ትውልድም ሆነ እድገታቸው በቀድሞው አጠራር በሸዋ ክፍለ አገር በጅባትና ሜጫ አውራጃ በአንቦ ወረዳ ቶኬ በሚባል አካባቢ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ቶኬ ራስ መስፍን ስለሺና ዶኬ ኢሬሳ በተባሉ ትምህርት ቤቶች ነው የተማሩት፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አምቦ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን የ11ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ወስደው ውጤታቸውን እየተጠበቁ ሳሉ ግን የአንደኛ ዙር ብሔራዊ ውትድርና ሲጀመር መሄድ አለብህ ተብለው ተይዘው ይታሰራሉ፡፡ ይሁንና ሌሊት ከእስር ቤት አምልጠው ከአካባቢዉ ተሰወሩና ለስድስት ወራት ያህል ቆዩ፡፡ ሁለተኛ ዙር ምልመላ ሲጀመር ግን ከወትድርና ማምለጥ እንደማይችሉ ተገነዘቡ፡፡ እናም ምድር ጦር ስፖርት ክለብ ውስጥ በነበረ የአክስታቸው ልጅ አማካኝነት ምድር ጦር ውስጥ በሚገኘው መቻል ስፖርት ክለብ ተቀጠሩ፡፡
በዚያ መሰረት አዳማ በሚገኘው ታንከኛ ማሰልጠኛ ክምፕ ውስጥ የውትድርና ትምህርት እንዲወስዱ ተላኩ፡፡ ለስድስት ወራት ውትድርና ትምህርታቸውን ተከታትለው ሲጨርሱ ወደ ምድር ጦር ስፖርት ክፍል ተመልሰው ለሶስት ወራት ያህል አገለገሉ፡፡ በመቀጠልም ወደ ሆለታ ገነት የመኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የመኮንነት ትምህርት ለሁለት ዓመት ተከታተሉና በምክትል መቶ አለቃነት ተመረቁ፡፡ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ እዚያዉ ጦር ትምህርት ቤት አዲስ እጩ መኮንኖችን ስፖርት እንዲያሰለጥኑ ተመድበው ለሁለት ዓመታት አገለገሉ፡፡ ሙሉ መቶ አለቃ ሲሆኑ ደግሞ ወደ ምድር ጦር ስፖርት ክፍል ተመለሱና በአትሌትክስና በመረብ ኳስ ሲሳተፉ ቆዩ፡፡
ከስፖርቱ ጎን ለጎን የጤና ረዳት ኮርስ ወስደው እየሰሩ የነበሩት እንግዳችን በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ላይ መፈንቅለ-መንግስት ተሞክሮ ሲከሽፍ ስፖርተኞች በሙያቸው ተመድበው ወደ ስራ ይግቡ ተባለና እሳቸውም ወደ ምድር ጦር መሳሪያ ጥገና እና እደላ ግምጃ ቤት ተመደቡ፡፡ እዚያው እየሰሩ ሳለ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን መጣና ለአንድ ሳምንት ከተማው እስኪረጋጋ ድረስ እሳቸውም ሆነ ሌሎች ሰራተኞች እቤታቸው እንዲቆዩ ተደረገ፡፡ ከአንድ ሳምንት በኋላ የጤና ባለሙያና መካኒኮች ስራ እንዲጀምር ጥሪ ተደረገላቸውና ዳግመኛ ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡ ይሁንና ሁኔታዎች እንዳሰቧቸው አልቀጠሉም፤ በሶማሊያ ጦርነት ወቅት የተበተኑ መሳሪያዎችን የመሰብሰብ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው በተላኩበት ወቅት ጓደኞቻቸው ተገድለው ጠበቋቸው፡፡
