ፎርደስግራስ፣ አልፋአልፋ፣ ሉሲኒያ፣ ላብላብ፣ የላም አተር (ካኦፒ)፣ ፒጃምፒ (የእርግብ አተር)፣ ፎደርቢት (የከብት ድንች)፣ ዲስሞዲየም፣ ሲናር፣ ፋለሪስ፣ ፓኒኮም፣ የሳር፣ የጥራጥሬና የሐረግ ዝርያዎች እንደ ሆለታ፣ ባኮ፣ አዳሚ ቱሉ ባሉ የእርሻ ምርምር ማዕከሎች በምርምር ተሻሽለው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማረጋገጫ የተሰጣቸው ለእንስሳት መኖ የሚውሉ ዝርያዎች ናቸው።
ፎስፈረስና ካልሺየም የተባሉ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በውስጣቸው የያዙት እነዚህ የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎች በጎችና ፍየሎችን ጨምሮ የወተት ላም ምርታማነትን ለመጨመር፣የሥጋ ከብቶችን ለማደለብ ተመራጭ መሆናቸውን ተጠቃሚዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የዝርያዎቹ ምርታማነት የሚለያይ ቢሆንም፣ አንድ ጊዜ በማሳ ላይ ተዘርቶ ደጋግሞ ምርት የሚሰጥ ዝርያም አለ። በአንዴ የተመረተውንም ረዘም ላለ ጊዜ በመጠቀም የመኖ እጥረትን ማቃለል እንደሚቻል መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በድርቆሽ መልክ አዘጋጅቶ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል፤ ይህም በተለይ በበጋው ወቅት የሚያጋጥመውን የመኖ እጥረት በማቃለል ረገድ የጎላ ሚና አለው። በአንድ ሄክታር መሬት ላይ አራት ኪሎ ግራም የተሻሻለ የመኖ ዘር ቢዘራ እስከ ስድስት ሜትር ኩብ ምርት ማግኘት እንደሚቻል ከአስር ዓመት በላይ በእንስሳት መኖ፣ የደን ዛፍ ችግኝ፣ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ዘር ብዜት ሥራ ላይ የቆዩት መንግሥቱ ተሰማ የእጽዋት ዘር አምራችና አቅራቢ ድርጅት ባለቤት አቶ መንግሥቱ ተሰማ ያስረዳሉ።
አቶ መንግሥቱ እንደሚገልጹት፤ የተለያየ ዝርያ ያላቸውን የእንስሳት መኖ የዘር ብዜት የሚያከናውኑት በሰሜን ሸዋ በ10ሄክታር መሬት፣ በወላይታ ላይ ደግሞ በ21 ሄክታር መሬት እንዲሁም ከአርሶ አደሮች ጋር በጋራ በመሆን ነው። በተለይም ከአርሶ አደሩ ጋር ሲሰሩ ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት መሰብሰብ ባለው ሂደት ክትትል ያደርጋሉ።
በዚህ ሂደትም አርሶ አደሩ ተሞክሮ ያገኝበታል። መሬቱን ለዘር ብዜት በማዋሉም ገቢ ያገኛል። ተረፈ ምርቱን ደግሞ ለእንስሳቱ መኖ በመጠቀም እንዲህ በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ ይሆናል።
በዚህ መንገድ ድርጅታቸው እስከ ሁለት ሺ አምስት መቶ ኩንታል የተለያዩ የመኖ ዝርያዎች በማልማት ለተጠቃሚው እንዲደርስ ያደርጋል። እንደ ዝርያው አይነት የዋጋ ልዩነት ቢኖረውም፣ አርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ ያገኛል። ከፍተኛው የመኖ ዘር ዋጋ በኪሎ ግራም አስከ ሁለት ሺ አምስት መቶ ብር ቢሆንም፣ በኪሎ ግራም በ40 ብር ሊገዛቸው የሚችሉ ዝርያዎች በመኖራቸው ሁሉም እንደአቅሙና ፍላጎቱ መጠቀም ይችላል።
ድርጅታቸው በአብዛኛው የመኖ ዝርያ አቅርቦቱን የሚያከናውነው በመንግሥት የጨረታ ሂደት ውስጥ በማለፍ ሲሆን፣ አርሶ አደሩን በተለያየ መንገድ የሚረዱ እንደ የዓለም ምግብ ድርጅት (ፋኦ) እና በኔዘርላንድ ድርጅት የሚደገፉ አርሶ አደሩን በግብርና የሚያግዙ ተቋማትም ግዥ ያከናውናሉ። ድርጅቱ በግላቸው ግዥ የሚፈጽሙ አርሶ አደር ደንበኞችም አሉት።
የተሻሻለ መኖ ዘር ብዜቱ ብዙ ሂደት ውስጥ አልፎ ጥቅም ላይ እንደሚውል የጠቀሱት አቶ መንግሥቱ፣ የዘር ብዜት የሚከናወንበት የማሳ ዝግጅት፣ የዘሩ ጥራትና አዘራሩ፣ በአበባው ወቅት ደግሞ የብቅለት መጠኑ በባለሙያ ክትትል እንደሚደረግበት ይገልጻሉ። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ምርቱ ከማሳ ላይ ከተሰበሰበ በኋላም ናሙና ተወስዶ በቤተሙከራ ፍተሻ ይደረግበታል። ድርጅታቸው ይህን ሁሉ የፍተሻ ሂደት የሚያልፈው በኦሮሚያ ክልል የደረጃና ቁጥጥር ባለሥልጣን በሚከናወን ክትትልና ቁጥጥር ነው። ከማሳ የተሰበሰበው የመኖ ዘር በብጠራና በለቀማ የበለጠ ጥራቱ እንዲረጋገጥም ድርጅታቸው ለዚህ ሥራ ሠራተኞችን ቀጥሮ ያሰራል።
የማከማቻ መጋዘንም ሰርቷል። ይህ ሁሉ ዝግጅት ጥራቱን የጠበቀ የመኖ ዘር ተጠቃሚው ዘንድ ለማድረስ ሲባል የሚደረግ እንደሆነ አቶ መንግሥቱ ያስረዳሉ። ለዜጎችም የሥራ ዕድል የፈጠረ ተቋም መሆኑም ሌላው የድርጅቱ መገለጫ ነው።
እርሳቸው እንዳሉት፤ መኖውን ለማምረት ያዘጋጁትን የዘር አይነት እና የዘር ብዜቱ የሚከናወንበት የእርሻ መሬት መጠን አመታዊ እቅድ ያወጣሉ። እቅዳቸውንም ለኦሮሚያ የግብርና ግብአት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስቀድመው ያቀርባሉ። እንዲህ የቅድመ እቅድ ዝግጅት ተደርጎ፣ በባለሙያዎችም ክትትልና ቁጥጥር ሥራ ተከናውኖ የመኖ ዘር ብዜት ሥራ በጥራት ውድቅ ወይንም ከተቀመጠው መሥፈርት በታች የሚሆንበት አጋጣሚ ስለሚፈጠር ያልተቋረጠ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ነው አቶ መንግሥቱ የተናገሩት።
አቶ መንግሥቱ በሥራው በቆዩባቸው አመታት በክፍተቶች ያጋጠሟቸውንና በጥንካሬም ያዩዋቸውን መልካም ጎኖች ገልጸውልናል። እርሳቸው ከአስር አመት በፊት የመኖ ዘር ብዜት ሥራ ውስጥ ሲገቡ በአርሶ አደሩ በኩል ዘሩን ለመጠቀም የነበረው ፍላጎት እጅግ አናሳ ነበር። ለአንዳንድ አርሶ አደሮች በነፃ በመስጠት እንዲጠቀሙ ለማበረታታትም የሞከሩባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። አንድ ቀን ፍላጎት እንደሚጨምር ግን እርግጠኛ በመሆን የጀመሩትን ጥረት ቀጠሉ።
