በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል አጋጥሞ የነበረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግሥት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ይህም ተሳክቶ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተካሄደው የሰላም ንግግር ውጤት አምጥቶ የሰላም ስምምነት ላይ መድረስ ተችሏል።
ይሄ የሰላም ስምምነት ወደ መሬት እንዲወርድ፣ በሕዝቡ መካከልም ሰላማዊ ግንኙነቱና አንድነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲሁም በጦርነቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል በርካታ ሥራዎች በቀጣይ መሠራት እንዳለባቸው ይታመናል። ከሁሉም በፊት ግን የሕዝቡን ስነልቡና ማረጋጋት እና የይቅር ባይነትን መንፈስ ወደፊት ማምጣት ቀዳሚ ሥራ መሆን እንዳለበት የተለያዩ ምሑራን ይናገራሉ። የትኞቹ ሥራዎች ላይ ማተኮርና ቅድሚያ መስጠት ይገባል ስንል ያነጋገርናቸው ምሑራንም የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተውናል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ እና የሥነልቦና ምሑሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ፤ አካላዊ ጉዳት በወራት እና በዓመታት ይታከማሉ፤ ጠባሳ ትተው ያልፋሉ፤ አንዳንዶቹ ይሽራሉ፤ ቆይተው ይድናሉ የስነልቦና ጉዳት ግን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊሸጋገር ይችላል ይላሉ
‹‹ በአካል ከደረሰው ጉዳት እና ከወደመው ንብረት ይልቅ እኔን እጅግ የሚሳስበኝ የደረሰው የሕይወት መጥፋት ብቻ ሳይሆን አዕምሮ ላይ የደረሰው ስብራት ነው ሁልጊዜም እንደምለው በጣሊያኖች በየካቲት 12 አዲስ አበባ ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋ ይኸው በሶስተኛው ትውልድ ሳይቀር ይዘከራል አራተኛው እና አምስተኛው ትውልድም እየመጣ ነው መዘከሩ አይቀርም ይሔ ጦርነት ደግሞ እኛው በእኛው ነው ይሔ ሲታሰብ የአዕምሮ ስብራትን ማሰብ በራሱ ያሳምማል ለማከምም በጣም ብዙ ሥራን ይጠይቃል›› ይላሉ የጦርነት ስነልቡና ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን ሲጠቅሱ፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚያብራሩት፤ የአዕምሮ ስብራት በአንድ ትውልድ ላይ ብቻ የማይቆም ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊሸጋገር የሚችል ትልቅ ጉዳይ ነው ስንል ጉዳቱ እጅግ ሰፊ፣ የተወሳሰበ እና ጥልቅ እንደሚሆን በማሰብ ነው
ሌላኛው የሥነ አዕምሮና የስነልቦና ባለሞያው ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሳሚ ወልዴ ፤ ጦርነት የሰዎችን አካላዊ ማንነት ብቻ ሳይሆን ሥነልቦና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ ስነልቦና ስንል ስነመለኮታዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ እስከማስከተል ይደርሳል ሰዎች ‹‹የማመልከው ፈጣሪ እያለ እንዴት ይህ ይሆናል ? ›› በማለት ከሃይማኖት እና ከዕምነት ውጪ የሚሆኑበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ማኅበረሰቡን አጠቃላይ ሰዎችን የመጥላት አዝማሚያ ይኖራል ጨለማን መፍራት፣ ለመተኛት መስጋት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀላሉ መቆጣት፣ መናደድ፣ መበሳጨት፣ ለኅብረት እና ለጓደኝነት አለመመቸት የጦርነቱ ስነልቦናዊ ጉዳት ውጤት እንደሚኖር አያጠራጥርም ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ከማኅበረሰብ መነጠል፣ ሁልጊዜም በተጠንቀቅ እና በስጋት ውስጥ መኖር፣ በተደጋጋሚ የጭንቀት ሆርሞን በመላው ሰውነት ስለሚሰራጭ በሕይወት ዘመናቸው ከሰዎች ጋር ከመብላት ከመጠጣት ይልቅ መጨነቅ እና መሸሽን የሚመርጡ ይኖራሉ ልባቸው ቶሎ ቶሎ የሚመታ እና የልብ ሕመም፣ ደም ግፊት እንዲሁም ለሌሎች ሕመሞችም የተጋለጡ ይሆናሉ እዚህ ላይ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በጦርነት በሚያጋጥም የሥነልቦና ችግር ምክንያት ከሌሎች ሰዎች ይልቅ በ15 እጥፍ ራሳቸውን ለማጥፋት የተጋለጡ፤ ከሌሎች ሰዎች ይልቅ በአራት እጥፍ ሱሰኛ የሚሆኑበት ዕድል ሰፊ ይሆናል ይላሉ
ሌላዋ የሥነልቦና ባለሞያ ወይዘሮ ሰብለ ኃይሉ በበኩላቸው፤ ጦርነት ከሚያስከትለው ሞት ፣ የንብረት ውድመት እና የአካል ጉዳት በተጨማሪ የሚያስከትለው
የስነልቦና ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ነው የጠቀሱት በዚህ ሳቢያ ተስፋ ማጣት፣ በተለይ ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ የሞተባቸው ደግሞ የብቸኝነት ስሜት የሚፈጠርባቸው ከመሆኑ በተጨማሪ በሕይወታቸው ተስፋ የሚቆርጡበት አጋጣሚም ይፈጠራል ከነዋሪዎች በተጨማሪ ወታደሩም የቅርብ ጓደኛው እና ሌሎችም በቅርብ ሲሞቱ ስለሚያይ ጭንቀት ይኖርበታል፡፡
የጦርነቱ ስነልቦናዊ ጉዳት ሲነሳ ከአዋቂዎች በተጨማሪ ሕፃናት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ያስረዳሉ ሕፃናት ራሳቸውን እና አካባቢያቸውን በቅጡ በማያውቁበት ዕድሜ ይህንን ጦርነት ማስተናገዳቸው የወደፊት ሕልውናቸው ላይ አደጋ ይጋረጣል ማኅበረሰቡ ላይ ዕምነት ያጣሉ፤ ‹‹ለምን ይህ ሆነ? ›› ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ስለማያገኙ ምላሽ በሌላቸው ጥያቄዎች ተወጥረው ይጨነቃሉ በማለት ይናገራሉ፡፡
የማኅበራዊ ስነልቦና ባለሙያ እና የሥነልቦና አማካሪ አቶ ደምመላሽ ይበልጣል በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ጦርነት ሰዎች ከሰዎች ጋር የሚያካሂዱት ውጊያ በመሆኑ የሰዎችን አካል ብቻ ሳይሆን አዕምሯዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነምሕዳራዊ ጉዳዮችን ሳይቀር የሚነካ ነው ጦርነት እና ሥነልቦና የሚያያዙ ነገሮች ሲሆኑ ሰዎች በጦርነት አካላቸው ሲጎዳ ማኅበራዊ ግንኙነታቸው ሲሻክር ሥነምሕዳራቸው ሲቃወስ የአዕምሮ ጤና ችግር ያጋጥማቸዋል በተለይ ባለፈው በሰሜኑ የኢትዮጵያ አካባቢ የነበረው ጦርነት ሲነሳ ንፁሓን በስፋት ሥነልቦናቸው ሊጎዳ እንደሚችል አያጠያይቅም፡፡
በጦርነቱ ጊዜ አስገድዶ መድፈር፣ ሕፃናትን ለጦርነት የማሰለፍ፣ ሰዎችን በእሳት እስከማቃጠል የደረሰ የሰውን ሥነልቦና በእጅጉ የሚጎዱ ተግባራት ሲፈፀሙ እንደነበር ይታወቃል ሰዎችን ማስፈራራት፣ ብሔር ተኮር የሆነ ጥላቻ እና ማዋረድም የነዋሪውን ሥነልቦና የሚጎዳ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም የሚሉት አቶ ደምመላሽ፤ በተጨማሪ ማኅበረሰቡ በየዕለቱ የሚጠቀሙባቸው ወይም አገልግሎት የሚያገኙባቸው ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማትም መፈራረሳቸው በሕዝቡ ስነልቦና ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ቀላል እንደማይሆን ያስረዳሉ
‹‹አንድን ማኅበረሰብ ከአንድ ማኅበረሰብ ጋር የሚያገናኙ መንገዶች እና ድልድዮች መሰበራቸው በራሱ የአዕምሮ ጤና ችግርን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አያጠያይቅም እንኳን ቤተሰባቸው ፊት ለፊታቸው ሲደፈር ማየት ቀርቶ፤ ከሚኖሩበት አካባቢ መፈናቀል እና መራቅ ብቻውን የስሜት ቀውስን እንደሚያስከትል እና የስሜት ቀውስ ደግሞ ወደ አዕምሮ ሕመም የሚያድግ በመሆኑ የጦርነቱ ሥነልቦናዊ ጉዳት ከፍተኛ ሊሆን ይችላል›› ይላሉ፡፡
ብዙ ነገሮችን ማጣት እና እንደማይገኝ ማሰብ ድብርት ውስጥ መክተቱ አይቀርም አሁን ደግሞ ነገሮች እየተረጋጉ ነዋሪው ወደ ቀድሞ ስፍራው እየተመለሰ ቢሆንም፤ ከቁሳዊ መልሶ ግንባታ ባሻገር ሥነልቦናዊ ጉዳቱን ማከም እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል የሚል ስጋት አለባቸው፡፡
በጦርነት ወቅት የሚያጋጥመው የሥነልቡና ቀውስ ሰፊ መሆኑን የጠቀሱት ምሑራኑ ሆኖም ግን መታከም የሚችል መሆኑን ሳይጠቁሙ አላለፉም። ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሳሚ ለሥነልቡና ስብራት ማከሚያ መፍትሔ ያሉትን ሲጠቁሙ፤ ለከፍተኛ የሥነልቦና ጉዳት ተጋላጮች የሆኑ ሰዎች ካለባቸው ችግር እንዲወጡ መጀመሪያ ጦርነቱ ስነልቦናዊ ጫና የፈጠረባቸው መሆኑን እንዲያውቁ እና አምነውም ችግሩን በተለያየ መንገድ እንዲከላከሉ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመው ጉዳቱን እንዲቀንሱ ማድረግ ነው ሌላው በዚህ ጉዳይ ላይ ሙያተኛ የሆኑ ሰዎችን በማሰባሰብ በጥናት ላይ የተመረኮዘ ሥራ እንዲሠሩ ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ሰብለ በበኩላቸው የተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሳሚን ሃሳብ በመጋራት በተጨማሪነት ደግሞ በጦርነቱ የፈራረሱ ትምህርት ቤቶችን መልሶ መገንባት፣ ጤና ጣቢያዎች፣ መንገዶች ፣ መኖሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎች እና ሌሎችንም መልሶ መገንባት በራሱ አካላዊ ድጋፍ ቢመስልም መልሶ መገንባቱ ሥነልቦናዊ ጥቅምም ይኖረዋል ሲሉ የመፍትሔ ሀሳብ ያሉትን አካፍለውናል።
ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የመፍትሔ ሀሳብ ሲሉ ያቀረቡት ደግሞ እናቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ከሁሉም በአዕምሮ ጤና በሥነልቦና ዙሪያ የሚሠሩ ባለሙያዎችን የማኅበረሰቡን ሥነልቡና በማከም ላይ ርብርብ ያስፈልጋል ሲሉ ነው የጦርነት ሥነልቦናዊ ጉዳት ቢባልም ይሔኛው እርስ በእርሳችን የደረሰ ስለሆነ ይቅርታ ማለት ባህላችን ነው ነገር ግን ሥነልቦናዊ ጉዳቱን ለመቀነስና በይቅርታ ለማከም የራሱ የሆነ ጥበብ ይፈልጋል እህት በወንድሙ ፣ ወንድም በእህቱ፤ ወላጅ በልጁ ፤ልጅ በወላጁ ላይ የተነሳበት ሁኔታ ስለነበር በጣም የሚያም በመሆኑ ብዙ ሥራ መሥራት የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።
‹‹ይሄ ጊዜ የሚፈጅ፤ በጥበብ መያዝ መካሔድ የሚገባው ጉዳይ ሲሆን፤ እኔና መሰሎቼ ብዙ አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅብናል የሥነልቦና ወይም የአዕምሮ ቁስል በጣም ከባድ ነው ቁስለቱ የቅርብ ጊዜ ነው ቶሎ ወደ ይቅርታ እና እርቀሰላም መግባትን ይጠይቃል ቶሎ ወደ ንስሐ ፣ ቶሎ ወደ ካሳ መግባትን ይጠይቃል ሽምግልና ያስፈልጋል ተጎጂዎች ቁስላቸው እንዲደርቅ መደረግ አለበት መታወስ ያስፈልጋል ቶሎ ካሳ መሰጠት አለበት ችግርን በሚገባ ፣ስህተትን በሚገባ አምኖ ተቀብሎ በይቅርታ መሔድ አንዱ ለአዕምሮ ቁስል መሻር የራሱን አስተዋፅ የሚበረክት መሆኑን ማስረዳት መፍትሔ ነው” ሲሉ ያብራራሉ፡፡
አቶ ደምመላሽ መፍትሔ ይሆናሉ ብለው የሚያምኑት፤ የሥነልቦና ባለሙያ፣ የአዕምሮ ጤና ባለሞያዎች፣ የማኅበራዊ ባለሙያዎችም ሆኑ የተለያዩ አካላት በጋራ በመንቀሳቀስ እና ንቅናቄ በመፍጠር በስፋት በጦርነቱ አካባቢ የነበረውን እና ያለውን የስነልቦና ጉዳት ለመቀነስ ሊሠራበት ይገባል ብለዋል።
