ሁል ጊዜም በጦርነት ቀዳሚ ተጎጂዎቹ ሕፃናት፤ ሴቶች፤ አቅመ ደካሞች ናቸው። የተለያዩ ጉዳቶች የሚደርሱትም በእነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ነው ። በተለይም ሰዎች በጦር ቀጠና ውስጥ መኖራቸው በራሱ ከባድ የሥነ ልቦና ጫና ከመፍጠሩም ባሻገር በውትድርና ላይ ተሳትፈው መገኘታቸው ደግሞ የማይሽር የሥነ ልቦና ጠባሳ ጥሎባቸው ያልፋል ።
ሰዎች በጦርነት ቀጠና ውስጥ ሲኖሩ ለተለያዩ ሥነ ልቦናዊም ሆነ መሠረታዊ ፍላጎቶችን የማጣት ችግር ይገጥማቸዋል። በተለይ በጦርነት ቀጠና ውስጥ መኖር መሠረታዊ ነገሮች እንደ ምግብ ልብስ መጠለያ እና የጤና አገልግሎት እንዳያገኙ ያደርጋል። ከሚኖሩበት ቦታ ወደ ሌላ ሊያውም ባልተረጋጋ መንፈስ የመፈናቀል ሁኔታ ሲደርስባቸው በስጋት ውስጥ ለመሆን ይገደዳሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከቤተሰብ መነጠል ሌላ አስከፊ የሥነ ልቦና ጫና የሚፈጥር ነገር ነው።
በተጨማሪም በካምፖች ውስጥ በጋራ መኖር ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ የሚያደርግ ስለሆነ ሰዎች እንዳይረጋጉ የራሱን ድርሻ ይወጣል። በተለይም ሕጻናትን ታዳጊዎች በመማሪያና በመቦረቂያ እድሜያቸውም ከትምህርት ይገለላሉ ከቤተሰብ ጋር ከተነጠሉ ለጭንቀት ይዳረጋሉ። በጦርነቱ ምክንያት የአካል መጉደልና ሕይወት ላይ አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሲደመሩ ደግሞ ለፍርሀትና ሰቆቃ ለጭንቀትና ድብርት ይጋለጣሉ።
ሰዎች በጦርነት ቀጠና ውስጥ መኖራቸው ከሚያስከትለው ሥነ ልቦናዊ ጫና በተጨማሪ ተገደው ወይም ተታለው በወታደርነት፣ በጦር ቀጠና ውስጥ በሰራተኝነት እንዲሁም በሰላይነት እና በመሳሰሉት መልኩ በግዳጅ ያገለግላሉ። ይህም ለከፋ የጤና፣ የሥነ ልቦናዊ እና ማሕበራዊ ችግሮች ይዳርጋቸዋል።
በጦር ሜዳ ውሎ ላይም ቢሆን የሚያሠቅቁ ነገሮችን ማየት፤ ፆታዊ ጥቃት፤ አዕምሮን ለሚጎዱ ነገሮች (ኬሚካሎች) መዳረግ (በተለይም የሚያደፋፍሩ መድሃኒቶች ከተሰጣቸው) በእነዚህ ሰዎች ላይ ስር የሰደደ የሥነ ልቦናዊና ማሕበራዊ ቀውሶች መከሰት በወደፊት ሕይወታቸው ላይ ጥቁር ጠባሳን ያስቀምጣል።
በዋነኛነት የሚታዩ ሥነልቦናዊ እና ማህበራዊ ችግሮች መካከል ድባቴና ጭንቀት፤ ድህረ አደጋ ጭንቀት ፣ የመገለል ችግር፣ ጥላቻ፣ጥቃት አድራሽ መሆን፣ የኀዘን ስሜት ውስጥ መሆን፤ ራስን ዝቅ አድርጎ መሳል፤ ራስን ከሌሎች መነጠል ከብዙ በጥቂቱ ናቸው።
የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ዶክተር ማስተዋል መኮንን እንደሚሉት ሥነ ልቦና ወይም ደግሞ የአእምሮ ጤና ብዙ ነገሮችን የያዘና የግለሰቦችን አስተሳሰብ ማህበራዊ መስተጋብር ስሜትን አብሮነትን እንዲሁም ባህሪያትን አጠቃሎ የሚይዝ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ሰዎች የሥነ ልቦና ወይም ደግሞ የአእምሮ ጉዳት ሲደረስባቸው በሕይወታቸው በርካታ የሚያጧቸውም ነገሮች አብረው ይመጣሉ፡፡
