የቴሌቭዥን ቻናሎችን ስቀያይር የርቀት መቆጣጠሪያው ባላገሩ ቴሌቭዥን ላይ ጣለኝ። የባላገሩ መሥራችና ባለቤት አብርሃም ወልዴ የባላገሩ ተወዳዳሪዎችን የሆነ ካምፕ የሚመስል ቦታ ውስጥ ሰብስቦ ያስተምራል። አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ስለቅዱስ ያሬድ እያወራ ነው የደረስኩት። የቴሌቭዥኑን የርቀት መቆጣጠሪያ አስቀምጬ በተመስጦ ማድመጥ ጀመርኩ። ተወዳዳሪዎችን ወደ መዝናኛ ቦታ (ደብረ ዘይት ኩሪፍቱ ሪዞርት) ወስዶ ገለጻ እያደረገላቸው ነው።
ፕሮግራሙ ከጀመረ በኋላ ስለነበር የደረስኩበት ያለፈኝን ክፍል ለመስማት በጣም ጓጓሁ። የዩትዩብ ቻናላቸው ላይ ይጭኑት ይሆን? ብየ በስስት መፈለግ ጀመርኩ፤ ሁሉንም ክፍሎች አገኘኋቸው። ስለሙዚቃ ምንነትና ታሪክ እነሆ ከባለሙያው አፍ የሰማኋቸውን ማካፈል ፈለኩ።
ሙዚቃ የሚለው ቃል ሞዚክ((mousike) ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው። አጻጻፋቸው(Spelling) የተለያየ ሊሆን ቢችልም በላቲን እና እንግሊዘኛም ቃሉ ተመሳሳይ ነው። ጥንታዊ አመጣጡ ግን ሞዚክ ከሚለው የግሪክ ቃል ነው። ትርጉሙም የድምጽ ጥበብ ማለት ነው። ሀሳብን እና ስሜትን መግለጽ ማለት ነው።
ሙዚቃን አብርሃም ወልዴ በአማርኛ ሲያብራራው ‹‹የአዕምሮን ኬሚስትሪ የሚቀይር ኃይል›› ይለዋል።
ሙዚቃ ጥበብም ሳይንስም ነው። የሒሳብ ባለሙያዎች ይስማማሉ አይስማሙም የሚለው ክርክር እንዳለ ሆኖ ‹‹ሙዚቃ የሒሳብ አባት ነው›› ይባላል። ሳይንስ ነው ማለት ነው። የራሱ ስሌቶችና ቀመሮች አሉት። በልምድ ብቻ ዘፈን የሚችሉ ሰዎች ሙዚቃን ሲማሩ ግን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ይከብዳቸዋል። በልማድ ግን ሙዚቃን ትምህርት አልሳካላቸው ያሉ ሰዎች የሚሰሩት ይመስላል፤ ግን ከባድ ሳይንስ ነው።
ሙዚቃ የሚሰራው ከድምጽ እና ከዝምታ (ፀጥታ) ነው። በሙዚቃ ውስጥ ዝምታ ከድምጽ እኩል ዋጋ አለው። በሙዚቃው መሃል ውስጥ ፀጥታው ባይኖር ረባሽ ድምጽ ነው የሚሆን።
ሙዚቃ መደበኛ እና ኢመደበኛ የሚባል አለው። መደበኛው፤ ቀደም ሲል በሸክላ እና በካሴት አሁን ደግሞ በሲዲ እና በተለያዩ ማጫወቻዎች በስቱዲዮ የተሰሩ መደበኛ ሙዚቃዎች ማለት ነው። ኢመደበኛ የሚባሉት ደግሞ በስሜት የምናንጎራጉረው ማለት ነው። በሰርግ እና በለቅሶ፣ እንዲሁም በተለያየ ሥራ ላይ ሆነን የሚዜሙት ማለት ነው። እነዚህ ዘፈኖች አንዳንድ ጊዜ በመደበኛ ዘፈኖች ሊዘፈኑ ይችላሉ። ለምሳሌ የእነ ፈረደ ጎላ፣ ሽሽግ ቸኮል፣ ንጋቷ ከልካይ፣ ካሳ ተሰማ፣ አሰፋ አባተ፣ ባህሩ ቃኜ የመሳሰሉት ዘፋኞች ከኢመደበኛ ዘፈኖች ተነስተው የዘፈኑ ናቸው። ኢመደበኛ ሙዚቃዎች በጭብጨባ የታጀቡ ነበሩ።
በመደበኛው ሙዚቃ ዘፈን የተጀመረው በእነ ጥላሁን ገሰሰ፣ መሀሙድ አህመድ፣ አስቴር አወቀ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ምኒልክ ወስናቸው…. የመሳሰሉት መደበኛ የሚባለውን የጀመሩ ናቸው።
አብርሃም እንደሚለው፤ መደበኛ የሚባለው ዘመናዊ (ኦርኬስትሬሽን) የተጀመረበት ስለሆነ ነው። ልጅ ሆነው ኢመደበኛውን ዘፍነው ይሆናል (የአሁን ወጣቶችም ኢመደበኛ ይዘፍናሉ)፤ ግን በአሁኑ የሙዚቃ ዓለም መደበኛ የሚባለው የኦርኬስትሬሽን ፎርም የያዘው ነው።
ሙዚቃ ከምን ይሰራል?
ከመሳሪያ አንፃር ሙዚቃ ከምን ይሰራል ከተባለ፤ ከክር፣ ከትንፋሽ እና ከምት ነው። የክር መስሪያ ማለት በንዝረት የሚመጣ ነው። መሳሪያዎቹም ከጅማት፣ ከጭራ(የፈረስ) እና ከሌሎች ንዝረት ከሚፈጥሩ ክሮች የሚሰራ ነው። ለምሳሌ፤ በገና፣ ክራር፣ መስንቆ፣ ዲታ፣ ዱል፣ የመሳሰሉት ናቸው። ዲታ እና ዱል ጋምቤላ እና ሲዳማ አካባቢዎች የሚታወቁ ናቸው።
የትንፋሽ መሳሪያዎች ደግሞ ዋሽንት፣ እምቢልታ፣ መለከት፣ ድንኬ(ሲዳማ ውስጥ)፣ ፓሬረሳ፣ ሁራ፣ ሁልዱዱዋ፣ ጨቸዝያ (ጋሞ ውስጥ)፣ ዛክ(ከፋ)፣ ፋንፋ፣ አኮርዲዮን፣ የመሳሰሉት ናቸው።
የምት የሙዚቃ መሳሪያዎች፤ ከበሮ፣ አታሞ፣ ነጋሪት፣ መቋሚያ፣ ጸናጽል፣ ቅል፣ ቻንቻ፣ የመሳሰሉት ይካተታሉ።
ቅኝት (Scale)
አራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች በመባል የሚታወቁት፤
ትዝታ፣ ባቲ፣ አንቺ ሆዬ እና አምባሰል ናቸው። እነዚህ የቅኝት አይነቶች በእነዚህ ስያሜዎች የተጠሩበት ምክንያት ቅኝቶቹ ታዋቂ በሆኑባቸው ዘፈኖች ነው።
ትዝታ የሚባለው ቅኝት የትዝታ ዜማዎችን ስለሚይዝ በዚሁ ተሰየመ። ቅኝቱ መጀመሪያ ነው የመጣ፤ ያኔ ስም አልነበረውም። የትዝታ ስሜት ቀስቃሽ ሆኖ ሲገኝ ግን ትዝታ ተባለ። ባቲ ደግሞ ‹‹ባቲ›› በሚለው የጥንት ዘፈን ነው። አንቺ ሆዬም ‹‹አንቺ ሆዬ ለኔ›› በሚለው ዘፈን ነው። አምባሰልም ‹‹አምባሰል›› በሚለው ዘፈን ነው።
ከአራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ‹‹መንዙማ ቅኝት›› የሚባል አምስተኛ ቅኝት ይሆናል እየተባለ ነው።
ሙዚቃ እና ትምህርት (ቅዱስ ያሬድ)
ዘመናዊ የሚባለው የሙዚቃ ትምህርት የውጭውን ዓለም መሰረት ያደረገ ነው። በተለይም ምዕራባውያን በሰፊው ሰርተውበታል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ኢትዮጵያዊውን ቅዱስ ያሬድ ስሙን ማንሳት አይፈልጉም። ለእነርሱ የዓለም የሙዚቃ ጀማሪዎች እነ ሰባቲያን፣ ባክ፣ ቤትኦቨን ናቸው። እነዚህን ሰዎች የሙዚቃን ኖታ የጻፉ ናቸው በማለት ልክ እንደ ሙዚቃ ፈጣሪ ነው የሚተርኩላቸው።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ስለኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ ምንም ማለት አይፈልጉም። የሚገርመው ግን እነዚህ የእነርሱ ሰዎች የተፈጠሩት ቅዱስ ያሬድ የሙዚቃ ኖታዎችን ከሠራ ከአንድ ሺህ 500 ዓመታት በኋላ ነው። የዓለም ስመ ገናና የሆነው ሞዛርት የተወለደው ከቅዱስ ያሬድ ከአንድ ሺህ 243 ዓመታት በኋላ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (1748 ዓ.ም) ነው። ቤትኦቨን የተወለደው ከቅዱስ ያሬድ አንድ ሺህ 258 ዓመታት በኋላ በ1763 ዓ.ም ነው።
አውሮፓውያን የዓለም የሙዚቃ ፈጣሪ በሚሏቸው እና በኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ መካከል በሺህ የሚቆጠሩ ዘመናት ልዩነት አለ። ስለቅዱስ ያሬድ ግን ምንም ማለት አይፈልጉም።
በነገራችን ላይ የአብርሃም ወለዴን ማብራሪያ እንደሰማሁ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በተመለከተ በፈረንጆች የተሰሩ ጥናቶች ካሉ ብየ የበይነ መረቡን ዓለም ማሰስ ጀምሬ ነበር። ‹‹Some aspects of indigenous Ethiopian music, Ecclesiastical and Secular›› በሚል ርዕስ የተሰራ ጥናት አገኘሁ። የኢትዮጵያ ሙዚቃ መነሻው ከሃይማኖት ጋር የተገናኘ መሆኑን ይገልጻል። በነገራችን ላይ የእነ ሞዛርትም እንደዚሁ ነው፤ መነሻቸው ሃይማኖት ነበር።
በጥናቶቻቸው ላይ ግን የምንታዘበው ነገር በራሳቸው ዘመናዊ ሙዚቃዎች ነው የሚገልጹት። ክራሩን፣ ዋሽንቱን፣ ከበሮውን… በራሱ ከማብራራት ይልቅ ወደ እነርሱ ያጠጋጉና ከእነርሱ የተኮረጀ ለማስመሰል ይሞክራሉ። እውነታው ግን እነዚህ የኢትዮጵያ የባህል የሙዚቃ መሳሪያዎ ለሺህ ዘመናት የኖሩ እና ፈጣሪዎቻቸውም የአውሮፓን ዘመናዊ መሳሪያዎች የማያውቁ መሆናቸው ነው።
የፈረንጆችን ጥናቶች ትዝብት በሌላ ጽሑፍ የምመለስበት ይሆናል፤ አሁን ወደ አብረሃም ወልዴ ማብራሪያ ልሂድ።
በ505 ዓ.ም የተወለደው ቅዱስ ያሬድ የዜማ ምልክቶችን ፈጥሯል። የራሱ የሙዚቃ ኖት ሰርቷል። ሦስቱ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ክፍሎች የሚባሉትም፤ ግዕዝ፣ ዕዝል እና አራራይ ናቸው።
የዜማ አይነቶች የሚባሉት ደግሞ፤ ድጓ፣ ጾም ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬ እና መዋስዕት ናቸው። ለእነዚህ ዜማዎችም ምልክቶች አሏቸው። የዜማ ምልክቶች የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው።
ድፋት፣ ደረት፣ ቅናት፣ ጭረት፣ ርክርክ፣ ይዘት፣ ሂደት፣ ቁርጥ፣ ድርስ እና አንብር የሚባሉት ናቸው። የየራሳቸው ቅርጽ ያላቸው ምልክቶች አሏቸው። አንድ ዜመኛ እነዚያን ምልክቶች እያየ ዜማውን ምን ማድረግ እንዳለበት ያስባል ማለት ነው።
ከቅዱስ ያሬድ በፊት (ከ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ማለት ነው) የነበረ ሰው እስካልተገኘ ድረስ የዓለም የሙዚቃ ጀማሪ የሚሆነው ቅዱስ ያሬድ ነው። ግን ማንም አውሮፓዊ ይህ እንድሆን አይፈልግም። የብዙ ነገሮች መነሻና ጀማሪ እነርሱ እንደሆኑ ተደርጎ ነው የሚተረክ። ይህ የበላይነት ሞራል ደግሞ የምርም ጠቅሟቸዋል። በትርክት የጀመሩት የበላይነት የኢኮኖሚም የሥልጣኔም የበላይ እንድሆኑ እያደረጋቸው ነው።
ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ብዙ ታዳጊ አገራት በራሳቸው የማይተማመኑ ሆነዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ቅዱስ ያሬድ ማን እንደሆነ የማያውቅ ይኖራል፤ ይሄው ኢትዮጵያዊ ግን ስለእነ ሞዛርት እና ቤትኦቨን ሙሉ ታሪክ ሊነግረን ይችላል። እነ ሽሽግ ቸኮል፣ ንጋቷ ከልካይ፣ ካሳ ተሰማ፣ ጌታመሳይ አበበ….. የመሳሰሉት በአሁን ወጣቶች ብዙም የሚታወቁ አይደሉም፤ ከዚያ ይልቅ የምዕራባውያን ዘፋኞችን የቀለምና የምግብ ምርጫ ሁሉ ሳይቀር መተንተን እንደ ዘመናዊነት የሚያስቆጥር ሆኗል።