ይህ ሁኔታ እጅግ ተስፋ ያስቆረጣቸው እንግዳችን ስራቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን ትተው ጫካ ገቡ፡፡ የኦነግ አባል ሆነው መታገል እንደጀመሩ ያሰቡት አልጠበቃቸውም፤ የድርጅቱ አባላት እርስበርስ የተከፋፈሉና በመካከላቸው የሌላን አካል ተልዕኮ የሚያስፈፅሙ መሆናቸውን ተረዱ፡፡ በተለይ ደግሞ እሳቸው ነጻ አወጣዋለሁ ብለው ላሰቡት ንፁህ ህዝብ ይልቅ እርስበርስ የማይተማን ፖለቲከኛ መሆኑ ክፉኛ ያበሳጫቸው ስለነበር ተቋውሟቸውን ባገኙት አጋጣሚ ማንሳት ጀመሩ፡፡ ይህም በአንዳንድ የኦነግ አመራሮች ጥርስ ውስጥ አስገባቸው፡፡
በሌላ በኩል እሳቸው ጫካ ሳሉ በሕወሓት ተላላኪዎች በተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸውም ነበር፡፡ በኋላ ነገሩ እየባሰ ሲመጣ እየታገሉ ወደ ሱማሊያ ተሰደዱ፤ ቀጠሉም ኬኒያ ገቡ፡፡ በኬኒያ እያሉም በተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው እኚሁ ሰው ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በእንግሊዟ ለንደን ከተማ ኑሯቸውን አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ምክር ቤት የቦርድ አባል በመሆንም የአገራቸው ጠበቃና ዲፕሎማት በመሆን የምዕራባውያኑን ተፅዕኖ ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡ ከእንግዳችን ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደ ትግል የገቡበት አጋጣሚ ያስታወሱንና ውይይታችንን እንጀምር ?
አቶ በንቲ፡- ደርግ ከወደቀና በጊዜው ከነበረው አገዛዝ ጋር ስራ ከጀመርኩኝ በኋላ በደርግ ጊዜ ከሱማሌ ጋር በተደረገው ጦርነት በምስራቅ ኢትዮጵያ ሄጄ የወደሙ መሳርያዎችን ሰብስበን ለመጠገን ከመካኒኮች ጋር ተልከን ነበር። በትዕዛዛችን መሰረትም 111 ታንኮችን ሰብስበን በመጠገን 68 ታንኮች ለስራ ዝግጁ አድርገን ከስድስት ወር ቆይታ በኋላ ታንኮቹን ወደ ድሬደዋ አመጣንና ወደ አዲስ አበባ ተመለስን። አዲስ አበባ ከተመለስኩኝ በኋላም ሰላም ለማስከበር ቡሩንዲ እንደምሄድ ተነገረኝና ያንን ግዳጅ እየተጠባበኩኝ ሳለሁ በጣም የምወዳቸዉ ጓድኞቼ ተገደሉ። ለምን ተገደሉ? ብዬ ስጠይቅ መንግስት እንደገደላቸው ሰማሁኝ። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች በዚህ ዓይነት ሁኔታ ከቀጠሉ በኋላ እኔንም አይተውኝም ብዬ ኦነግን ተቀላቀልኩ። ወጣቶችን በማደራጀትና በማስታጠቅ በድብቅ በሜጫና ቱለማ ልማት ማህበር ስር የወጣቶች ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኜ መስራት ጀመርኩኝ።
ታስቦ የነበረው ምርጫ ሊሳካ ባለመቻሉና ቻርተሩም በመፍረሱ ኦነግ ወደጫካ ተመለሰ። ከዚያ በኋላ በአዲስ አበባ፣ በወሊሶ፣ በአምቦ በስለላ ሰራዊት በማደራጀት የወቅቱን አገዛዝ መውጫና መግቢያ አሳጣናት። በዚህ አይነት እንቅስቃሴ ያደራጀነው ሰራዊት ቁጥር እየጨመረ እኔንም ክትትል ስለበዛብኝ ኦነግ ወደአለበት ሃረርጌ በረሃ ለመሄድ ወሰንኩኝ። እናም ለማንም ሳልናግር አንድ የሦስት ዓመትና የሁለት ወር ልጆቼን ለእናታቸው በመተው የነበረችኝን ስድስት ሺህ ብርና አንድ ቶዮታ መኪና በመያዝ ሶስት ሆነን ድሬደዋ ገባን። ድሬደዋ 15 ቀን ከቆየሁ በሁዋላ የመኪናዬን ቁልፍ አንዱን ለደጋፊዎች ከነመኪናዉ አንዱን ራሴ ይዤ ወደ በርሃ ገባሁ።
በርሃ ከደርስኩ በኋላ ቁልፉንና ገንዘቡን እዛ ቦታ ላይ ለሚገኘው አዛዥ ሰጥቼ የመጣሁበትን ምክንያትና በሸዋ ውስጥ በተለያየ ቦታ ሰራዊት አደራጅተን በወቅቱ ከነበረው አገዛዝ እየተፋለምን መሆናችንን አስረዳሁት። በኋላም አዲስ ምልምሎችን የማሰልጠን ኃላፊነት ተሰጥቶኝ ለሶስት ወራት አሰለጠንኩኝ። ሁለቱ ጓደኞቼ ግን ሌላ ቦታ ተመደቡ፤ እኔ እዛው ማሰልጠኛ ካምፕ ተመድቤ የተለያየ ውጊያዎች ላይ ብሳተፍም ምንም ጉዳት ሳይደርስብኝ ቆየሁኝ።
አዲስ ዘመን፡- በሕወሓት ተላላኪዎችም ሆነ በኦነግ ሰዎች የመግደል ሙከራ ተደርጎቦት እንደነበር ይታወቃል። እስቲ ይህን ያብራሩልን?
አቶ በንቲ፡– ልክ ነሽ ። እ.ኤ.አ በ1994 የኦነግ ገዳይ ቡድን ሪሳ የሚባል ግሩፕ እኔና ጓደኛዬን ለመግደል ተልኮ ቢመጣም ሳይመቸው ቀርቶ ከግድያው አመለጥን። ሆኖም ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ለሶስተኛ ጊዜ ሊገሉን ተዘጋጅተው ሳለ እኔ በአጋጣሚ ወጥቼ አላገኙኝም፤ ጓደኛዬም ወደ ሰላሌ ሄዶ ስለነበረ እኛን ሲያጡን አልይ አደረ የሚባልና የጋላሳ ድልቦ ቀኝ እጅ የነበረን ሰው ገደሉት። እኔም አገር ሰላም ነው ከወጣሁበት ወደ ጫካ ስመለስ ያገኙኛል፤ አንደኛው ‹‹ከየት መጣህ?›› ብሎ ጠየቀኝ፤ እኔም የመጣሁት ከአዲስ አበባ መሆኑን ግን ደግሞ ትውልዴ አምቦ መሆኑን ስነግረው ደንግጦ ‹‹ወይኔ ወንድሜ! እራሴን በራሴ በልቼ ነበር፤ አንተና ኣብደታን ግደል ተብለን ከዚህ ጋር ሶስት ጊዜ አጣናቹ፤ እናንተን ስናጣ አልይ ኣዳሬን ገድለን መጣን›› አለኝ። እኔም ያላሰብኩት ስለነበር በጣም ደነገጥኩና ለምን ገደላችሁት ብዬ ስጠይቀው በኦሮሞ ስም የተደራጀ እብሶ የሚባል የተደራጀ ጠላት ቡድን ተልዕኮ ተሰጥቷቸው እንደሆነ ነገረኝ። መደንገጤን ያዩ ሌሎች አባላት ደግሞ በሳምንቱ መሳሪያዬን ተቀብለውኝ ‹‹ስምንት ቁጥር›› በሚባለው መንገድ አስረውኝ ቀጠቀጡኝ። በዚህ መልኩ ለሁለት ወር ታስሬ ከቆየሁ በኋላ ሌላ ቦታ ተልኬ እንድታከም ተደረኩኝ፤ ብታከምም ግን አሁንም ድረስ እጄ አይሰራም፤ ከባድ እቃ ማንሳት አልችልም።
የሚገርምሽ ከስድስት ወር በኋላ ደግሞ አጠቃላይ ስብሰባ ላይ ጠርተውኝ ስለተደረገብኝ ነገር ይቅርታ ጠየቁኝ። ምንም ማድረግ ባልችልም ባደረጉት ትግል በሰራዊቱና በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅ ሆንኩኝ። አንድ ቀን በጊዜው ከነበረው አገዛዝ ጋር ባደረግነው እልህ አስጨራሽ ውጊያ እግሬ ላይ በሁለት ጥይት ተመታሁ። ከዚያ ውጭ ምንም ጉዳት ደርሶብኝ አያውቅም። በመጨረሻ እ.ኤ.አ በ1996 መጨረሻ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እኛን ለማጥፋት ዘመቻ ከፈተብን፤ ያንን ዘመቻ መቋቋም አልቻልንም፤ አዛዦች በአንድ ወንዝ ውስጥ ሰብስበውን ‹‹የተከፈተብን ዘመቻ ከብዶብናል፤ ተበታትነን መኖር አለብን፤ ከሶስት ወር በኋላ እዚሁ እንገናኝ›› አሉን። ለካ አንዳንዶቹ ከአገዛዙ ጋር ይሰሩ ኖሮ እነሱ እንደሄዱ እኛ ከወንዙ ውስጥ ስንወጣ በጠላት ተከበብን፤ ውጊያ ጀመርን ያለቀው አለቀ፤ ሌላው ተበታተነ፤ እኔም ብቻዬን ቀረሁኝ። ለሶስት ወራት በባሌ ተራራና ቆላማ ስንከራተት የሚበላ አጥቼ ቁልቋል እየበላሁ ቆየሁኝ። በመጨረሻ ግን ቁልቋሉም ጠፋ፤ መሬቱ ሁሉ ደረቀ፤ ራሃቡ ሲጠናብኝ ሃያ የተባለ አፈር እየበላሁ በየቦታው ተደብቀው ያሉትን ቁሰለኞች ማሰባሰብ ጀመርኩኝ።
የዚያዉ አካባቢ ተበትነው የገቡ 68 ልጆች ይዤ ወደ ሱማሌ ጉዞ ጀመርን። በጣም የሚገርምሽ በጉዞ ላይ ሆነንም አንድም የምንበላው ምግብ የለንም ነበር። ለ28 ቀናት በቅጠልና በውሃ ብቻ ተጉዘን የሱማሌ ድንበር ስናቋርጥ በሁለት ክላሽ ጠመንጃ አንድ ግመል ገዝተን በላን። በዚያው እለት ሁለት ልጆች ሞቱብን፤ ከዚያ በፊት ደግሞ ሕወሓት ከፊታችን ጠብቆን ተኩስ ከፈተብን ሶስቱ ልጆች ሞተውብን ነበር። በኋላም ከበባውን ሰብረን ወጣንና በ32ኛ ቀናች ሁዱር የምትባልና በሁሴን አይዲድ የምትቆጣጠር የሱማሌ ድንበር ላይ የምትገኝ ከተማ ገባንና ሱማሌዎች ተረከቡን።
ሱማሌ ከገባን በኋላ ጠፍተው የነበሩት አዛዦች ከአሜሪካና ከአውሮፖ ሞቃዲሾ ላይ ተሰብስበው ምርጫ አካሄዱ። ከዚያ በኋላ ግን እኔ እንድገደል ሰው ተላከብኝ፤ ሆኖም አስቀድሞ መረጃ ስለደረሰኝ ሊገድሉኝ የመጡት ከሰራዊቱ ውስጥ ቢጠሩኝም ወደ እነሱ ሳልሄድ በሩጫ አመለጥኳቸዉ። ተኩሰውም ኣላገኙኝም። በሶስት ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ከሄድኩኝ በኋላ ሁሴን አይዲድ አይሮፕላን ልኮልኝ ወደ ሞቃድሾ ወሰደኝ። በኋላም ጉዳያችን በሽምግልና እንዲያልቅ ተደረገ፤ ይቅርታም ተጠየኩኝ።
እ.ኤ.አ በ1999 ደግሞ ከውጭ ሀገር ሰራዊትና መሳሪያ ሲመጣልን ይህንን ሰራዊት ይዘን ወደ ኢትዮጵያ እንመለስ ብለን ጥያቄ ስናቀርብ እናንተ አትመለሱም ብለውን ያንን ሰራዊት ቤዳቦ የምትባል ቦታ ወስደው አስጨረሱት። ከዚያ በኋላ እኔም ከትግሉ ተስፋ ቆርጬ ትቼ ወጣው። ሆኖም አሁንም እንድገደል ወስነው ማሳዳዳቸውን አላቆሙም ነበር። ግን ሊያገኙኝ አልቻሉም። ኬኒያ ናይሮቢ ከገባሁኝ በኋላም ከመታሰር ጀምሮ በጥይት ሶስት ጊዜ በላይ የመግደል ሙከራ ተደርጎብኛል። አንድ ጊዜ እንዳውም በሁለት ጥይት በግራ በኩል ከጡቴ በላይ ተመትቼ አሁን ድረስ ጉዳቱ ብዙ ችግር አድርሶብኛል። ወደ እንግሊዝ ለመሄድ አንድ ወር ሲቀረኝ መርዝ አጠጥተውኝ ሆስፒታል ገብቼ ተርፌያለሁ። አሁን በምኖርበት አገር ሳይቀር ተደራጅተው መጥተውብኝ አዋርጄ ነው የመለስኳቸው። እስካሁን በርካታ የግድያ ሙከራዎች ቢደረጉብኝም ፈጣሪ እንደሰው ባለመሆኑና እሱ ከፈቀደው ቀን ውጭ ሊሆን ስለማይችል እስካሁን በህይወት አለሁኝ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ የውጭ ኃይሎች የሚፈጽሙት ሴራና በመንግስት ላይ የሚያደርጉት ጫና በእርሶ እምነት የምን ፍላጎት ነው?
አቶ በንቲ፡– በእኔ እምነት የውጭ ጠላቶቻችን አንድ እንዳንሆን፤ እንዳንስማማ፣ ወደ ልማት እንዳንገባ፤ እንዳንማርና ከመሃይምነት እንዳንወጣ ያደረጉት ከጥንትም ቢሆን በአባቶቻችን በአድዋ ላይ ድባቅ በመመታታቸው ቂም ስለያዙብን ነው። ይህቺ ደሃ ሃገር ትላንት አዋርዳናለች፤ ለዘመናት ለእኛ ሳትገዛ ነው የኖረችው፤ አሁንም የእኛ ትዕዛዝ የማትቀበልናት በሚል በቂም በቀል ተነሳስተው የሚያደርጉት ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ የጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ ሌላውን አገር ለመቆጣጠር የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ በመሆኑ የኢትዮጵያ ካመለጠቻቸው አፍሪካ ላይ እንደፈለጉ መሽከርከር እንደማይችሉ ስለተገነዘቡ ነው። በመሆኑም አሁን ላይ የደከመች፤ የተሰባበረችና የተበታተነች ኢትዮጵያ እንድትሆን በጠላትነት መንፈስ የሚያደርጉት ነው።
እኛ ራሳችንን ከቻልና እና ከድህነት ከወጣን ለሃያላኑ አንታዘዝም፤ እርዳታቸውንም አንፈልግም። ይህ ሲሆን ደግሞ እነሱ ኑሯቸው፤ ኢኮኖሚያቸው የተመሰረተው በአፍሪካ ላይ ስለሆነ ያንን ያጣሉ። በተጨማሪም ትላንትም አባቶቻችን ድል እንዳደረጓቸው እኛም ድል ስናደርጋቸው በዚህ የተነሳ እኛ ደግሞ በተራቸው ማንበርከክ አለብን በሚል ነው ዓላማችንን ይፈጽሙልናል የሚሏቸውን ኃይሎች ተላላኪ አድርገው ሲጠቁሙባቸው የቆዩት። በአድዋ ላይ ጥለውት የሄዱትን የክፋት ዘር አሁንም ከመቶ ዓመት በኋላ ለመድገም እየሰሩ ነው ያሉት። በተለይ ለውጡ ሲመጣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቁጭት ከድህነት መውጣት አለብን ብሎ ሲነሳ ከድህነት እንዳንወጣና የእነሱን ፍላጎት ብቻ እንድናስፈፅሞ ሲሉ የማይምሱት ጉድጓድ የለም። እርግጥ ነው ተላላኪ መንግሥት በነበረበት ዘመን ቅኝ አልተገዛንም ብንልም በስውር በተላላኪዎቻቸው አማካኝነት ተገዝተን ነው የኖርነው። ለውጡ ሲመጣ ግን ይህንን ማስቀጠል ስላልቻሉ ነው እንቅልፍ አጥተው እያተራመሱን ያሉት።
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ኃይሎች ጫና በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት እያየለ መጥቷል። በዋናነትም ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ በውስጥ ጉዳይ ላይ እያደረጉት ያሉትን ጣልቃ ገብነት እንዴት ያዩታል?
አቶ በንቲ፡– አንዳንድ የምዕራቡ አገራት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የሚገቡት፤ በተለይ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ ጫና እያደረጉ ያሉት ለኢትዮጵያ ህዝብ አስበው ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም መከበር እንደሆነ ግልፅ ነው። በሚል ነው። ምክንያቱም እነሱ ህዝብ የመረጠውን መንግስት አንቀበልም ብለው ትናንትም በስውር ሲያስተዳድሩን የነበረው በዚህ በተላላኪዎች አማካኝነት ስለነበረና የእሱ መውደቅ ደግሞ እነሱ ተልዕኳቸውን እንዳይፈፅሞ ስለሚያደርጋቸው ነው። በመሆኑም ከእነሱ አስተዳደር ውጭ መኖር አትችሉም በሚል ሊገዙን፤ ሊያንበረክኩን ይፈልጋሉ፤ እኛ ደግሞ አንገዛም ብለን ሉዓዊነታችንን ላለማስደፈር እየታገልን ነው ያለነው።
አስቀድሜ እንዳልኩሽ ልዩነት እንዲኖረን ያደረጉት እነሱ ናቸው። አሁንም በዚህ ጦርነት የምዕራባውያኑ ፍላጎትና አላማ ገሃድ ወጥቷል። ደጋግመው የኢትዮጵያ ጉዳይ አጀንዳ የሚያደርጉት የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት የሚሉትን ለማስታጠቅና ህይወት ለመዝራት ነው እንጂ ለኢትዮጵያ ህዝብ ብሎም ለትግራይ ህዝብ አስበው አይደለም። ይሁንና ጠላቶቻችን መመከት የምንችለው አንድ ሆነን በፍቅር ስንቆም ነው። አንድነታችንን እስካጠነከርን ድረስ ግን ተፅዕኖው ሊጎዳን አይችልም።
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ተፅዕኖውን በመከላከል ረገድ ዲያስፖራው ምን እየሰራ ነው፤ ምንስ ይጠበቅበታል?
