አሁን አሁን የወንጀል አይነቶች እየበረከቱና እየረቀቁ መሆናቸውን ስንሰማ ወደየት እየሄድን ነው ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ ያደርገናል። የወንጀልና ወንጀለኞች መብዛት ለምን ይሆን ብለን እንድናስብ ያደርገናል፤ የፍትህ ውሳኔዎች ክብደትና ቅለትንም እንድንመዝን እንገደዳለን። በከተሞች አካባቢ የቤት ሰራተኞች በአሰሪዎቻቸው ላይ፤ በሚንከባከቡዋቸው ሕጻናት ላይ አሰቃቂ ወንጀሎችን ፈጸሙ የሚል መጥፎ ዜና መስማትም ተደጋግሞ የሚያጋጥም ክስተት ሆኗል። ከዚህ በተቃራኒም የቤት ሰራተኞች በአሰሪዎቻቸው አሰቃቂ ወንጀል ተፈጸመባቸው፣ ተደፈሩ፣ ተገደሉ፣… ሌላም ሌላም ወንጀል ተፈጸመባቸው የሚሉ የወንጀል ዜናዎች በስፋት ይሰማሉ። በህብረተሰቡም በኩል አስተማሪ ቅጣት ባለመኖሩ ነው የሚሉ ቅሬታዎችና አስተያየቶችም ይደመጣሉ። በአንዳንዶች በኩል ደግሞ ጉዳዮች ወደ መገናኛ ብዙሃን በማህበራዊ ድረ ገጾች አማካይነት በስፋት ስለሚራገቡ እንጂ በመብዛቱ ምክንያት አይደለም የሚሉ ክርክሮችም ይደመጣሉ። የሥነልቡናና የሕግ ባለሙያዎችም እንደሙያቸው ምክንያት ያሉትን ሲገልጹ ይሰማሉ። ያም ሆነ ይህ አንድም የሰው ልጅ ሕይወት መጥፋት የለበትም፤ የሰው ልጆችን ሕይወት የሚያጠፉ በሰዎች ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የሚፈጽሙ፤ አካል የሚያጎድሉ ሁሉ ወንጀለኞች በመሆናቸው አስተማሪ ቅጣት ሊጣልባቸው ይገባል የሚለው በሁሉም ዘንድ ገዢ ሃሳብ ነው።
በቅርቡ የሰማነው የወንጀል አይነት ደግሞ ትናንት በሩቁ ስንሰማው የነበረው የተመሳሳይ ጾታ ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን። ይሄ የኢትዮጵያን ሕግ፣ ባህልና ሃይማኖትን የሚጻረር ጉዳይ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት በ“ሴቭ ዘ ቺልድረን ካናዳ” እና በ“ብራይት ፎር ቺልድረንስ ቮለንተር አሶሴሽን” ትብብር የተካሄደ ጥናት እንዳመለከተው፤ በከተማችን አዲስ አበባ ከሚፈፀሙ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች መካከል 22 በመቶ የሚደርሱት የተፈፀሙት በወንዶች ላይ ነው፡፡ ሴቶቹም ላይ ቢሆን ቁጥሩ ከፍ ባይልም ይህን መሰል ጥቃቶች መኖራቸው ተመላክቷል። ዛሬ ‹‹በተናጋሪው ዶሴ ›› አምዳችን በዚህ ዙሪያ ላስነብባችሁ የወደዱኩት ጉዳይ በቤት አሰሪዋ አስገድዶ መደፈር፣ ግፍና በደል ስለተፈጸመባት ወጣት የቤት ሰራተኛ እና ፍትህ ስለሰጠው ውሳኔ ነው።
ያላሰበችው የገጠማት ወጣት
ወጣት ናት ገና በአፍላዎቹ የእድሜ ክልል የምትገኝ። በዛ ላይ ቀይ ቆንጆ ደንቦል ያለች ፍልቅልቅ ወጣት ናት – እቴነሽ ባህሩ። እቴነሽ እንደ አብዛኞቹ የትውልድ ቀዬቸውን ለቀው እንደሚሰደዱ ወጣቶች አዲስ አበባ ሄዶ መስራትን ህልሟ አድርጋ ነበር ያደገችው። በልጅቷ እንደ አካባቢዋ ታዳጊዎች ሁሉ በእረኝነት ነው። ከብቶች በመጠበቅ ውሃ በመቅዳት ቤተሰቦቿን ታገለግላለች። ሆኖም እድሜዋ ከልጅነት ወደ ወጣትነት ሲሸጋገር የልጅነት ህልሟ ወደሆነችው የአዲስ አበባ ከተማ በአስራ አምስት ዓመቷ ትመጣለች።
