንዲህ አይነት ነገር አለ፡፡ አንዳንዱ ቤት በጣም ከመሸ ሲሆን ሌላው ቤት ደግሞ ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት በመሄጃ ሰዓት ልጆች የቤት ሥራ እንሥራ ይላሉ፡፡ ወላጅም የትምህርት ቤት መግቢያ ሰዓት እንዳይረፍድ የቤት ሥራውን ልጁ መልሱን እየጻፈ ወላጅ መልሱን እየተናገረ ይሠራና ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳል፡፡
እንዲህ ዓይነት ነገር አንዳንዴ የሚጋጥም ቢሆንም ሲደጋገም ግን ችግር መሆኑ አይቀርም፡፡ የልጁን የቤት ሥራ አንዳንዴ ወላጅ ሌላ ጊዜ አስጠኚ ፤ አንዳንዴ ታላቅ ወንድም ወይም እህት ፤ ሌላ ጊዜ ጎረቤት ያለ ደህና የሚባል ሰው እየሠራለት ይቀጥላል፡፡ ልጅም እንዝላልነትን በዚህ መልኩ እየተለማመደ ይሄዳል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ልጅ ወላጅን አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ከትቶ የእሱን ፍላጎት እንዲፈጽሙ እና ግዴታውን እንዲወጡለት ማድረግን ይለማመዳል፡፡ ይህ አደገኛ ልምምድ ያድግና ከፍ ሲል ወንጀል ፈጽሞ ወላጆቹ መጥተው እንዲያስፈቱት ፤ ገንዘብ አውድሞ እንዲከፍሉለት ፤ መኪና አጋጭቶ መጥተው ዋስ እንዲሆኑት ወዘተ መጠበቅን ይለምዳል፡፡ ለእንዝላልነት ዋጋ እንደሚከፈል መማር ያለበት በጊዜ ገና በልጅነቱ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡
ይህን ከፍ ባለ አውድ ስንመለከተው በሀገር ደረጃ መንግሥትን እና ሕዝብን የማይሆን አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ከትተው የሚፈልጉትን የሚያስፈጽሙ ብዙ
ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ነጋዴው ከመንግሥት አንዳች ነገር ይፈልጋል ፤ ነገር ግን መንግሥት ያንን እንደማይፈጽምለት ያውቃል፡፡ ስለዚህም ለዚህ እንደ መፍትሔ የሚከተለው መንገድ ላይ ምርትን መያዝ ነው፡፡ መንግሥት ይህን ሳቦታጅ ይለዋል፡፡ ምርትን ይደብቃል፣ፍላጎት እያየለ ይሄዳል፣ፍላጎት እየጨመረ ሲሄድ ግን አቅርቦት ታግቶ ተይዟል፣ይሄኔ የዋጋ ውድነት ይፈጠራል፣ሕዝብ መቆጣት ይጀምራል፡፡ የሚቆጣው ግን ነጋዴውን አይደለም ፤ የሚቆጣው እና የሚያማርረው መንግሥትን
ነው፡፡ ለዚህ ብዙ ጊዜ መንግሥት የሚወስደው አማራጭ ለነጋዴው ፍላጎት ሸብረክ ማለት አልያም ቁጣው እያየለ ቢሄድም ዝም ማለት ነው፡፡ መንግሥት የሚመርጠው የመጀመሪያውን እንደሆነ እርግጥ ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥት የነጋዴውን የቤት ሥራ ሠርቶ ምርቱን ያስለቅቃል፡፡ ነጋዴውም በጉልበት የመንግሥትን እጅ ጠምዝዞ ፍላጎቱን አስፈጸመ ማለት ነው፡፡
እንደኔ ግምት እንዲህ የሚያደርጉት ከመሸ የቤት ሥራ እንሥራ እያሉ ወላጅን የሚያስጨንቁት ልጆች አይነት ናቸው፡፡ የቤት ሥራው እንደተደበቀው ምርት ነው፡፡ መምህሩ ምርትን እንደሚጠብቀው ሕዝብ
ነው፡፡ ወላጅ እንደ መንግሥት ነው፡፡ ወላጅ ሳይወድ በግድ የመምህርን ቁጣ ለማስታገስ የልጁን የቤት ሥራ ይሠራል፡፡ ልጅ ለእንዝላልነቱ ሳይቀጣበት
ያልፋል፡፡ ነጋዴም እንዲሁ ለፈጠረው ሳቦታጅ እና ላስከተለው ችግር ተጠያቂ ሳይሆን ይሾልካል፡፡
ወላጅ ልጁን ይወዳል ፤ መንግሥትም የልማት አጋሩ ነውና ባለሀብትን ይወዳል፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ የምንወደው ላይ መጨከን ግድ ይሆናል፡፡ ለልጅህ ዛሬ አንተ የትምህርት ቤት የቤት ሥራውን ልትሠራለት ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ነገ ለሚገጥመው የሕይወት የቤት ሥራ ዝግጁ እያደረግከው አይደለም፡፡ አድጎ ሥራ ላይ ፤ ትዳር ላይ ፤ ማኅበራዊ ኑሮ ላይ የሚገጥመውን ፈተና ወላጅ አይወጣለትም፡፡ በተመሳሳይም መንግሥት ዛሬ ተንከባክቦ ያለ ብዙ ተጠያቂነት የያዛቸው ነጋዴዎች ዛሬ ላይ የፈለጉትን ማግኘት ቢችሉም ይህ የመንግሥት የዛሬ እንክብካቤ ግን ሉላዊ እየሆነች በመጣች ዓለም ውስጥ ለሚገጥማቸው ብርቱ ተግዳሮት ምንም
አያግዛቸውም፡፡ ለማብቃት ተብሎ የሚደረግ ትዕግስት እና ቻይነት እንደ ነገ ግን ባለሀብት ሽፍታን ይፈጥራል፡፡ ስለዚህም የተወሰነ ተጠያቂነት ሊኖርባቸው የተገባ ነው፡፡
እንዲያው በጥቅሉ ለማለት የተፈለገው መልዕክት ምንድን ነው ፤ አንዳንዴ የምንወዳቸውን ሰዎች እንዲያድጉ ከፈለግን በተወሰነ መልኩ ኃላፊነት እንዲወስዱ እናድርግ ነው፡፡ ልጅ የቤት ሥራ አስታውሶ ካልሠራ አስተማሪው እንዲገስጸው መተው አለብን፡፡ ተግሳጽ አይገድለውም፡፡ ነገ መምህሩ ሊቀጣው ይችላል በሚል የቤት ሥራውን ተቀብሎ መሥራት ግን ልጁን በቋሚነት ያጠፋዋል፡፡ ይህ ለመማር ማስተማሩ ሥራ ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ጉዳይ የሚያስፈልግ መርሕ ነው፡፡ አንዳንዴ ተጠያቂነት የምንወዳቸው ሰዎችን የተወሰነ ችግር ቢያስከትልባቸውም በዘለቄታው ግን ጤናማ ያደርጋቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በምንም ሁኔታ የምንወዳቸው ሰዎች መውደዳችንን እንደ እድል ብቻ እየተመለከቱ የእነሱን ጣጣ እንድንወጣላቸው እንዲያደርጉ አንፍቀድ፡፡ ነጋዴ ገበያውን ሳቦታጅ ማድረግ እንደሌለበት ሁሉ ሰዎችም ፍቅርን ሳቦታጅ ማድረግ የለባቸውም ፤ እንዲያደርጉም ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ኅዳር 3/ 2015 ዓ.ም