የሰዎች ሥነ ልቦና በተለያዩ ምክንያቶች ሊጎዳ አልያም እክል ሊደርስበት ይችላል የሚሉት ዶክተር ማስተዋል በራሱ በግለሰቡ ሁኔታ ሊጎዳ የሚችል ሲሆን ይህም ማለት ራሱ ግለሰቡ ሥነልቦናውን የሚጎዳ ተግባር ሲፈጽም፤ሊጎዳ ይችላል ካሉ በኋላ በተለይም ለሰዎች ቅርብ የሆኑ ብሎም የሚገዙባቸውና ሊተላለፏቸው የማይፈልጉ እንደ እምነት ፤ሃይማኖት እንዲሁም ባህል የመሳሰሉ ነገሮችን የሚቃረኑ ነገሮች ሲያደርጉ ሥነ ልቦናቸው ላይ ጫና ሊፈጠር ይችላል፡፡ በሌላ በኩልም እንደ ማህበረሰብ የተቀመጡ እሴቶችን የሚጎዱ ከሆነ አእምሯቸው ላይ ጫና ሊያድር ይችላል፤ የኑሮ ውድነት አለመመቸት ብሎም ውጣ ውረድ መብዛት የትዳር አለመመቸት የሰውን ሥነ ልቦና ከሚጎዱ ነገሮች መካከል የሚጠቀሱ ስለመሆናቸውም ያብራራሉ፡፡
በተለይም ጦርነት የሰዎችን ሥነ ልቦና ከሚጎዱ ነገሮች መካከል ግንባር ቀደሙን ቦታ ይይዛል የሚሉት ዶክተር ማስተዋል ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ጦርነት ማንንም የማይመርጥ ሁሉን የሚያሸብር መሆኑ ነው፡፡ በተለይም የጦርነት ቀጠና ውስጥ ያሉ ሰዎች ህጻናት እንዲሁም ሴቶች ከፍ ላለ መጨነቅ ፤መረበሽ፤ የጦርነቱ ሰለባ መሆን፤ መደፈር ፤መንገላታት መሰደድ ስለሚገጥማቸው ሥነ ልቦናቸው ይጎዳል አንዳንዴም ከፍ ላለ የአእምሮ ጤና እክል ሊዳርጋቸው ይችላል ይላሉ፡፡
የሥነ ልቦና ችግሩ ጦርነት ቀጠናው ላይ ያሉትን ብቻ በመጉዳት አይመለስም የሚሉት ዶክተር ማስተዋል እንኳን በቅርብ ርቀት ያለን ሰው ይቅርና እኛ ከሩቅ ሆነን በተለያዩ መንገዶች በምንሰማቸው ዜናዎች መደናገጥ መረበሽ መስጋት ይፈጠርብናል ፤ ይህ በራሱ አይባባስ እንጂ ከፍ ያለ የሥነ ልቦና ጫና ነው በማለት ያብራራሉ፡፡
የሥነ ልቦና ችግር ትንሽ (ማይነር) ከሆነ አእምሯዊ ጉዳት እስከ ከፍ ያለ የአእምሮ ጤና መዛባት ድረስ የመድረስ አቅም አለው፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት እንደ አገር ሁላችንም የዚህ ሰለባ ሆነናል፤ ነገር ግን በቀጥታ በቦታው ላይ ያሉ ሰዎች ደግሞ የተባባሰ የሥነ ልቦና ጫና ውስጥ እንዳሉ ይሰማኛል፡፡ በመሆኑም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከፍ ያለ ስራ መስራት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
የሰሜኑን የአገራችን ክፍል ላይ ስራዎች ሰርቻለሁ የሚሉት ዶክተር ማስተዋል በዚህም በጣም ሰፊ የሆነ የሥነ ልቦና ጉዳት ይታያል፡፡ በመሆኑም ከገቡበት ችግር ይወጡ ዘንድ ብሎም ወደተባባሰ የአእምሮ ጤና መዛባት እንዳይገቡ ስራዎች ዛሬ ነገ ሳይባሉ ሊጀመሩ እንደሚገባም ነው የሚገልጹት፡፡
በአገራችን ያለው የሥነ ልቦና ህክምና ያን ያህል የተጠናከረና የባለሙያውም ቁጥር ብዙ ባይሆንም አሁን ባለው ሁኔታና ባሉት ባለሙያዎች ስራዎችን መስራት ግን ይቻላል ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ አገር መሰል ችግሮች ሲደርሱ የሃይማኖት አባቶችን ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች ተሳትፎ መደረግ ይኖርባቸዋል፡፡