ታዳጊዋ ወጣት አዲስ አበባ አክስቷ ቤት አርፋ የከተማዋን አየር ከተለማመደች በኋላ በአቅሟ ልትሰራው የምትችለው የቤት ሰራተኛነት ስራ ይፈለግላታል። በዚሁ መሰረት አቅሟን ያገናዘበ መጀመሪያ በሞግዚትነት ትቀጠራለች። እዛም የተወሰነ ጊዜ ከቆየች በኋላ ሙሉ ሰራተኝነት የተሻለ ገንዘብ ያስገኝልኛል በማለት የቤት ሰራተኛ ሆና ብዙ ቤተሰብ ያለበት ቤት ትገባለች። ወጣቷ ከልጅነቷ ጋር ተደምሮ በአናት በአናቱ የሚደራረበውን ስራ መቋቋም ያቅታታል።
ስድስት የቤተሰብ አባላት ያሉበትን ቤተሰብ ቀጥ አድርጋ ለማስተዳደር በአፍላ ጉልበቷ አልሆንላት ያላት ልጅ ከድካምም አልፎ ለህመም ትዳረጋለች። ስራውን እርግፍ አድርጋ በመተው ከአክስቷ ጋር የተወሰነ ጊዜ ከተቀመጠች በኋላ ታገግማለች። ወደቀድሞ አቋሟ መመለሷን የተመለከተችው አክስቷ ቀለል ያለ ስራ መስራት እንድትችል በሰው በሰው ታጠያይቅላት ጀመር። በኋላም አንድ ቤት ተገኘ “አንዲት ብቸኛ ሴትን መንከባከብ ብቻ ነው፤ ስራው አያደክምም…” ይሏትና ሰብለወንጌል እያሱ በተባለች ግለሰብ ቤት ትቀጠራለች።
እውነትም እንደተባለው የከበደ ስራ አልነበረም። ለእሷና ለቀጣሪዋ የሚሆን ምግብ ማዘጋጀት የሁለቱን ፅዳት መጠበቅና እጅግ በጣም አነስተኛ የሚባሉ ስራዎችን ከመስራት ያለፈ የሚያደክማት ስራ አትሰራም ነበር። ድካሟ እየለቀቃት ሰውነቷ እየተመለሰ ሲሄድ ግን የቀጣሪዋ አስተያየት እየተቀየረባት ሄደ። ግራ የሚያጋባ ስሜት እየተሰማት የሆዷን በሆዷ ይዛ ዝም አለች። ሁኔታውን ግን በልቧ ከትታ እሷም የሚሆነውን ነገር ማድመጥና ማየት የየእለት ስራዋ አደረገች።
“ሴትን በዚህ መልክ የሚያዩትና የሚመኙት ወንዶች አይደሉም እንዴ? ለምን ግን እንደዚህ ታየኛለች፣ ትነካኛለች …?” የሚል ጥያቄ ወጣት እቴነሽ ልብ ውስጥ ይመላለሳል። ብዙን ጊዜ ከቤት እንድትወጣና ከሌሎች ሰዎች ጋር እንድታወራ ስለማይፈቀድላት ለማንም መማከር አልቻለቸም ነበር። ከጎረቤት ጋር ቆማ ብታያት በጩኸት ስለምታስበረግጋት ተደብቃ የሚናፍቃትን ደጅ ከማየት ያለፌ ከቤት ወደ ውጭ ውልፍት አትልም ነበር።
“ከዚህ ሁሉ ለምን እረፍት ጠይቄ ለአክስቴ የሆነውን አልነግራትም…” ትልና እረፍት ትጠይቃለች። በመልሱ ግን መሄድ እንደማትችል የተነገራት ወጣት ግራ በመጋባት ውስጥ ሆና ልቧ በስጋት ተወጥሮ ምን ማድረግ እንዳለባት እያሰላሰለች በነበረበት ወቅት ነው የላሰበችው ድርጊት የተፈፀመባት።
ዱብዳው
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 አልታድ ሚካኤል ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነው። የ30 ዓመት እድሜ ያላት የእቴነሽ ቀጣሪ ሰብለ ወንጌል እያሱ ተከራይታ ከምትኖርበት ቤት ውስጥ ነው ይህ ድርጊት የፈፀመችው። በቤት ሰራተኝነት ያመጣቻትን ወጣት እቴነሽን ባላሰበችውና ባልጠበቀችው ሁኔታ በግንቦት ወር 2012 ዓ.ም አንድ ምሽት ላይ ጥቃት ታደርስባታለች።
