ኢትዮጵያ በዘመኗ በርካታ ህልውናዋን የሚጋፉ እብሪት የወጠራቸው ሀገራት ወረራ ፈጽመው ጥቅምና ፍላጎታቸውን ለመጫን ተፈታትነዋታል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ጀግና መውለድ ታውቅበታለችና ጀግኖች ልጆቿ ጠላቶቿን በጦርና በጋሻ ተፋልመው እንደአመጣጣቸው በመመለስ ሉዓላዊት ሀገር አስረክበውናል።
አሸባሪው ሕወሓት ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ለ27 ዓመታት እንደፈለገ በሕዝብ ሰብዓዊ መብቶች ላይ ሲረማመድ ቆይቶ ሀገሪቱን ለውድቀት የዳረገ ዘረፋ በማካሔዱና በዚህ ጦስ የነበረውን የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን በማጣቱ ገና በለውጡ ጅማሬ የሕወሓት አመራሮች ሀገራዊ ለውጡን ማጥላላትን ሥራዬ ብለው ተያያዙት።
የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ መቀመጫውን በትግራይ ክልል አድርጎ ከትግራይ ሕዝብ ጋር እድሜ ልኩን የኖረ ሠራዊት ነው። ዕዙ በሰውና በመሣሪያ የመከላከያን ከፍተኛ ድርሻ የያዘ የተቋሙ ግዙፍ ኃይል ነበር። ወቅቱ መኸር በመሆኑ ሠራዊቱ የአርሶ አደሩን ሰብል መሰብሰብ እና በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የአንበጣ መንጋ በማባረር ውሎ አዳሩን ከትግራይ ገበሬ ጋር አድርጓል።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሕወሓት ከሰው ልጅ በማይጠበቅ ጭካኔና በዓለም መድረክ ባልታየ ክህደት ለዘመናት በቀበሮ ጉድጓድ እየኖረ ሲጠብቀው የኖረውን የሰሜን ዕዝ ሠራዊት በተኛበት ጥቃት ከፈተበት። ሀገር እንጠብቅ ሕዝብ እናገልግል ያሉ፤ ቀን ገበሬ ሌሊት ጥበቃ ሆነው ለበርካታ ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ፣ ቀን ሀሩሩ ሌሊት ብርዱ ሳይበግራቸው፣ ክረምት ከበጋ የሚለፉ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች በሕወሓት የክህደት በትር ሀገር አማን ብለው በተኙበት ተወጉ።
በዚያ ጥቃት ብዙዎቹ የሰሜን ዕዝ አባላት በግፈኛው የሕወሓት ጥቃት ተገደሉ። በቅጡ እንኳ ሳይቀበሩ ጅብና አሞራ በላቸው። በሬሳቸው ላይ ከበሮ እየደለቁ ጨፈሩበት፡፡ ብዙዎቹ እየቆሰሉ አካላቸውን አጡ። እንዲሁም ታፍነው በርሃብና ውሃ ጥም እየተቀጡ ተንገላቱ። እነኝህ ታፋኝ የሰሜን ዕዝ አባላት በግፈኞች ዱላ ተደበደቡ። ተገደሉ። ሴት የሠራዊቱ አባላት በጉልበተኞች ተደፈሩ።
ሕወሓት ምንም እንኳ የሰሜን ዕዝን ሲያጠቃ በብሔር እየመረጠ በርካታ ጓዶችን ይግደል እንጂ በወቅቱ “የራሴ” ለሚላቸው የትግራይ ተወላጆች እንኳ ከመጨከን ወደ ኋላ አላለም። የሰሜን ዕዝን በሚያጠቃበት ወቅት ለሴራው ያልተባበሩትን በርካታ የትግራይ ተወላጅ የሰሜን ዕዝ ሠራዊት አመራሮችንና አባላትን ገድሎ የጭካኔውን ጥግ አሳይቶናል።
የሰሜን ዕዝ አባላት ትምህርት ቤት ሠርተው ሕፃናት ይማሩ ባሉ፣ ጤና ጣቢያ ሠርተው የእናቶችንና የሕፃናትን ሞት እንቀንስ ባሉ፤ የውሃ ጉድጓድ ቆፍረው እናቶችን ከሸክም በገላገሉ የተከፈላቸው ወሮታ የግፈኛው ሕወሓት ጥይት ሆነ።
ሕወሓት ከሃያ ዓመታት በላይ ትግራይ ክልል እየኖረ ከአነስተኛ ደመወዙ ቀንሶ ገንዘብ አዋጥቶ፣ እጁና ትክሻው እስኪላጥ ድንጋይ ፈልጦና ተሸክሞ ትምህርት ቤት፣ ጤና ኬላ፣ የወጣቶች መዝናኛ የገነባ፤ የክረምቱን ጭቃ ሳይጠየፍ የአርሶ አደሩን ሰብል ሲኮተኩት እና ሲያርም ከርሞ፤ ጠዋት ብርዱን ቀን ፀሐዩን ሳይፈራ የደረሰውን ሰብል ሲያጭድ እና ሲወቃ፤ ምሽግ ውስጥ እየኖረ የጠበቀውን፣ የሞተለትንና የቆሰለለትን የሰሜን ዕዝ ሠራዊትን ክዶ የወጋ የጭካኔና የክህደት ጥግ መታወቂያው የሆነ የማፍያዎች ጥርቅም ነው።
አሸባሪው ሕወሓት የጥቅምት 24ቱ የሰሜን ዕዝ የክህደት ጥቃት አልበቃው ብሎ ለሌላ ጦርነት ከመሰለፍ ወደ ኋላ አላለም። በ2013 ዓ.ም ሰኔ ወር መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ሠራዊቱን ከትግራይ ባስወጣበት ወቅት በየበርሃው ተበታትኖ የነበረውን ታጣቂውን አሰባስቦ የአፋርና አማራ ክልሎችን በስፋት ወረረ። በዚህ ወረራ ወቅትም አመራሮቹ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ መሔድ ካለባቸው እንደሚሔዱ እየማሉ ተናገሩ።
