ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት ጤናማና አምራች ዜጋ ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ ስፖርት የማይናቅ ሚና አለው። ስለስፖርት ሲነሳ ደግሞ የማዘውተሪያ ስፍራ ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ማነቆ በመሆን ተደጋግሞ ከሚነሱ ችግሮች መካከል ደግሞ ይህ የማዘውተሪያ ስፍራ ጉዳይ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
ምንም እንኳን የማዘውተሪያ ስፍራዎች በአገሪቱ የሉም ማለት ባይቻልም ያሉትም ወይ ምቹ አይደሉም ወይ ደግሞ ለሌላ አገልግሎት ታጥረው የተቀመጡ ናቸው። አብዛኞቹም ለግንባታዎች ውለዋል። በዚህም ምክኒያት ወጣቶች በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ከስፖርት ርቀው አልባሌ ቦታ ለመዋል ተገደው ቆይተዋል። የእነዚህ አነስተኛ ሜዳዎች ጥያቄም ዘወትር ሳይነሳ ውሎ አድሮ አያውቅም።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ነዋሪዎች የዘወትር ጥያቄ ለመመለስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትንንሽ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን የመመለስና ነባሮቹንም በተሻለ መንገድ ለማደስ ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል። የፌዴራል መንግስትም ይህን በመደገፍ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ይታወቃል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ 15 ሜዳ ወይም በተለምዶ ቤለር ሜዳ በሚል የሚታወቀው አነስተኛ ሜዳ በከተማዋ ከሚገኙ ጥቂት የማዘውተሪያ ስፍራዎች አንዱ ነው። ሜዳውን እንደሌሎቹ ለግንባታ ለማዋል ብዙ ጥረት ቢደረግም ይሁንና እጣ ፋንታው ግን የተፈለገው እንዲሆን አልፈቀደም። ይህ ሳይሆን በመቅረቱም የአካባቢው ወጣቶች ምንም እንኳን ሜዳው ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ክረምት በጭቃና በጋ በአዋራ ኳስ ሲያንከባልሉበት፣ የእግር ኳስ ውድድሮችና ልምምዶችም ሲካሄዱበት ቆይቷል። በቅዱስ ጊዮርጊስና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም ባህር ተሻግሮ እስከ ቤልጂየም ሊጎች የዘለቀ ስኬት የነበረውን ባዩ ሙሉን የመሳሰሉ በርካታ ተጫዋቾችን ያፈራው የቤለር ሜዳ ዛሬ ወደ ሌላ ምእራፍ ተሸጋግሯል።
ለስፖርት ምቹ ያልሆኑ ነገሮች ዛሬ ሜዳው ላይ አይታዩም። አዋራና ጭቃም ታሪክ ሆነው ሜዳው የአርቴፊሻል ሳር ለብሶ ባደጉት አገራት እንደምንመለከታቸው ማዘውተሪያ ስፍራዎች ደረጃውን ጠብቆ ወደ አዲስ ምእራፍ ተሸጋግሯል። የቤለር ሜዳ ለዚህ የበቃውም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በአዲስ መልኩ አስገንብተው በመጠናቀቁ ከትናንት በስቲያ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት በመሆኑ ነው ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማዘውተሪያ ስፍራውን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን ባበሰሩበት ወቅትም፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን በየአካባቢው በማስፋፋት የተሻለ ስብዕና ያለው ትውልድ መገንባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራው ግንባታ የክረምት በጎ ፈቃድ ፕሮጀክት አካል መሆኑም ታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ለወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ በመገንባት የተሻለ ስብእና እንዲኖራቸው መስራት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኙ ኤምባሲዎችን ጨምሮ ሌሎች አካላት ይህንን ተሞክሮ ማስፋት እንዳለባቸውም አክለዋል።
“ወጣቶች መልካም ነገር ማየት ይገባቸዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህ ደግሞ የተሻለ ስብዕና ያላቸውን ወጣቶች መገንባት የሚያስችሉ ማእከላት እንደሚያስፈልጉ አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ተቋማት መገንባታቸውን በማስታወስም፣ አሁን ባለው ሁኔታ በአገር አቀፍ ደረጃ 9 ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ መሆናቸውን እንደምሳሌ ጠቅሰዋል።
የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መስፋፋት ወጣቶች በተሻለ ስብእና ተገንብተው ለነገ አገር ተረካቢነት ብቁ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በየአካባቢው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እንዲስፋፋ ሊሰሩ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተሻለ አቅም ያላት አገር መሆኗን አንስተውም፤ ይህን አቅም ለልማት ለማዋል ደግሞ ወጣቶችን ማብቃት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አኳያ መንግስት በቴክኖሎጂና መልካም ስብዕና የተገነቡ አገር ተረካቢ ወጣቶችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የበለጸገች፣ ያደገችና የአፍሪካ ኩራት የሆነች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማስረከብ በትብብር መስራት አለብን ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ታዳጊ አማኑ ዩሀንስና ወጣት ኤሊያስ አብድረህማን በበኩላቸው የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራው ከዚህ ቀደም ለስፖርታዊ ጨዋታ ምቹ እንዳልነበር ለኢዜአ አስተያየት ሰጥተዋል። የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራው እንደ አዲስ እንዲገነባ ላደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2015