ቀድመው የተነበዩትን አሁን ላይ ማየት ችለዋል። በዚህ ወቅት የተሻሻለ የእንስሳት መኖ ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል። መንግሥትም የተሻሻለ የእንስሳት መኖ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት መስጠቱም አስፈላጊነቱን ያረጋግጣል።በአፋር፣ ባሌ፣ ሶማሌ ቆላማ የአገሪቱ አካባቢዎች የእንስሳት መኖ በመሥኖ እንዲለማ ጭምር በመንግሥት እንቅስቃሴ መደረጉ የዘር ብዜትና ልማት ሥራን ቀድመው ለጀመሩት ትልቅ ብርታትና የበለጠ የሚያነሳሳ ነው።
አገራዊ ተነሳሽነቱ ቀድሞ ተጀምሮ ቢሆንና የተሻሻለ መኖ ልማቱ ቢጠናከር የኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት ምንጭ የሆኑት የቦረና ከብቶች በውሃና በመኖ እጥረት ለድርቅ ባልተጋለጡና ብዙ እንስሳትም ለከፋ ጉዳት ባልተዳረጉ ነበር ይላሉ። ከዚህ በኋላም የተጀመረው ተነሳሽነት ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ባይ ናቸው።
አቶ መንግሥቱ በተግዳሮት ካነሱት አንዱ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘው ነው። የዘር ብዜቱን ሲያከናውኑ በራሳቸው የጥራት ደረጃውን እያረጋገጡ የሚያመርቱበት ሂደት ቢኖር በሥራቸው የበለጠ እርግጠኛ ለመሆን ያግዛቸዋል።
በቅርቡ በስካይላይት ሆቴል የተካሄደው የዶሮ ኤክስፖና ሰባተኛው የእንስሳት ሀብት ዐውደርዕይ ላይ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ቢቀርቡም እርሳቸው የሚፈልጉት ቴክኖሎጂ አልገጠማቸውም። እሳቸው ግን ተስፋ አልቆረጡም ቴክኖሎጂውን ካገኙ በራሳቸው ለመሥራት ቤተሙከራ (ላብራቶሪ) አዘጋጅተዋል። ቴክኖሎጂውን ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ ላይም ይገኛሉ። በዚህ በኩል የመንግሥት ድጋፍን ይፈልጋሉ።
የዘር ብዜት የሚከናወንበት የእርሻ መሬትም በትራክተር ቢታረስና ከአጨዳ እስከ ምርት መሰብሰብ በዘመናዊ መሣሪያ ቢታገዝ በምርታማነትም በጥራትም ተጠቃሚ መሆን ይቻላል ብለዋል። ቴክኖሎጂ መጠቀም ከተቻለ ከዘር ብዜቱ በተጨማሪ ለአመጋገብ ምቹ የሆነ መኖ ማዘጋጀት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ኤክስፖው መዘጋጀቱ ቴክኖሎጂዎችን ለማግኘት፣ አንዱ ከሌላው የልምድ ልውውጥ ለማድረግ፣ የገበያ እድል ለማስፋት ከማገዙ በተጨማሪ መንግሥት በመኖ ዘር ብዜትና ልማት ላይ የተሰማሩትን ማሳተፉ ለመኖ ልማቱ መስፋፋት የሰጠውን ትኩረት ማሳያም አድርገው ወስደዋል።
