ሰውየው ከቦረና እስከ ሰበር ድረስ ዘልቀው የማይደፈረውን ደፍረው፤ ጥርሳቸውንም ነክሰው መብታቸውን ለማስከበር ጥረታቸውን ጀምረዋል፡፡ ወዲህ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት ቀጥታ ፍርድ ቤት ለመቅረብ አይገደድም፡፡ በዛሬው ዕትማችን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ውሣኔዎች በሚል የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የጥናትና ህግ ድጋፍ ዳይሬክቶሬት በ2008 ዓ.ም ከውሳኔዎች መካከል ለህትመት ካበቃቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ይሆናል። የሰነድ መለያ ቁጥር 98541 ያለው የክርክር ጉዳይ ህዳር 10 ቀን 2007 ዓ.ም የመጨረሻውን ውሳኔ ያገኛል። ታዲያ አምስት ዳኞች ከፍርድ መንበሩ ተሰይመው የመጨረሻ የተባለውን ውሳኔ ሊበይኑ ነው፡፡ በዚህ መዝገብ አመልካች አቶ አለማየሁ ኦላና በአካል ተገኝተው እንዲሁም ተጠሪው የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት (UNDP) በጥሪ ታልፎ በአካል በሌሉበት የፍርዱን መጨረሻ ቃል ይጠባበቃሉ፡፡ የፍርድ ሚዛን ወደየት ይሆን?
የላቤን ዋጋ…
የሰበር ጉዳይ የቀረበው አመልካች በተጠሪ ላይ የአሠሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 ድንጋጌዎችን መሰረት አድርገው ያቀረቡት ክስ ተጠሪ በሌለበት ታይቶ በክርክሩ ከተረጋገጠበት የፍሬ ነገር ጉዳዮች በመነሳት አመልካች የተለያዩ ክፍያዎች በተጠሪ እንዲከፍሏቸው በወረዳው ፍርድ ቤት በተወሰነው መሰረት የአፈጻጸም መዝገብ ከፍተው ክርክሩ በመታየት ላይ እያለ ተጠሪ የመከሰስ መብት የለውም ተብሎ የአፈጻጸም መዝገቡ በሁሉም የበታች ፍርድ ቤቶች መዘጋቱ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ተብሎ ነው፡፡
አመልካች ተጠሪ ከህግ ውጭ ከሥራ አሰናብቶኛል በማለት ካሳና የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፍሏቸው ይወሰን ዘንድ አቤት አሉ፡፡ በያበሎ ወረዳ ፍርድ ቤት በተጠሪ ላይ ክስ መስርተው የአሁኑ ተጠሪ በሌለበት ጉዳዩ እንዲታይ ተደርጎ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ስንብቱ ሕገ ወጥ መሆኑን በመደምደም ለአመልካች ካሳና የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈሉ በማለት ወስኗል፡፡ አመልካች ውሳኔውን ለማስፈፀም በወረዳው ፍርድ ቤት የአፈጻጸም ክስ ከፍተው ጉዳዩ መታየት ከጀመረ በኋላ የወረዳው ፍርድ ቤት ጉዳዩን መርምሮ የተባበሩት መንግስታት ኮንቬንሽንን አንቀፅ 2(3) በዋቢነት ጠቅሶ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለውም በማለት የአፈጻጸም መዝገቡን ዘግቶታል።
ይግባኝ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት
በዚህ ትዕዛዝ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለቦረና ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡ አመልካች ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታቸውን አቅርበውም ችሎቱ ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪን ያስቀርባል የሚል ትዕዛዝ ሰጥቶ ተጠሪ ሊቀርብ ባለመቻሉ መልስ መስጠቱ የታለፈ ሲሆን ችሎቱ ጉዳዩን መርምሮ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ሆኖ አመልካች የሚከራከሩት የተባበሩት መንግስታት አካል ከሆነው ድርጅት ጋር መሆኑን፣ ከእንደዚህ አይነት ድርጅቶች ጋር የሚደረግ ግንኙነት በአዋጅ ቁጥር 377/1996 የማይገዛ መሆኑ በተጠቃሹ አዋጅ አንቀጽ 3(ሀ) ስር መመልከቱን፣ ተጠሪና መሠል አካላት በሕግ የተለየ ከለላ ያላቸው መሆኑ በተባበሩት መንግስታት ቻርተር አንቀጽ 105፣ በተባበሩት መንግስታት ጥቅምና የተለየ ከለላን በተመለከተ ለመደንገግ በወጣው ስምምነት አንቀጽ 