ነገር ግን ይላሉ ዶክተር ማስተዋል አሁን ላይ የደረስንበት የሥልጣኔ ደረጃ ሰዎች ለማህበራዊ ሚዲያው የሚሰጡት ትኩረት አኗኗራችን እንዲሁም ሌሎች ገፊ ምክንያቶች በተለይም የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ሰዎችን ለመስማት ያለው ፍላጎት አናሳ ነው፤ ችግሩንም በእነሱ ብቻ እንቀርፈዋለን ማለትም ከባድ ነው፡፡ በመሆኑም የተከሰተውን ጉዳት ለመቀነስ ቅድሚያ ህብረተሰቡ ስለ አእምሮ ጤናና ሌሎች ጉዳዮች ግንዛቤን እንዲያገኝ በመገናኛ ብዙሃን ተከታታይነት ያለው ስራን መስራት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
“…..እንደ አለመታደል ሆኖ በአእምሮ ጤና ላይ ያለን ግንዛቤ በጣም አናሳ ነው፡፡ ሰዎች ትንሽ አካላቸው ሲታመም ምንነቱን ለማወቅ ከዚያም መፍትሔ ለመፈለግ የሚያርጉትን ጥረት ያህል ለአእምሯቸው መታወክ ትኩረት አይሰጡም፤ ስሜታቸውንም አይገልጹም ፤ ይህ መታፈን ደግሞ ለተባባሰ ችግር የሚዳርግ በመሆኑ ከሁሉም ስራችን ሊቀድም የሚገባው በአእምሮ ጤና አጠባበቅ ላይ የምናደርገው የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባር ሊሆን ይገባል” ብለዋል፡፡
አእምሯችን ጥንቃቄ ይሻል በተለይም እንዲህ በጦርነት ውስጥ ማለፋችን ግድ ሲሆን ከማህበራዊ ሚዲያው እንዲሁም ከሌሎች እያየን ወደአእምሯችን የምንልካቸው መልዕክቶች ላይ ከፍ ያለ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል፤ እነዚህ ሲጠረቃቀሙም ጉዳታቸው ከፍ የሚል በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
አሁን ካለንበት ሁኔታ አንጻር በጦርነቱ አካባቢዎችና በሌሎችም ቦታዎች ላይ በቡድን፣ በተናጥል፣ እንዲሁም በማህበረሰብ ሊሆን ይችላል የሥነ ልቦናና የማህበራዊ ደህንነት የሚባለውን ህክምና መስጠት ያስፈልጋል፡፡
አሁን እንደ አገር ያሉንን የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ከሃይማኖት አባቶች ጋር በማቀናጀት ለስራው ማዘጋጀት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው፤ ሌላው የህብረተሰቡ ውይይት ያስፈልጋል ፤ ምክንያቱ ደግሞ አእምሮን የምታክመው መጀመሪያ በውይይት ውስጡ ያለውን ነገር እንዲያወጣ በማድረግ ነው፤ ቂም በቀል፣ ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ጎጠኝነቱ ሁሉ አእምሮን የሚያውኩ በሽታዎች በመሆናቸው ህብረተሰቡን እያቀራረቡና እያወያዩ ለአእምሮ ጤና ችግር ከሚፈጥረው እሳቤ ማስወጣት ያስፈልጋል፡፡
በሌላ በኩል ህብረተሰቡ ሳይተዋወቅ በራሱ ጎጥ ውስጥ ተደብቆ አንዱ ለአንዱ ጠላት የሚመስለውን ነገር ትኩረት ሰጥቶ መስራት፤ ማቀራረብ፣ ማወያየት፣ ያስፈልጋል፡፡ የመገናኛ ብዙሃኑም ይህንኑ ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንደሚያስፈልጋቸው አብራርተዋል፡፡
ጦርነት በርካታ አስከፊ ጎኖች ያሉት ነው፡፡ በተለይም ሰዎችን በዚህ መሰሉ የአእምሮ መዛባት ውስጥ በማስገባት በኩል ወደር የለውም ፤ በመሆኑም አሁን ለይ እንደ አገርና ህዝብ ትኩረታችን ሊሆን የሚገባው በጦርነቱ ወቅት ሥነ ልቦናዊ ጫና የደረሰባቸውን ወገኖቻችንን ከገቡበት ችግር እንዲወጡ በማገዙ ላይ ነው፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 3/ 2015 ዓ.ም