የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በ1991 ዓ.ም በጻፉት አንድ መጣጥፍ፤ ዋና ዋና የታሪክ ክስተቶች ውዝግብ ያለባቸው ናቸው ይላሉ። ጭፍን የሆነ ድጋፍ እና ጭፍን የሆነ አድናቆት ያላቸው ናቸው ይላሉ።
በእርግጥ ይህን ለማወቅ የታሪክ ባለሙያን አስተያየት መጥቀስም አያስፈልግም፤ ምክንያቱም ለማንም ተራ ግለሰብ ሁሉ ግልጽ ነው። በታሪካዊ ክስተቶቻችን ላይ ምክንያታዊ አተያይ የለንም፤ የሚታየው ጭፍን ጥላቻ እና ጭፍን አድናቆት ነው። በአንፃራዊነት የጋራ መግባባት ያለው ከውጭ አገራት ጋር በተደረጉ ጦርነቶች ነው።
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን 106 ዓመታትን ወደኋላ ሄደን የሰገሌን ጦርነት ልናስታውስ ነው። የሰገሌ ጦርነት የተካሄደው በዚህ ሳምንት ጥቅምት 17 ቀን 1909 ዓ.ም ነበር።
የሰገሌ ጦርነት በሥልጣን ሽኩቻ ከተደረጉ የእርስበርስ ጦርነቶች ሁሉ በአስከፊነቱ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው። ከዛሬ 106 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ምን ያህል ይሆን ነበር? የሚለውን ታሳቢ እናድርግና 16 ሺህ ያህል ሰዎች የተጨፋጨፉበት ጦርነት ነው።
የሰገሌ ጦርነት መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ሚካኤል በመኳንንቱና ኢትዮጵያን ለመቀራመት አሰፍስፈው ይጠብቁ በነበሩ ቄሳራውያን(እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን) ኃይሎች ሴራ ከአልጋ ወራሽነታቸው ከተሻሩ በኋላ፣ አባታቸው ንጉሥ ሚካኤል አሊ የልጃቸውን ስልጣን ለማስመለስ ከማዕከላዊ መንግሥቱ ጦር ጋር የመጨረሻውን ጦርነት ያደረጉበት ነው።
በ1906 ዓ.ም በልጃቸው አማካኝነት ‹‹የወሎ፣ የትግሬና የጎጃም ንጉሥ›› ተብለው የተሾሙት ንጉሥ ሚካኤል አሊ፣ በ1909 ዓ.ም የልጃቸውን ከዙፋን መሻር ሲሰሙ ‹‹ቢያጠፋ እንኳ እኔ እመክርና አርመው የነበረውን ልጄን እንዴት ሳያማክሩኝ የአባቱን ዙፋን ያስለቅቁታል?›› በማለት ‹‹የጠፋ ልጄን አፋልጉኝ›› ብለው 80 ሺህ ወታደሮቻቸውን አስከትለው ወደ ሸዋ ዘመቱ።
የንጉሥ ሚካኤልን ጦር ለመግጠም በማዕከላዊው መንግሥት በኩል 120 ሺህ ጦር ተዘጋጅቶ የመጀመሪያው ጦርነት ከዋናው ጦርነት ቀደም ብሎ ጥቅምት 7 ቀን 1909 ዓ.ም በደብረ ብርሃንና አንኮበር መካከል በሚገኘው ቶራ መስክ ላይ ተካሄደ።
በቶራ መስክ ጦርነትም የንጉሥ ሚካኤል ጦር አሸነፈ። በዚህ ውጊያ ላይ የሸዋው የጦር መሪ ራስ ልዑልሰገድ አጥናፍሰገድን ጨምሮ በርካታ የጦር አዛዦችና ወታደሮች አለቁ። ለጦርነቱ 120 ሺህ ጦር ይዘጋጅ እንጂ ከዚህ መካከል ቁጥሩ በርከት ያለው የሸዋ ጦር ከንጉሥ ሚካኤል ጦር ጋር የተዋጋው ሰገሌ ላይ ነበር።
ከድሉ በኋላም፤ የጦር ሚኒስትሩና የማዕከላዊው መንግሥት ቁልፍ ሰው የነበሩት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) ገፀ በረከትና ላይ ላዩን ሲያዩት እርቅ ውስጥ ውስጡን ደግሞ ማዘናጊያ የመሰለ ቃላት በመላክ የወሎው ጌታና ጦራቸው ተዘናግተው እንዲቆዩ አደረጉ። ‹‹በሰላም መወያቱ ይሻላል›› የሚል ሃሳብ ያለውና ውሉ ያልለየውን ቃል የሰሙት ንጉሥ ሚካኤልም የመጀመሪያው ድላቸውን እንደጨበጡ ሰገሌ ሜዳ ላይ ሰፍረው ቆዩ።
ከቶራ መስኩ ጦርነት 10 ቀናት በኋላ ዋናውን ጦርነት ጥቅምት 17 ቀን 1909 ዓ.ም የንጉሥ ሚካኤል ጦርና የማዕከላዊው መንግሥት ጦር ሰገሌ በተባለው ሜዳማ ስፍራ ላይ ከባድ ጦርነት አካሄዱ። የማዕከላዊው መንግሥት ቁልፍ ሰው በነበሩት በጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ እቅድ አውጪነትና መሪነት ለቀናት ያህል በስውር ከበባ ሲያደርግ የቆየው የማዕከላዊው መንግሥት ጦር የወሎን ጦር ባላሰበው መንገድ አጠቃው።
በዚህ ጦርነት ላይ የጦር ሰራዊቱ ጠቅላይ አዛዥ ሆነው የዘመቱት ራስ ተፈሪ መኮንን ሲሆኑ ከእርሳቸው ጋርም ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ እና ራስ ካሳ ኃይሉ መሪ ሆነው ተሳትፈዋል። በውጊያውም የንጉሥ ሚካኤል ጦር ያለቀው አልቆ የተረፈው ሲበታተን ንጉሥ ሚካኤልም ተማረኩ። የሰገሌው ጦርነት ከዓድዋ ጦርነት በኋላ ብዙ ሰው ያለቀበት ከባዱ ውጊያ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል።
ንጉሥ ሚካኤል በሰገሌው ጦርነት ተሸንፈው፣ ተማርከው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ሲያልፉ ክብራቸው ተዋርዶ እንደነበር የታሪክ ጸሐፍት አስፍረውታል።
‹‹ሐበሻና የሰገሌው አብዮት›› የሚለውን መፅሐፍ የፃፈው እንግሊዛዊ ጸሐፊ በበኩሉ‹‹ …ንጉሥ ሚካኤል ሀገሪቱ አሉኝ ከምትላቸው ጀግና የግዛት አስተዳዳሪዎችና የጦር መሪዎች አንዱ ነበሩ … ያ ከንቱ ልጅ ከከብራቸው ዝቅ እንዲሉ አደረጋቸው…›› በማለት ጽፏል።
በእርግጥ የዚህ መጽሐፍ ፀሐፊ እንግሊዛዊ በመሆኑና እንግሊዝ ከማዕከላዊው መንግሥት ሹማምንት ጋር በማሴር ልጅ ኢያሱ ከዙፋናቸው እንዲሻሩ ትልቁን ድርሻ የተወጣች ቄሳራዊ ኃይል ስለሆነች ፀሐፊው እንደዚያ ብለው ቢጽፉ የሚገርም አይደለም፤ በመጽሐፉ ውስጥ በርካታ የተዛቡ ታሪኮች አሉ የሚል ወቀሳም ሲቀርብበት ነበር።
‹‹ተፈሪ መኮንን፡ ረጅሙ የስልጣን ጉዞ›› በሚለው የክቡር አምባሳደር ዘውዴ ረታ መጽሐፍ ላይም ስለ ጦርነቱና ከውጊያው በኋላ ስለተፈፀሙት ድርጊቶች ተብራርቷል።
በሰገሌው ጦርነት ላይ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እንዳለ የተለያዩ የታሪክ ጸሐፊዎች ጽፈዋል። ልጅ ኢያሱ መፈንቅለ መንግሥት እንድደረግባቸው አድርገዋል። በነገራችን ላይ እርሳቸው በቀጥታ ‹‹መፈንቅለ መንግሥት›› ባይሉትም ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ‹‹ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ›› በሚለው መጽሐፋቸው መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም በልጅ ኢያሱ ላይ የተደረገውን አድማ በገደምዳሜው ገልጸውታል። ካህናቱና መኳንንቱ ከዚህ በኋላ ልጅ ኢያሱን አውርደን የአጼ ምኒልክን ልጅ ዘውዲቱን አንግሰናል ማለታቸውን ራሳቸው አጼ ኃይለሥላሴ ጽፈዋል።
ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ከአድዋ ድል በኋላ የቆዩባቸው አስር ዓመታት (ከ1888 ዓ.ም እስከ 1898 ዓ.ም) የሰላምና የመረጋጋት ወቅት እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ንጉሡ ታመው አልጋ ላይ ሳሉ የሥልጣን ሽኩቻ እንዳያገረሽ በማሰብ መላ ዘየዱ። በወቅቱ በጎረቤት አገራት የቅኝ ግዛት ይዘው የነበሩት እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን በለንደን የሦስትዮሽ ውል ተፈራርመው «እርስዎ ድንገት ቢያርፉ አገር እንዳትበጠበጥ ሦስታችን መንግሥታት የበላይ ጠባቂ ሆነን አገር ለማረጋጋት…» የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ ለምኒልክ ይልካሉ።
ንጉሡም አገሪቱን ለጅቦች አሳልፎ ላለመስጠት ለሦስቱ አገራት ቅኝ ገዥዎች በማያሻማ መልክ ግልፅ ያለ መልዕክት አስተላለፉ። « እኔ ብሞት ኢትዮጵያ በአልጋ ወራሼ አማካይነት ትቀጥላለች፤ የተረጋጋ ሥርዓትም እናቆማለንና አታስቡ » ካሉ በኋላ እርምጃዎችን ወሰዱ።
በወቅቱ ንጉሥ ምኒልክ ሲሞቱ በይፋ ያልተገለጸበት ምክንያትም የአገር ውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ ይቀሰቀሳል፤ በጎረቤት አገሮች ያሉ ያደፈጡት ቅኝ ገዥዎችም አደጋ እንዳይደቅኑ በመስጋት ሊሆን እንደሚችል ሰነዶች ያስረዳሉ።
በወቅቱ በ1900 ዓ.ም በሀገሪቱ የመጀመሪያውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት አቋቋሙ። ከወሎው ኢማም መሀመድ አሊ (ራስ ሚካኤል) የተወለደው የልጅ ልጃቸው ልጅ ኢያሱ አልጋ ወራሻቸው መሆኑን አወጁ።
ልጅ እያሱ ገና ልጅ ስለነበሩም የሸዋው ራስ ተሰማ ናደውን የልጅ ኢያሱ ሞግዚት አድርገው ሰየሙ። ራስ ተሰማ ሲሞቱ ሌላ ሞግዚት ለመሰየም እየተከናወነ ባለው ተግባር በመኳንንቱ ዘንድ እኔ እሆን እኔ እሆን የሚል ነገር ተከሰተ፤ ሁኔታው ያላማራቸው ልጅ እያሱ በሸዋ ሞግዚት አያስፈልገኝም ወደሚል ድምዳሜ ደረሱ። ይህ የሚሆነው አጼ ምኒልክ ታመው በነበሩበት ወቅት ነው።
ልጅ ኢያሱ በአስተዳደር ቆይታቸው በጠረፍ አካባቢዎች የሚያደርጉት ተደጋጋሚ ጉብኝት በመኳንንቱ ዘንድ አልተወደደም።
በአገር ውስጥ ከሃይማኖት ጋር ጭምር የተያያዘ ሽኩቻ ሲነዛ በውጭ ደግሞ፤ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ከእንግሊዝ ፈረንሳይና ጣሊያን በተፃራሪ ደረጃ ለነበሩት ጀርመንና ቱርክ ድጋፋቸውን አሳይተዋል በሚልም በሌሎቹ ነጮች ዘንድ ጥርስ ተነከሰባቸው፤ በአገር ውስጥም አድማ ተጠነሰሰባቸው።
በእነዚህ ምክንያቶች በልጅ ኢያሱ መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ከሥልጣን ተሽረው (መፈንቅለ መንግሥት) ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥት እና ተፈሪ መኮንን ደግሞ አልጋ ወራሽ መሆናቸው ይፋ ተደረገ።
ይህኔ ነው የልጅ ኢያሱ አባት ጦራቸውን አዝምተው ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር በተደረገ ጦርነት ያ ሁሉ ደም አፋሳሽ እልቂት የተከሰተው።
እንግዲህ ከዚህ ምን እንማራለን ከተባለ፤ የውጭ ሴራ ከድሮም ጀምሮ የነበረ መሆኑን እና የውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ ድሮም የነበረ መሆኑ ነው። የሥልጣን ፍላጎት እንጂ የዘር አለመሆኑን ነው። ምክንያቱም የተላለቀው የአንድ አካባቢ ሕዝብ ነው። ልጅ ኢያሱ የአጼ ምኒልክ የልጅ ልጅ ነው። ዘውዲቱ የአጼ ምኒልክ ልጅ ናት። ስለዚህ ኢያሱን ገልብጦ ዘውዲቱን ማንገስ ከሥልጣን ፍላጎት ውጭ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?
ከመቶ ምናምን ዓመታት በፊት የነበሩ የታሪክ ክስቶችን የምናስታውሰው ዛሬ ዓለም የሥልጣኔ ማማ ላይ ባለበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን ነው። ስለዚህ ዘመኑን የሚመጥን አስተሳሰብ ይኑረን እና ታሪክን እንዲህ በታሪክነቱ ብቻ የምናስታውሰው እንሁን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20 ቀን 2015 ዓ.ም