ዲሞክራሲ ያግባባል የሚሉ የመኖራቸውን ያህል፤ በፍጹም የሚሉትም ብዙ ናቸው። ዲሞክራሲ የግል ነው (በሃገር ደረጃ ማለት ነው) የሚሉ የመኖራቸውንም ያህል፤ አይደለም፣ ዲሞክራሲ የጋራ ነው የሚሉ ወገኖች በተቃርኖ ቆመው ሲፋለሙ ማየት ከተጀመረ ጊዜው ቆየ። ለዚህ ደግሞ ማሳያው ”ምሥራቁ ዓለም” እና ”ምዕራቡ ዓለም” የሚሉት፣ ከተራ አቅጣጫ አመልካችነት የዘለሉት ፅንሰ ሀሳቦች ናቸው።
የ”ምሥራቁ ዓለም” እና ”ምዕራቡ አለም” ንትርክ የቆየ ነው። በቆይታውም አባልቷቸዋል፤ አጨራርሷቸዋልም። ”ሁለቱ ዝሆኖች …” እንደሚባለው ሁሉ በመሐል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንጹሐን ተቀጥፈዋል። በተለይ አፍሪካ ፍዳዋን አይታለች። ዝርዝሩ የትየለሌ ነው። በርዕሳችን ለመጠቆም እንደ ሞከርነው፣ ዲሞክራሲን የተመለከተው የአሁኑ ዘመን ክርክር ፈርጀ ብዙ ነው።
አንደኛው፣ በተለይ ምሥራቁ ክፍል ”ዲሞክራሲን በተግባር” (Democracy In Action) ሲል፤ ምዕራቡ ዓለም ግን ዲሞክራሲን አየር ላይ አንጠልጥሎ፣ ከሰብዓዊ መብቶች ጋር አጣብቆ፣ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ዘንግቶ …. የራሱን መሬት ያልረገጠ ብያኔ ሲሰጥ ይታያል። ለዚህ ደግሞ ማስረጃው የሰሞኑ የአሜሪካና ቻይና እሰጥ አገባ ነው።
እንደ ”የቻይና ዲሞክራሲ” አራማጆች አስተያየት ትክክለኛ ዲሞክራሲ እውን እየሆነ፤ እውነተኛው ዲሞክራሲ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው 98.99 በመቶ ሕዝቧን ከከፋ ድህነትና ረሀብ በማውጣት የዓለም ኃያል ወደ መሆኑ በመጣችው ቻይና ነው። የአሜሪካው፣ ሊብራልም ይበሉት ምንም፣ በድህነት ለሚኖሩት ሃገራት ቀርቶ ለራሷም ምንም ሲያደርግላት፣ ሰላምና ደህንነቷን ሲያስጠብቅላት … አልታየም። በምትኩ እየታየ ያለው ማኅበራዊ ምስቅልቅሎሽ ነው።
የአሜሪካንን አጠቃላይ ወንጀል፣ ዘረኝነት … በተመለከተ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ሰብስቦ የያዘውንና The most dangerous city in the US has been revealed ወይም/እና 10 Most Dangerous Cities in the US እንዲሁም Revealed – America’s safest and most dangerous cities in 2022 በሚል ርዕሶች ለንባብ የበቁት፤ ከዩኤን ጀምሮ እስከ ዩኔስኮ፤ ከአምነስቲ ጀምሮ እስከ ሂዩማን ራይት ዎች …. ድረስ ያሉት ሰነዶች ሳይቀሩ የሚያረጋግጡት ይህንኑ፤ ዘረኝነት፣ አፈና … በዩኤስ አሜሪካ መንሰራፋቱን ነው።
