በወጣትነታቸው በስኬት የታጀበ ታሪክ ካላቸው እንቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል አንዷ ናት። እሷ የምትሳተፍባቸው ውድድሮች ላይ የሚነግሰው አሸናፊ ትሆናለች የሚለው ሃሳብ ሳይሆን ሰዓት አሻሽላ የክብረወሰን ባለቤት ትሆናለች የሚለው ግምት ነው። ስክነት መገለጫዋ የሆነው ትሁቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ፤ በ24 ዓመቷ ሦስት የዓለም ክብረወሰኖችን እንዲሁም በርካታ ዓለም አቀፍ ክብሮችን በመቀዳጀት ደማቅ ታሪክ ጽፋለች።
በወጣቶች አገር አቋራጭ ውድድር የዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮችን በስኬት የተቀላቀለችው ለተሰንበት፣ ለቁጥር የሚታክቱ ድሎችን በዓለም አቀፍ መድረኮች አጣጥማለች። በቶኪዮ ኦሊምፒክ የ10 ሺሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት ስትሆን፤ ከወራት በፊት በኦሪጎን በተካሄደው እንዲሁም በዶሃው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ደግሞ በዚሁ ርቀት የወርቅና የብር ሜዳሊያዎችን አጥልቃለች። ከሁለት ዓመት በፊት በቫሌንሲያ በተካሄደ ውድድር በ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰንን ከ4ሰከንዶች በላይ በማሻሻል የግሏ ማድረግ ችላለች። ባለፈው ዓመት ደግሞ በሆላንዳዊቷ አትሌት የተሻሻለውን የ10ሺ ሜትር ክብረወሰን ከሁለት ቀናት በኋላ ሄንግሎ ላይ በመስበር ክብሩን በእጇ አስገብታለች። በዚያው ዓመት በቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን ተሳትፋም ሦስተኛውን የዓለም ክብረወሰን በማስመዝገብም የዓለምን ሕዝብ አጀብ አሰኝታለች።
በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ሩጫዎች የምትታወቀው ለተሰንበት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግማሽ ማራቶን ውድድሮች ላይ ተካፍላ ስኬታማነቷን አረጋግጣለች። አሁን ደግሞ ጊዜው ወደ ረጅሙ የአትሌቲክስ ርቀት ማራቶን የምትሸጋገርበት መሆኑን አስታውቃለች። ማራቶንን አንድ ብላ የምትጀምርበት ውድድርም አምና የክብረወሰን ባለቤት በሆነችበት ቫሌንሲያ ሲሆን፤ በቀጣዩ ኅዳር ወር 2015ዓ.ም ይካሄዳል። ይህንን ተከትሎም የስፖርት ቤተሰቡ ምን አዲስ ነገር ታሳይ ይሆን በሚል ከወዲሁ በጉጉት እየተጠባበቀ ይገኛል።
በርካታ ስመጥር አትሌቶችን ያካተተው የኤንኤን የሩጫ ቡድን አባል የሆነችው ለተሰንበት በቡድኑ ድረገጽ የሩጫ ሕይወቷን በሚመለከት እንደሚከተለው ገልጻለች። ከመነሻዋ የጀመረችው ለተሰንበት ከእናቷ ተኬን በኩረጽዮን እና ግደይ ታደሰ በትግራይ እንዳመስቀል አካባቢ እንደተወለደች ትናገራለች። አራት እህቶችና ሁለት ወንድሞችም አሏት። ተማሪ ሳለች የአውሮፕላን አብራሪ አሊያም ዶክተር የመሆን ህልም ነበራት። በዚህ ምክንያትም በሩጫ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳልነበራት ታስታውሳለች። ነገር ግን አንድ መምህሯ መሮጥ እንዳለባትና በዚህም ከራሷ አልፋ ቤተሰቦቿንም መርዳት እንደምትችል ይነግራት ነበር። ከእሷ ባለፈም ለቤተሰቦቿ ልጃቸው ጥሩ ሯጭ መሆን እንደምትችል ሊያሳምናቸው ጥረት ያደርግ ነበር። በዚህም ተሳክቶለት ከቤተሰብ ፈቃድ አግኝታ ሩጫን ጀመረች።
በትውልድ አካባቢዋ ያሉ ሴቶች በትዳር ለመኖር እንጂ ሩጫን የሚያስቡ አልነበሩም። ማህበረሰቡ እጅግ ወግ አጥባቂና ሃይማኖተኛ በመሆኑ የተነሳም ሴት ልጅ እንኳን ቁምጣ ለብሳ ልትሮጥ ቀርቶ በሱሪ መታየቷ በራሱ ነውር ነው። ይህ ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም የተለሰንበት አባት ግን ሩጫ ሥራዋ በመሆኑ አስፈላጊውን የስፖርት ትጥቅ እንድትለብስ ይነግሯት እንደነበር ጠንካራዋ አትሌት ታስታውሳለች። አይናፋሯ ለተሰንበት ከልምምድ በኋላ በሚኖራት የእረፍት ሰዓቷ እንዲሁም እሁድ እሁድ በሃይማኖት ስፍራዎች መገኘት እንደሚያስደስታት ትናገራለች።
በርካታ ስኬቶችን ስታጣጥም ከጀርባዋ በመሆን መንገድ የሚመራት አሰልጣኟ ኃይሌ ኢያሱ ይባላል። በ2006ዓ.ም በትራንስ የአትሌቲክስ ክለብ ውስጥ ነበር የተዋወቁት። አሰልጣኝ ኃይሌ ከለተሰንበት ጋር እንደተዋወቁ የጋራ እቅድ ማስቀመጣቸውን ይገልጻል። ይኸውም የዓለም ክብረወሰንን በ5ሺ ሜትር እና 10ሺ ሜትር እስከ ማራቶን የሚል ነበር። ይህንንም አብረው ለማሳካት ያስችላቸው ዘንድ በፊርማቸው ነበር ቃል የተገባቡት። ለዚህ ምክንያት የሆነው ደግሞ ከሌሎች አትሌቶች ይልቅ እሷ ተሰጥኦ ያላት አትሌት መሆኗን ስለተመለከተ ነበር። በዚህም መሠረት በተያዘው ዓመት ማራቶንን ለመሞከር መብቃታቸውንም ይገልጻል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2015