ጭቃ እያቦኩ የሚጫወቱ የአንድ ሰፈር ልጆች ናቸው።በተለመደው የጨዋታ ቦታቸው ላይ ሆነው ዝማሬን ይዘምራሉ።እጃቸውን በጭቃ ውስጥ እንዳደረጉ ጭቃውን እያቦኩ መዝሙር ይዘምራሉ፤ የሰላምን ዝማሬ።በመንገድ ላይ ልጆቹን እያየ የሚያልፈው ሰው ሁሉ ‘አይ ልጅነት ማማሩ’ ይላል።በጭቃ የተበከለው ልብስ ሳያሳቅቃቸው፤ እፍረትም ሳይሰማቸው፤ ድምጻቸው ለሙዚቃ አመቺ መሆን አለመሆኑ ጉዳያቸው ሳይሆን የሚዘምሩ።ከዝማሬው ሲመለሱ ደግሞ መልሰው ጭቃውን ያቦካሉ፤ በጭቃውም የሚፎካከሩበትን ቤት ይሰራሉ፤ የሰሩትንም ቤት መልሰው ያፈርሳሉ፤ ሊጣሉም ሆነ ሊደባደቡም ይችላሉ፤ ልጅነት።
ከልጆቹ እልፍ ባለው ዛፍ ስር የተሰበሰቡ አዋቂዎች ሸንጎ ተቀምጠዋል፤ የተጣሉትን ለማስታረቅ።በሁለት አዋቂዎች መካከል የተፈጠረውን ጥል ለማርገብ የአካባቢው ሽማግሌዎች ለማስታረቅ ጥረት እያደረጉ ናቸው።ሁለቱም ወገኖች የየራሳቸውን እውነት አቅርበው አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ጥረት እያደረጉ ከስሜት ጋር የተቀላቀለ የቃላት ውርዋሮ ውስጥ ናቸው።አንደኛው ግለሰብ ወይ ፍንክች ‘የእኔን በደል ተመልክታችሁ እልባት የማትሰጡኝ ከሆነ ፍትሕ የለችም ማለት ነው፤ ወይ ፍንክች’ ይላል።‘እንዲህ ሆኖ፤ እንዲያ ተከትሎ፤ በዚህ ወጥቶ በዚያ ወርዶ ወዘተ’ ይላል።ሌላኛው ወገንም ሽማግሌዎቹን አመስግኖ የራሱን ድምጽ ያሰማል።የሁለቱን ወገን የሚሰሙት ሽማግሌዎች ደግሞ ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት በተመስጦ ናቸው።የግራ ቀኙ ክርክር ተሰምቶ በማለቁ ሽማግሌዎች የሚናገሩበት ምዕራፍ ላይ ሲደርስ ሰብሳቢው ሽማግሌም ንግግራቸውን ጀመሩ፤
“የሁለቱንም ወገን ንግግር አደመጥን፤ እኛ ደግሞ እንናገር።ልጆቼ እኔ ሁላችሁንም የምመክረው እዚያ ጋር ጭቃ እያቦኩ ያሉትን ልጆች እንድትመለከቱ ነው።ልጆቹን ተመልክቶ ጭቃ እያቦኩ፤ በአቦኩት ጭቃ ቤት እየሰሩ፤ የሰሩትን ቤት መልሰው እያፈረሱ፤ መልሰውም እየሰሩ፤ እንዲሁም እየተጣሉ፤ ከጥል መልስ ደግሞ አብረው እየዘመሩ፤ በዙሪያቸው ለሚሆነው ነገር ቦታን ባለመስጠት በራሳቸው ዓለም ውስጥ ሆነው የሚኖሩ ናቸው።ይህ የሚያሳየው ግጭት ሊያጋጥም የሚችል ልንቀንሰው እንጂ ልናጠፋው የማንችል መሆኑን ነው።ወደ እናንተ ጉዳይ ስመጣ ሁሉም ነገር ክርር ያለ ሆኖ አገኘሁት።ሁሉም እኔ ያልኩት ካልሆነ በማለት ነገሩን ሁሉ አክርሮ የመያዝ ከጉዳዩ በላይ የከረረ።ምድራችን አንድ ወገን የፈለገውን በሙሉ የሚያደርግባት አይደለችም።ሁላችንም በጋራ በሰላም እንድንኖር፤ ሁላችንም አሸናፊ እንድንሆን አንዳችን ለሌላችን ፍላጎት ቦታን የምንሰጥበት፤ አንዳንዴም ለትልቁ ሰላም ሲባል የምንተወው ትናንሽ ነገር ያለበት አካሄድ የግድ የሚልበት ነው።
ለአሁኑ ጉዳያችሁን ሰማን አንድ ጥያቄ ግን ለእናንተ ላቅርብ፤ እስከአሁን በራሳችሁ ጫማ ውስጥ ሆናችሁ ተናገራችሁ፤ እስኪ አሁን ደግሞ በሌላኛው ወገን ጫማ ውስጥ ሆናችሁ ደግሞ ክርክራችሁን አሰሙ።ሌላኛው ወገን ያመመውን ህመም እያሰባችሁ የሌላውን ወገን እውነት አቅርቡለት።ሌላኛው ወገን እንዲሰማለት የሚፈልገውን እናንተ እስኪ አሰሙለት።” በማለት መድረኩን መልሰው ለግራ ቀኙ ሰጡ።ሁለቱም ወገኖች የሌላኛውን ወገን እውነት ላይ ቆመው እንደ ባለጉዳዩ አድርገው ደስ ባይላቸውም እንዲሁም የራሳቸውን ለማቅረብ በስሜት ውስጥ ሆነው እንዳቀረቡት ባይሆንም፤ የሽማግሌውን ቃል መፈጸም ያለበት ነበርና ለማሰማት ሞከሩ።ሰላምን መፍጠር ብቻም ሳይሆን ሰላምን ስለማብዛት የሽማግሌዎችን ቃል አክብረው ተናገሩ።ወደ መፍትሔው በሽማግሌዎቹ በኩል ለመድረስ ጥረት እያደረጉ፤
በዛሬው ጽሁፍ ሰላምን ስለማብዛት እንጽፋለን።ሰላምን መፍጠር፤ መጠበቅ እንዲሁም ማብዛት ከግለሰብ እስከ አገር እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ለማንም ማስረዳት አስፈላጊ አይደለም፤ ሁሉም ይረዳዋል።ሰላምን ለማብዛት አስፈላጊ የሆኑ ነጥቦችን በሰላም ዙሪያ፤ ችግርን በመፍታት ዙሪያ፤ አዎንታዊ ተጽእኖ በመፍጠር አቅጣጫ ጥናት ካደረጉ አጥኚዎች የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን መነሻ በማድረግ እንመልከት።
በአንድ አገር የፖለቲካ ማህበረሰብ እንዲሁም እስከ ግለሰብ ድረስ ባሉ ደረጃዎች ችግር ማጋጠሙ አይቀሬ ነው።በግለሰብ ህይወት ውስጥ፤ በትዳር፤ በአካባቢ፤ በእምነት ቦታዎች፤ በአገር ወዘተ ደረጃ የሚፈጠሩ ችግሮች ሁሌም ይኖራሉ።ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ በማሰብ ችግር ፈቺ ሆኖ መገኘት ለማንኛውም ሰው የሚያስመሰግን ነው።በመጽሐፍ ቅዱስ “የሚያስተራርቁ ብጹዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” በማለት ማስታረቅ የሚያሰጠውን ትልቅ ቦታ ያሳያል።ችግር ፈቺነት ባህል በሆነባቸው አካባቢዎች ችግር በመፍታት ሂደት ውስጥ ወደ ውጤት መድረስ የሚቻልበት እድሉ ሰፊ ነው።ሰላምን ለመፍጠርም ሆነ ለማብዛት ችግር ፈቺነት ያለውን ሚና ተመልክቶ ወደ ግጭት የሚወስዱ ነገሮችን ከስራቸው ለመንቀል መስራት አትራፊ ያደርጋል።
እያንዳንዱ ሰው በተሰማራበት ዘርፍ ምንም ይሁን ምን ችግሮችን መጋፈጡ አይቀሬ ነው።የምንኖረው ውስብስብና ብዝሃ ህይወት ባለበት ዓለም ውስጥ ስለሆነ፤ ስራዎች የሚሰሩት ከሰዎች ጋር በሚፈጠር ግንኙነት ውስጥ ስለሆነ እና የምንጋፈጣቸውን ሁሉንም ሁኔታዎች ልንቆጣጠራቸው የምንችላቸው ስላልሆኑ ችግሮች ይከሰታሉ፤ ችግር ፈቺነት ደግሞ ሊኖር ግድ ነው፤ ሰላምን ለመፍጠርም ሆነ ለማብዛት።