ወንጀል (በየአይነቱ)፣ አስገድዶ መድፈር፣ በመብት መጓደል ምክንያት ራስን ማጥፋት እና የመሳሰሉት በአሜሪካ ምን ያህል እድሜ ጠገብ እንደሆኑ የሚያስረዳውን፣ የእነ Gabbidon & Greene (2005b:37) ሥራዎችንም መመልከት ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ፣ አሁንም ድረስ አሜሪካ ሌላውን ዓለም አፍኖ ለመያዝ የምትጠቀመው ”ሰብዓዊ መብት ጥሰት” የሚለው ነው።
አሁን አሁን በተከታያይ እየወጡ ያሉት መረጃዎች እንደሚያሳዩት አሜሪካ አንድም ጊዜ (በተለይም ለሌላው ዓለም) ከወረቀት በዘለለ፣ ከሀሳባዊ፣ ቃለ-ነቢብነት ባለፈ ዲሞክራት ሆና አታውቅም። ከላይ ከጠቀስናቸውና ሌሎች በርካታ ሥራዎች መረዳት እንደሚቻለው ዘርን መሠረት ያደረገ ግጭት፣ አድልኦ፣ ድህነት፣ ቀለምን መሠረት ያደረገ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ ነጮችን ወደ ብልፅግና ጥቁሮችን ወደ ወንጀል የሚመራ ስር የሰደደ (redlining ይሉታል)ና አግላይ አሠራር ለአሜሪካ የታከተና የሰለቸ እንጂ ብርቅ አሠራር አይደለም። ”በመሆኑም” ይላሉ ተቺዎቹ ”የአሜሪካ ዲሞክራሲ እንኳን ለሌላው ሊተርፍ ለራሱም ያልሆነ አፍአዊ ነው።”
ጉዳዩን የበለጠ ግልፅ ለማድረግ በሁለቱ፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እርስ በእርስ ለሚገሸላለጡት፣ በተያዩ ቁጥር ሳንጃ የሚሞሻለቁት (እስካሁን ባይዋጉም)፣ ባገኙት መድረክ ሁሉ የሚዛዛቱትን፣ በአሜሪካና ቻይና መካከል ያለውን ልዩነት እንመልከት።
ዲሞክራሲ ለአሜሪካ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዓለምን የመቆጣጠሪያ ስልት ነው፤ ተኩሶ መጣያ ሽጉጥ ነው። ለቻይና ደግሞ የሕልውና፣ የመኖር አለመኖር፣ በልቶ የማደርና አለማደር ጉዳይ ነው። የቻይና ዲሞክራሲ ለአሜሪካ አፋኝ ነው። የአሜሪካ ዲሞክራሲ ለቻይና የውሸት (ሲውዶ-ዲሞክራሲ) ነው፤ የአንድ ወገን የበላይነትን ማስቀጠያና የቀረውን አለም መጨቆኛ መሣሪያ ነው።
የቻይና ሰብዓዊ መብት አያያዝ ለአሜሪካ የሚዋጥ አይደለም። ”ምክንያት?” ስትባል የቻይና ሕዝብ ታፍኗል ነው መልሷ። የአሜሪካ አስተዳደር ለቻይና ”ጋንግ-ባዝድ ሩል” (የጡንቻ) ሥርዓት ሲሆን፤ የቻይና አስተዳደር ለቻይና ”ሩል- ባዝድ ሲስተም” (ሕግ መራሽ) ሥርዓት ነው። በመርሕ ደረጃም እንዲሁ ነው፤ ልዩነታቸው እስከ ወዲያኛው የሚያቀራርባቸው ሁሉ አይመስልም።
የአሜሪካ መርሕ፣ ማለትም አሜሪካ የምትከተለው መርሕ ለቻይና የአምባገነንት መርሕን ሲሆን፤ ቻይና የምትከተለው መርሕ ለአሜሪካ ዘመናዊ ቅኝ አገዛዝ (በተለይ በአፍሪካ) ነው። ሁለቱም እንደ መርሕ እንከተለዋለን የሚሉት ግን አላቸው፤ ቻይና መርሄ ”ቅድሚያ ሰው” (People-First Deplomacy) የሚል ነው፤ የመንግሥት ተግባራት በሙሉ (በዓለም አቀፍ ደረጃ) ለሰዎች ቅድሚያ የሚሰጡና ካሉበት ችግር የሚያወጡ፤ ለእኩል እኩልነት የሚሠሩ መሆን አለባቸው የሚል ነው ።
አሜሪካ ደግሞ ”ዲሞክራሲ ያለገደብ ሊከበር ይገባል” በሚል ፈሊጥ ዓለምን ማተራመስ ነው ” ዓለም አቀፍ ግንኙነትን በተመለከተም ልዩነታቸው በቀላሉ የሚታረቅ የአይደለም። ምክንያቱ ደግሞ የአንድ ሃገር (ወገን) የበላይነት በቻይናም ይሁን በሩሲያ (አሁን አፍሪካንም እየጨመረ ይገኛል) ተቀባይነት ስለሌለው ነው።
የእድገት መርሐቸውም የማይገናኝ ሲሆን፣ አሜሪካ በእርዳታ ላይ ስትመሠረት ቻይና ደግሞ አብሮ ማደግ ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ ደግሞ፣ እንደ ብዙዎቹ አስተያየት ቻይና በቀላሉ አፍሪካውያን ልብ ውስጥ እንድትገባ ረድቷቷል።
ቻይና ዓለም አቀፍ ግንኙነቴ በእኩያነትና አካታችነት (መልቲላተራሊዝም) ላይ የተመሠረተ ነው ስትል፤ አሜሪካ ደግሞ ዓለም አቀፍ ግንኙነቴ የውጪ ፖሊሲዬ ላይ የሰፈረው ነው ባይ ነች። ለዚህ የአሜሪካ አቋም የፑቲን መልስ ደግሞ ለየት የሚል ሲሆን፤ እሱም ”የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ የአሜሪካ እንጂ የዓለም የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ አይደለም” የሚል ነው።
የቻይናና ሩሲያን ወዳጅነት እንደ አሜሪካ ጠላትነት የሚቆጥረው የባይደን አስተዳደር ዓለምን ሊመራና ሊቆጣጠር የሚገባው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንጂ ሌላ ሊሆን አይገባም ባይ ነው ።
እንደ ሁለቱ፣ በተለይም እንደ ቻይና አተያይና አቋም ግን ዓለምን ሊመራ የሚገባው፤ ዓለምም ሊገዛለት የሚገባው ሕግ ቢኖር አንድ ሲሆን፣ እሱም የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ብቻ ነው። በቃ፣ እሱና እሱ እንጂ የአሜሪካ ምኗም ሆነ ምኗ የራሷ እንጂ ለሌላው ዓለም ሊሆንም ሆነ ሊተርፍ የሚችለው ነገር የለውም።
እንደሚታወቀው፣ ዲሞክራሲ ፈርጁም ሆነ ቅርንጫፉ፤ ብያኔውም ሆነ ዓይነቱ ብዙ ነው። በተለይ በአካዳሚው መስክ ከተመለከትነው ስለ ዲሞክራሲ ያልተባለ የለም። በእስከዛሬው ሂደትም የአሜሪካና አውሮፓ ዴሞክራሲ እንደ ሞዴል ተወስዶ አርአያነቱ ሲጠቀስ ነው የኖረው።
ይሁን እንጂ የጊዜ ጉዳይ ሆኖም ይሁን ሌላ፣ ይህ ”ሞዴል ዲሞክራሲ” አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። እንደውም እንደ አንዳንዶቹ አተያይ ገና ድሮ አልቆለታል። አሁን ያለው ሁኔታ የአሜሪካ ቀስት ወደ ታች፤ የምሥራቁ ዓለም (በተለይ የሩሲያና ቻይና) ቀስት ወደ ላይ የሚያሳይበት የሽግግር ወቅት ነው። ይህ እንዳይሆን ከተፈለገ አሜሪካ አንድ እድል ብቻ አላት፤ የበላይነትን አስወግዳ ከቀረው ዓለም ጋር በእኩልነት መኖርን መቀበል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም