ስንዴ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ እንዲሁም ሌሎች አገራችን የምታመርታቸው ጤናማ የሆኑና ጤናንም ለመጠበቅ ትልቅ አቅም ያላቸው ስለመሆናቸው ተደጋግሞ ይነሳልⵆ መነሳትም ብቻ ሳይሆን ሁሉም አንደ አቅሙ ከገበታው ባይለያቸው ተብሎም በጤና ባለሙያዎች ይመከራልⵆ መንግስትም ግሪን ሌጋሲ በሚል እነዚህ ምርቶች አንድም ከጤና በረከታቸው ሁለትም በምግብ እህል እራስን ከመቻል አንጻር ይለመዱ ይዘወተሩ ባህልም ይሆኑ ዘንድ ሰፋ ያለ ስራን እየሰራባቸው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሰሞኑ በምድረገነቷ አርባ ምንጭ ከተማ ላይ በመገኘት “የሌማት ቱርፋትን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ” ይፋ አድርገዋልⵆ ይህ የሌማት ቱሩፋት አገራችን ውስጥ የሚመረቱ ለጤናም በምግብ እህል ራስን ከመቻል አኳያም ከፍ ያለ ጥቅም ይኖራቸዋል የተባሉ የአትክልትና ፍራፍሬ አይነቶችን ለማስለመድ አዲስ የልማት ዘመቻ የሚጀመርበት ነውⵆ
እስከ ዛሬ ጤናማ ያልሆኑ እንደ ስኳር፣ በመደበኛ የቤት ውስጥ ሙቀት የሚረጋ ዘይትና የአትክልት ቅቤ፣ የጨው መጠናቸው የበዛባቸው ምግቦችና መጠጦች፤ አዘውትረን በመመገባችን በዓለም ላይ እየተንሰራፉ ለመጡት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና ለሌሎች የጤና ችግሮች ተጋላጭ ሆነን ቆይተናልⵆ በሌላ በኩልም ፈጣንና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን አብዝተን መጠቀማችንም ለልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች የልብ ድካምና ስትሮክ፣ ካንሰር፣ ሥር የሰደዱ የመተንፈሻ አካላት ህመሞች እንዲሁም ሥር ለሰደደ የሳምባ ምችና አስም። የስኳር በሽታም አጋልጦናል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ብዙ ሰዎች በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን ገዝቶ የመጠቀም ልምድ እያደበሩ በመሆኑም እነሱን ለማከም አገር ከፍ ያለ ወጪ ውስጥም ወድቃለች።
እ.ኤ.አ. በ 2019 በአገሪቱ የተመዘገበው 39 ነጥብ 2 በመቶ አጠቃላይ ሞት ተላላፊ ባልሆኑ ህመሞች ማለትም እንደ ልብ፣ ስትሮክ፣ የስኳር በሽታና ካንሰር ባሉ ሥር በሰደዱ በሽታዎች ምክንያት መሆኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃዎች ያመላክታሉ።
በ2017 ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አጠቃላይ የመንግስት ወጪም 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን በዚሁ ዓመት ይህ ወጪ ደግሞ 31 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የኢኮኖሚ ኪሳራ እንዳደረሰም ነው መረጃው የሚያመለክቱት። ይህም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 1 ነጥብ 84 በመቶ አካባቢ ይይዛል እንደማለት ነው።
