ፍጥረታት ተፈጥሮ ከሰጠቻቸው ባህርይ፣ ቅርፅና ቀለም ውጭ ሊለወጡ ባይችሉም በእርጅና ምክንያት ግን ባህርያቸው፣ መልካቸው አልያም ቅርፃቸው ሊቀየር እንደሚችል ይታወቃል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በሁኔታዎች አጋጣሚና በተለይም በሰው ልጆች ጥረት ፍጥረታት ባህሪያቸውን ባይለውጡ እንኳን ቅርፃቸውን ሊለውጡ ይችላሉ፡፡
ፖም ፖም የተሰኘው ውሻ ምስጋና ለተንከባካቢው ይግባውና ከውሻነት ወደ እንቁላልነት በመቀየሩ በማህበራዊ ሚዲያ ‹‹የሰሞኑ መነጋገሪያ ዜና ሆኗል›› ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ከወደ ሲንጋፖር አስነብቧል፡፡
እንደ ፅሁፉ ከሆነ፤ በትርፍ ሰዓቷ ውሻ መንከባከብ ልማዷ የሆነው ሲንጋፖራዊት የፖሜራንያን የውሾች ዝርያ የሆነውንና ፖም ፖም የተሰኘውን ውሻ በቤቷ ታሳድጋለች፡፡ ለውሻው የምታደርገው የተለየ እንክብካቤም ውሻውን ከውሻነት ወደ እንቁላልነት ቀይሮታል፡፡ የእንቁላሉን ውሻ ምስልና ቪዲዮ በማህበራዊ ትስስር ገፅ ትለቃለች፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ውሻው ዝነኛ ሆና ያርፈዋል፡፡ በርካቶችም ‹‹ውሻ ወደ እንቁላልነት ተቀየረ››
በሚል ተገርመው በማህበራዊ ትስስር ገፆች አማካኝነት መረጃውን ይቀባበላሉ፡፡ ‹‹እንቁላሉ ውሻ›› በማለት እስከ መጥራትም ይደርሳሉ፡፡
እንዲህ የበርካቶች መነጋገሪያ የሆነው ውሻ በርግጥም የእውነት ወደ እንቁላልነት ተቀይሮ ሳይሆን የእንቁላል ቅርፅ በመያዙ ነው ሲል ፅሁፉ የገለፀ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ የውሻው ተንከባካቢ ያላሰለሰ ጥረት ትልቁን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሷል፡፡ ተንከባካቢዋ፣ ውሻው የእንቁላል ቅርፅ እንዲይዝ ገላውን በየቀኑ ካጠበች በኋላ የእንቁላል ቅርፅ እንዲይዝ ሰውነቱን አሽተዋለች::
ውሻውም ጉዳዩ ሳይገባው አልቀረም መሰል ለመታጠቡም ለመታሸቱም ፍቃደኝነቱን ገልጿል፡፡ ልክ እንደሌሎቹ ውሾች ሁሉ ጆሮዎቹን ከማቆም ይልቅ ለጥ እንዲሉ ማድረግን ለምዷል፡፡ የፀጉሮቹ እኩል መከርከምና ነጭ ቀለም መሆን ተዳምረው ውሻውን እንቁላል እንዲመስል አድርገውታል፡፡
ውሻ ተንከባካቢዋ፣ ይህን ሁሉ ማድረጓ ብዙ ትኩረት አገኛለሁ የሚል ሃሳብ ባይኖራትም ውሻው የእንቁላል ቅርፅ እንዲይዝ ከተደረገ በኋላ ግን በማህበራዊ ትስስር ገፅ አማካኝነት ‹‹የሰሞኑ አነጋጋሪ ክስተት ሆናለች›› ሲል ፅሁፉ አመላክቷል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2011
በአስናቀ ፀጋዬ