የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች ቁጥር ከቀጣዩ የፈረንጆች አዲስ አመት ጀምሮ በሃያ አንድ እንደሚያድግ ታውቋል። የዓለም አትሌቲክስ በየአመቱ በተለያዩ የዓለማችን ከተሞች ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች መካከል ከቤት ውጪ እንደ ዳይመንድሊግና የጎዳና ላይ ውድድሮች ተጠቃሽ ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የቤት ውስጥ ውድድሮችን የበለጠ በማነቃቃት ለሜዳ ተግባራት፣ ለአጭርና መካከለኛ ርቀት አትሌቶች የውድድር እድሎችን በማስፋት የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮችን በተለያዩ ከተሞች እያካሄደ ይገኛል። በዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የዓለማችን አትሌቶች ተጠቃሚ እየሆኑና ራሳቸውን በትልቅ መድረክ የማሳየት እድል እያገኙ ነው።
የዓለም አትሌቲክስ ይህን የቤት ውስጥ የዙር ውድድር የበለጠ በማስፋትም ከመጪው 2023 ጀምሮ ሃያ አንድ ተጨማሪ ውድድሮችን እንደሚያካሂድ አሳውቋል። ይህም በአጠቃላይ በአመት የሚያካሂዳቸውን ውድድሮች ቁጥር ወደ ሃምሳ አራት አሳድጎታል።
መካሄድ ከጀመረ ስምንተኛ አመቱን በመጪው 2023 የሚይዘው የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድር ውስጥ በሰባት ከተሞች የሚካሄዱ ውድድሮች የወርቅ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል። የመጀመሪያው የዙር ውድድርም በመጪው ጥር መጨረሻ በጀርመን ካርልሹ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እድገት እያሳየ ይገኛል። በ2020 ሰባት ውድድሮች ይካሄዱ የነበረ ሲሆን በ2021 ወደ ሃያ አራት ማደግ ችሏል። በ2022 ደግሞ ሰላሳ ሦስት ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን በ2023 ወደ ሃምሳ አራት ማደግ ችሏል።
የውድድሮቹ ቁጥር መጨመር ፉክክሮችን የሚያስተናግዱ በርካታ የዓለም ከተሞችን በስፋት ተደራሽ እንደሚያደርግ የዓለም አትሌቲክስ ገልጿል። በዚህም አስራ ዘጠኝ የተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ውድድሩን እንደሚያስተናግዱ የተገለጸ ሲሆን ቀሪዎቹን ውድድሮች ደግሞ የደቡብ አሜሪካና ኤሽያ ከተሞች እንደሚያስተናግዱ ታውቋል።
በ2023 የውድድር አመት የወርቅ ደረጃ ከተሰጣቸው ውድድሮች በተጨማሪ የብርና የነሐስ ደረጃ የተሰጣቸው በርካታ ውድድሮችም በተለያዩ ከተሞች ይካሄዳሉ። በነዚህ ውድድሮች ፉክክር የሚደረግባቸው ርቀቶችም የሚሰጣቸው ደረጃ በየአመቱ እንደሚቀያየር ተጠቁሟል።
በ2023 የውድድር አመት በተለያዩ ከተሞች ውድድሮች ሲካሄዱ የወርቅ ደረጃ ከተሰጣቸው ርቀቶች መካከል የሴቶች ስልሳ ሜትር፣ስምንት መቶ፣ ሦስት ሺና አምስት ሺ ሜትሮች ይገኙበታል። በተመሳሳይ በሴቶች ምርኩዝ ዝላይ፣ ስሉስ ዝላይና አሎሎ ውርወራ ውድድሮችም በወርቅ ደረጃ እንደሚካሄዱ ታውቋል። በወንዶች መካከልም አራት መቶ፣ አንድ ሺ አምስት መቶ፣ ስልሳ ሜትር መሰናክል፣ ከፍታ ዝላይና ርዝመት ዝላይ በወርቅ ደረጃ ይካሄዳሉ።
በነዚህ ውድድሮች አትሌቶች ከተካፈሉባቸው ፉክክሮች ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡባቸው ሦስት ውድድሮች ተመርጠው ከተወዳደሩ በኋላ በአጠቃላይ ነጥብ ብልጫ ያገኘ አትሌት አሸናፊ ይሆናል። ለዚህም የአስር ሺ ዶላር ሽልማትና ከአስር ሺ በላይ ዩሮ ጉርሻ ተዘጋጅቶለታል።
የአጠቃላይ የዙር ውድድሩ አሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማት እንዳለ ሆኖ በእያንዳንዱ የወርቅ ደረጃ ባለው ፉክክር ቢያንስ ሰባት ሺ ዶላር ሽልማት እንደ አጠቃላይ የተዘጋጀ ሲሆን አሸናፊ የሚሆን አትሌትም እስከ ሦስት ሺ ዶላር የሚያገኝ ይሆናል።
የብር ደረጃ በተሰጣቸው ውድድሮች በአጠቃላይ ከአርባ ሺ ዶላር በላይ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ፉክክር አሸናፊ የሚሆን አትሌት ቢያንስ አራት ሺ ዶላር ተሸላሚ ይሆናል። የነሐስ ደረጃ በተሰጣቸው እያንዳንዱ ውድድሮች ደግሞ አጠቃላይ ከአስራ ሁለት ሺ ዶላር በላይ ሽልማት የቀረበ ሲሆን ለአንድ ውድድር አሸናፊ አትሌት ሁለት ሺ አምስት መቶ ዶላር ሽልማት ይበረከታል።
በተለያዩ የውድድር ዓይነቶች አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች ከገንዘብ ሽልማት በተጨማሪ በ2024 ግላስጎ በሚካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በቀጥታ ተሳታፊ መሆኑን ያረጋግጣል።
የወርቅ ደረጃ ያላቸውን ውድድሮች የሚያስተናግዱት ከተሞች የጀርመኗ ካርልሹ ቀዳሚ ናት። በአሜሪካ ቦስተንና ኒውዮርክ፣ በፈረንሳይ ሌቪን፣ በስፔን ማድሪድ፣ በፖላንድ ቶረንና በእንግሊዝ በርሚንግሃም የሚካሄዱ ፉክክሮች የወርቅ ደረጃ የተሰጣቸው ሆነዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2015