በዓለማችን ታላላቅ ከተሞች በየአመቱ ከሚካሄዱ የማራቶን ውድድሮች አንዱ የሆነው የፍራንክፈርት ማራቶን በመጪው እሁድ ይካሄዳል። በጀርመኗ ከተማ ፍራንክፈርት የሚካሄደው ይህ ውድድር በኮቪድ-19 ስጋት ባለፉት ሁለት አመታት ሳይካሄድ ቆይቶ ዘንድሮ ሲመለስ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደሚሳተፉ ታውቋል።
በወንዶች መካከል በሚካሄደው ውድድር ርቀቱን ከ2:10 በታች ማጠናቀቅ የቻሉ ዘጠኝ አትሌቶች ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በተመሳሳይ በሴቶች መካከል በሚካሄደው ፉክክርም ርቀቱን ከ2:25 በታች ማጠናቀቅ የቻሉ ስምንት አትሌቶች እንደሚሳተፉ የውድድሩ አዘጋጆች ገልጸዋል።
በወንዶች መካከል በሚካሄደው ፉክክር ሁለት ወጣት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተለየ ብቃት እንደሚያሳዩ ተስፋ የተጣለባቸው ሲሆን፣ ፈጣን ሰዓት በሚመዘገብበት በዚህ ውድድር የቦታውን ክብረወሰን እንደሚያሻሽሉ ይጠበቃል። በተለይም የሃያ አራት አመቱ ኢትዮጵያዊ አትሌት በተስፋ ጌታሁን ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ በ2019 አምስተርዳም ላይ ሮጦ 2:05:28 የሆነ የራሱን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ችሏል። ይህ አትሌት በዘንድሮው የፍራንክፈርት ማራቶን ከሚሳተፉ አትሌቶች ሁሉ የመጀመሪያ ፈጣን ሰዓት ያለው ነው። ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት የያዘው ሌላኛው የሃያ ሁለት አመት አትሌት ገብሩ ረዳኸኝ በተመሳሳይ ባለፈው ግንቦት ባርሴሎና ላይ 2:05:58 ማስመዝገብ የቻለ ጠንካራ አትሌት በመሆኑ ትልቅ የአሸናፊነት ግምት ሊሰጠው ችሏል።
ሁለቱ ወጣት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በፍራንክፈርት አዲስ የማራቶን ታሪክ የመጻፍ ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነ አዘጋጆቹ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ከሁለቱ አትሌቶች በተጨማሪ በውድድሩ ሁለት ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኬንያዊው አትሌት ማርቲን ኮስጌ ጠንካራ ተፎካካሪ ከመሆን ባለፈ ለአሸናፊነት ግምት ከሚሰጣቸው ጠንካራ አትሌቶች ዋነኛው ነው። ይህ አትሌት በ2016 እና 2018 ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ የቻለ ሲሆን 2017 ላይ ደግሞ አራተኛ ደረጃን ይዞ እንደጨረሰ ይታወቃል። በ2018 ውድድሩም ላይ 2:06:41 የሆነ የራሱን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል። ሌላው ኢትዮጵያዊ አትሌት ደሬ ኡልፋታ በ2:08:42 ሰዓት ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። አትሌት አሸናፊ ገብሩም የመጀመሪያውን የማራቶን ውድድር እንደሚያደርግ ታውቋል።
በሴቶች መካከል በሚካሄደው ውድድር ማራቶንን ከ2:25 በታች ማጠናቀቅ የቻሉ በርካታ አትሌቶች ሲሳተፉ የዘንድሮው ሁለተኛው ነው። ከዚህ ቀደም በ2018 አስር ያህል አትሌቶች ከ2:25 በታች ሰዓት ይዘው አስደናቂ ፉክክር አሳይተዋል። ዘንድሮ ደግሞ ስምንት ያህል አትሌቶች ይህን ሰዓት ይዘው የሚያደርጉት ፉክክር ተጠባቂ ነው። ኬንያዊቷ አትሌት ሳሊ ካፕቲች በቀዳሚነት የሚጠቀሰው 2:21:09 ሰዓት ያስመዘገበች ጠንካራ አትሌት ስትሆን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የሺ ቸኮል በ2:21:17 የሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት ሆና ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም እኤአ በ2015 የቤጂንግ የዓለም ቻምፒዮና አሸናፊ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ማሬ ዲባባን ተከትላ በሁለተኝነት ያጠናቀቀችው ኬንያዊቷ ሄላህ ኪፕሮፕ በ2:21:27 ሦስተኛውን ፈጣን ሰዓት ይዛ ትፎካከራለች። አታለል አንሙት፣ዝናሽ ለማና መሠረት አበባየሁ የተባሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በውድድሩ ተፎካካሪ ይሆናሉ።
ለሰላሳ ዘጠነኛ ጊዜ በመጪው እሁድ በሚካሄደው የፍራንክፈርት ማራቶን ከአስራ ሁለት እስከ ሃያ ሺ ተሳታፊዎች የጀርመኗን ከተማ እንደሚያደምቁ ታውቋል። «በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ከሁለት አመት ቆይታ በኋላ ውድድሩ ሲመለስ በማራቶን ጠንካራ አትሌቶችን አካቶ ነው፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ለተሳታፊዎችም ውድድሩ አስደናቂ ይሆናል፣ ያለፉት አመታት የውድድሩን ባህል በማስቀጠልም የፍራንክፈርት ማራቶንን ዳግም ታላቅ የማድረግ ጥረታችን ይቀጥላል» በማለት የውድድሩ ዳይሬክተር ጆ ሺንድለር ለመገናኛ ብዙኃን አስተያየት ሰጥተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2015