2(2) እና 3 ስር መደንገጉን፣ ኢትዮጵያም ይህንኑ ስምምነት መፈረሟን በዋቢነት ጠቀሰ፡፡ ከመነሻውም ተጠሪ በወረዳው ፍርድ ቤት መከሰሱ ተገቢነት እንደሌለው፣ አመልካች ያላቸው መፍትሔም በ”United Nations Commission on International Trade Law (UNCITRAL)” ደንቦች መሰረት ከተጠሪ ጋር ባላቸው ስምምነት መሰረት በእርቅ መጨረስ መሆኑን፣ በዋናው ጉዳይ ስልጣን የሌለው ፍርድ ቤት ጉዳዩን አይቶ መወሰኑን ከተጠሪ ጥቅምና ከባለ መብቶች አንፃር ሲታይ ዋናውን ውሳኔ ሕጋዊ የማያደርገው መሆኑን ዝርዝሮ የበታች ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለንም በማለት የአፈጻጸም መዝገብ መዝጋታቸውን በመቀበል የአመልካችን የሰበር አቤቱታ ውድቅ አድርጎታል፡፡
ወደ ሰበር
የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነበር፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም በዋናው ጉዳይ ላይ ተጠሪ ቀርቦ ባልተከራከረበት ሁኔታ በአፈጻጸም መዝገብ የተጠሪን ያለመከሰስ ከለላ በመጥቅስ ዋናውን ውሳኔ ውድቅ ማድረግ ሥነ ሥርዓታዊና የሕግ የበላይነት እንዲሁም አመልካች እንደ ዜጋ ፍትህ የማግኘት መብት ያላቸው መሆኑን ያላገናዘበ ነው በማለት ተከራከሩ፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ባለመቅረቡ በጽሑፍ መልስ መስጠቱ ታለፈ፡፡
ዲፕሎማቲክና ሚሲዮኖችን ያጣቀሰው ምርመራ
ሰበር ችሎት ጉዳዩን ከበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ምርመራ ጀመረ፡፡ ፍሬ ነገሩ በአመልካችና በተጠሪ መካከል የተነሳው ግንኙነት የቅጥር ውልን መሰረት ያደረገ ሲሆን ዋናው ክርክር በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አግባብ ታይቶ ዳኝነት ማግኘቱን የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡ የተለያዩ ዓይነት በቅጥር ላይ የተመሰረቱ የሥራ ግንኙነቶች የሚኖሩ ሲሆን ግንኙነቶቹ የሚገዙበት የሕግ አግባብም ይለያያል፡፡ አዋጅ ቁጥር 377/1996 ተፈፃሚ የማይሆንባቸው ግንኙነቶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ይህ አዋጅ በየትኞቹ ላይ ተፈጻሚነት ሊኖረው እንደሚችል በዋነኝነት የሚመራው የአዋጁን የተፈጻሚነት ወሰን የደነገገው አንቀጽ 3 ነው፡፡ ለዚህ ጉዳይ ቀጥተኛ አግባብነት ያለው የአንቀጹ ድንጋጌ በንዑስ ቁጥር ሶስት በፊደል “ሀ” ስር የተመለከተው ሲሆን በዚህ ንዑስ ድንጋጌ ስር የስራ ግንኙነቱ በንዑስ አንቀጽ ሁለት ስር የሚወድቁ ባለመሆናቸው በአዋጁ አንቀጽ 1 መሰረት በቀጥታ ሊፈጸምባቸው የሚችል ቢሆንም በንኡስ አንቀጽ 3 ስር በተገለጹት ሁኔታዎች መሰረት ከአዋጁ ሽፋን ውጭ ሊደረጉ የሚችሉ የስራ ግንኙነቶችን የሚመለከት ነው የሚል ሃሳብም በምርመራው ተካተተ፡፡
በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰሩ የዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚመሰርቱት የሥራ ግንኙነት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መሰረት ወይም ኢትዮጵያ በምትፈርማቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት በአዋጁ ሊሸፈኑ እንደማይችሉ ተመልክቷል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይሁንታ…
በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 3 ድንጋጌዎች ሲታዩ አዋጁ በአጠቃላይ በአሰሪና ሰራተኛ መካከል በሚቋቋም በቅጥር ላይ በተመሰረተ የስራ ግንኙነት ላይ ተፈጻሚነት የሚኖረው ቢሆንም በአዋጁ 260 በግልጽ በተደነገጉ ሌላ ህግ በሚገዛቸው ግንኙነቶች ላይ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ያስገነዝባሉ፡፡ በተጨማሪም አሁንም አዋጁ የሚሸፍናቸው የሥራ ግንኙነቶች ሊሆኑ ቢችሉም ነገር ግን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም ኢትዮጵያ የምትፈርማቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በሚወስኑት መሰረት ከአዋጁ ሽፋን ውጭ ሊደረጉ የሚችሉ መሆኑን ተመለከተ፡፡
በመሆኑም ሕግ አውጪው የዲፕሎማቲክ ግንኙነቶችን ስምምነትና ልምድን ለማክበር ሲባል የውጭ ዲፕሎማቲክ ሚስዮኖቹና ኢትዮጵያውን ሠራተኞቻቸው የሚያደርጉት የቅጥር ግንኙነት ላይ የአሰሪና ሰራተኛ ሕግ ተፈጻሚ እንዳይሆን ያደረገ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም በሕጉ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ወይም ኢትዮጵያ ከውጭ ድርጅቶች ጋር በምትፈራረምባቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት አዋጅ ቁጥር 377/1996 ተፈፃሚ እንዳይሆን የሚደረግበት አግባብ መኖሩን ሕግ አውጪ በግልፅ ያስቀመጠው ጉዳይ ነው፡፡
የአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 3(3((ሀ)) መሰረታዊ ዓላማ የውጭ አገር መንግሥታት ተወካዮችን ሉአላዊነት እና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለማክበር ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን በተጨባጭ ባለው ሁኔታ ደግሞ የውጭ ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ጋር ስምምነት ተፈራርመው ይኼው የመንግስት አካል በእነዚህ ተቋሞች ተቀጥረው የሚሰሩት ኢትዮጵያውንን መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚያስችል ሥርዓት ዘርግቶ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች በተካተተው አግባብ የተፈጠረው አለመግባባት ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማግባባትና በድርድር እንዲፈታ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው፡፡
የመንግስት ፍርድ ቤት የማይቀርበው ድርጅት
የአመልካች ክርክር ያቀረቡት ግንኙነቱ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 3(3(ሀ)) መሰረት ሊገዛ ከማይችል አካል ጋር ነው፡፡ ተጠሪ የተባበሩት መንግስታት አካል ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ጥቅምና የተለየ ከለላን በተመለከተ በተደነገገ ስምምነትም በማንኛውም መንግስት ፍርድ ቤቶች ተከሶ መቅረብ የሌለበት መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ቻርተር አንቀፅ 105 እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት ጥቅምና የተለየ ከለላን በተመለከተ በተደነገገው ስምምነት አንቀጽ 2(2) እና 3 ስር በግልጽ ተመልክቷል፡፡ አመልካች በዚህ ረገድ የሚያቀርቡት ክርክር የሌለ ቢሆንም አሁን አጥብቀው የሚከራከሩት በዋናው ጉዳይ ውሳኔ ከአረፈ በውሳኔው መሰረት ከሚፈጸም በስተቀር የተጠሪ በሕግ ያለው የተለየ ከለላ እንደ አቢይ ምክንያት ተወስዶ አፈፃፀሙ ሊቆም የሚችልበት አግባብ የለም በሚል ነው፡፡
በሕግ አግባብ የተሰጠ ፍርድ ዋጋ እንዳይኖረው የሚደረገው የአፈጻጸም ትዕዛዝ ተገቢነት እንደሌለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥነ-ሥርዓት ህግ ቁጥር 378 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነ ዘበው ጉዳይ ነው፡ ፡ በሕግ አግባብ ታይቶ የተሰጠን ውሳኔ በሕጉ አግባብ ማስፈፀም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 78(1) እና 79(1) እና (4) ስር የተረጋገጠውንና የተከበረውን የነጻ ፍርድ ቤት መኖርንና የዳኝነት ስልጣን በአግባቡ ተግባራዊ የሚያደርገው እና በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 37 ስር የተረጋገጠው የዜጎች ፍትህ የማግኘት መብትም ውጤት ባለው መልኩ ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድ መሆኑ ታመነበት፡፡
