ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ትምህርቱ እንዴት ነው? በደንብ ተጀምሯል አይደል? እንደውም የሴሚስተሩ ፈተና እየተቃረበ እንደሆነ ይሰማኛል። ስለዚህም በደንብ እያጠናችሁ እንደሆነ አስባለሁ። ደግሞ እናንተ ጎበዞች ስለሆናችሁ ለፈተና ብቻ በሚል አትዘጋጁም። ሁልጊዜ አንባቢ ናችሁ። ይህንን ግን አጠናክራችሁ መቀጠል አለባችሁ። ምክንያቱም አንባቢ ካልሆናችሁ ውጤታማ መሆን አትችሉም። በዚያ ላይ ህልማችሁ ላይ በምንም መልኩ አትደርሱም።
ልጆች ምን መሆን ትፈልጋላችሁ? መምህር፣ ዶክተር፣ ፖሊስ፣ ኢንጂነር፤ ተመራማሪ ወዘተ እያላችሁ ዘረዘራችሁ አይደል? ግን ይህንን ማወቅ ብቻ ህልማችሁ ላይ አያደርሳችሁም። ከዚያ አለፍ ያለ ተግባር መከወን አለባችሁ። አሁን ባላችሁበት ደረጃ ማድረግ የምትችሉት ደግሞ አንድና አንድ ነው። ፍላጎታችሁን መሰረት አድርጋችሁ መንቀሳቀስና በትምህርታችሁ ጎበዝ መሆን። ይህንን እውን ያደረጉ ሁለት እህትማማቾችን ለዛሬ ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ። ስለዚህም ከእነርሱ ተሞክሮ ወስዳችሁ ህልመኛ ብቻ ሳይሆን ታታሪም ልጅ መሆን አለባችሁ።
መጀመሪያ ያነጋገርኳት ልጅ አኒታ ሙሴ ትባላለች። እድሜዋ ስምንት ቢሆንም በጣም ተግባቢና ንቁ ልጅ ናት። ሰው በጣም ትወዳለች፤ ያልገባትን መጠየቅ፣ የማታውቀውን ጠይቆ መረዳትም መለያ ባህሪዋ ነው። በትምህርት ቤቷ በጣም ጎበዝ ተማሪ ስትሆን በየክፍል ደረጃው ላይ የተማሪዎች ተወካይ በመሆን ተማሪዎችን ታገለግላለች። አሁንም ይህንኑ ተግባሯን እንደቀጠለች ነው።
ልጆችዬ አኒታ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን፤ ፊሊፐርስ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ነው የምትማረው። በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎችን በማገዝ በኩል ያላሰለሰ ጥረት የምታደርግ ልጅ ነች። በዚህም ተማሪዎች በጣም ይወዷታል። እርሷም ብትሆን ፍቅሯንም ሆነ እውቀቷን እንዲሁም ያላትን ነገር ሳትሰስት ትሰጣቸዋለች።
አኒታ መሆን የምትፈልገው ጠቅላይ ሚኒስትር ነው።
ምክንያቷ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ በተፈጥሮም ሆነ በእውቀት የታደለ የለምና ዓለም አገራት ይህንን እንዲያውቁ ማድረግ ትፈልጋለችና ነው። በተጨማሪም በሀገራችን የሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ባለመኖሩና አገር በመምራት ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ሀላፊነት ለመወጣት ስለምትፈልግ ነው።
‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን በደንብ አገርን ማወቅ ያስፈልጋል፤ አገር ወዳድ መሆንም እንዲሁ። ከዚህ ትይዩ በትምህርት ጎበዝ መሆን ግድ ነው›› ትላለች። ስለዚህም ለዚህ የሚያበቃትን ሥራ ከወዲሁ እያከናወነች ነው። አንደኛው ትምህርቷን በአግባቡ መከታተልና በፕሮግራም ማጥናት ነው። ለዚህ ደግሞ አክስታችን የሚሏት ሩት የምትባል አስጠኚ አለቻቸውና በብዙ መልኩ ታግዛቸዋለች። ጨዋታቸውን ጭምር ከትምህርት ጋር በማያያዝ ስለሚጫወቱ ውጤታማ ለመሆን እንዳገዛትም ትናገራለች። ሌላኛው አኒታ የምታደርገው ነገር አመራርን ከትምህርት ቤት ጀምራ እየተለማመደችው መሄድ ነው። እስከ አሁን በነበራት ቆይታም ትምህርት ቤቱ የሚሰጣትን ኃላፊነት ተቀብላ በውጤታማነት አከውናለች።
አኒታ ለልጆች የምትመክረው ነገር አለ። የመጀመሪያው ትምህርታችሁን ውደዱ፤ ለሕልማችሁ ሥሩ የሚል ሲሆን፤ ሌላው አገር ወዳድና አገራችሁን የምታውቁ ሁኑ የሚል ነው። አትችሉም የሚሏችሁን ሰዎች ችላችሁ በማሳየት አሳምኗቸው። በመጨረሻ ጓደኛችሁን ስትመርጡ በአለው ቁስና ብልጭልጭ ነገር ሳይሆን ባለው ሰውኛ ባህሪ ብቻ መሆን አለበት የሚል ነው።
ሁለተኛ ያነጋገርኳት ልጅ የአኒታ ታላቅ እህትን ናኦሚ ሙሴን ነው። የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነች። እድሜዋ ደግሞ 10 ነው። እርሷም እንደ እህቷ በትምህርቷ ጎበዝ ስትሆን፤ የክፍል ተጠሪ በመሆን የሚሰጧትን ኃላፊነቶች በትጋት የምትወጣ ነች። ስዕል መሳል በጣም ትወዳለች። ይህ ፍላጎቷ ደግሞ ተፈጥሮን አድናቂ አድርጓታል። የአገሯንም ውበት በተለየ ምልከታ እንድታያት አስችሏታል።
ናኦሚ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ብትማርም የዓለም አቀፉን እውቀት ለማወቅ እንጂ አገሯን ለመተው እንዳልሆነም ታምናለች። በዚህም ሌሎች ጓደኞቿ አሜሪካና ሌሎች አገራትን ሲያደንቁ ስታይ ትበሳጫለች። ምክንያቱም በእርሷ እምነት ኢትዮጵያ ውብና የአማረ ተፈጥሮ ባለቤት ነች፤ ያልተደፈረ ማንነት ያላትና ጀግና ሕዝብ የሞላባት አገር ነች። ስለዚህም ከማንም ጋር አትወዳደርም። በዚህም ሁሌ ምኞቷ ኢትዮጵያን የሚያስጠራ ሥራ መስራት ነው። አንዱ አስጠራበታለሁ የምትለው በቴክኖሎጂው ዘርፍ የራሷ ብራንድ ያላት አገር ማስባልን ነው። ለዚህ ደግሞ የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪና ተመራማሪ መሆን ሕልሟ ነው።
ልጆች ናኦሚ እንደ ቶሺባ፤ ዴልና ኤችፒ አይነት ብራንዶች በኢትዮጵያዊ ስሞች መፈልሰፍ ትፈልጋለች። በተጨማሪም በስዕል ስራዎቿ መታወቅና የምትፈልገውን መረጃ ማስተላለፍ ትፈልጋለች። ከዚህ ጎን ለጎን ልታጣው የማትፈልገው ነገርና ብሰራው የምትለው ምኞቷ ተጽዕኖ የሚፈጠርባቸውን ልጆች ማገዝ ነው። አሁንም በተለያዩ ምክንያቶች ችግር የሚያጋጥማቸውን ልጆች እያገዘች እንደሆነም አጫውታኛለች።
ልጆች ናኦሚ ህልሟን ለማሳካት አንድ ነገር ማድረግ ትፈልጋለች። በመማር ማስተማሩ ሂደት ውስጥ ለፍላጎቷ ወደሚቀርበው ትምህርት በጣም ማዘንበል ትፈልጋለች። ለዚያ የሚያግዙ የተለያዩ እውቀቶችን ለመቅሰም ከኢንተርኔት ላይ ታነባለች።
ናኦሚ ለልጆች የምትመክረው ነገር የመጀመሪያው የቤተሰብ ምክር ስሙ የሚለውን ነው። ለዚህ ደግሞ ቤተሰብ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ታስገነዝባለች። ልጆቻቸው አገር ወዳድ፤ ስነምግባር ያላቸው፤ በትምህርታቸው ጎበዝና ለህልማቸው የሚሰሩ እንዲሆኑላቸው ሳይሰስቱ ሊመክሯቸው ይገባል ባይም ነች። ምክንያቱም እርሷና እህቷ በአባታቸውና በእናታቸው ምክር ታግዘው የሚፈልጉበት ቦታ ለመድረስ እየሮጡ ነው። በትምህርት ቤት ጭምር ተወዳጅ የመሆን መሰረታቸው እርሱ እንደሆነ ታነሳለች። እንደውም በዚህ አጋጣሚ ይህንን ላደረጉላቸው ቤተሰቦቿ ምስጋናን ታቀርባለች።
ልጆች አኒታና እህቷን እንዴት አገኛችኋቸው? ብዙ ቁምነገር አስጨበጧችሁ አይደል? በሉ ለዛሬ በዚህ ሀሳባችንን እንቋጭ። በሚቀጥለው ሳምንት በሌላ ፕሮግራም እስክንገናኝ መልካም ሰንበት ይሁንላችሁ!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/ 2015 ዓ.ም