በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት ለሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የሚሆኑ ቡድኖችን ለመለየት ከሚካሄዱ የማጣሪያ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማህበር (ሴካፋ) የሚያሰናዳው ውድድር ነው። ዘንድሮም ይህ ውድድር ለ14ኛ ጊዜ በሱዳን አስተናጋጅነት ከቀናት በፊት መካሄድ መጀመሩ ይታወሳል። የዚህ ውድድር ተካፋይ ከሆኑ አገራት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንም ነገ የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚያከናውን ይሆናል።
በሱዳን አዘጋጅነት ሰባት አገራት የሚካፈሉበት ይህ ውድድር በአል ሂላል ስታዲየም ከተጀመረ ቀናትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በምድብ አንድ የተደለደሉ አገራት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ማከናወን ችለዋል። በዚህም መሰረት የውድድሩ አዘጋጅ የሆነችው ሱዳን ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለ ግብ መለያየት ችለዋል። በብሩንዲ እና ጅቡቲ መካከል የተካሄደው ጨዋታ ደግሞ በብሩንዲ የ5 ለምንም ሰፊ የግብ ልዩነት ሊጠናቀቅ ችሏል። በዚህ ጨዋታ አርተር ኒቢኮራ የተባለው ተጫዋች ሶስት ግቦች በማስቆጠር ቀዳሚው ተጫዋች ለመሆንም ችሏል።
በምድብ ሁለት ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ሲደለደሉ፤ ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ጋር የመጀመሪያውን ጨዋታ ነገ የምታካሂድ ይሆናል። በቀጣይ ደግሞ ካለፈው ዓመት የሴካፋ አሸናፊው ዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር የሚገናኝ ይሆናል። በአሰልጣኝ እድሉ ደረጀ የሚራው ወጣት ቡድኑ ከተያዘው ወር የመጀመሪያ ቀናት አንስቶ ወደ ዝግጅት የገባ ሲሆን፤ ተጫዋቾቹ ከውድድር የተሰባሰቡ እንደመሆኑ በታክቲክ እና የፍጥነት ስራዎች ላይ አተኩሮ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይ የአሸናፊነት ስነልቦናን እንዲላበሱም በአሰልጣኞች ቡድን በትኩረት የተሰራበት መሆኑንም አሰልጣኙ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት አሳውቀዋል። በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ልምምድ ሲያደርግ የቆየው ቡድኑ ያለበትን አቋም ለመለካትም ከመቻል ከ20 ዓመት በታች ቡድን ጋር ተጫውቶ 3ለ0 በሆነ ውጤት ነበር ያሸነፈው።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እና ዋና ጸሀፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን፤ ቡድኑ ወደ ሱዳን ከማቅናቱ አስቀድሞ ልምምዱን በሚያከናውንበት ስፍራ ተገኝተው ልምምዱን ተከታትለዋል። አቶ ኢሳያስ ባደረጉት ንግግርም፤ ይህ ውድድር ለአፍሪካ ዋንጫ አቋራጭ የሆነ ውድድር ነው፤ በመሆኑም ይህንን ዕድል መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። ቡድኑ ያለበት ምድብ ከዞኑ ጠንካራ አገራት ጋር በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ በመጫወትና ጥቂት ጨዋታዎችን በአሸናፊነት መወጣት በግብጽ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ መልካም አጋጣሚ በመሆኑና አጋጣሚውን በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። በመጨረሻም ለቡድኑ አባላት መልካም እድል እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል።
ቡድኑ ባለፈው እሁድ ጥቅምት 20/2015 ዓ.ም ወደ ሱዳን የተጓዘ ሲሆን፤ አመሻሽ ላይም ልምምድ መጀመሩን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሳውቋል። የወጣት ብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ እድሉ የዛሬውን ጨዋታ አስመልክቶም፤ የመጀመሪያ ጨዋታ ወሳኝ መሆኑን ይገልጻሉ። ቡድኑ ከታንዛኒያ ጋር የሚኖረው ጨዋታ የማለፍና ያለማለፍ እድሉን የሚያሰፋ እንደመሆኑ ቡድኑ ትኩረት አድርጎ ይጫወታል። ከሌሎች የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ይህንን መረዳት በመቻሉ ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ አሸንፎ ለመውጣት ማቀዱንም አሰልጣኙ አመላክተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2015