አፈፃፃም
በፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ ትርጉም እንዲኖረው የማድረግ ውጤት ያለውና በተገቢው መንገ ድም መፈፀም ያለበት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ግን ለማን ኛውም ጉዳዮች ሁሉ ይሰራል ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ ተገቢ ያልሆነ ሕጋዊ ውጤት የሚያስከትል መሆኑ እሙን ነው ይላል የዶሴው ዝርዝር። በእርግጥ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 212 ድንጋጌ ስር በስነ ስርዓት ጉድለት አንድ ፍርድ ውድቅ ሊሆን እንደማይችል የተመለከተ ሲሆን ይህ ግን የሚሰራው የፍትሐ ብሔር ሥነ ስርዓት ሕጉ ተፈፃሚነት ወስንን መሰረት በማድረግ በሌላ አኳኋን እንዲፈፀም በሕግ ባልተደነገገበት ሁኔታ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
በመሆኑም ከመነሻውም ኢትዮጵያ በፈረመችው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሰረት በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ላለመዳኘት ነገር ግን ከኢትዮጵያ ዜጎች ጋር ለመሰረተው ግንኙነት በሌላ አግባብ ጉዳዩን ለመጨረስ የሚያስችል ስርዓት ያለው ወገን በዋናው ክርክር ጊዜ ቀርቦ ባለመከራከሩና በይግባኝ ጉዳዩን ባለማሳረሙ ምክንያት ብቻ ስልጣን የሌለው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ እንዲፈጽም የሚገደድበት አግባብ የለም፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጉዳይ የተለየ ባሕርይ ስንነሳ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ ቁጥር 212 እና 4 ድንጋጌዎች አንድ ላይ ተጣምረው ሲታዩ አፈፃፀሙ ዋጋ ያለውን ፍርድ መሰረት ያደረገ ነው፣ ጉዳዩ ከስነ ስርዓት ጉድለት ጋር የተያያዘ ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አላገኘንም፡፡
ተጠሪ በሕግ የተጠበቀለት የከለላ መብትና ጥቅም እያለው ስልጣን የሌለው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ እንዲፈጽም ማድረግ ሕግ አውጪው የዲፕሎማቲክ ግንኙነቶችን ልምድን ለማክበር ሲባል በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 3(3(ሀ)) ስር ያስቀመጠውን ድንጋጌ ዋጋ የሚያሳጣው እና በዲፕሎማቲክ ግንኙነቱም አሉታዊ ውጤት የሚያስከትል በመሆኑ ተመራጭ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ሲጠቃለልም የጉዳዩ ልዩ ባህርይ ሲታይ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 212 ድንጋጌን ጠቅሶ አፈፃፀሙን ማስቀጠል የሚቻልበት አግባብ ስለሌለና አመልካችም እንደዜጋ መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በኩል በዘረጋው ስርዓት መሰረት መብትና ጥቅማቸውን የሚያስከበሩበት ሁኔታ ያለ በመሆኑ የሕግ የበላይነት አልተከበረም፣ ዜጋ ፍትህ የማግኘት ሕገ መንግስታዊ መብት ተጥሷል ለማለት ስላልተቻለ የክልሉ ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከታዩን ወስኗል፡፡
ውሳኔ
በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመለያ ቁጥር 163639 ታህሳስ 07 ቀን 2006 ዓ.ም የበታች ፍርድ ቤቶችን ትዕዛዝ በማፅናት የተሰጠው ውሳኔ በፍትሃ ብሔር ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 348(1) መሰረት የፀና ሲሆን፤ የአመልካች የአፈጻጸም ክስ መዘጋቱ ተገቢ ነው ሲል በይኗል፡፡ አመልካች አለኝ የሚሉትን መብትና ጥቅም በሌላ አግባብ ከመጠየቅ ይህ ውሳኔ አያግዳቸውም ሲልም ሰበር ዶሴውን ዘግቶታል፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/ 2015 ዓ.ም