መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር ዓመት መሪ እቅድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምሰሶ በሚል ከያዛቸው አምስት ዋና ዋና ዘርፎች አንዱ የማዕድን ዘርፍ ነው። ይህን ተከትሎም የዘርፉ ማነቆ ሆነው የቆዩ የአሠራር፣ የፖሊሲ፣የመመሪያና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ጥናቶች እንዲካሄዱ ምቹ ሁኔታ ተፈጥረዋል።
ይህም ሀገሪቱ ያላትን እምቅ የማዕድን ሀብት አውጥቶ ለመጠቀም በተለይ ባለሀብቶች በዘርፉ በስፋት እንዲሠማሩ፣ በዘርፉ የተሠማሩትም ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ፣ አነስተኛ ማዕድን አምራቾች አቅም እንዲጎለብት፣ በባህላዊ አመራረት ውስጥ የቆየውን የማዕድን ዘርፍ ልማት አመራረት ለማሻሻልና ለመለወጥ.ወዘተ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። በግብይት ላይም ተመሳሳይ ተግባሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ከጸጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ እንዲሁም የዓለም ስጋት ሆኖ በቆየው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየውን የማዕድን ልማትና ግብይት ለማነቃቃትም መንግሥት የተለያዩ ተግባሮችን ሲያከናውን ቆይቷል። በክልሎች የተለያዩ ሲምፖዚየሞች፣ የእውቅና መርሐ ግብሮች ተካሂደዋል።
ከትናንት ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ሲምፖዚየምም የሀገሪቱን እምቅ አቅም በማስተዋወቅ ፣ ባለሀብቶችን ለመሳብ፣ ወዘተ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። በማዕድን ልማት፣ በንግድ እንዲሁም ቴክኖሎጂ በማቅረብ በዘርፉ የተሠማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች እንዲገናኙ እድል ፈጥሯል። በማዕድን ልማቱ አቅም በመፍጠር ከውጭ የሚገቡ የማዕድን ውጤቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እንደ ሀገር የተያዘውን አቅጣጫ ከግብ ለማድረስ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ማሳያ ናቸው።
ለጌጣጌጥ የሚውሉ የከበሩ ማዕድናትን ጨምሮ ለግንባታና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ እምቅ የማዕድን ሀብቶቿን ለሌላው ዓለም ማስተዋወቅንና ኢንቨስትመንትን መሳብን ታሳቢ ባደረገው በዚህ ሲምፖዚየም ላይ በዘርፉ ከተሠማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በተጨማሪ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሚሳተፉበት መሆኑ ለዘርፉ የተሰጠው ሌላው የትኩረት ማሳያ ነው። እንዲህ ያሉ ጥረቶችን በማድረግ ዘርፉን የሚመራው የማዕድን ሚኒስቴር ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።
በዘርፉ ላይ እየተከናወነ ስላለው እንቅስቃሴና ሲምፖዚየሙን አስመልክቶ ሰሞኑን ማብራሪያ የሰጡት የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ዑማ እንደገለጹት፤ ዘርፉ የኢኮኖሚ ዋልታ ተብለው ከተለዩት ውስጥ አንዱ ነው። መንግሥት ከወሰዳቸው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች (ሪፎርም) መካከል የማዕድን ዘርፍ ይጠቀሳል።
ሀገራዊ ለውጡ ከተደረገ ወዲህ ባለፉት አራት ዓመታት መንግሥት መጠነ ሰፊ ተግባራትን በማከናወን ዘርፉን የማነቃቃት ሥራ ማከናወኑን ሚኒስትሩ ይገልጻሉ። በቅድሚያም ከተወሰዱት የማሻሻያ እርምጃዎች ፖሊሲና አዋጅ ማውጣት እንደሚጠቅስ አመልክተው፣ በዚህም መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ባለሀብቱን ሊያሠራ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ችሏል ይላሉ። ሀገሪቱ የገጠማት የውስጥ የሰላም እጦት እየተፈታ መምጣቱን ጠቅሰው፣ በዘርፉ የተጀመረውን እንቅስቃሴ የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም ማካሄድ ትክክለኛው ጊዜ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ጂኦሎጂ ኢንስቲትዩትና በሌሎች አካላት ጭምር በጥናት የተለዩ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ተስፋ የተጣለባቸው እምቅ የማዕድን ሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ ያሉት ሚኒስትሩ፣ ያለው የሀብት ክምችት ሀገሪቱን በዘርፉ ከሌላው ዓለም እኩል ተርታ የሚያሰልፏት እንደሆነም ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ የማዕድን ሀብቱን የማልማቱ ሥራ ባለሀብቱን በሚስብና በሚያሠራ ፖሊሲና መመሪያ ባለመደገፉ ከዘርፉ የሚገኘው ጥቅም ኢኮኖሚውን ከፍ በሚያደርግ ደረጃ ላይ ያለ እንዳልሆነ አመልክተዋል። ይህ በመሆኑም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጭ ለኢንዱስትሪና ለግንባታ ዘርፍ የሚውሉ ግብዓቶች ወደ ሀገር ሲገቡ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
በራስ ሀብት ለመጠቀም ብሎም ለውጭ ገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅምን ለማሳደግ አሠራሮችን ማሻሻልና መቀየር የግድ መሆኑን አመልክተው፣ ለሦስት ቀናት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ሲምፖዚየም ዘርፉን ለማሻሻል በመንግሥት እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል። ‹‹በሲምፖዚየሙ ላይ ያለንን እምቅ የማዕድን ሀብት እያስተዋወቅን፣ያመረትነውንም በመሸጥ፣ የሀገር ውስጥ የዘርፉ ኩባንያዎች የተሻለ ቴክኖሎጂ ካላቸው ልምድ እንዲያገኙና በሽርክናም የሚሠሩበትን እድል እንዲፈጠርላቸው በማድረግ በሀገራችን የተሻለ የማዕድን ልማት እንዲፈጠር እናደርጋለን›› ሲሉም ተናግረዋል።
በሲምፖዚየሙ ላይ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርትና አገልግሎታቸውን እንደሚያቀርቡ ጠቅሰው፣ በፋብሪካ ዋጋ የሚቀርቡ የግንባታና የኢንዱስትሪ ውጤቶችም እንደሚኖሩም አመልክተዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች በዘርፉ ላይ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎችን ማግኘት እንዲሁም በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ በዘርፉ ማየት አንዱ የማዕድን ዘርፍ ተግዳሮት እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ በኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ባለው ተሞክሮ እንደ ወርቅ ያለ
ማዕድን ሳይቀር በቤተሙከራ ፍተሻ እንዲካሄድ ናሙና የሚላከው ከሀገር ውጭ እንደሆነና ለዚህም ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚከፈል አመልክተዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በራስ አቅም በመሥራት ወጭን ለማስቀረት አቅምን ማጠናከር ያስፈልጋል፤ መንግሥትም በዚህ ረገድ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህ ረገድ የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር በሲምፖዚየሙ ከሚሳተፉ ዓለምአቀፍ ልምድ ካላቸው የዘርፉ ኩባንያዎችና ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች መልካም ተሞክሮዎችን ማግኘት ይቻላል።
ለሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለኃይል ግብዓት የሚውለው የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለማቅረብ እየተደረገ ያለው ጥረት ራስን ለመቻል ከተደረጉ ጥረቶች መካከል ይጠቀሳል። የሀብት ክምችቱ በመኖሩ በዘርፉ ለመሠማራት ለሚፈልግ ባለሀብት ምቹ ማድረግ ብቻ ነው የሚጠበቀው። በዚህ ረገድም ባለሀብቶች ፍላጎት እያሳዩ ነው። በኢትዮጵያ ሲምፖዚየም እንደሚካሔድ መገለጹን ተከትሎ ብቻ በከሰል ድንጋይ ልማት ፍላጎት ያሳዩ ሦስት ኩባንያዎች ማግኘት ተችሏል። በዚህ ልማት ፍቃድ አግኝተው የተሠማሩ አሉ። ፍላጎት ያላቸውን በማስተናገድና በልማቱ የሚሳተፉትን ለመሳብ ከተሠራ በአራትና አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አሁን እየተስተዋለ ያለውን የሲሚንቶ ምርት አቅርቦትና የዋጋ ውድነት ችግር መፍታት ይቻላል።
አምራች አንዱስትሪዎቹ የሚያነሷቸውን የግብዓት አቅርቦቶች ችግር ለመፍታት መንግሥት ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። አምራች ኢንዱስትሪዎቹ በእነርሱ በኩል የሚስተዋለውንም ክፍተት ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል።
በሀገሪቱ ከሚገኙት ወደ 14 ከሚሆኑት ሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች በተሟላ ቁመና ውስጥ ሆነው ምርታማ የሆኑት ከአራት አይበልጡም። አብዛኞቹ መሠረታዊ የሆነ የአሠራር ችግር ወይንም ክፍተት አለባቸው። ማምረት ከሚጠበቅባቸው በታች ነው የሚያመርቱት። ይህን ደግሞ መንግሥትም ያውቃል። እነርሱም ያመኑት ጉዳይ ነው።
ጥሩ ከሚያመርቱት ጋር ተመሳሳይ ግብዓት እየተጠቀሙ ከሚጠበቅባቸው በታች ለምን እንደሚያመርቱ ራሳቸውን መፈተሽ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ። ኢንዱስትሪዎቹ ውስጣዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው አስገነዝበዋል። መንግሥትም ግብረ ኃይል በማቋቋም የሚያግዛቸው አካል ሊኖር የሚገባ በመሆኑን ላይ ስምምነት ላይ ደርሷል ይላሉ። በዚህ መልኩ ክፍተቶችን በመሙላት እና አስፈላጊ ነገሮችን በማቅረብ፣ ከመንግሥት የሚጠበቀውንም በመሥራት የዘርፉን ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ በተጠቃሚው በኩል የግብዓት አቅርቦት ፍላጎት መጨመሩ መዘንጋት እንደሌለበትም ሚኒስትሩ አውስተዋል።
በተመሳሳይ በብረት አቅርቦትና በዋጋ መናር በኩል ያለውን ክፍተትም መንግሥት ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔዎችን በማስቀመጥ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። በተለይም የብረት ማዕድንን ጥቅም ላይ በማዋል በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚሠራ ነው ያመለከቱት። ሲምፖዚየሙ እነዚህን ሁሉ የመንግሥት እቅዶችና እንቅስቃሴዎች ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል።
ሀገራዊ ሰላም ለማስፈን ጥረት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት ዓለም አቀፍ የማዕድንና የቴክኖሎጂ ሲምፖዚየም በኢትዮጵያ መካሄዱና ስለሚኖረው እድል የምጣኔ ሀብትና የፖሊሲ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋን ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ ፤ ሲምፖዚየሙ ሀገርን በማስተዋወቅ፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንደሚያስችል ይገልጻሉ።
በመድረኩ ጥያቄዎችን የሚያነሱና ምላሽ የሚፈልጉ ኩባንያዎች እንደሚኖሩም ጠቅሰው፣ ዝግጁ ሆኖ መገኘትም ያስፈልጋል ነው የሚሉት። የሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች ለጥቅማቸው ሲሉ የሚመጡ መሆናቸው መዘንጋት እንደሌለበትም የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ይናገራሉ።
ሌላው ከሲምፖዚየሙ ጋር መታየት ያለበት ከሲምፖዚየሙ የሚገኘውን ጥቅም ወደተግባር ለመቀየር ያለውን ዝግጁነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ይላሉ። በቀደሙት ተሞክሮዎች በተለያየ የማዕድን ሥራ ለመሠማራት ሀገር ውስጥ የገቡ የውጭ ኩባንያዎች የጀመሩትን ሥራ አቋርጠው ወደመጡበት የሚመለሱበት ሁኔታ ማስተዋላቸውን ይጠቅሳሉ፤ ለአብነትም የተፈጥሮ ጋዝ ማዕድንን በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል እንደ ሀገር የሚደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም፣ ወደ ተግባር ሳይቀየሩ እየተንከባለሉ ዓመታትን ማስቆጠራቸውን ያብራራሉ። በመሆኑም የጋዝ ምርት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ እየተገዛ መሆኑን ይናገራሉ። ይህ ምርት በአሁኑ ጊዜ ዋጋው እየናረ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና እያሳደረ ነው ይላሉ። ሲምፖዚየሙ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሊጠቅም እንደሚችልም ይናገራሉ።