አብዛኛዎቹ ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ጤናማ ባልሆነ አመጋገባችን ምክንያት የሚከሰቱብን መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፤ ጤናማ የአመጋገብ ልማድን በመከተል ራሳችንና ቤተሰባችንን ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መከላከልም እንዲሁም እንደ አገር የተያዘውን የግሪን ሌጋሲ ዘመቻ ተግባራዊ እያደረግን በአገራችን ምርት መጠቀምን መልመድ የሁሉም ኃላፊነት ነው።
የስነ ምግብና የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ዘላለም ደበበም አለማችን ላይ ጤናማ ያልሆኑ አመጋገቦች የሰውን ልጆች እየጎዱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስር እንዲሰዱ ምክንያት እየሆኑና ሰዎች ያለ እድሜያቸው እንዲሞቱ እያስገደዱ ስለመሆኑ ይናገራሉⵆ
ጤናማ ያልሆኑ አመጋገቦች ከተፈጥሮ ውጪ በሆኑ ምርቶች የተዋቀረ ምግብን አዘውትሮ መመገብ ማለት ነው፤ የሚሉት ዶክተር ዘላለም ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ አደጋዎች ብዙ ናቸው።. አካላዊ እና አእምሯዊ እድገታችን በምንመገባቸው ንጥረ-ምግቦች ላይ የተመሰረተ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሚዛናዊ እና ጤናማ ያልሆነ እድገት እንዲፈጠር ያደርግልⵆ ይህ ሁኔታ ደግሞ በልጆችና በታዳጊዎች ላይ የጎላ ተጽዕኖን ይፈጥራል፡፡
በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምርቶች፣ የማምረቻ ሂደት ያላቸው ኬሚካሎች፣ ጣዕምን የሚያሻሽሉ ንጥረ ነገሮች፣ ማቅለሚያዎች ለጤና አደገኛ የሆኑ ሁሉንም አይነት ንጥረ ነገሮችን ያካትታሉ ይላሉ። እነዚህ ምግቦች ደግሞ በአጭርና በረጅም ጊዜ በጤና ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ከማድረሳቸውም በላይ በተለይ በልጆች ዘንድ ሱስ የመሆን ሂደታቸው ሰፊ ነው።
ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት የኢንዱስትሪ መጋገሪያዎች በስኳር የተሞሉ ኬኮች ጣዕም የሚያሻሽሉ ንጥረ ነገሮች ፋሽን አድርገው ነበር የሚሉት ዶክተር ዘላለም፤ እነዚህ ምርቶች በልጆች አመጋገብ ውስጥ እየተለመዱም መምጣታቸው ግን አሁንም በልጆቻችን አካላዊና አእምሯዊ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን ከማሳደሩም በላይ አዋቂዎችም በማዘውተራቸው ምክንያት ከላይ ለገለጽናቸው ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች መበራከት የራሳቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን ያብራራሉ።
እንደ ዶክተር ዘላለም ገለጻ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ምግብ በሚሰጡ ሬስቶራንቶች የሚዘጋጁ ምግቦች እጅግ የተቀነባበሩና ምግቡን ለማዘጋጀት ተጨማሪ ጊዜን እንዳይወስዱ በፍጥነት የሚዘጋጁ ናቸውⵆ የዚህ አይነት ምርቶች በቅባት የተሞሉ በመሆናቸው ጤናማ አይደሉም።
እነዚህ ምርቶች ጣዕምን የሚያሻሽሉ፣ የበለፀጉ እና ለመመገብ ቀላል የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ይዘዋል የሚሉት ዶክትር ዘላለም ለዚህም ነው ሱስ የሚያስይዙት፤ ሲበሉም መጠናቸውን ለመወሰን አስቸጋሪ የሚሆነው፤ ነገር ግን ጨዋማ መክሰስ መብላት ከፈለጉ የተጠበሱ ፍራፍሬዎችን መምረጥ ተገቢ ስለመሆኑም ይናገራሉ።
በምድጃ ውስጥ ቀድመው የበሰሉ ምርቶች መኖራቸው ገንቢ እና ጤናማ ምግብ ለማዘጋጀት ጊዜ ለሌላቸው መፍትሄ ነውⵆ የቀዘቀዙ ምግቦች በአብዛኛው ከፍተኛ መጠን ያለው የሳቹሬትድ ስብ ይይዛሉ እና በዘይት መቀቀል አለባቸው ይህም ተጨማሪ ስብን ይጨምራል በዚህ ምክንያት አስቀድመው የተዘጋጁ ምግቦች ጤናማ ምግብ አይደሉምና የቤተሰብ አመጋገብ አካል መሆን የለባቸውም ብለዋል፡፡
ጤናማ አመጋገብ እንዲኖረን የሚያደርጉ የተፈጥሮ ምርቶች ናቸው። ፍራፍሬዎች፣ አትክልት፣ ሁሉም ዓይነት ሥጋ፣ ዓሳ፣ የወተት ተዋጽኦዎች፣ እንቁላል፣ ጥራጥሬ፣ ናቸው። በአጭሩ፣ አንዳንድ የአመጋገብ አስተዋፅዖ ያላቸው ከሁሉም ቡድኖች የተውጣጡ ምግቦች ማለት ናቸው።
ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ የሚጀምረው ምግቡን ካለመመጠን ነው የሚሉት ዶክተር ዘላለም የምንመገበው ምግብ ወይ በዝቷል አልያም በቂ አይደለም፤ ለምሳሌ ያልተፈተጉ ብለን የምንላቸውና ኮልስትሮልን ጨምሮ በርካታ ህመሞችን የሚከላከሉልን ምግቦች በዕለት ተዕለት አመጋገባችን ውስጥ ከሌሉ ወይም በቂ ካልሆኑ፤ ፍራፍሬና አትክልቶችን ከገበታችን የማናካትት ከሆነ፤ ፈሳሽ በበቂ ሁኔታ ካልጠጣን፤ በቂ እንቅስቃሴ እናደርጋለን ወይ የሚሉት ዋና ዋና ሀሳቦች መሆናቸውን ይናገራሉ።
በሌላ በኩልም በእለት ተዕለት አመጋገባችን ላይ ጨው߹ቅባት፤ ስኳር ያለመጠን የበዛባቸውን የምግብ አይነቶች የምናዘወትር ከሆነም በራሱ ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ አካሄድ ከመሆኑም በላይ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የመጋለጥ እድልንም በእጥፍ የሚጨምሩ መሆናቸውን ዶክተር ዘላለም ይናገራሉ።
ዶክተር ዘላለም እንደሚናገሩት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ተላላፊ ላልሆኑ ህመሞች በተለይም ለልብ ህመም፤ ለስኳር፤ ለሳምባ ምችና ለካንሰር ህመሞች ዋና መነሻ ተብለው የሚጠቀሱት ጤናማና በቂ ያልሆኑ የአመጋገብ ልምዶች መሆናቸውን ያብራራሉ።
በአገራችን እነዚህ ህመሞች ቀደም ባለው ጊዜ የሀብታም ህመም ይባሉ ነበር፤ አሁን ላይ ግን በጣም በርካቶች በዚህ ህመም እየተጎዱ ነው፤ ነገር ግን እነዚህ ህመሞች እንዳይከሰቱ የሚያስችሉ መረጃዎችን በማግኘት በኩልም ሰፊ ክፍተቶች አሉ።
አሁን ላይ ጤናማ ባልሆነ አመጋገባችን ከሚመጡ ህመሞች መካከል ስኳር ከጠቅላላው ማህበረሰባችን 4 በመቶ ያህሉን ያጠቃል፤ ይህ አሃዝ ደግሞ በዋና ዋና ከተሞች ላይ ቁጥሩ ከፍ ይላል፤ ልብና የደም መዘዋወሪያ ህመሞች በቀጣይነት ትልቁን የጉዳት መጠን የሚያስከትሉ ናቸው። ጉዳታቸው ደግሞ ከፍ የሚለው ከፍ ያለ የህመም ደረጃ ላይ እስከሚደርሱ ድረስ ምንም አይነት የህመም ምልክት አለማሳየታቸው ነው። በመሆኑም እንደ አገር ከሚሞተው የሰው ቁጥር መካከል 52 በመቶው በእነዚህ ህመሞች የሚሞት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 8 በመቶው በቂ ምግብ ወይንም ደግሞ ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን ባለመከተል የሚደርስ ነው ይላሉ ዶክተር ዘላለም።
ጤናማ ባልሆነ አመጋገባችን ምክንያት የሚከሰቱትን ህመሞች ለማከም ደግሞ አገርም ብዙ ሃብትን ሙአለንዋይ ታፈሳለች የሚሉት ዶክተር ዘላለም ለህከምና ከሚወጣው በላይ አምራቹ ኃይል ታሞ እቤት በመቅረቱ በስራ ገበታው ላይ ባለመገኘቱ ቢገኝም ውጤታማ ስራን መስራት ባለመቻሉ ብሎም በመሞቱ የምታጣው ብዙ ነው በማለት ያስረዳሉ።
ዶክተር ዘላለም እንደሚሉት መጀመሪያ ልናደርግ የሚገባን ነገር ችግሩ ምኑ ጋር ነው? የሚለውን ማየት ነው፡፡ ይህንን ካወቅን በራሳችን የምንሄድባቸው ርምጃዎች ውጤታማ ያደርጉናል። በሌላ በኩል መረጃዎችን መከታተል የጤና ባለሙያ ምክርን መተግበር ያስፈልጋል። ጤናማ ያልሆነን አመጋገባችንን ለማስተካከል መከተል ካለብን ነገር አንዱ አትክልትና ፍራፍሬን ከምግባችን ውስጥ አለመለየት ነው፡፡ በዚህም በቀን ቢያንስ 400 መቶ ግራም መመገብ በህክምናው ተመካሪ ነው የሚሉት ዶክተር ዘላለም ይህ ማለት ምናልባት ሁለት ሙዝ ወይም አንድ ብርቱካን አንድ ሙዝ ሊሆን ይችላል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጎመን፣ ካሮት፣ ቆስጣ፣ ሰላጣ፣ ቀይ ስር ያሉትን አትከልቶች በምግባችን ውስጥ በማካተት ጤናችንን መጠበቅ ይገባል ባይ ናቸው። ሌላው መክሰስ ተብሎ ወይንም ደግሞ በመንገድ ላይ ስንጓዝ ደከም ሲለን ከመንገዱ ዳርቻ ገዝተን የምንመገባቸው ምግቦች በጣም ጤናማ ያልሆኑ ከመሆናቸው የተነሳ በመንገድ ላይ የሚሸጡ ምግቦችን ማስወገድን ይመክራሉ።
ዶክተር ዘላለም እንደሚሉት የፋብሪካ ውጤቶች የሆኑ ምግቦችን ተወት በማድረግ በቤታችን የሚዘጋጁ ከተቻለም ደግሞ አሰር ያላቸውን ምግብ ማዘውተር በጣም አስፈላጊ መሆኑን በመናገር በአገራችን ተፈጥሯዊና ጥሩ የምግብነት ይዘት ያላቸውን እንደ አቮካዶ፣ኦቾሎኒ፣ ተልባ፣ድብርቅ፣ ጥቁር አዝሙድ በመጠቀም ምግባችንን ማስተካከል ይገባናል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የትኛውንም አይነት ምግብ ተመግበን ቁጭ ማለት ገዳይ ነው የሚሉት ዶክተር ዘላለም በቀንም ቢያንስ ለግማሽ ሰዓት እንቅስቃሴን ማድረግ ይገባል።
ከአመጋገባችን አንዱና ዋናው ልናስወግደው የሚገባው ነገር ጨው ነው፤ ይህም ሲባል አንድ አዋቂ ሰው በቀን በጣም ቢበዛ ከሚመገባቸው ምግቦች ከአንድ የሻይ ማንኪያ በላይ ጨው መጠቀም አያስፈልገውምⵆ ጨውን መቀነስ ደግሞ ጤናን በማሻሻል በኩል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው ይላሉ ዶክተር ዘላለም።
ስኳርም በተመሳሳይ ለአንድ አዋቂ ሰው በቀን ከአምስት የሻይ ማንኪያ መብለጥ የለበትም፣ ስኳር የበዛባቸው ምግቦችን መቀነስም ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንዳለውም ያስረዳሉ።
በመሆኑም ጤናማ ያልሆነ አመጋገብን ከምግብ ስርዓታችን አስወግደን ጤናችንን መጠበቅ እንደሚገባን የሚናገሩት ዶክተር ዘላለም ይህንን ማድረግ ማሰብ እንጂ ብዙ ወጪንም የሚጠይቅ አለመሆኑን በመግለጽ ሁሉም ማህበረሰብ በተቻለ መጠን ዘመናዊነት ያመጣውን ያልተስተካከለ አመጋገብ ሊያስወግድ እንደሚገባ መክረዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/ 2015 ዓ.ም