ነገሩ እንዲህ ነው በእለቱ ትንሽ መጠጥ ቀማምሳ የመጣችው አሰሪ ይዛ የመጣችውን አረቄ እቴነሽ በግድ እንድትጠጣ ታደርጋታለች። ከዛም በኋላ በቢላዋ በማስፈራራት ልብሷን ሙሉ በሙሉ በማስወለቅ እና ኢሰብአዊ ድርጊት ትፈጽምባታለች ፤ ቀጥላም አፏን በነጠላ በማፈን የሴቶች ፀጉር መስሪያ ፓይስትራ ሶኬቱን በመሰካት በግል ተበዳይ ብልት ውስጥ በኃይል በመክተት የግል ተበዳይ ድንግልና እንዲገረሰስ እና ደም እንዲፈሳት ካደረገቻትም በኋላ ፀያፍ ድርጊት ፈፅምባታለች፡፡
ባለሰበችው ፍጥነት ያላሰበችው ዱበዳ የወረደባት ወጣት ራሷን ለማስጣል የተለያዩ ሙከራዎች ብታደርግም አቅም ታጣለች። ቀጣሪዋ የፈፀመችው ፀያፍ ድርጊት አልበቃ ብሏት በተደጋጋሚ ጊዜ በቢራ ጠርሙስ እና በታኮ ጫማ ግንባሯን፣ ጆሮዋን፣ አፍንጫዋን እንዲሁም እግር እና እጇን የመታቻት ሲሆን በዚህም ጆሮዋ እንዲጎዳ ፤ የላይኛው የፊት ጥርሷ እንዲሰበር ከማድረጓም በላይ የፈላ ውሃ የተጎጂዋ ደረት ላይ በመድፋት አካሏ እንዲላጥ አድርጋለች፡ ፡ በተጨማሪም በቢላዋ ጀርባዋን በመውጋት ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስባት በማድረጓ የግል ተበዳይ በዚህ ተደጋጋሚ ጥቃት ምክንያት ሰውነቷ ላይ ጠባሳዎች ሊፈጠሩ ችለዋል፡፡
ሴትዮዋ ከቤት በምትወጣበት ጊዜ የግል ተበዳይ ላይ ቆልፋባት የምትወጣ በመሆኑ ድርጊቱ ከተፈጸሙበት ከመጋቢት 27/2012 ዓ.ም እስከ ግንቦት 19/2013 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ውስጥ ተጎጂዋ በቤት ውስጥ ምግብ እና የፀሃይ ብርሃን ተከልክላ ለአንድ ዓመት ከሁለት ወር በማቆየት በስቃይ ላይ ስቃይ ስትደራርብባት ቆይታለች፡፡
የማምለጥ ሙከራ
የሰቆቃው ብዛት “ከዚህስ ሞት ይሻላል” እንድትል ያደረጋትን ይህን ጥቃት ለማምለጥ አቅሟን ማጠናከር ጀመረች። በኋላ መስኮት ጋር ጠጋ ብላ ሰው ሲያልፍ የማንኳኳት ሙከራ ብታደርግም ማንም ሰው ሊያያት አልቻለም ነበር። ቀስ ብላ ድምጿን ለማሰማት ብትሞክርም ያም ሊሰራላት አልቻለም ነበር። በመጨረሻም የግል ተበዳይ በወረቀት ፅፋ በመስኮት ቀዳዳ ትጥላለች። የጣለችውን ወረቀት አንድ ግለሰብ በማግኘቱ የፖሊስ አባላት ይሰጣል። ያኔ ፖሊሶች ለምርመራ ቤቷ በተገኙ ጊዜ ተበዳይን አልጋ ስር ደብቃት እጅ ከፍንጅ ተያዘች።
የፖሊስ ምርመራ
የግለሰቡን ጥቆማ ተከትሎ ሰብለወንጌል እያሱ ቤት የተገኘው ፖሊስ ቤቷን እንድታሳይ ያደረገው ጥረት በሴትዮዋ እንቢታ ምክንያት ቢጓተትም፤ ፖሊስ ይዞ የመጣውን ማዘዣ በማሳየት ገብቶ ቤቱን ሲፈትሽ እጅግ በጣም የተጎዳች ወጣት በአሰቃቂ ሁኔታ አልጋ ስር ተደብቃ ይመለከቷታል። ያየውን በካሜራ በማስቀመጥ የሰውና የህክምና ማስረጃን በማሰባሰብ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የቦሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዐቃቤ ሕግ ያቀርባል።
በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የቦሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዐቃቤ ሕግ ከፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ እና በመመርመር ክስ ሊያስመሰርት የሚያስችል በቂ ማስረጃ መኖሩን በማመን በ1996 ዓ.ም የወጣውን በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ወንጀል ሕግ አንቀፅ 630/2/ሀ/ እና /ለ/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በፈፀመችው ከባድ የግብረ ሰዶም እና ለንፅህና ክብር ተቃራኒ የሆኑ ሌሎች ድርጊቶች ወንጀል፣ አንቀፅ 555/ሀ/ እና /ለ/ በመተላለፍ በፈፀመችው ታስቦ የሚፈፀም ከባድ የአካል ጉዳት ማድረስ እና አንቀፅ 590/ሀ/፣ /ሐ/ እና 2/ለ/በመተላለፍ በፈፀመችው ከሕግ ውጪ ይዞ ማስቀመጥ ወንጀል 3 ክሶችን መስርቶባት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በዚህም መሰረት ተከሳሽ የቀረበባትን ክስ ክዳ ተየተከራከረች ሲሆን ዐቃቤ ሕግ ክሱን ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰው፣ የሰነድ፣ ገላጭና ኤግዝቢት ማስረጃዎች አቅርቦ አሰምቷል፡፡ ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ወንጀል ችሎት ተከሳሽ በቀረበባት ሁሉም ክስ ስር እንድትከላከል ብይን ቢሰጥም ተከሳሽ ያቀረበቻቸው ሶስት የመከላከያ ምስክሮችን የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ ማስተባበል ሳይችሉ በመቅረታቸው በተከሰሰችባቸው ክሶች ሁሉ ስር ጥፋተኛ ነሽ ሲል የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ውሳኔ
የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ወንጀል ችሎት ጥቅምት 17 ቀን 2015ዓ.ም በዋለው ችሎት የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ከሰማ በኋላ ተከሳሽ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑዋን፣ የቀድሞ የወንጀል ሪከርድ የሌለባት መሆኑን፣ ህመምተኛ መሆኑዋን እና የበጎ ስራ ላይ ትሰማራ የነበረ መሆኑን የሚገልፅ ማስረጃዎችን ተቀብሎ በድምሩ አራት የቅጣት ማቅለያ ተይዞላት ተከሳሽን ያርማል፤ ሌላውን ያስጠነቅቃል በማለት ተከሳሽን በ 14 ዓመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ ሲል የቅጣት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ኅዳር 3/ 2015 ዓ.ም