አቶ በንቲ፡- በዲያስፖራው በኩል በመጀመሪያ ይሄ ለውጥ ሲመጣ በጣም ደስ የሚል አንድነት ፍቅር ኃይል ነበረን። እንደሚታወቀው ጠላቶቻችን በመካከላችን በረጩብን መርዝ ምክንያት ከፊሉ በመንግስት ላይ ያኮረፉ ነበሩ። ሌላው ደግሞ ፖለቲከኞች ‹‹እኔ አውቅልሃለሁ›› በሚል በጎሰኝነት እንድንከፋፈል አድርገውን ነበር። ይሁንና የጠላቶቻችንን ሴራ እንዲጋለጥ በዲያስፖራው የተግባር ምክር ቤትም ሆነ ሌሎች አካላት ካደረጉ በኋላ አሁን ላይ አብዛኛው ዲያስፖራ ወደ አንድ መንፈስ መጥቷል። ከዚያም አልፈን በአገራችን አንድነት አንደራደርም ብለን፤ በአንድነት ቆመን በሰላማዊ ሰልፍ፤ እውቀት ያለው በእውቀቱ፤ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፤ ጉልበት ያለውም በጉልበቱ እየተባበርን አብረን እየሰራን ነው። ውጭ ከምናደርገው ትግል ባሻገር መከላከያችንና ህዝባችንን ለመደገፍ የተግባር ምክር ቤቱ አባላት በተለያየ ዙር አገር ቤት ድረስ በመምጣት አጋርነቱን አረጋግጧል። ምክር ቤቱ ጠላቶቻንን ‹‹ኢትዮጵያ ፈርሳለች፤ አገሪቱን ለቃችሁ ውጡ›› እያሉ የሃሰት ፕሮፖጋዳ በሚነዙበት ወቅት የዲያስፖራ ምክር ቤት አሰባስቦ 500 የሚሆኑ የዲያስፖራ አባላትን ይዞ መጥቷል። ከዚያም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባቀረቡት ጥሪ መሰረት አባቶቻችን ወደ አገራቸው ገብተው አጋርነታቸውን አሳይተዋል። ይህም ለኢትዮጵያ መፍረስ ጉድጓድ ሲቆፍሩ የነበሩ ጠላቶቻችንን አሸነፍን ማለት ነው። ህዝባችንን ለመከፋፈል የሚፈልጉ የጠላቶቻችንን ተላላኪዎችና ፖለቲከኞች ነን ባዮች እቅድ ሊሳካላቸው አልቻለም። እኛም በየሚዲያዎቹ እየዞርን ህዝባችንን እያስተማርን ነው። ፈጣሪ ይመስገን አሁን ላይ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው ዲያስፖራ ወደአንድነትና ፍቅር መጥቷል። ቀን ከሌሊት ሳይል ስራውንም ሆነ የግል ህይወቱን በመተው ለአገሩ ጥቅም ዘብ የቆመበት ጊዜ ነው ያለነው። በቀጣይም ይኸው ትግላችንን ተጠናክሮ ነው የሚቀጥለው።
በየሚዲያው ላይ እንደሰማሽው ደግሞ አንዳንድ አገራት እያደረጉ ያሉትን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ በያለበት አገር ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ተቋውሞውን እያሰማ ነው። በቀጣይም በአሜሪካና በሌሎችም አገራት ተመሳሳይ ልክ እንደ ‹‹No More›› አይነት ከባድ ነውጥ የሚያስነሳ የተቃውሞ ሰልፍ ይካሄዳል። በተለይ እኛ በምኖርበት አገር ለንደን ከተማ ላይ ከፍተኛ የሆነና በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ የሚሳተፍበት የተቋውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ዝግጅታችንን አጠናቀናል። ከሁሉም አቅጣጫ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያኖች ድጋፋቸውን እያረጋገጡልን ነው ያሉት። በእውቀታቸውና ጉልበታቸውና ገንዘባቸውን ሳይሰስቱ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው። ህዝባችን ለዚህ ቆርጦ ተነስቷል። ትልቁ ነገር ምንድን ነው አገር ቤት ውስጥ ያሉትም፤ ውጭ ያሉትም በመናበብ እየሰራን መሆኑ ነው።
በሌላ በኩል ግን ዲያስፖራው በአገሩ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ሲመጣ አንዳንድ በመንግስት ስር የተሸጎጡ አካላት በቢሮክራሲና በሙስና አማርረው ያመጣውን ገንዘብ እንዲያጠፋ አድርገው ያለምንም ውጤት ተመልሶ እንዲወጣ ያደረጉበት ሁኔታ አለ። ይህም ቁጥሩ ቀላል የማይባለውን ዲያስፖራ አስኮርፎታል። ከዚህም በተጨማሪ በመንግስት ላይ ጥላቻና ዘመቻ ወሬ መንዛት ጀምረው ነበር። ይህም ማለት መንግስት ውስጥ ያሉ ሰዎች ህዝብ ወደ መንግስት እንዳይቀርብ ያደረጉበት ሁኔታ ፈጥሮ ነበር።
ይሁንና በዲያስፖራው ምክር ቤት አማካኝነት ይህንን አጀንዳ ለዲያስፖራው ያቀበለውና ዲያስፖራው በመንግስት ላይ እምነት እንዳይኖረው ያደረገውን ጠላት ሴራ በማጋለጥ ከፍተኛ ርብርብ አድርገናል። አሁን ላይ ብዙዎቹ ሴራውንና ያለውን ችግር ተረድተው ከዚህ ተግባራቸው ታቅበዋል፤ ተመልሰውም አገራቸውን በመደገፍ ላይ ነው የሚገኙት።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በምግብ እህል ራሷን ለመቻል በተለይ የስንዴን ምርታማነት እያሳደገች ነው። ይህ የልማት ስራ ያላስደሰታቸው የምዕራቡ አገራት በኢኮኖሚ ደረጃ እያደረጉ ያሉትን አሻጥር እንዴት ያዩታል?
አቶ በንቲ፡- በነገራችን ላይ የስንዴው ልማት ብቻ አይደለም ሌሎችንም የልማት ስራዎች ማስፋት ይገባናል። ምክንያቱም እርዳታ ጠባቂ የሆነ መንግስትና ህዝብ መቼም ቢሆን በሁለት እግሩ መቆም አይችልም። የሚገርመው ነገር በአፍሪካ ውስጥ ጥሬ ሃብቷ ያልተበላው ኢትዮጵያ ብቻ ነች። ይህንን ጥሬ ሃብት ትኩስና ወጣት ሃብት እያለን እስከዛሬ መለመናችን በራሱ ሊያሳፍረንና ሊያስቆጨን ይገባል። በእርግጥ የነበረው አስተዳደር በራሱ የሚኖረው አስተዋፅኦ አለ። በንጉሱ ጊዜ የቴክኖሎጂ አቅማችን ወደኋላ አስቀርቶናል፤ በደርግ ዘመን ኮሎኔል መንግስቱ አጋዥ አላገኙም ነበር። በነገራችን ላይ መንግስቱ ሃይለማርያም ሲናገሩ የነበሩት ሁሉ አሁን በተግባር እያየነው ነው ያለው። እሳቸው ለአገራቸው ብዙ ራዕይ ቢኖራቸውም አሁን እንደምናየው በምዕራባውያኑ ተንኮል ከአገራቸው ወጡ።
ስለዚህ አሁንም መንግስታችን እያለማ ያለው ስንዴ አይደለም ኢትዮጵያን አፍሪካንም ጭምር መመገብ ይችላል። ስለዚህ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መንግስት ለምን ይህንን አላደረገም ከሚል እኔ ምን አደረኩኝ ለዚህች አገር ብሎ ራሱን ሊጠይቅ ይገባል። ይህንን ማድረግ ከቻልን እንለወጣለን፤ ከጠባቂነት ወጥተን እናድጋለን፤ ከማንም ጋር ደረታችንን ነፍተን የምንኖርበት ሁኔታ ይፈጠራል ባይ ነኝ። እኛ ኢትዮጵውያን ነን፤ ቀኝ አልተገዛንም፤ አንገዛም፤ ትላንት ረሃብተኛና መሃይም ያደረጋችሁን እናንተ ናችሁ። አሁን ነቅተናል፤ ከችግር ለመውጣት በራሳችን እንቆማለን ከሚያከብሩን ጋር ኃይላችንን አጠናክረን እንቆማለን። ከማንኛው ጠላት ጋር ተጋፍጠን የአገራችን ህልውና እናስጠብቃለን።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ በንቲ፡– እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/ 2015 ዓ.ም