ፈርጣማ ወጣት ነው። ዕድሜው ከሃያዎቹ መጨረሻ አይዘልም። ወጣት አድማሱ አብረሃም ሥራ የለውም፤ በትምህርቱም ብዙ አልገፋም። በተቃራኒው ምኞቱ ትልቅ ነው። ሃብታም መሆን ይፈልጋል። ነገር ግን ሃብታም ለመሆን የሚያስችለውን መንገድ አይከተልም። ሠርቶ ጥሮና ግሮ በማደግ አያምንም። ከቤተሰቦቹ ሊወርሰው የሚችለው ሃብት የለውም። እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ ሃብታም ለመሆን ብቻ ይመኛል።
ሠርቶ ሳይሆን ሰርቆም ቢሆን ሚሊየነር መሆንን አጥብቆ ይሻል። የቀን ሠራተኛ ሆኖ በጉልበቱ እንደሚያገለግል ሲገልፅ ቁመናውን እና ጉልበቱን ያየ ለመቅጠር አያመነታም። ነገር ግን የእርሱ ፍላጎት ሥራ አይደለም። ገንዘብ ማግኘት ብቻ ነው። ካልተሠራ ገንዘብ እንደማይገኝ አያገናዝብም። የውስጡን የሚያውቅ የለም፤ ፍላጎቱን መርምረው ሳያረጋግጡ፤ በስፖርት የዳበረው ሰውነቱ ያለምንም የአቅም ችግር ሥራውን ለማከናወን ያስችለዋል ብለው በማመን በቀን ሠራተኝነት ለመሥራት ሲጠይቅ የማይቀጥረው የለም።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ላፍቶ መስጊድ አካባቢ የሚገኘው ፓወር የተሰኘው የቻይና ካምፓኒ ወጣት አድማሱን በተለየ መልኩ ስቦታል። ሌላ ቦታ በቀን ሠራተኝነት ከመቀጠር ይልቅ እዛ መቀጠር በፍጥነት ሃብታም ለመሆን ያመቻል ብሎ ገምቷል። ስለዚህ ወደ ካምፓኒው በመሔድ መሥራት እንደሚፈልግ ገለፀ፤ ተቋሙም ወጣት አድማሱን ለመቅጠር ሲወስን ይሠራል ብሎ በማመን ነበር። ከሌሎች ሠራተኞች ጋር ተባብሮ እንደሚሠራ በመገመት የተካሔደው ቅጥር መጨረሻው እንደሚያምር ቢታሰብም እንደተገመተው አልሆነም።
የማሽኖቹ ጉዳይ
ካምፓኒው ግንባታ ሲያካሂድ የጉልበት ሠራተኛውን ድካም የሚቀንሱ ማሽኖችን ይጠቀማል። በዚህም ሠራተኞቹ ይደሰታሉ ተብሎ ይታሰባል። እንደቀድሞ አሸዋ በሳጥን ሰፍሮ የሲሚንቶ ከረጢት ቀዶ ውሃ እየጨመሩ በአካፋ ቀኑን ሙሉ ሲያቦኩ መዋል የለም። ካምፓኒው ግንባታ ሲያከናውን አሸዋውን እና ሲሚንቶውን ጠጠሩንም ጨምሮ ውሃ ሲታከልበት በፍጥነት የሚያቦካ ሚክሰር የተሰኘው ማሽን ይጠቀማል።
ይህ በግንባታ ቦታዎቹ ላይ እጅግ ተፈላጊ የሆነው ሚክሰር እና አርማታ መጠቅጠቂያ የወጣት አድማሱን ቀልብ ስቧል። ያ ብቻ አይደለም። አርማታ ሲሞላም በቀን ሠራተኛው ጉልበት አይደለም። አርማታ የሚሞላው በመጠቅጠቂያ ቫይብሬተር ነው። ወጣት አድማሱ እነዚህ ማሽኖች የሚሠሩትን ሥራ እያየ የጉልበት ሠራተኞችን ምን ያህል እንደሚያግዙ በመገመት በማሽኑ እያሠራ ያለውን ካምፓኒ ከማመስገን ይልቅ በሃሳቡ ሌላ ነገር መመላለስ ጀመረ። ሲያወጣ እና ሲያወርድ ‹‹እነዚህን ማሽኖች መስረቅ ምን ያህል ከባድ ይሆናል?›› ብሎ ማውጠንጠኑን ተያያዘው። ቀን ሲሠራባቸው ተውሎ ሲመሽ ጊቢው ውስጥ እንደቀልድ ተትተው የተለየ ጥበቃ ሳይደረግላቸው የሚያድሩ በመሆናቸው ማሽኖቹን መስረቅ አዳጋች እንደማይሆን ገመተ።
የስርቆት ምክር
ወጣቱ ‹‹ማሽኖቹ ቢሸጡ ስንት ያወጣሉ?›› በማለት የዋጋ ጥናት ማድረግ ጀመረ። ከ100 ሺህ ብር በላይ እንደሚያገኝ በመገመት በሚያገኘው ገንዘብ ምን እንደሚያደርግ አቀደ። ስለዚህ አላመነታም ለመስረቅ ወሰነ። የሚተባበሩትን መለመለ፤ በእርሱ መሪነት እና በሌሎቹም አጋፋሪነት ስርቆቱን ለማከናወን መዶለት ጀመረ።