ሌላው ያነሱት በምርምር ተቋማት የወጡ የተሻሻሉ የመኖ ዘሮች ጥቅም ላይ ከዋሉ ከተወሰኑ አመታት በኋላ እየቀነሱ ስለሚሄዱ ቶሎ መተካት የሚኖርባቸው መሆኑን ነው። መሥራች ዘር በፍጥነት የመተካቱ ሁኔታ እጅግ የዘገየ በመሆኑና በአቅርቦት እጥረት በሚፈለገው ልክ የመተካቱ ሥራ እየተከናወነ አለመሆኑን ይጠቁማሉ። በዚህ ረገድ በምርምር ተቋማት በኩል ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ።
እሳቸው አንዳሉት፤ ዘርፉን በገንዘብ ወይንም ለመደገፍ የሚደረግ ጥረት የለም። በተለይ በባንኮች በኩል ብድር አልተመቻቸም። ለሥራ መነሻም ሆነ ለማስፋፋት ካፒታል ቢመቻች የበለጠ በመሥራት አቅርቦትን ማሳደግ ይቻላል።
የመኖ ማባዣ መሬት ለማግኘትም ተግዳሮት መኖሩን የጠቆሙት አቶ መንግሥቱ፣ አሁን ላይ የሚንቀሳቀሱት ከአርሶ አደር በኪራይ በሚያገኙት የእርሻ መሬት ላይ መሆኑን ይገልጻሉ፤ የመሬት የኮንትራት ዋጋም ውድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከመንግሥት መሬት ቢያገኙ ግን በስፋት በማምረት አርሶአደሩ በጥራት፣ በአይነትና በተመጣጣኝ ዋጋም ዘር የሚያገኝበት እድል ይፈጠራል ብለዋል።
የተሻሻለ የመኖ ልማት በኩታገጠም (ክላስተር) ቢታገዝ ውጤታማነቱ ከፍተኛ እንደሚሆንም ሀሳብ ሰጥተዋል። እርሳቸው፤ በተሻሻለ የእንስሳት መኖ ዘር ብዜትና ልማት ላይ የተሰማሩ ተሰባስበው ማህበር በመመሥረት ዘርፉ አድጎ ውጤታማ የሚሆንበትን ለማመቻቸት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውንና ከሁለት አመት በፊት ማህበር መሥርተው በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
አቶ መንግሥቱ ከዘር ብዜት ማሳ ሰብስበው በብጠራና በለቀማ በጥራት አዘጋጅተው በማገዝ ለገበያ ዝግጁ ያደረጉትን የተሻሻለ የመኖ ዘር የማየት ዕድሉን አግኝተናል። እይታን የሚስቡ የተለያዩ ዘርፎችን ነው ያየነው። ከሙያው ውጭ ለሆነ ሰው ዘሮቹ ወደ ሳርነት ተቀይረው ለመኖ ይውላሉ ብሎ ለመቀበል ያዳግታል። ዘሩን ከባእድ ነገር ንክኪ ነፃ እንዲሆን ተደርጎ በመጋዘን ውስጥ በማስቀመጥ የተደረገውንም ጥንቃቄ ተመልክተናል። ስማቸው ተለጥፎበት በጠርሙስ ውስጥ የተቀመጡት የተለያዩ የመኖ ዘሮችም ትኩረትን ይስባሉ። በዚህ መንገድ የተዘጋጀ የተሻሻለ የእንስሳት መኖ በኢትዮጵያ ውስጥ ተዘጋጅቶ መቅረቡ ደስ የሚያሰኝ ሆኖ ነው ያገኘነው።
አቶ መንግሥቱ በሥራቸው ደስተኛ መሆናቸውን ከፊታቸው ገጽታ፣ ለሙያውም ቅርበት እንዳላቸው ከገለጻቸው መገንዘብ ችለናል። እርሳቸው እንደነገሩን ትምርታቸው ከግብርና ጋር የተያያዘ ከመሆኑ በተጨማሪ በዘርፉ በመንግሥት ተቋም ተቀጥረው ለአስር ዓመት ያህል አገልግለዋል። በግላቸው ወደ ሥራው ገብተው ለመምራት ያልተቸገሩበት ሚስጥርም የሙያው ባለቤት በመሆናቸው ነው።
ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ፣ በዓለምም ታዋቂ ሆና በተሻሻለ የመኖ ዝርያ የእንስሳት ምርታማነት እንዲጨምር ባለመደረጉ ከሌላው ዓለም ወደኋላ መቅረቷን በቁጭት ይገልጻሉ። ይህን ለመለወጥ እርሳቸውን ጨምሮ በዘርፉ ላይ የሚገኙት ጥረት ወሳኝ እንደሆነና የሚችሉትንም እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ከእርሻ ሥራ ጎን ለጎን ከብቶችን በማድለብና ከሚያረቧቸው የወተት ላሞች የሚያገኙትን የወተት ምርት ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ላለፉት 12 ዓመታት ሲሰሩ መቆየታቸውን ያጫወቱን በዓለምጤና አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ዘውዴ እሸቱ ሲናር የተባለውን የተሻሻለ የመኖ ዝርያ ቀድመው ለከብቶቻቸው አለመመገባቸውን በቁጭት ይገልጻሉ። ሲናር የተባለውን የመኖ ዘር በጓደኛቸው አማካኝነት ከአቶ መንግሥቱ በነጻ አግኝተው መጠቀም ከጀመሩ ሁለት አመት ሆኗቸዋል። ቀደም ሲል ፋጉሎ በሚባለው የዘይት ተረፈ ምርት አንድ ከብት አደልቦ ለገበያ ለማድረስ እስከ አምስት ወር ጊዜ ይወስድባቸው ነበር። ፉሩሽካ ከሚመግቧቸው የወተት ላሞች የሚያገኙት የወተት መጠንም አነስተኛ ነው። ሲናር መኖን ለከብቶቻቸው መመገብ ከጀመሩ ወዲህ ግን በሶስት ወር ጊዜ አደልበው ለገበያ ማቅረብ ችለዋል። የላሞቻቸው የወተት ምርታማነትም ጨምሯል። የከብቶቻቸው ሰውነትም ከቀድሞው የተሻለ ሆኖ ነው ያገኙት።
አርሶ አደሩ ስለአዘራሩና አጠቃቀሙም እንደገለጹት፤ ሰብል በተሰበሰበ ማሳ ላይ ነው የመኖ ዘሩን የሚዘሩት። መኖው በመጠኑ ወፍራም ሲሆን፣ በመኮትኮት (ቾፕ) በማድረግ ከሌላ ግብአት ወይንም ገለባ ጋር በመቀላቀል ነው ለበሬዎቻቸው የሚሰጧቸው። ለወተት ላሞች ደግሞ ፉሩሽካ ከሚባለው ግብአት ጋር ይመግቧቸዋል።
ለከብቶቻቸው የተሻሻለ መኖ ማቅረብ በመቻላቸው በዚህ ወቅት ከብቶቻቸውን የሣር ግጦሽ ወደ ሚገኝበት ለማሰማራት የሚያጋጥማቸውን የእረኛ ችግር አቃልሎላቸዋል።ልጆችም ትምህርት ቤት ስለሚውሉ የሚጠብቅ የለም። በአሁኑ ወቅት ግጦሽም አይገኝም። በተለይ በጋ ላይ የመኖ እጥረት የከፋ በመሆኑ ክፍተቱን ይሞላላቸዋል።
አርሶ አደሩን በአካባቢያቸው ስላለው ተሞክሮም ጠይቀናቸው እርሳቸውን ጨምሮ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው አርሶ አደሮች ናቸው መኖውን መጠቀም የጀመሩት። የግጦሽ ሣር መጥፋቱና ከእረኛ ጋርም ተያይዞ እየተቸገሩ በመሆናቸው እንዲሁም ቀድመው የጀመሩት ያገኙትን ጥቅም በማየት ተሞክሮ ለማግኘት አንዳንዶች ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተሻሻለው የመኖ ዝርያ ላይ ያለው ግንዛቤ ቢዳብርና አቅርቦትም ቢኖር ከፍተኛ ለውጥ እንደሚገኝበትም ገልጸዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም