
ጎንደር፦ በህግ እና በህክምና ትምህርቶች ላይ የተቀመጠው የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና ውጤታማ መሆኑ ስለታመነበት፤ በሌሎች የትምህርት አይነቶች በፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሰሞኑን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመላ ኢትዮጵያ የመንግስተ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የህግ ትምህርት ቤቶች የጋራ ውይይት (ኮንሶርቲየም) ተካሂዷል። በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ሳሙኤል እንደገለጹት፤ የዩኒቨርሲቲ የህግ እና የህክምና ትምህርቶች የመውጫ ፈተና የምሩቃኑን ብቃት በማሻሻል ረገድ ውጤታማ መሆኑ ታምኖበታል። በመሆኑም በሌሎች የትምህርት አይነቶችም ላይ የመውጫ ፈተናውን ተግባራዊ ለማድረግ የመጀመሪያ ጥናት ተካሂዶ ውይይት እየተደረገበት ነው። በዘንድሮ ዓመት የአፈፃፀም መመሪያ ወጥቶለት ተግባራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል።
እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻ፤ ከመውጫ ፈተናው በኋላ ወደስራ የገቡ ተመራቂዎች በስራ ዓለም ውጤታማ መሆናቸው በመታየቱ የመውጫ ፈተናውን ወደሌሎች ትምህርቶች እንዲስፋፋ ማድረግ እንደሚገባ በባለሙያ ተጠንቷል።
የመውጫ ፈተናው ለተማሪውም ሆነ ለአስተማሪው ጠቃሚ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ደሳለኝ፤ ፈተናውን የሚያልፉ ተማሪዎች በስራ ዓለም እኩል እንዲታዩ እና ስራቸውም ላይ ብቃት እንዲኖራቸው ያግዛል። በሌላ በኩል በመውጫ ፈተና ተማሪዎቻቸው ዝቅተኛ ውጤት እንዳያመጡ መምህራን ተግተው እንዲሰሩ መነሳሳት እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ዲን ረዳት ፕሮፌሰር አበበ አሰፋ በበኩላቸው ፤ የከፍተኛ ትምህርተ ተቋማት የህግ ትምህርት መውጫ ፈተና ለህግ ትምህርት ጥራት ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። የመውጫ ፈተና አሰጣጡ በኢትዮጵያ ጅምር ላይ ቢሆንም በተለያዩ አገራት ተሞክሮ ውጤታማ የሆነ አሰራር መሆኑን አስታውሰው፤ የመውጫ ፈተና አንድ ተማሪ የከፍተኛ ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ ከዕውቀት ከክህሎት እና ከአመለካከት አንፃር ምን ያህል አድጓል የሚለውን መስፈርት ማሟላቱን ለማረጋገጥ የሚሰጥ መመዘኛ ነው። ፈተናው የሽምደዳ ሳይሆን ለዘርፉ የሚያስፈልገውን መሰረታዊ እውቀት ለመለካት ነው የሚሰጠው። በዚህም ተማሪዎቹ ቢያንስ ዝቅተኛውን መስፈርት ያሟላ የተቀራረበ እውቀት ይዘው እንዲወጡ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።
የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና የህግ እና የህክምና ተማሪዎች የትምህርት ጊዜያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የሚሰጥ የአጠቃላይ ትምህርቱ መመዘኛ ፈተና ነው። የፈተናዎቹን ማለፊያ ነጥብ ያላመጣ ማንኛውም ተማሪ ፈተናውን እስከሚያልፍ ድረስ የዲግሪ ማስረጃ አያገኝም።
ጌትነት የተስፋማርያም