ከሰላሳ ዓመት በፊት የታተሙ ጋዜጦች የዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ትኩረት ናቸው። ከመራረጥናቸው ዘገባዎች መካከል አሁን ካለንበት ወቅት ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው። በደርግና በወያኔ መካከል የተካሔደው ድርድር፣ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ስለሚረዱበት ሁኔታ እንዲሁም የዋጋ ንረትን የተመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች በዘገባዎቹ የተዳሰሱ ናቸው።
የሰላም ውይይቱ ተሳታፊ ቡድን ተሰየመ
. ተሳታፊዎች ገንቢ ሀሳብ ይዘው እንዲቀርቡ መንግሥታት ጥሪ አቀረቡ
(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ መንግሥትና በተቃዋሚ ቡድኖች መካከል በመጪው ሰኞ ለንደን ላይ ተሳታፊ የሚሆነውን ቡድን የመንግሥት ምክር ቤት ሰየመ።
የሰላም ልዑካን ቡድኑን የሰየመው በጓድ ሌተናል ጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ የፖለቲካ ቢሮ አባልና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሰብሳቢነት የመንግሥት ምክር ቤት ትናንት ከቀትር በፊት ባደረገው ስብሰባ ነው።
ጓድ ተስፋዬ ዲንቃ የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ የፖለቲካ ቢሮ ተለዋጭ አባልና ጠቅላይ ሚኒስትር የቡድኑ መሪ እንዲሆኑ በምክር ቤቱ ተሰይመዋል። በሀገራችን ያለው የወቅቱ እጅግ አሳሳቢ ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የብሔራዊ ሸንጐ 3ኛ አስቸኳይ ጉባኤ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረትና እንዲሁም የመንግሥት ምክር ቤት ሰሞኑን የመፍትሔ ሀሳቦችን ጨምሮ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከሁሉም በፊት ሰላም ይገኝ ዘንድ ለአፋጣኝ መፍትሔ በሚያደርገው ጥረት ለንደን ላይ የሚደረገው የሰላም ውይይት የተሳካ እንዲሆን በመድረኩ ላይ ተሳትፎ ለሚያደርገው ቡድን አስፈላጊውን መመሪያ ሰጥቷል።
መንግሥትን በመወከል በውይይቱ የሚሳተፈው ቡድን በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ውስጥ የሚደረገው የእርስ በእርስ ጦርነት ቆሞ የሽግግር መንግሥት ይመሠረት ዘንድ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርና ተገቢውን አስተዋፅኦ ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን የመንግሥት ምክር ቤት ገልጿል።
(ግንቦት 17 ቀን 1983 ከወጣው
አዲስ ዘመን )
ስደተኞችና ከስደት የተመለሱት ስለሚረዱበት ሁኔታ ውይይት ተካሄደ
(ኢዜአ)፤ ከሶማሊያ ተፈናቅለው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞችና ከሶማሊያ ወደ አገራቸው የተመለሱትን ኢትዮጵያውያንን መርዳት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የተነጋገረ ስብሰባ ትናንት በማዕከላዊ ፕላን ብሔራዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ተካሒዷል ።
ለስደተኞቹ ዕርዳታ የሚደርስበትን ሁኔታ የሚከታተለውና በቅርቡ የተቋቋመው የሶማሊያ ስደተኞች ድጋፍ ሰጪ ከፍተኛ ብሔራዊ ኮሚቴ ባዘጋጀው በዚሁ ስብሰባ ላይ የዓለም አቀፍ እርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች ተወካዮች ተካፍለዋል።
ጓድ ሽመልስ አዱኛ የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፤ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኮሚቴው አስተባባሪ ለተሳታፊዎች ባደረጉት ገለጻ፤ የሶማሊያ ስደተኞችንና ወደ ሀገራቸው የተመለሱትን ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት እስካሁን መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ጋር በመተባበር ያልተቆጠበ ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱን አውስተው፤ ለተልዕኮውም መሳካት የዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ሲያደርግ የነበረውን ትብብር ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም በቂ ምግብ ውሃ መጠለያና መድኃኒት ለማቅረብ ከእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ያልተቆጠበ ትብብርና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አመልክተው በተለይም ለዚሁ አቅርቦት የወሳኝነት ሚና ያለው የትራንስፖርት ችግር መቃለልና አፋጣኝ መፍትሔ ማግኘት እንደሚገባው አስረድተዋል።
ቀደም ሲል በተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር የአፍሪካ አህጉር ተወካዮች፤ ከአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች ጋር በመሆን በሥፍራው ባደረጓቸው ጉብኝቶች የጉዳዩን አሳሳቢነት መጠቆማቸውን ጓድ ሚኒስትሩ ገልጸው፤ ይህን ችግር አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኝ ዕርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች ያላሰለሰ ድጋፍ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል። ከሶማሊያ ፈልሰው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የሶማሊያ ስደተኞች 640 ሺህ ሲሆኑ ወደ አገራቸው የተመለሱት ኢትዮጵያውያን ደግሞ 246 ሺህ ናቸው።
(መጋቢት 17 ቀን 1983
አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
በዋጋ ንረትና ሥርጭት መዛባት ጉዳይ ላይ ውይይት ተካሄደ
(ኢዜአ)፤ ሀገራችን አሁን የምትገኝበት እጅግ አሳሳቢ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በተከሰተው የዋጋ ንረትና የሥርጭት መዛባት ጉዳይ ላይ በንግዱ ዘርፍ ከተሰማራው ኅብረተሰብ ጋር ተወያይቶ የጋራ ግንዛቤ ለመውሰድና መፍትሔ ለመፈለግ የሚያስችል ስብሰባ ትናንት ተካሂዷል።
ጓድ ግዛው ንጉሤ የአዲስ አበባ አካባቢ ዋና አስተዳደር በዚሁ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ፤ ወያኔ አገርን ለመከፋፈል በየአካባቢው በከፈተው ጦርነት ምክንያት የተናጋው የኅብረተሰቡ ሰላምና አንድነት ለማስከበር ከፍተኛ እንቅስቃሴ በሚያካሂድበት በአሁኑ ወቅት ነጋዴው በምርቶችና ሸቀጦች ላይ ዋጋ ከመጨመር እንዲቆጠብ አሳስበዋል።
መንግሥት የንግዱ ኢኮኖሚ መስክ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ እንዲደራጅ፤ እንዲመራና ለአጠቃላይ ኅብረተሰብም ሆነ በዘርፉ ለተሰማራው ዜጋ የተሻለ ጥቅም እንዲሰጥ ለማድረግ የሚቻለው ሁሉ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጓድ ግዛው ጠቅሰው፤ ከየወቅቱ ፍላጐትና በተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተስማሚ የሚሆኑ ፖሊሲዎችን፤ ሕጎችን፤ መመሪያዎችንና ደንቦችን አውጥቶ ሥራ ላይ በማዋል ንግዱ ከግብታዊነት ተላቆ የተሻለ ሥርዓት እንዲይዝ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስረድተዋል።
(መጋቢት 24 ቀን 1983
አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
ደን የጨፈጨፉ ተቀጡ
ነገሌ፤ (ኢዜአ) በቦረና አስተዳደር አካባቢ ደን ጨፍጭፈዋል ተብለው የተከሰሱ ግለሰቦች እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት ጽኑ እሥራት እንዲቀጡ የሊበን አውራጃ ፍርድ ቤት ሰሞኑን ፈርዶባቸዋል።
ዶይ ጐዳና፣ ዶቶ ጠዲቻና ካስዪ በኩቲ የተባሉት ግለሰቦች በማንኩሳ ቀበሌ የሚገኘውን ደን በሕገወጥ መንገድ ጨፍጭፈው ለሽያጭ ሲያዘጋጁ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።
ተከሳሾቹ ጥፋታቸው በበቂ ማስረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ እንዳንዳቸው በአንድ ዓመት እሥራት እንዲቀጡና ለሽያጭ የተዘጋጀው የተጠረበ የማዕዘን እንጨትም ለመንግሥት በውርስ ገቢ እንዲሆን በተጨማሪ ወስኗል።
(ግንቦት 10 ቀን 1983 ከወጣው
አዲስ ዘመን ጋዜጣ )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2015