በአማራና አፋር ክልሎች ምንም የማያውቁ ንፁሃን ላይ ከባድ መሣሪያ በመተኮስ እና በጅምላ በመረሸን የጥፋት መሐላቸውን በተግባር አሳዩን። ጭና፣ ጋሊኮማ፣ እና ሌሎች ቦታዎች ላይ ያለርህራሔ ንፁሃን ዜጎችን በጅምላ ገደሉ። ከትልልቅ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እስከ የገበሬው ቤት ድረስ ዘረፉ፤ አወደሙ፤ አቃጠሉ። የአርሶ አደሩን ሰብል አጭደውና ወቅተው ከመውሰድ እስከ በእሳት ማቃጠል የደረሰ ጉዳት አደረሱ። ህሊናቸውን የሸጡ ሕወሓታውያን ከመነኩሴ እስከ ህፃናት ያሉ ሴቶችን አስገድደው ደፈሩ።
የጀመሩት ወረራ በጀግናው ሠራዊታችን ጠንካራ ምት ተፈረካክሶ ከአፋርና አማራ ክልል ተጠራርገው ሲወጡ መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት አድርጎ ባለበት ሰአት ነሐሴ 18 ቀን ሦስተኛ ወረራ ከፈቱ።
ደብተር ይዘው ትምህርት ቤት መሔድ ከነበረባቸው ህፃናት እስከ መነኩሴ ድረስ በግድ ወደ ግንባር በማምጣት የትግራይን ሕዝብ ለጥይት ማብረጃነት ተጠቀሙበት፡፡ ሕወሓት ከሀገር ውስጥ ባንዳዎች እስከ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመተባበር ወረራ ቢከፍትም የብርቱውን ሠራዊታችንን ክንድ መቋቋም አልቻለም። ትንሽ ድል ሲያገኝ የሚፎክረው፤ ሲሸነፍ ደግሞ የሚያለቅሰው ሕወሓት ከኢትዮጵያ ሕዝብ በዘረፈው ከፍተኛ ሀብት የውጭ ሀገር ሰዎችን (ሎቢስት) ቀጥሮ ፕሮፓጋንዳ ቢያስነዛም ውጤቱ ኪሳራ ሆኖበታል።
ይህን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልዕኮውን ለማሳካትም አንዴ በጦርነት ሌላ ጊዜ ደግሞ በድርድር ጊዜ ሸምቶ ለማገገም ያለመታከት እየሠራ ይገኛል። ግን እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን። በየትኛውም ግንባር እንፈተናለን እንጂ ፈጽሞ አንሸነፍም።
ምንም እንኳ አሸባሪው ሕወሓት ቀደም ብሎ በሰሜን ዕዝ ላይ ቀጥሎም በመላው ኢትዮጵያ ላይ የፈጸመው ጥቃትና ወረራ መዘዙ እስከዛሬ ድረስ ዘልቆ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያታያን ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጫና ያስከተለ ቢሆንም ሁሉንም በአሸናፊነትና ድል እየተወጣን እንገኛለን።
ከመላው ሕዝባችን ጋር ሆነን ባደረግነው ታላቅ ተጋድሎ ሕወሓት ራሱ በለኮሰው ጦርነት ሊጠፋ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰናል፡፡ የሰማዕታቱን ፍሬ የምናይበትና ድሉን የምንዘክርበት ወቅት ላይ ነን።
እኛ አደራ የምንዘነጋ ሳንሆን የወንድሞቻችንን፣ የኢትዮጵያን ክብርና የግዛት አንድነት የማስጠበቅ ተጋድሎ ከዳር ለማድረስ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት በጀግንነት ለመክፈል የተዘጋጀን ነን።
አሸባሪው ሕወሓት የፈፀመብን በደልና ሰቆቃ ተቆጥሮ የማያልቅ በታሪክና ትውልድ ፊት ይቅርታ የማይቸረው ነው፡፡ በወንድሞቻችን ላይ የደረሰውን ግፍና መከራም መቼም አንረሳውም፡፡ ነገር ግን እኛ እንደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኃይል ሕዝብና ሀገርን አጽንተን የምናስቀጥል ሕዝባዊ ሠራዊት ነን፡፡
ስለሆነም በደልን ስንቆጥር የምንኖር ሳንሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ በተለይም የትግራይን ሕዝብ ከሕወሓት የዘመናት ባርነትና ጭቆና ነፃ ለማውጣት የከፈልነውንና እየከፈልን ያለነውን መስዋዕትነት አጠናክረን በመቀጠል የመጨረሻው የድል ዋዜማ ላይ ሆነን ሰማዕታትን እየዘከርን ኢትዮጵያችንን አስከብረን በአሸባሪው ሕወሓት መቃብር ላይ ድላችንን እናበስራለን።
“ጥቅምት 24ን መቼም አንረሳውም!!”
ክብርና ሞገስ ለተሰዉ ሰማዕታት!!
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም