በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመው ክህደትና ሠራዊቱ የተጨፈጨፈበት ሁለተኛ ዓመት ባለፈው ጥቅምት 24 በልዩ ሁኔታ ታስቦ መዋሉ ይታወሳል፡፡ የተፈፀመው ግፍ ሁለተኛ ዓመት በሚታሰብበት ዋዜማ መንግሥት ከሕውሓት ጋር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በናጄሪያው የቀድሞው መሪ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ አማካኝነት የሰላም ውይይት አካሂዶ ሕውሓት ጦሩን ሊያወርድ፣ በሀገሪቱም ሰላምን ለማስፈን ተስሟምቷል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያ በተመድ ጉባዔ የዛሬ ሃምሳ ዓመት በናይጄሪያ ቢያፍራ የነበረውን ጦርነት ለማብረድና ዕርቅ ለማውረድ ጥረት እያደረገች መሆኑ በጋዜጣችን ተዘግቦ ነበር፡፡በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ አምዳችንን ያንን ታሪክ የሚያስታውሰንን ዘገባ መለስ ብለን እንቃኛለን፡፡ በተጨማሪም በዚያ ወቅት አንድ ለማኝ ሞተው በማሰሮ 430 ብር ስለመገኘቱ በጋዜጣው ተዘግቦ የነበረን ክስተት አካተናል፡፡ መቼም ይህ ክስተት በዜና የተዘገበው በወቅቱ 430 ብር ትልቅ ዋጋ ስለነበረው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሐረር አጭር ቀሚስ በለበሱ ላይ በፖሊስ ስለሚደረገው ቁጥጥር እና ሌሎችም ዜናዎችንም አካተን እነሆ ብለናል፡፡
በናይጄሪያ ውስጥ ሰላም እንዲገኝ ኢትዮጵያ ትጥራለች
-ከተማ ይፍሩ በተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ
ከተባበሩት መንግሥታት፤(ሮይተር) ኢትዮጵያ የናይጄሪያን የርስ በርስ ጦርነት ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት እንዲቀጥል አሳሰበች፡፡
ማሳሰቢያውን ለተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ናቸው፡፡ ክቡርነታቸው በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀመንበርነት የሚመራው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የናይጄሪያ አስታራቂ ኮሚቴ ፤ጦርነቱን ለማቆም ከፍ ያለ ጥረት ማድረጉን ገልጠዋል፡፡
ክቡር አቶ ከተማ መንግሥታቸው ይህ አሳዛኝ ዕልቂት በሰላማዊ መንገድ ፍጻሜ እንዲያገኝ የሚያደርገውን ጥረት የማያቋርጥ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ክቡር አቶ ከተማ፤ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያለውን ልዩነት ለማስወገድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቂ እርምጃ ስላልወሰደ ፤ ወደፊት ይህን አጉል እምነት ለማገድ በቂ የሆነ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታትድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተገኙትን የኢትዮጵያ መልእክተኞች የሚመሩት አቶ ከተማ ይፍሩ ፤በደቡብ አፍሪካና በሮዴዚያ ውስጥ ያሉት የጥቂት ነጮች መንግሥታት፤ሥፍራዎቻቸውን ለይበልጡ ጥቁር አፍሪካውያን ሕዝብ መንግሥታት እንዲለቁ በጉዳዩ ኃያላን ሀገሮች እንዲተባበሩ አሳስበዋል፡፡ፖርቱጋልም ሕገወጥ ሥልጣኗን መከታ በማድረግ በአፍሪካውያን ላይ የምትፈጽመውን በደል እንድታቆም መጠየቃቸው ታውቋል፡፡ክቡር ሚኒስትሩ ስለ አፍሪካ ጉዳዮች ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከዊልያም ሮጀርስ ጋር ተነጋግረዋል፡፡
( መስከረም 29 ቀን 1962 ከወጣው አዲስ ዘመን )
ለማኙ አቶ ወልደማርያም ሞቱ
–ከራስጌያቸው ማሰሮ 430 ብር ተቀብሮ !
