ኢትዮጵያ አመቱን ሙሉ የሚፈሱ ትላልቅ ወንዞች እንዲሁም ሐይቆችና ለኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫና ለመስኖ የተገነቡ ግዙፍ ግድቦች ባለቤት ናት። እነዚህ የውሃ መገኛዎች የሀገሪቱ አሳ ሀብት ምንጮችም ናቸው።
ሀይቆቹ የአሣ ሀብት በስፋት ይመረትባቸዋል፤ ከነዚህ የውሃ አካላት ወደ 94ሺ ቶን አሣ ሊመረት እንደሚችል የቅርብ ጊዜ ጥናቶችን ዋቢ ያደረገ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለከታል። ከሐይቆች የሚመረተው አሣ ለገበያ እየቀረበ ለከተሞች ፍጆታ የሚውል ሲሆን፣የወንዞቹ ደግሞ በገጠሩ ህዝብ ለምግብነት ይውላል። የአሳ ሀብቱ በስፋት በሚገኝባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖረው ማህበረሰብ የአሳ ምርቱን ለምግብነት ብቻ ሳይሆን ለገበያ በማዋል በገቢ ምንጭነት ይጠቀሙበታል።
በአንድ ወቅት በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰፊ የአሳ ሀብት ታሳቢ ያደረገ የአሳ ምርትን በፋብሪካ ደረጃ በማቀነባበር ለውጭ ገበያ የማቅረብ እቅድ እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በአሳ ልማት በኩል በቀጣይ በአባይ ግድብ ልማቱን ማካሄድ የሚያስችል እምቅ አቅም ስለመኖሩ ከመጠቆሙ በቀር በቀጣይ ሊካሄድ ስለሚችል ሰፊ የአሳ ልማት እስከ አሁን ብዙም የተሰማ የለም።
የአሳ ሀብትን በማልማትም ሆነ ለምግብነት በመጠቀም በኩል ክፍተቶች ሲስተዋሉ ኖረዋል። ከህዝቡ አመለካከት የተነሳ አሳ ለምግብነት የሚውልበት ሁኔታ ውስን ሆኖ ነበር፤ በእዚህ በኩል ብዙም የሚሰማ ችግር አይደለም።
አመራረቱ ግን አሁንም ስራው ከዘልማድና ባህላዊ አሰራር ብዙም እንዳልወጣ ያመለክታል። በአንዳንድ አካባቢዎች የአሳ ሀብቱን ከማልማት ይልቅ ህገወጥ አሳ አስጋሪዎች በአሳ ሀብቱ ላይ ጉዳት እያደረሱ ስለመሆናቸው ሲነገር ይደመጣል። ይህ ሁሉ ችግር ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን የገቢ ምንጭ እንዳሳነሰው ነው የሚጠቆመው።
ዛሬም በዘርፉ ላይ ጎልቶ የወጣ ሥራ እየታየ እንዳልሆነ ይጠቆማል። በሀገሪቱ የአሳ ሀብት በስፋት እያለ ሀገሪቱ አሁንም የአሳ ምርት ውጤቶችን ከውጭ ሀገሮች እያስገባች ትገኛለች። ከተለያዩ ሀገራት የሚገቡ የአሣ ውጤቶችና ምርቶች እንደ ሱፐርማርኬት ባሉ በሰፋፊ መገበያያዎችና ሆቴል ቤቶች የሚታየው ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል። ይህም በሀገር ውስጥ በዘርፉ ሥራዎች ስላለመሰራታቸው እንደ አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷም ቢሆን ከአፍሪካ ቀዳሚ፣ከዓለም ደግሞ በአስረኛ ደረጃ ላይ ትጠቀሳለች። አብዛኛው የግብርና ሥራም በእንስሳት ጉልበት የሚከናወን መሆኑ ይታወቃል። የእንስሳት ሀብቱ ከዚህ በተጨማሪም ለሥጋ ምርት ይውላል። ይህ ሁኔታም የእንስሳት ሀብት በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላቅ ያለ ድርሻ እንዲኖረው አድርጎታል።
እንዲያውም ሆኖ ግን የአሳና እንስሳት ዘርፉ ክፍለኢኮኖሚው ላይ የሚጠበቀውን ያህል ድርሻ እንዳላበረከተ ይገለጻል። በሌላ በኩልም በድንበሮች አካባቢ በሚፈፀም ህገወጥ ግብይት የተነሳ ከዘርፉ መገኘት ያለበት ጥቅም እየተገኘ አይደለም።
ኢትዮጵያ የአሳና የእንስሳት ሀብቷን በተቀናጀ አግባብ ማልማት ባለመቻሏ፣ በግብይት ላይም በሚገባ ባለመስራቷ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ቀርቶ ለዜጎቿም በበቂ ሁኔታ ማቅረብ አልቻለችም። በተለይ በእንስሳት ሀብት ላይ የሚስተዋለው ህገወጥ ንግድ ችግሩ የበለጠ እንዲባባስ አድርጓል። ይህ ሁኔታ እስከመቼ ድረስ ይዘልቃል? በሚል በብዙዎች አስተያየት ይሰጣሉ።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሣ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቅሩ ረጋሣ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ካላት የውሃ ሀብት በተለያየ መልኩ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራች ትገኛለች። ወጣቶች ተደራጅተው በአሣ ልማት ላይ እንዲሰሩ እድል እየተፈጠረ ነው። ግብርና ሚኒስቴርም በባህርዳር፣ ሰበታ፣ ዝዋይ፣ ደቡብና ሲዳማ ባሉት የአሳ ጫጩት ማባዣ ማዕከላት የአሣ ጫጩቶችን በማበዛት በተለያዩ የውሃ አካላት ውስጥ በመጨመር ልማቱ እንዲከናወን ያግዛል።
በወንዞችና በተፈጥሮ ሐይቆች ብቻ ሲከናወን የቆየውን የአሣ ልማት በየአካባቢው ለአሣ ልማት የሚውሉ ሰው ሰራሽ ኩሬዎች(ፖንዶች) በማዘጋጀት እየተሰራ ሲሆን፣ በዚህም የአሳ ምርታማነትን መጨመር ተችሏል። ይሁንና ምርታማነቱ ቢሻሻልም ለውጭ ገበያ ማቅረብ ግን አልተጀመረም።
በዚህ ረገድ ያለው ተሞክሮ በቋንጣ መልክ (ስሞክድ ፊሽ) በሚባል ዘዴ ከጋምቤላ አካባቢ ወደ ደቡብ ሱዳንና አንዳንድ ሀገራት የመላክ ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም፣ ስራው የተጠናከረ አይደለም። በዘርፉ ከፍተኛ ሥራ መሥራት ይጠበቃል።
በሶማሊያ ድንበር አካባቢ ያልተቀነባበረ የአሣ ምርት በህገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባም እንደተደረሰበት ጠቅሰው፣ ሀገሪቱ ባሏት የውሃ ሀብቶች ሁሉ አሳ የማምረት አቅሟን ካሳደገች እነዚህን ሁሉ ክፍተቶች መቅረፍ ይቻላል ነው የሚሉት።
የአባይ ግድብም ለአሣ ልማቱ ከፍተኛ ግብአት እንደሚሆን ይጠበቃል። በዚህ ረገድ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት(ኢጋድ) ኢትዮጵያን በመግባቢያ ሰነድ ያሳተፈ ‹‹ብሉ ኢኮኖሚ ስትራተጅ›› በሚል አጀንዳ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ይህን ጥረት ለማሳካት የግብርና ሚኒስቴርን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አስፈጻሚ ተቋማትንም የጋራ ትብብር ይጠይቃል። በዚህ መልኩ ከተሰራ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባለፈ ዜጎችን በሥርአተ ምግብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻልበት ዕድል ይፈጠራል።
በእንስሳት ሀብት ልማት በኩል ስላለውም ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ ትታወቃለች። ሀገሪቱ በአጠቃላይ ወደ 70 ሚሊየን የሚጠጋ የከብት ሀብት አላት። ካለው የከብት ሀብት 95 በመቶ የሚሆነው የሀገረሰብ ነው። የከብት ሀብቱ በአንድ በኩል ለግብርና ሥራ ይውላል። ከዚህ አገልግሎት በኃላ ደግሞ ለሥጋ ምርት እንዲውል ይደረጋል።
ከከብት ሀብቷ መካከልም ወደ 15 ሚሊየን የሚጠጉት በሬዎች ናቸው። ይህም በእርሻ ሥራው ለሰብል ልማት በከፍተኛ ሁኔታ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። የተቀረው ደግሞ እንዲደልብ ተደርጎ ለገበያ እየቀረበ ለሥጋ ምግብ ፍጆታ ይውላል። ሀገሪቱ ወደ 15 ሚሊየን የሚጠጋ የወተት ላሞችም አሏት። ከነዚህ ውስጥም ወደ ሰባት ሚሊየን የሚሆኑት የሚታለቡ ናቸው።
የሀገሪቱ እንስሳት በተለያዩ ምክንያቶች የሥጋና የወተት ምርታማነታቸው ዝቅተኛ ነው። በዚህ የተነሳ በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ክፍተት ይታያል፤ ይህን ክፍተት ለመሙላት በመንግስት በኩል የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው እንስሳትን በማዳቀል ምርታማነታቸውን የመጨመር ሥራ እየተሰራ ይገኛል። በተከናወነው የዝርያ ማሻሻያ ዘዴ ከአንድ ላም በአማካይ በቀን እስከ 15 ሊትር ወተት ማግኘት የሚቻልበት ዕድል እየተፈጠረ ነው።
በተለምዶ የፈረንጅ ላም የምትባለው ወይንም በተሻሻለ ዝርያ የተገኘች አንዲት ላም የምትሰጠው የወተት ምርት አስር ሀገረሰብ ላሞች የሚሰጡትን ወተት ያህላል። ይህ ትልቅ ለውጥ ነው። አሁንም ግን የተጠቃሚውን ፍላጎት ለማሟላት ብዙ መሥራት ይጠይቃል።
አሁን ባለው መረጃ በኢትዮጵያ በነፍስ ወከፍ የወተት ምርት ፍላጎት 70 ሊትር ነው። ይህ ደግሞ የዓለምጤና ድርጅት ካወጣው መስፈርት በታች ነው። በዘርፉ ያለውን ፍላጎትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን መሠረት በማድረግ ግብርና ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ በእንስሳት እርባታና ምርታማነት ማሳደግ ላይ እየሰራ ይገኛል።
እንስሳቱ ምርታማነታቸው እንዲጨምር የተመጣጠነ መኖ ማግኘት ይኖርባቸዋል፤ በዚህ ረገድም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ይገልጸሉ። በጤናም የተጠበቁ እንዲሆኑ በህክምና አገልግሎቱ ላይ ክትትልና ቁጥጥሩ መጠናከሩን የጠቀሱት አቶ ፍቅሩ፤በተለይም የሥጋ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ጤንነቱ የተጠበቀ የሥጋ ምርት ማቅረብ እንደአንድ መሥፈርት የሚታይ መሆኑንና የበሽታ መከላከል ሥራው አስፈላጊነትን አስረድተዋል።
እንደ ሚኒስትርዴኤታው ገለጻ፤ በግብርናው ሥራው በሬ ጠምዶ ከማረስ ወደ ሜካናይዜሽን ለመሸጋገር እየተደረገ ያለው ጅማሮ ተጠናክሮ ከቀጠለ ወደ 15 ሚሊየን የሚጠጋው የእንስሳት ሀብት ሙሉ ለሙሉ ለሥጋ ምርት የሚውልበት ሁኔታ ይፈጠራል፤ ያኔ ደግሞ የእንስሳት ሀብቱ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚው ገቢ ላይ ለውጥ ያመጣል።
ሚኒስትር ዴኤታው ህገወጦች የቁም እንስሳ በህገወጥ መንገድ በሶማሊያ፣ በጅቡቲ፣ በኬኒያ በሌሎችም ጎረቤት ሀገሮች በኩል እንዲወጡ እያደረጉ መሆናቸውን ይገልጻሉ። እንስሳቱ በህገወጥ መንገድ ከሀገር መውጣታቸው ብቻ ሳይሆን የሚያሳስበው፣ በሌላ ሀገር የምስክር ወረቀት አማካኝነት ለመካከለኛው ምሥራቅ፣ሰሜኑ ክፍልና ለሌሎችም ሀገራት ለገበያ የሚቀርቡት ሁኔታ ነው ይላሉ። በእንስሳት ሊገኝ የሚችል ጥቅምን ከሚያሳጡ ምክንያቶች ይሄ አንዱ በመሆን ይጠቀሳል ሲሉ ያብራራሉ።
በመንግሥት ክትትልና ቁጥጥር ብቻ ይህን ተግዳሮት ማስቀረት አይቻልም ይላሉ ሚኒስትር ዴኤታው። የህዝብ ባለቤትነት፣ ተቆርቋሪነትና ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ። በመንግሥት ቁርጠኝነት እየተከናወነ እንዳለው የስንዴ ልማትና የአረንጓዴ አሻራ መርህ ግብር በእንስሳት ልማቱም የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት በሚኒስቴሩ በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህን ተልእኮ ይዞ ሲነሳ የግል ባለሀብቱን በእጅጉ በማበረታታት ነው። አሁን ባለው አንቅስቃሴም በገበሬው መንደር ከሚከናወነው የእንስሳት ልማት በተጨማሪ የግሉ ዘርፉ የላቀ ሚና እየተወጣ ይገኛል።
አሁን ገበያው ላይ እየቀረበ ያለው የዶሮና ዶሮ ውጤት ምርት በግሉ ዘርፍ የሚለማ መሆኑንም ጠቅሰው፣ የግሉ ዘርፍ በስፋት ባይንቀሳቀስ ኖሮ አንድ የሀገረሰብ ዶሮ በአመት በምርታመርተው 40 እንቁላል የተጠቃሚውን ፍላጎት ለማሟላት ያዳግት ነበር ሲሉ ያብራራሉ። የተሻሻለ ዝርያ ካላት አንድ ዶሮ በአመት እስከ ሶስት መቶ እንቁላል ማግኘት እንደሚቻልም ጠቅሰው፣ይህ ጥረት ክፍተቱን በመጠኑም ቢሆን ለመቀነስ ያግዛል ይላሉ።
በወተት ልማቱም ቢሆን ተደራጅተውና በግላቸው የሚሰሩ ባለሀብቶች ናቸው ፍላጎትን ለማሟላት ጥረት እያደረጉ የሚገኙት ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ይጠቅሳሉ። በቴክኖሎጂ የታገዘ የእንስሳት ልማት ለማካሄድ በመንግሥት በኩል እየተከናወነ ባለው ሥራ የወተት ላሞችን በብዛት ለማግኘት እንዲቻል ወደ 12ሺ ኮርማዎች ከውጭ ሀገር እንዲገቡ መደረጉን ይጠቅሳሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በከብት ልማቱ ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉም መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ ጊደር እየቀረበ ይገኛል። ይህም በአዳ በርጋ፣ቻግኒ፣ወላይታሶዶ፣ወልቂጤ፣ላይ ካለፈው በጀት አመት ጀምሮ እየተከናወነ ባለው ጊደር የማባዛት ሥራ ጊደር ለሚፈልጉ በማቅረብ ፍላጎትን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ነው። ዘንድሮ ደግሞ ሶስት የማባዣ ማእከሎችን በመጨመር የማባዛቱን ሥራ ለማስፋት እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
ሰሞኑን በስካይላይት ሆቴል የተከፈተው የዶሮ ኤክስፖና ሰባተኛው የእንስሳት ሀብት ዐውደርዕይ በግብርናው ዘርፍ በተለይም በእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ልማት ላይ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴና ጥረት ያመለክታል። በዚህ ዝግጅት ላይ የወተት፣ የእንቁላል ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች የማስተዋወቅ ስራ ተካሂዷል፤ በዘርፉ በተከናወኑት ሥራዎች የተገኙ ውጤቶችን ማየት ተችሏል፤ የገበያ ትስስር ለመፍጠርም እድል የተገኘበት ነው።
በዚህ ዐወደ ርዕይ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ10 ሀገራት የተውጣጡ በቴክኖሎጂ፣በእንስሳትና እንስሳት ውጤት ልማት ላይ የተሰማሩ 70 የሚሆኑ ኩባንያዎች መሳተፋቸውም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
መንግስት በያዘው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና በመኸር እርሻ በስንዴ ልማት እየተካሄደ ባለው ርብርብ ሀገሪቱ ስኬታማ እየሆነች መጥታለች። መንግስት ይህን ልማቱን በዶሮ፣ እንቁላልና ወተት ልማት ላይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስታወቁ ይታወሳል። በመሆኑም መሰል ኤክስፖዎች በእንስሳት ሀብት ለተያዘው ምርታማነትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ የጎላ አስተዋጽኦ የሚኖራቸው አንደመሆኑ በስፋት ሊካሄዱ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2015