በሀገሪቱ ላለፉት ሁለት ዓመታት የዘለቀው አለመረጋጋት በማዕድን ልማቱ ላይ ጫና ማሳደሩን ያስታወሱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ አሁን እየተፈጠረ ባለው ሰላም በተለይ የማዕድን ሀብት የሚገኝባቸውን አካባቢዎች የበለጠ ሰላም ማድረግ እንደሚገባ ያመለክታሉ።
የማዕድን ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ማዕድኑ የሚገኝባቸውን ሥፍራዎች ከፀጥታ ስጋት ነጻ ማድረግ እንደሚጠበቅ አስታውቀው፣ በሲምፖዚየሙም የሚካፈሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የፀጥታው ጉዳይ አንዱ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። ጥያቄውን መመለስ ከተቻለ ፍላጎት ይኖራቸዋል ብለዋል።
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ በዘርፉ ውጤት ለማስመዝገብ ኃላፊነቱ የአንድ አካል ብቻ መሆን የለበትም። ከፍተኛው ድርሻ የመንግሥት ቢሆንም፣ ማዕድኑ የሚገኝበት ሥፍራ ወይንም ከክልልና ከቀበሌ ጀምሮ እስከላይኛው እርከን የሚገኘው አካል በኃላፊነት መሥራት ይኖርበታል።
ኢትዮጵያ ለማዳበሪያ የሚውል ፖታሽ የተባለው የማዕድን ሀብት እያላት ለግብርና ሥራ የሚውል ማዳበሪያ ከውጭ በግዥ ታስገባለች። ይህ ደግሞ ኢኮኖሚዋ በግብርና ላይ ለተመሠረተ ሀገር እጅግ ይጎዳል። እያንዳንዱ አካል በሀገር ውስጥ ያለው ማዕድን እንዲለማ በማድረግ በኩል በትኩረትና በኃላፊነት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።
የማዕድን ኢንቨስትመንት ከባድ እንደሆነና ገቢውም እንዲሁ ከፍተኛ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ ከዘርፉ ገቢ ለማግኘት መሠረተ ልማት ምቹ በማድረግና የኩባንያዎቹን ፍላጎት በማሟላት ዝግጁ መሆን ይጠበቃል ብለዋል።
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ሁሉንም ኩባንያዎች ማመን እንደማያስፈልግና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ። እርሳቸው እንዳሉት፤ የተሰጣቸውን የማዕድን ሥፍራ ባለማልማታቸውና በጊዜ ገደባቸውም ባለመጠቀማቸው ፍቃዳቸው የተሰረዘባቸው ኩባንያዎች መኖራቸው በተለያየ ጊዜ ተገልጿል። እንዲህ አይነቱ ችግር በመንግሥት ላይ ተጨማሪ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ጠቅሰው፣ ፍቃዱ ከመሰጠቱ በፊት ለመሥራት የሚያስችል ክህሎትና የገንዘብ አቅም እንዲሁም ገበያ እንዳላቸው ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
ተገቢው ጥንቃቄ ባለመደረጉ እንደ ኮንጎ ያሉ የማዕድን ሀብት ያላቸው አፍሪካ ሀገራት በዝርፊያ መጎዳታቸውን አስታውሰው፣ እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎችን በማየት ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ። ችግሩን መከላከል የሚቻለው ደግሞ በተለይ ማዕድኑ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ኩባንያዎችን መምራትና ማስተዳደር የሚችል ብቃት ያለው የሕዝብ አስተዳደር መፍጠር ሲቻል መሆኑንም ጠቁመዋል።
የማዕድን ሀብት በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ እንደሆነ ያመለከቱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ከእርሻ ውጤት ከሚገኘው በተሻለም ሀብት ሊያስገኝ እንደሚችል ነው ያመለከቱት። ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለማስቀረት የሚያስችል እንደሆነም ይናገራሉ። በሀገሪቱ ለመኪና የሚውል የባትሪ፣ለእጅ ስልክና ለሌሎችም የኤሌክትሪክ ግብዓት የሚውሉ የማዕድን ዓይነቶች መኖራቸውን በአብነት ጠቅሰዋል።
ከትናንት ጀምሮ ለሦስት ቀናት ከሚቆየው ሲምፖዚየም ቱሩፋቶችን የሚያስገኝ እንደሆነ ይጠበቃል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ኅዳር 2/ 2015 ዓ.ም