በስፖርት ክብርንና ድልን ለማግኘት አቋራጭ መንገድን መከተል በተለይ በአትሌቲክስ ስፖርት ጎልቶ ይታያል። ታዲያ በዚህ ስፖርት በተሻለ ውጤታማ የሆኑ አገራት በዓለም አቀፍ የጸረ አበረታች ቅመሞች ተቆጣጣሪ ተቋማት በአይነቁራኛ ነው የሚጠበቁት። በአትሌቲክስ ስፖርት በተለይም በረጅም ርቀቶች የበላይነቱን የተቆጣጠሩት የምስራቅ አፍሪካ አገራት አትሌቶችም ለዚህ ጉዳይ ተጋላጭ መሆናቸው ይነገራል። በእርግጥም ተጠቃሚነቱ በተለያዩ ጊዜያት በመረጋገጡ ክትትሉም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ከምስራቅ አፍሪካዊያኑ የአትሌቲክስ አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን በ2010 ዓ.ም ስድስት አትሌቶች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ለቅጣት መዳረጋቸውን የኢትዮጵያ ጸረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያሳያል። ከ2011 ዓ.ም-2014 ዓ.ም ባሉት እያንዳንዱ ዓመታት ደግሞ ሶስት ሶስት አትሌቶች ተጠቃሚ መሆናቸው ተረጋግጧል። ይህ ቁጥር እንደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቢሆንም ከሌላው ዓለም አንጻር ከስጋት ቀጣና የወጣ ነው። ይህ ሊሆን የቻለውም አገሪቷ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ የሰራችበት በመሆኑ በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተምሳሌት አድርጓታል።
በአንጻሩ የምንጊዜም የኢትዮጵያ ተፎካካሪ የሆነችው ኬንያ በአበረታች ቅመሞች ማጥ መውጣት አልቻለችም። ይኸውም ንጹህ ተወዳዳሪነትን ተግባራዊ እያደረጉ ላሉት አትሌቶች ውጤት እንዲያጡ በባዕድ ነገር እገዛ የሚሮጡት ደግሞ የማይገባቸውን ድል እንዲያገኙ ማድረጉ አሳሳቢ ነው። ኬንያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ከአትሌቲክስ ስፖርት ሙሉ ለሙሉ ከተወገደችው ሩሲያ ልምድ ያልወሰደና ወደ ቅጣት የመንደርደር ሁኔታ የሚታይበት መሆኑም ግልጽ ነው። በዚህ የፈረንጆች ዓመት ብቻ በአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት ተጠያቂ የሆኑ ኬንያውያን አትሌቶች ቁጥር 20 መድረሱን አፍሪካን አትሌቲክስ ዩናይትድ የተባለ ድረገጽ ያስነብባል።
በዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የአበረታች ቅመሞች ላይ ከሚሰራው አካል (AIU) የተገኘው ማስረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ፤ በቅርቡ እንኳን ሁለት አትሌቶች ባልተገባ ሁኔታ መሮጣቸው ተረጋግጧል። የመጀመሪያዋ አትሌት ያለፈው ዓመት የቦስተን ማራቶን አሸናፊ የነበረችው ዲያና ኪፕዮኬ ስትሆን፤ የተከለከለ መድሃኒት መጠቀሟ እንዲሁም ይህንን ለመሸፈንም የተሳሳተ መረጃ በመስጠቷ ከድሏ ማግስት ነው የተረጋገጠባት። ቤቲ ሌምፐስ ደግሞ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የፓሪስ ግማሽ ማራቶን አሸናፊ ስትሆን አትሌቷ ርቀቱን ሮጦ ለመጨረስ የፈጀባት ጊዜም 65:46 ነበር። አትሌቷ ያልተገባ መድሃኒት ከመጠቀሟ ባለፈ የተሳሳተ መረጃ መስጠቷ ተረጋግጦባት ለቅጣት ተዳርጋለች።
በተያዘው ዓመት ብቻ ሌሎች ሶስት አትሌቶችም በተመሳሳይ ሁኔታ ዓለም አቀፉ የጸረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ የከለከላቸውን መድሃኒቶች ተጠቅመው በመገኘታቸው ለሶስት ሶስት ዓመታት ዕገዳ መዳረጋቸውን መረጃው ያመላክታል። የፍራንስ 24 ዘገባ ደግሞ 25 ኬንያውያን አትሌቶች በአበረታች ንጥረነገሮች ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጦባቸው ለቅጣት መዳረጋቸውን ነው ያስነበበው። እንደ መረጃው ከሆነም 19 የሚሆኑት በዚህ ዓመት ተጠቅመው የተገኙ ናቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞም የዓለም የማራቶን ክብረወሰን ባለቤቱና ዕውቁ ኬንያዊ አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ ሁኔታውን ‹‹አሳፋሪ›› ሲል ነበር የገለጸው። ከኬንያ አትሌቲክስ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት በርናባስ ኮሪር ሁኔታውን በጥንቃቄ እየተመለከቱት መሆኑን ነው የገለጹት። የቀድሞው አትሌት ኬንያ የሩሲያ አትሌቲክስ ባቀናበት መንገድ እየተጓዘች ስለመሆኑም ነው ያስጠነቀቁት።
በዚህ ዓመት በኬንያ ከተመዘገቡት የስፖርት አበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት ቅሌት በተለይ የታየው በጎዳና ላይ ሩጫ አትሌቶች ነው። ታዲያ ይህ ጉዳይ የሚያሳየው አትሌቶች ከእነዚህ ውድድሮች በሚያገኟቸው ከፍተኛ መጠን ላለው የገንዘብ ሽልማት ሲሉ ለተጠቃሚነት እንደሚዳረጉ ነው። የኬንያ ጸረ አበረታች ቅመሞች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ኃላፊ የሆኑት ሳራ ሺቡትስ፤ አብዛኛዎቹ አትሌቶች ከደሃ ቤተሰብ የተገኙ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። በመሆኑም በዓለም አቀፉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የቆየው ውድድር ዳግም መመለሱ አትሌቶች ለገንዘብ ሲሉ ተገቢ ያልሆነ ነገር ውስጥ እንዲገኙ ያደረጋቸው መሆኑንም ነው የገለጹት። በመሆኑም ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል የተደረገው ዓይነት ርብርብ የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነትን ለመግታት የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት እንዳለበትም ነው ኃላፊዋ የገለፁት።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም