ባለፈው ሐሙስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በአዲስ መልኩ የተገነባው 15 ሜዳ በአራዳ ክፍለ ከተማ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት በመሆኑ ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሜዳውን እንደ አዲስ ለማሰራት ሌሎችን አነሳስተው ምርቃቱም ላይ የተገኙት ይህ ሜዳ ከሌሎች የተለየ ምን ቢኖረው ነው የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም።
ሜዳው ቀበና አካባቢ የሚገኘው በተለምዶ «የቤሌር እግር ሜዳ ነው»። «ይህ ስፍራ ብዙዎቻችን ከምናስበው በላይ ታዋቂና አንጋፋ እግር ኳስ ተጫዋቾችን አፍርቷል። ነገር ግን ለበርካታ ጊዜያት ተረስቶ የቆሻሻ መጣያ ሆኖ ነበር። የአካባቢው ታዳጊዎችም ማዘውተሪያ ስፍራ አልነበራቸውም። የ15 ሜዳና አካባቢው የጤና እግር ኳስ ማህበር ይህን ለስፖርት ማዘውተሪያነት ምቹ ያልሆነ ስፍራ እንደሌሎቹ ማዘውተሪያዎች ለግንባታ እንዳይውል ከመታገል ጀምሮ ምቹ ያልነበረውን ሜዳ አፅድተው ለብዙ ወጣቶች መዋያ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
ሜዳው የነበረውን የቀድሞ ስም ለመመለስ፣ ጤናን መሰረት አድርጎ ስፖርትን ከማበረታታት ባለፈ ለታዳጊ ወጣቶች ተስፋ የሚፈነጥቁ ስራዎችን በመስራትም ተመስጋኞች ናቸው። ዛሬ ይህ ሜዳ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በአርቴፊሻል መጫወቻ ሜዳ አጊጦ የተለየ ውበት ተላብሳል። የቤሌር ሜዳ ከዚህ ቀደም ለኢትዮጰያ እግር ኳስ ያበረከተው አስተዋ ከፍተኛ እንደመሆኑ ይህን ክብርና ውብ ገፅታ ማግኘቱ ቢያንሰው እንጂ
አይበዛበትም። ለብዙ ዓመታት «የቆሻሻ መጣያ እና መፀዳጃ» ሆኖ የአካባቢውን ሰው ለጤና ችግር ሲያጋልጥ የቆየው ይህ ሜዳ በጤና ማህበሩ የተሻለ ስፍራ ሆኖ ቆይቷል። ዛሬ የተላበሰው አዲስ ገፅታም ሜዳው በታሪክ ያፈራቸውን እውቅ ተጫዋቾች በስፖርት ማህደር አምዳችን ከብዙ በጥቂቱ እንድናስታውስ አድርጎናል ።
አሰልጣኝ ንጉሴ ገብሬ
አስረኛው የአፍሪካ ዋንጫና በ1974 በሊቢያ በተዘጋጀው 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ያስቻሉ ተጠቃሽ ተጫዋቾችን አገራችን አፍርታለች። ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ውለታ ከሰሩት ተጫዋቾች መካከልም መንግስቱ ወርቁ፣ ይድነቃቸው
ተሰማ ንጉሴ ገብሬ በቀዳሚነት የሚጠሩ ናቸው። በእነዚህ ሁለት የመጨረሻዎቹ የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው ውስጥ አንዱ የሆነው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋችና አሰልጣኝነት ንጉሴ ገብሬ በታሪካዊው «የቤሌር ሜዳ ላይ ኳስን ካንከባለሉት» ውስጥ የሚጠቀስ ነው።
በ 1 9 4 8 ዓ . ም የተወለደው ንጉሴ ገብሬ በአዲስ አበባ ቀበና አካባቢ ተወልዶ አድጓል። ለንጉሴ ስኬት ቤሌር ትልቅ ትርጉም ነበራት። እርሱም «በልጅነቴ እንደ ማንኛውም ታዳጊ ሰፈር ውስጥ እግር ኳስ እጫወት ነበር። በትምህርት ቤት ቆይታዬም ኳስ ተጫውቻለሁ» በማለት በአንድ ወቅት ሲናገር ተደምጣል። የንጉሴ የልጅነት የእግር ኳስ ጨዋታው የሚጀምረው በዚችሁ ሜዳ ላይ ነበር። ንጉሴ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ከ1967 እስከ1983 ለ16 ዓመታት ያህል ተጫውቷል።
ባዩ ሙሉ
ሌላኛው በቤሌር ሜዳ ተጫውተው ለስኬት ከበቁ ታዋቂ አግር ኳስ ተጫዋቾች ውስጥ ባዩ ሙሉ ተጠቃሽ ነው። በኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍቃሪ ልብ ውስጥ ያለው ባዩ «የቤሌር ሜዳ» እድል ቀንቶት በታዋቂው የቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን ለመጫወት በር ተከፍቶለታል። ባዩ የመጀመሪያውን የምሥራቅ አፍሪካ የታዳጊዎች ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ ይዘው ከመጡ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሲሆን የርሱ ድርሻ ጉልህም ነበር። ከዚህም ሌላ ኬንያ ባዘጋጀችው «የሴካፋ ሻምፒዮና» ላይ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ለመመረጥም በቅቷል። የምሥራቅ አፍሪካ ውድድር ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር ውጪ በሩዋንዳ ዋንጫ ስታነሳ በፍፃሜው ጨዋታ ላይ የማሸነፊያዎቹን ሁለት ግቦች አስቆጥሯል። ባዩ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት አመት በዋናው ክለብ ተሰልፎ ተጫውቷል። የእግር ኳስ ህይወቱ ከማብቃቱም በፊት በቤልጂየም አገር ለረጅም ጊዜ ተጫውቷል። የቀበናዋ ቤሌር ሜዳም ካበቀለቻቸው የአገር ባለውለታዎች ተርታ አሰልፋዋለች።
የቀድሞው ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እና በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአሁኑ ሰአት ተሳትፎ የሚያደርገው መቻልን በማሰልጠን ላይ የሚገኘው ዮሀንስ ሳህሌም በዚህች ታሪካዊ ሜዳ ላይ እግራቸውን ካሟሹ እውቅ የካስ ሰዎች አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል። ጌቱ ተሾመ «ድክሬ»፣ ፓውሎስ ማንጎ የመሳሰሉቱ በትንሿ ሜዳ ላይ ኳስን ሲያንሸራሽሩ ነበር። የወደፊት እንጀራቸውንም የወሰነችው ይህቸው ሜዳ ነበረች። በቅርብ ጊዜም ይህቺ ታሪካዊ ሜዳ እንደ ቀድሞው ባይሆን እንኳን ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና ለቅዱስ ጊዮርጊስና ሌሎች ታላላቅ ክለቦች የተጫወተው ናትናኤል ዘለቀን አፍርታለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2015