የ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ውድድር የሚጀመርበት ቀን በአንድ ሳምንት ሲራዘም ውድድሮቹ የሚካሄዱባቸው ከተሞችም ተለይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር ከሚደረጉ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው አንደኛ ሊግ የ2015 ውድድር የሚጀመርበት ቀን ቀደም ብሎ የታወቀ ቢሆንም ክለቦች ከክፍያ እና ከዝግጅት ጊዜ መጥበብ ጋር በተያያዘ ባቀረቡት የይራዘምልን ጥያቄ ስለመራዘሙ ሶከር ኢትዮጵያ ዘግቧል። ኅዳር 3/2015 ዓ.ም እንደሚጀመር ተገልፆ የነበረው ውድድሩ ኅዳር 10/2015 ዓ.ም እንዲጀመር ተወስኗል።
ወደ ሃምሳ አምስት የሚጠጉ ክለቦችን በአምስት ምድቦች ከፍሎ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ውድድር የመጀመሪያው ዙር ፉክክሮች የሚከወኑበት አምስት ከተሞችም ተለይተው ታውቀዋል፡፡ በዚህም ሀዋሳ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ደብረማርቆስ፣ አሰላ እና ቢሾፍቱ ከተሞች የመጀመሪያውን ዙር ውድድር ለማስተናገድ መመረጣቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡ የምድብ ድልድሉ እና የዕጣ ማውጣት መርሐ-ግብሩ ደግሞ ጥቅምት 29 እንደሚከወን ቀደም ብሎ መገለጹ ይታወሳል፡፡በተመሳሳይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር የሚደረገው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ከዘንድሮው ዓመት ጀምሮ በዘመነ መልኩ የተለያዩ መስፈርቶች ወጥተውለት እንደሚደረግ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዚህ ዓመት ለማድረግ ካሰባቸው ስራዎች መካከል የከፍተኛ ሊግ ውድድርን በዘመነ መልኩ ማካሄድ የሚለው ይጠቀሳል፡ ፡ ውድድሩ ዘንድሮ ከሦስቱ ምድቦች በድምሩ አስራ አምስት ክለቦች ወደ አንደኛው ሊግ የሚወርዱ ሲሆን ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ደግሞ በሁለት ምድብ ተከፍሎ የውድድሩን ጥራት ከፍ በማድረግ ለማከናወን መታሰቡንም ከቀናት በፊት መሰማቱ ይታወሳል፡ ፡ ጨዋታዎች ቀጥታ የኦንላይን ቴሌቪዥን ስርጭትን እንደሚያገኙ የተገለጸ ሲሆን ከፊፋ ፕላስ ጋር በመቀናጀት ሽፋን እንዲያገኝ መታቀዱ ይታወቃል፡፡
ውድድሩ በፊፋ ፕላስ አማካኝነት በሆላንዱ ኢለቨን ሰቨን በተሰኘ ካምፓኒ አማካኝነት ስርጭቱ የሚተላለፍ ሲሆን ለስርጭቱም ጥራት ያለው ሜዳ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ፌዴሬሽኑ ሦስት ሜዳዎችን እንደለየ የሶከር ኢትዮጵያ መረጃ ያመለክታል። ለዚህም የሆሳዕናው አቢዩ ኤርሳሞ ስታዲየም፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ እና የባህር ዳር ስታዲየም ውድድሩ እንዲካሄድባቸው ሲወሰን አንድ ተጨማሪ ሜዳንም ለማካተት የጥራት ጉዳይ እየታየ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
እንደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዲኤስቲቪ ስርጭት ሁሉ የከፍተኛ ሊግ ክለቦችም ቀደም ብለው ለቀጥታ ስርጭቱ እንዲመች የክለባቸውን ታሪክ በአግባቡ ሰድረው ማቅረብ እንዳለባቸው እንዲሁም ደግሞ ከትጥቅ አጠቃቀም ማለትም የመለያ፣ ቁምጣ እና የካሶቶኒ አጠቃቀማቸው ሳይዘበራረቅ ወጥነት ያለው ተመሳሳይ ይዘትን የተላበሰ ሆኖ ለውድድሩ መቅረብ እንደሚገባቸውም በግልፅ በመመሪያ መልክ ለክለቦች ተቀምጦላቸዋል፡፡ በተለይ ክለቦች ወጥነት ያለውን ትጥቅን መጠቀማቸው ከማርኬቲንግ ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ በገቢ ራሳቸው ለማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ በጥብቅ ትኩረት እንዲሰጡትም ስለ መገለፁ በዘገባው ተጠቁሟል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2015