የሚከተሉት ነጥቦች በየትኛውም ደረጃ ሰላምን የሚያደፈርስ ችግር ከመፈጠሩ በፊትና ከተፈጠረ በኋላ ማድረግ የሚገባንን ማወቅ ሰላምን ለማብዛት የሚረዳ ነው።
1. ሰላምን የሚያሳጡ ችግሮችን አስቀድመው ማንበብ መቻል፣
ችግሮች የማይቀሩ ስለሆነ አስቀድሞ ለማየት መሞከር ችግሩ በዝቶ ከሚያመጣው ጉዳት የመትረፍ እድልን ይሰጣል። ጠንካራ መሪዎች አስቀድመው ችግሮች ሳይመጡ ሊተነብዩአቸው ይሞክራሉ።መንገዶች ሁሉ ቀላል እንደሆኑ የሚያስብ ሰዎች ሁልጊዜ ከችግር ጋር ተጋፍጠው ችግርን በመፍታት ላይ ተጠምደው ይገኛሉ።ነገሮችን መርምሮ ሊመጣ የሚገባውን መለየት መቻል አስፈላጊ ነው።
2. የሰላም እድልን ለማስፋት ተጨባጭ እውነታን በአግባቡ መረዳት መቻል፣
ተጨባጭ እውነትን በመካድ ውስጥ መገኘት አንዳንዴ አላስፈላጊን ዋጋ ያስከፍላል።ሰላምን ለማብዛት ሁል ጊዜ ተጨባጩን እውነት መረዳትና ለእውነታው ምላሽ መስጠትን ይጠይቃል።ሰዎች ለሚገጥማቸው ችግሮች በተለያየ መንገድ ምላሽ ይሰጣሉ፤ አንዳንዱ ችግሩን ለመቀበል ባለመፍቀድ ምላሽ ሲሰጥ ሌላው ደግሞ ችግሩን ለመቀበል ይፈቅዱና ከነችግሩ መኖር ላይ ራሳቸውን ያገኛሉ፤ አስተዋይ ሰዎች ግን ችግሩን ተቀብለው ነገሮችን ጥሩ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ።መሪዎች ሁልጊዜ ችግርን ተቀብለው ነገር ግን ለማስተካከል ጥረት የሚያደርጉ መሆን አለባቸው።
ዛሬ በተለያየ አቅጣጫ የሚገጥመንን የሰላም ችግር ለመፍታት ላለንበት እውነታ ተጨባጭ ምላሽን ለመስጠት መሞከር ብልህነት እንጂ ሞኝነት ሊሆን አይችልም።ከእውነታ በተቃራኒው በሚደረግ ጉዞ ውስጥ ግን በመጨረሻ ለኪሳራ የሚዳርግ ክስተት ውስጥ ልንገኝ ያስችለናል።
3. ከትናንሽ ጉዳዮች ራስን ማቀብ፣
ሁሉም ሰው ከጥቃቅን ነገሮች ይልቅ ዋናውን ነገር በማሰብ መኖር ቢችል አትራፊ ይሆናል።መሪዎች ትልቁን ምስል እያዩ መምራት ይኖርባቸዋል።ከትልቅ ምስል በትንንሽ ጉዳዮች ላይ ተጠምደው የሚገኙ ሰዎች በስሜት ብቻ እየተመሩ መሄድን ምርጫቸው ያደረጉ ናቸው።እንዲሁም በዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ በመግባት አንኳር የሆነውን ጉዳይ ከመመልከት መስነፍም የለባቸውም።
ሰላምን ለማብዛት በዝርዝር ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ትልቁን ምስል መመልከት አትራፊ ያደርጋል።ምንም ይሁን ምን ሰዎች እንዳይሞቱ፤ ሰላማቸውን እንዳያጡ፤ የሚመገቡት እንዳያጡ፤ ወዘተ ሌላውን ዝርዝር ጉዳይ ግን በመተማመን መንፈስ በጊዜ ውስጥ እያዩ መሄድ በፖለቲካው መድረክ ለሚፈጥሩ ቅራኔዎች የተሻለው መንገድ ይመስላል።
4. ወደ ሰላም የሚያደርስ ቅደም ተከተልን መከተል፣
ችግሮችን ለመፍታት ይቻል ዘንድ ቅደምተከተል ወሳኝነት አለው።ወደ ጦርነት ለመግባት የሂደት ውጤት እንደሆነው ሁሉ ከጦርነት ወደ ሰላም ለመድረስ እንዲሁ ቅደምተከተል ያስፈልጋል።ቅደምተከተሉን ሁሉም በጥንቃቄ ሊቀርጽ ይገባዋል።እያንዳንዱ ግለሰብ እንደ ግለሰብ የቅደምተከተል ሃላፊነት አለበት።የጦርነትን የአንድ ወገን አሰላለፍ ደግፎ የቆመ ነገሮች ወደ ሰላም እንዲመጡ በሚሰራበት ጊዜ ትኩረቱ ሰላምን መስበክ ላይ መሆኑ ጥርጥር የለውም።መሪዎች ከሁሉም በላይ ቅደምተከተልን የማስተካከል ሃላፊነት አለባቸው።
በግል ሕይወታችን የሚገጥመን ማናቸውም ሰላም ማጣትን አሸንፈን ለመውጣት ምን መቅደም ምንስ መከተል እንዳለበት በማመን ለአካሄዳችን ጥንቃቄ ማድረግ ጠቢብነት ነው።ሁሉንም ነገር በአንዴ ማሳካት የሚቻልበት ዓለም ውስጥ ባለመሆናችን ቅደም ተከተል አስፈላጊ ነው።በታሪክ ውስጥ ያሉ ቅራኔዎች ሳይፈቱ አንዱ ቅራኔ ወደ ሌላ የቅራኔ ምእራፍ ሊገባ የቻለው የቅደም ተከተል መዛነፍ መሆኑን ማሰብ አለብን።በትዳር ውስጥ የሚኖር ቅራኔ ቶሎ ካልተፈታ ይባዛል የሚባለውም በዚህ ምክንያት ነው።በሌሎች ግንኙነቶችም ውስጥ ልዩነቶች ሲኖሩ ቶሎ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ተገቢነት አለው።የቱ ይቅደም የቱስ ይከተል የሚለውን ግምት ውስጥ በማስገባት።
ጠቢብነት ቅደም ተከተሎችን አስተካክሎ ለመፍትሔው አንድ እርምጃ ወደፊት መቅረብ መቻል ነው። ሪቻርድ ስሎማ የተባሉ ሰው ሁሉንም ችግሮች አንድ በአንድ ልትፈታ አትሞክር ነገርግን ቅደምተከተል ሰጥተህ ተራበተራ ልትፈታቸው ሞክር በማለት ይመክራሉ።በችግር አፈታት ዙሪያ መሪዎች የሚቸገሩት በዙሪያቸው በርካታ ችግሮች ኖረው ችግሮችን እንዴት ባለ ቅደም ተከተል መፍታት እንደሚችሉ አለማወቃቸው ላይ ነው።በዙሪያህ ልትፈታቸው የሚገቡት ችግሮች ብዙ ከሆነ በቅድሚያ አሁን ልትፈታ የምትችለውን በማስቀደም ሌላውን ለማስከተል ሞክር።
5. ሰላምን ዋናው ግብ በማድረግ በየትኛውም ተግዳሮት ውስጥ አለመተው፣
ሰላምን መፍጠር፤ ሰላምን ማብዛት፤ ሰላምን መጠበቅ በክፋት በተሞላች ምድር ውስጥ በቀላሉ የሚቻል ነገር አለመሆኑን መረዳት አስፈላጊ ነው።ሰላምን ዋናው ግብ ያደረገ ሰው በየትኛውም ተግዳሮት ውስጥ ቢያልፍም ግቡን ተከትሎ ወደፊት ይራመዳል እንጂ ወደኋላ አይመለስም።መሪዎች በተግዳሮት ግብን ማእከል አድርገው የሚጎዙ ናቸው።ሰላምን ማእከል አድርጎ መጓዝ ስሜትን ማረቅን፤ ከጥቅቃን ነገር ትልቁን ምስል መመልከትን፤ ከዛሬ ይልቅ አሻግሮ ነገን መመልከትን ይጠይቃል።
ደራሲ ጆርጅ ማቲው እንዲህ አሉ የምታስበው ነገር ማለት በህይወትህ ውስጥ ካሉት ነገሮች የሚበልጠው ማለት ነው።ከምትሰማው በላይ፣ ከምትኖርበት ቦታ በላይ፣ ከማህበራዊ መስተጋብርህ በላይ እንዲሁም ስለ አንተ ሰዎች ከሚያስቡትም በላይ ነው።ሁሉም ፈተናዎች እራስህን ከእራስህ ጋር የሚያስተዋውቁህ ናቸው።ፈተናዎችህ እንዴት እንደምታስብና እንዴትም እንደተሰራህ የሚያሳዩህ ናቸው።
ከችግሮችህ ጋር ፊት ለፊት ስትጋፈጥ እንዴት ነው ምላሽ የምትሰጠው? ችላ ብለኸው በራሱ ጊዜ እንደሚሄድ ታስባለህ? ለመፍታት አቅም እንደሌለህ ሆኖም ይሰማሃል? ችግርን ለመፍታት ጥሩ ያልሆነ ልምድ ከእዚህ ቀደም ኖሮህ ተስፋ ቆርጠህስ ይሆን ወይንስ ፈተና ሲመጣ ለመጋፈጥ ፍቃደኛ ነህ? ፈተናዎች ገጥመውህ ስታሸንፋቸው ችግሮችን የመፍታት አቅምህን ያዳብሩታል።በየጊዜው የሚገጥምህን ችግር እየፈታህ በሄድክ ቁጥር በሂደቱ የምትማራው ነገርም ይበዛል።ነገር ግን ልትፈታው ካልሞከርክ ትወድቃለህ።
የቤት-ስራ አድርገህ የምትወስደው
ችግር የመፍታት አቅምህን ለማሻሻል የሚከተለውን አድርግ፣
ችግሩን ተመልከት፡ – ችግሮችን ከመጋፈጥ ይልቅ መግፋትን የምትመርጥ ከሆነ ከእዚያ ውጣና ችግርህን ተመልከት።በምትጋፈጠው ጊዜ ስለሆነ ልምድ የምታገኘው ተጋፈጠው።መፍትሄ ሊገኝላቸው የሚገቡ በዙሪያህ ያሉትን ነገሮች መፍትሄ ለመፈለግ ጥረት አድርግ በሂደትም የችግር አፈታት አቅምህን እያዳበርክ ትመጣለህ።
የመፍቻ መንገድን ቀይስ – አንዳንድ ሰዎች ችግርን በመፍታት ውስጥ ከባድ ወቅትን ያሳልፋሉ፤ ምክንያቱም ችግርን የመፍታት ልምድ የላቸውም።የሚከተለውን TEACH የተሰኘውን ሂደት ተከተል፣
TIME – ችግሩን ከመሰረቱ ለመረዳት ጊዜ ውሰድ፣
EXPOSURE – ሌሎች እንዴት እንደሚሰሩ ለማወቅ ሞክር፣
ASSISTANCE – ቡድንህ ሁሉንም አቅጣጫ እንዲረዱ አድርግ፣
CREATIVITY – የተለያዩ መፍትሄዎችን አስብባቸው፣
HIT IT – የተሻለ የምትለውን መፍትሄ ተግብር
ዙሪያህን ችግር ፈቺዎች እንዲኖሩ አድርግ – አንተ ጥሩ ችግሩን መፍታት የምትችል ሰው ካልሆንክ ሊፈቱ የሚችሉ ሰዎችን ወደ ቡድንህ አምጣ።እነርሱም የአንተን ክፍተት በመሙላት ደግሞም ከችግር አፈታታቸው ትምህርት ልትወስድባቸው ትችላለህ።
እለታዊ ጉርሻ፣
ቦክሰኛው ግኒ ቱኒ የከባድ ሚዛን የዓለም ሻምፒዮን የሆነው ጄክ ድምፒሲን በማሸነፍ ነበር።አብዛኛው ሰው ቱኒ ማን እንደሆነ አያውቅም ነበር።ይህ ሰው ታዋቂ ከመሆኑ በፊት ሁለቱም እጆቹ ይሰበሩና ወደ ዶክተር ይቀርባል።ዶክተሩም በደረሰበት የእጅ ስብራት ምክንያት የዓለም ሻምፒዮን የመሆን እድል እንደ ሌለው ይነግረዋል።እርሱ ግን ሻምፒዮን መሆን ባልችም ግን ቦክሰኛ ሆኜ ከመቀጠል ወደ ኋላ አልመለስም በማለት ይቀጥላል።ነገርግን ሻምፒዮን መሆንም ቻለ።በመንገድህ ላይ በሚመጣ መሰናክል ከህልምህ እንዳትቀር ጥረት አድርግ።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/ 2015 ዓ.ም