የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለሴካፋ ዞን ውድድር ወደ ሱዳን ያቀናል። ባለፉት በርካታ ቀናት በአዲስ አበባ የካፍ አካዳሚ ዝግጅቱን ሲያደርግ የቆየው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በቅርቡ በተሾሙት አሰልጣኝ እድሉ ደረጄ እየተመራ ከቀናት በፊት ከመቻል የ20 ዓመት በታች ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አከናውኖ 3-0 አሸንፏል።
በሱዳን አስተናጋጅነት የሚካሄደው የሴካፋ ዞን ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ጥቅምት 18 የሚጀምር ሲሆን ኢትዮጵያ በምድብ ሁለት ከታንዛንያ እና ዩጋንዳ ጋር መደልደሏ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የምድብ ጨዋታም በመጪው ረቡእ ከታንዛኒያ ጋር እንደምታደርግ ከውድድሩ መርሃግብር ለመረዳት ተችሏል።
ለኢትዮጵያ እግር ካስ ፌዴሬሽን ዩቲዩብ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ እድሉ፣ እሳቸውና ምክትሎቻቸው ቡድኑን ለማሰልጠን ሲመጡ የአጭር ጊዜ ኮንትራት ቢፈራረሙም በቅርብ የሚጠብቃቸው የሴካፋ ውድድርን ጨምሮ ወደ ፊት በሚያስመዘግቡት ውጤት መሰረት ረጅም ውል ሊሰጣቸው እንደሚችል በቃል ደረጃ መስማማታቸውን ገልፀዋል፡፡ ለሴካፋው ውድድር ዝግጅት ሲጀምሩም በይፋ ጥሪ ካቀረቡላቸው አርባ ስምንት ተጫዋቾች በተጨማሪ ክፍተት ያለባቸው ቦታዎች ላይ ከየክለቦች ሌሎች ተጫዋቾችን እንዳመጡ ተናግረዋል፡፡
ለብሔራዊ ቡድኑ ከተጠሩት አብዛኞቹ ተጫዋቾች በባቱ፣ጎንደርና አሰላ ከተሞች በተካሄዱ ውድድሮች ላይ የታዩ መሆናቸውን የጠቆሙት አሰልጣኙ፣ ተጫዋቾቹ በልምምድ ላይ የቆዩ በመሆናቸው አሁን እያደረጉ የሚገኙት ዝግጅት በቅርብ ካለው ውድድር ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በሴካፋ ውድድር ቡድኑ የት ድረስ እንደሚጓዝ ለመናገር በቅድሚያ የተጋጣሚ ቡድኖች ያሉበትን ወቅታዊ አቀም ማወቅ እንደሚጠይቅ የተናገሩት አሰልጣኝ እድሉ፣ በእንዲህ አይነት ውድድሮች ሁሉም ቡድኖች ከስር ጀምሮ ተሰርቶባቸው በቂ ዝግጅት አድርገው እንደሚመጡ አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ባለው አቅም መሰረት በሚጠቅመው አጨዋወት መሰረት ትኩረት አድርጎ በመዘጋጀት ከሱዳን ጥሩ ውጤት ይዞ ይመጣል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡
ሰባት ቡድኖች በሚሳተፉበት የዘንድሮው ከ20 አመት በታች የሴካፋ ውድድር ለፍጻሜ የሚቀርቡ ሁለት ቡድኖች በ2023 የአፍሪካ ከ20 አመት በታች አፍሪካ ዋንጫ ላይ በቀጥታ ይሳተፋሉ።
የሴካፋ ከ20 አመት በታች ውድድር በመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ እግር ኳስ ምክር ቤት አማካኝነት ሃያ አባል አገራትን ያካተተ አንጋፋ የውድድር መድረክ ሆኖ እኤአ ከ1971 ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
ውድድሩ ብዙ ጊዜ በየሁለት አመቱ አልፎ አልፎም በሶስትና አራት አመት ልዩነት ሲካሄድ ቆይቷል። ኢትዮጵያም ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ አስራ ሁለት ውድድሮች በሶስቱ ዋንጫ ማንሳት ችላለች። ይህም እኤአ በ1995 ኬንያ ባስተናገደችው ውድድር በፍጻሜ ጨዋታ ታንዛኒያን በመርታት ለመጀመሪያ ጊዜ ቻምፒዮን የሆነችበት አንዱ ነው። በቀጣይም ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ባስተናገደችው ብቸኛ ውድድር እኤአ በ1996 ዩጋንዳን በፍጻሜ ጨዋታ አሸንፋ ያነሳችው ዋንጫ ተጠቃሽ ሲሆን፣ እኤአ 2005 ላይ ዛንዚባር ባስተናገደችው ውድድር ቡሩንዲን በፍጻሜ ጨዋታ አሸንፋ ቻምፒዮን እንደነበረች ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ሶስት ጊዜ ቻምፒዮን በመሆን ስኬታማ ከሚባሉ አገራት አንዷ ስትሆን ዩጋንዳ አራት ጊዜ የዋንጫ ባለቤት በመሆን ቀዳሚ ናት። ሁለቱ አገራት (ኢትዮጵያና ዩጋንዳ) ዘንድሮ ሱዳን በኦምዱርማን አል ሂላል ስቴድየም አስራ ሶስተኛውን ውድድር ስታዘጋጅ በአንድ ምድብ ተደልድለዋል። በሁለተኛው የምድብ ጨዋታቸውም በቀጣዩ ሳምንት የሚገናኙ ይሆናል።
በምድብ አንድ አስተናጋጇ ሱዳን ከቡሩንዲ፣ደቡብ ሱዳንና ጅቡቲ ጋር ተደልድለዋል። ውድድሩ በመጪው አርብ ሲጀመርም ሱዳን በመክፈቻው ጨዋታ ጎረቤቷ ደቡብ ሱዳንን ትገጥማለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16 / 2015