ይህ ሁሉ ለምን ሆነ ከተባለ ለራሳችን ዋጋ ስለማንሰጥ ነው። ምዕራባውያን ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት
በጦርነት እና በድርቅ ጊዜ ከታዳጊ አገራት የሚያነሷቸውን ፎቶዎች በማሳየት ነው። ‹‹ተመልከቱ የእኛንና የእነርሱን ልዩነት›› እያሉ ነው። ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ፎቶ የሚያነሱት እና ዘጋቢ ፊልም የሚሰሩት ምን ላይ እንደሆነ ግልጽ ነው። የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን የሳይንስ ሙዚየማችን ላይ ወይም ጎርጎራ ፕሮጀክት ላይ ዘጋቢ ፊልም ሊሰሩ አይችሉም።
የሙዚቃ እና ሌሎች የጥበብ ሥራዎቻችንም እንዲህ ነው በራሳችን ድክመት ዓለም አቀፍ ዝና እንዳያገኙ ያደርግናቸው። በቀጣይ እንዲያውም አስፈሪው ነገር የሙዚየም ታሪክ እንዳይሆኑ ነው። አንዳንድ የሬዲዮ ጣቢያዎች (ፋና እና ኤፍ ኤም አዲስ 97.1) ላይ ካልሆነ በስተቀር የድሮ ዘፈኖች ብዙም አይሰሙም።
አብርሃም እንደሚለው፤ የእነ ቅዱስ ያሬድ ሙዚቃ ጀማሪነት ከተነገረ እነ ቤትኦቨን ይደበዝዛሉ። ስለዚህ በተቻለ መጠን ‹‹ቅዱስ ያሬድ ደግሞ ማነው!›› እንድባል ነው የሚፈልጉት። ኢትዮጵያዊ የሆነ ነገር እንድጎላ አይፈለግም። የራሱ የአብርሃም ወለዴን ገጠመኝ እዚሁ ላይ ልጥቀስ።
ከአንድ የውጭ አገር መምህሩ ጋር ብዙ ጊዜ ይጨቃጨቅ ነበር። ድርሰት ጻፉ ተብሎ አብርሃም ስለ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ መጻፍ ፈለገ። መምህሩ አልፈቀደለትም። ስለ ሉሲ ወይም ስለ ዓባይ መጻፍ ፈለገ። በእነርሱም ሊስማማ አልቻለም። ‹‹እነዚህ አንተ የምትፈጥራቸው ታሪኮች ናቸው፤ ማን ያውቃቸዋል? ስለሚታወቁ ነገሮች ጻፍ›› አለው። የሚታወቁ ማለት እንግዲህ የግድ ነጭ የሆነ ማለት ነው።
ይህ መምህር ከልጅነቱ ጀምሮ ያደገው የሌላ አገር ነገር ትንሽ እንደሆነ ተደርጎ ነው። ስነ ልቦናው ከራሳቸው ሰዎች ውጭ ያለውን አይቀልም። ስለዚህ ለራሳችን ክብር መስጠት አለብን።
የባህል ሙዚቃ አጀማመር፣ የዘመናዊ ሙዚቃ አጀማመር፣ የሙዚቃ ማህበራዊ ፋይዳዎች እና ለሙዚቃ መበላሸት ችግሮች የተባሉትን በዛሬው ዓምድ መጨረስ ስለማንችል ለሁለተኛ ክፍል የግድ ቀጠሮ ልንይዝ ነው። ሳምንት በክፍል ሁለት እንመለስበታለን። በተለይም ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ በሚደረው ጉዞ ከክቡር ዘበኛ ወደ ማዕከላዊ ዕዝ፣ ከዕዞች ወደ ፖሊስ ኦርኬስትራ እና ባንዶች የነበረውን እንቅስቃሴ እንቃኛለን። እስከዚያ መልካም ሳምንት!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2015