አሰበ ተፈሪ ፡-(ኢ-ዜ-አ-) በሐረርጌ ጠቅላ ግዛት በጨርጨር አውራጃ በዶባ ወረዳ በልመና ይተዳደሩ የነበሩትና በሕመም ሞት ባለፈው ጳጉሜ ፫ ቀን ፷፩ ዓ ም ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩት በአቶ ወልደ ማርያም መኖሪያ ጐጆ ውስጥ በማሰሮ የተቀመጠ ፬፻፴፫ ብር ከ፺ ሳንቲም መገኘቱን የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በልመና ይተዳደሩ የነበሩት እኝሁ አቶ ወልደማርያም ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ወዲህ ይኖሩባት የነበረችው አነስተኛ ጐጆ ሳትከፈት ቆይታ ነበር፡፡ሁኔታውን ለማጣራት የወረዳው ገዢ ፤የወረዳው ፖሊስ ረዳት አዛዥና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ሰሞኑን ጐጆዋ ተከፍታ ስትፈተሸ በሟቹ ራስጌ በነበረው ማሰሮ ፬፻፴፫ ብር ከ፺ ሳንቲም ሊገኝ ችሏል፡፡ከተገኘው ገንዘብ ውስጥ ፪፻፺፭ ብር ከ፶ ሳንቲም ነጭ ሽልንግ ፤፹ ብር ከ፳፭ ሳንቲም ባለ ሃያ አምስት ሳንቲም መሆኑ ተገልጧል፡፡
ከተገኘው ገንዘብ ውስጥ ለከሰል ፲፭ ብር ከ፸፭ ሳንቲም ወጪ ሲሆን ፤ተራፊውንም ፬፻፲፰ ብር ከ፲፭ ሳንቲም የዶባ ወረዳ ግዛት ፖሊስ ጽሕፈት ቤት መረከቡ ተረጋግጧል፡፡
ስለዚህ የሟች ወራሽ ወይም ተወላጅ የሆነ ሰው ማስረጃውን አቅርቦ ገንዘቡን ለመረከብ መቻሉን የአውራጃው ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል ፡፡
( መስከረም 29 ቀን 1962 ከወጣው አዲስ ዘመን )
የአጭር ቀሚስ ቁጥጥር በሐረር
ሐረር፡ (ኢ-ዜ-አ-) በሐረር ከተማ ውስጥ አጫጭር ቀሚስ እየለበሱ በሚዘዋወሩት ሴቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የሐረር አውራጃ ፖሊስ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ኃይለሚካኤል ገብሬ ገለጡ፡፡
በተደረገው ቁጥጥር መሠረት በሐረር ከተማ ውስጥ የሀገርን ባህል የሚያጎድፍ ልብስ ለብሰው የተገኙት ፷፯ ልጃገረዶችና ሴቶች ፪ኛ ፖሊስ ጣቢያ እየቀረቡ ዳግመኛ ላለመልበስ መፈረማቸውን ሌተናል ኮሎኔል ኃይለ ሚካኤል አስረድተዋል፡፡
ይኸው አፈጻጸም ለወደፊቱ በየጣቢያው ተላልፎ በሚገባ በሥራ ላይ እንደሚውል ታውቋል፡፡
በዚሁ ይዞታ በከተማው ውስጥ ይታይ ነበረው የአጭር ቀሚስ ለባሾች ቁጥር መቀነሱንና ለወደፊት ጨርሶ እንደሚጠፋ ሌተናል ኮሎኔል ኃይለሚካኤል ገብሬ እምነታቸው መሆኑን ገልጠዋል፡፡
( ጥቅምት 2 ቀን 1962 ከወጣው አዲስ ዘመን )
የድኩላ ሥጋ ሰው ገደለ
–አሥሩ በጠና ታመዋል
ነቀምቴ፤(ኢ-ዜ-አ-) በወጥመድ ተይዞ የተገደለ የድኩላ ሥጋ በተመገቡ የአንድ ቤተሰብ አባል በሆኑ አሥራ አንድ ሰዎች ላይ የሞትና ጤና ጉዳት መድረሱ ተገለጠ፡፡ ቡልቻ ቶኬ የተባለ ሰው መስከረም ፳፪ ቀን ፷፪ ዓ-ም – አንድ ድኩላ በወጥመድ ይዞ ከገደለ በኋላ ወደ ቤት ወስዶ አሥራ አንዱም ቤተ ሰቦች ሥጋውን መመገብ ጀመሩ፡፡በዚሁ ጊዜ ከመካከላቸው ቡርሜሣ ወዳጆ ይባል የነበረው ወዲያውኑ ታምሞ ሲሞት ፤ የቀሩት ዐስሩ ሰዎች በጠና ታምመው በሕክምና ላይ ይገኛሉ፡፡
የድኩላው ሥጋ በመመገብ የሞትና በጤና ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በወለጋ ጠቅላይ ግዛት በቄለም አውራጃ የአንሲሎ ወረዳ ኗሪ መሆናቸው ታውቋል፡፡
(ጥቅምት 6 ቀን 1962 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/ 2015 ዓ.ም