ሆኖም ‹‹ማን ይገዛናል?›› የሚል ጥያቄ ተነሳ፤ ‹‹ከተሰረቀ በኋላስ የት ማስቀመጥ ይቻላል? ›› የሚል ተጨማሪ ሃሳብ ተሰነዘረ፤ ወጣት አድማሱ አብረሃም ቦሌ አካባቢ ማሽኖችን የሚሸጡ እና የሚያከራዩ ስለመኖራቸው መረጃ እንዳለው ተናገረ። የማሽኖቹ ዋጋም ሚክሰሩ እስከ 100 ሺህ ብር መጠቅጠቂያው ደግሞ 20 ሺህ ብር የሚያወጣ መሆኑን ገለፀላቸው። ዕቅድ ከማውጣት ጀምሮ የስርቆት ወንጀሉን በመሪነት ለማከናወን ያቀደው ወጣት ደምሰው፤ ከተሰረቀ በኋላ የት አቆይተው መሸጥ እንደሚችሉም ማሰብ ጀመረ።
‹‹ ማሽኖቹን ቀድሞ ሰርቆ አሳድሮ ከመሸጥ ይልቅ፤ ገዢ አዘጋጅቶ በጠዋት ሰርቆ ወዲያው በመኪና ጭኖ ገዢው ጋር ማድረስ ይቻላል። ›› ብሎ ሃሳብ አቀረበ። ተባባሪዎቹም ‹‹ምርጥ ሃሳብ ነው፤ መኪና እንዴት እናዘጋጅ?›› አሉ። ‹‹መኪናውን የተሰረቀ ዕቃ ይዞ እንደሚሔድ ሳይሆን የራሳችንን ዕቃ እንደሚወስድልን ገልፀን ባገኘነው ተሽከርካሪ ይዘን እንሂድ›› ተባብለው ተስማሙ።
ኅዳር 20 ቀን 2011 ዓ.ም
ወጣት አድማሱ እንዴት አድርገው ማሽኑን ሰርቀው ገዢው ጋር እንደሚያደርሱ እያሰላሰለ ሌሊቱን በጭንቀት አሳለፈ። ማልዶ ተነሳ፤ ጨለማው ለቆ ብርሃን ታየ። ፀሐይ መውጣት ስትጀምር ተባባሪዎቹን አሰባሰበ። ላፍቶ መስኪድ አካባቢ ተገናኙ። አንደኛው ሔዶ ተሽከርካሪ አመጣ። ወጣት አድማሱና ተባባሪዎቹ ግንባታው ቦታ ላይ ከሥራ ሰዓት ቀደም ብለው ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ላይ ደረሱ። ምንም እንዳልተፈጠረ ወደ ጊቢው ዘለቁ። ልክ ከኪራይ ከመጣበት ቦታ ለመመለስ እንደሚወስዱ አድርገው ሚክሰሩንም ሆነ ቫይብሬተሩን መኪናው ላይ ተባብረው ጫኑ። በፍጥነት ጉዞ ወደ ቦሌ ሆነ።
ማሽን ገዢው
አቶ ኑርሁሴን የግንባታ ማሽነሪዎችን ይገዛሉ፤ ይሸጣሉ፤ ለተቋራጮች ያከራያሉ። የሚገዙት፣ የሚሸጡትም ሆነ የሚያከራዩት አዲስም ሆነ አሮጌ ማሽን በመሆኑ ማንኛውም ትልቅ ካምፓኒም ሆነ አነስተኛ ተቋራጭ እርሳቸው ጋር ሄዶ ይከራያል። አንዳንዱ የቻለና የፈለገ ደግሞ ማሽኖችን ከመከራየት አልፎ ይገዛል።
አቶ ኑርሁሴን ማከራየት እና መሸጥ ብቻ ሳይሆን ‹‹የሚሸጥ ማሽን አለ። ›› ከተባለ ለመግዛት ዝግጁ ናቸው። እንደተለመደው የሲሚንቶ፣ አሸዋና ጠጠር ማቡኪያ ሚክሰርንም ሆነ የአርማታ መጠቅጠቂያ ቫይብሬተርን ለማከራየት እና አትርፎ ለመሸጥ ተወዳድረው ይገዛሉ። ጥቅም ላይ የዋለ የሚሸጥ ሚክሰር እና ቫይብሬተር መኖሩን ሰምተው ለመግዛት ዕቃውን ለማየት ኅዳር 20 ቀን 2011 ዓ.ም ሰው ቀጥረዋል።
እነአድማሱ ለአቶ ኑርሁሴን ዕቃውን ለመሸጥ በጠዋት ወደ ቦሌ ገሰገሱ። አቶ ኑር ሁሴን በበኩላቸው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ቀበሌ መዝናኛ ክበብ አካባቢ በሚገኘው የግንባታ ማሽነሪዎች መሸጫና ማከራያ ድርጅታቸው ተገኝተው የሚገዙትን ማሽን በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