ሌላው ደግሞ መንግሥት የራሱን ሥራ መሥራት አለበት ነገር ግን ጉዳዩ እጅግ ከባድ እና ውስብስብ በመሆኑ ለመንግሥት ብቻ ከመተው ይልቅ ግለሰቦች እና እርዳታ የሚሰጡ ተቋማት ከወደመው ንብረት በተጨማሪ የሥነልቦና ጉዳቱንም በተወሰነ መንገድ ለመቀነስ ጥረት ማድረግ እና በቅንጅት መሥራት አለባቸው የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡
‹‹የጦርነቱ ተጎጂዎች ችግር ውስጥ የገቡት ወደው ባለመሆኑ፤ ይህንን የጦርነቱን ሥነልቦና ቁስል የሚሽርበት ሁኔታ እንዲፈጠር ቢያንስ ዛሬ ተጎጂዎች መብላት እና መጠጣት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ላይ መሠራት አለበት የሚያድሩበት እና የሚመገቡበት ሁኔታ ከተፈጠረ በኋላ በተጨማሪነት ሥነልቦናው ላይም ተመሳሳይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት አለበት እዚህ ላይ ሁሉም የየራሱን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል›› ይላሉ፡፡
የአዕምሮ ጤና ጉዳቱ የራስን ሕይወት እስከማጥፋት የሚዘልቅ ሲሆን፤ ከማብላት እና ከማጠጣት ያልተናነሰ ትኩረት በመስጠት የተለያየ መፍትሔ ለማምጣት ጥረት መደረግ አለበት ለምሳሌ ያህል ማኅበራዊ ሕይወት በራሱ አንዱ የሥነልቦና ሕክምና በመሆኑ የእምነት ተቋማት አባቶች አካባቢው ከጦርነት የጭንቀት መንፈስ እንዲላቀቅን የሥነልቦና ጉዳቱ እንዲቀንስ ምዕመኑን ማረጋጋት እና ማስተማር ላይ መሥራት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡
ወታደሮችም በበኩላቸው ነገሮች እያለፉ፤ ችግሩ እየተፈታ መሆኑን በመግለፅ ሕዝቡን የማረጋጋት ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል መንግሥትም ከዕለት ደራሽ እርዳታ በተጨማሪ መሥራት ይጠበቅበታል ሁሉም በሚችለው አቅም ለተጎጂዎች አለንላችሁ ቢል በራሱ አንድ የሥነልቦና ችግሩን ማቃለል መሆኑን በመጠቆም ነገር ግን ደግሞ የኢትዮጵያ የሥነልቦና ማኅበር (የኢትዮጵያ የሳይኮሎጂ ማኅበር) የመሳሰሉ የሙያ ማኅበራት እና ሌሎችም መንግሥታዊ ያልሆኑ የሙያ ማኅበራት አባላቶቻቸውን በማነቃቃት የዘመቻ ሥራ ቢሠሩና በሚችሉት አቅም አስተባብረው ማኅበረሰቡ ጋር ደርሰው የማማከር የተጠፋፉ ቤተሰቦች የማገናኘት እና ሌሎችም መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎችን ሊሠሩ ይችላሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ይገልፃሉ፡፡
በመጨረሻም አቶ ደምመላሽ፤ ጉዳዩ ሰፊ ጉዳቱም እጅግ ትልቅ ስለሆነ ቀጣይነት ያለው ሥነልቡናን የማከም ሥራ መሠራት አለበት እዚህ ላይ የሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዚህ ዙሪያ መሥራት የሚችሉ የገንዘብ አቅም ካላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሥራት ችግሩን ለማቃለል ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት፡፡
ሁሉም ምሑራን የተስማሙት ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ለኅብረተሰቡ የሚያስፈልገው የተጎዳውን ሥነልቡና በሚያክም መልኩ በእምነት ተቋማት አባቶች ፣በታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ሰፊ ሥራ መሥራት ነው ። ልክ የምግብና የመጠጥ ያህል ተጎጂዎች የሥነልቡና ሕክምና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። የወደሙ መሠረተ ልማቶችን በኅብረት መልሶ መገንባት እና በይቅርታ መተላለፍን ወደፊት ማምጣት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በሁሉም ወገን ጠንካራ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/ 2015 ዓ.ም