ሊገዟቸው የመጡላቸውን ማሽነሪዎች ሲያዩ ግራ ተጋቡ፤ ነገር ግን እንዳይታወቅባቸው ተጠንቅቀው እነአድማሱ ዕቃውን አውርደው ዋጋውን እንዲደራደሩ ጋበዟቸው። እነአድማሱ በደስታ ወደ ድርጅቱ ገቡ። አቶ ኑርሁሴን አሁን እንዲገዙ የመጡላቸው ማሽኖች ራሳቸው ለፓወር ቻይና ኩባንያ ማከራየታቸውን አልተጠራጠሩም። የገዛ ዕቃቸው ለሽያጭ መምጣቱ ሳቅ ሳቅ እንዲላቸው አስገድዷቸዋል። ስልክ ለመደወል ወደ ቢሯቸው ውስጥ ሲገቡ፤ አድማሱ በበኩሉ ተባባሪዎቹን እርሱ የሽያጩን ጉዳይ እንደሚጨርስ አሳምኖ ሸኛቸው።
አቶ ኑርሁሴን ተረጋግተው ወደ ካምፓኒው ስልክ ደወሉ። እርሳቸው ያከራዩት ዕቃ እንዲገዙት የመጣላቸው መሆኑን ገለፁ። ቀጥለው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ደወሉ፤ በቅርብ በሥራ ላይ የነበሩ ፖሊሶች ተላኩላቸው።
ወጣት አድማሱ ማሽኑን ሽጦ ገንዘቡን ባንክ ለመጨመር እና የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ ጓጉቷል። አቶ ኑርሁሴን የዕቃው ባለቤት ይሆናሉ ብሎ ፍፁም አልገመተም። እርሳቸውም ደህና አድርገው አዘናግተውታል።
ጥሪ የደረሳቸው ፖሊሶች ወደ ድርጅቱ ሲገቡ፤ ወጣት አድማሱ የሚገባበት ጠፋው። ለማምለጥ አልሞከረም። ሁለቱንም እጆቹን ዘርግቶ ለመታሰር አዘጋጀ። ፖሊሶቹ ተጠርጣሪ አድማሱን እና የማሽኖቹ ባለንብረት ነኝ ያሉትን አቶ ኑርሁሴንን ይዘው ወደ ላፍቶ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አመሩ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ተጠርጣሪ አድማሱ ላይ ምርመራ ማካሔድ ጀመረ። ፓወር የተሰኘው የቻይና ካምፓኒ ከአቶ ኑርሁሴን ማሽኖቹን እንደተከራየ ተረጋገጠ። አቶ ኑርሁሴን የማሽኖቹ ባለቤት ስለመሆናቸው ማረጋገጫ አቀረቡ። ለጊዜው ካልተያዙ ግለሰቦች ጋር በመተባበር ተጠርጣሪ አድማሱ አብረሃም ስርቆት መፈፀሙን ፖሊስ ባካሔደው ምርመራ አረጋገጠ። ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጦ የክስ መከላከያውን እንዲያቀርብ ዕድል ሰጠው። ሆኖም ተከሳሹ አድማሱ ስለወንጀሉ ፈጽሞ አላስተባበለም። ተጠርጣሪው ስርቆቱን እንደፈፀመ አመነ።
ውሳኔ
በበቂ ማስረጃዎችና መረጃዎች ተጠናክሮ የቀረበለትን ክስ ሲመረምር የቆየው የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ምድብ ችሎት በተከሳሹ ላይ የመጨረሻውን ፍርድ ለማሳለፍ በቀጠሮ ተገኘ፡፡ ፍርድ ቤቱ በዕለቱ በሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ተጠርጣሪ አድማሱ አብረሃም ስርቆቱን እንደፈፀመ የሚያመላክቱ መረጃዎች በበቂ መጠን በመገኘታቸው፤ በጥር 8 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተጠርጣሪ አድማሱ አብረሃም ያለማንም አነሳሽነት ሆን ብሎ ራሱ የስርቆት ወንጀሉን በማቀናበር ድርጊቱን በመፈፀሙ በ5 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ አሳለፈ፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2015