ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ የጎዳና ላይ ውድድሮች ውጤታማ በመሆን አጠናቀዋል።ከእነዚህ መካከል አንዱ በስፔን ቫሌንሲያ የተካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር ከፍተኛ ትንቅንቅ በማድረግ በውጤታማነት አጠናቀዋል።በመላው ዓለም ከሚካሄዱ የ21ኪሎ ሜትር ሩጫዎች መካከል ከቀዳሚዎቹ አንዱ የሆነው የቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን በበርካታ አትሌቶች ዘንድ ተመራጭ ነው።በተለይ በከተማዋ ባለው ምቹ የአየር ሁኔታ ምክንያት ፈጣን ሰዓት የሚመዘገብበት በመሆኑም ይታወቃል።
ከትናንት በስቲያ በተካሄደው በዚህ ውድድር ግን የተጠበቀው ሳይሆን እጅግ ሞቃታማ በነበረው የአየር ሁኔታ ምክንያት ውድድሩ ፈጣን እንዳልነበረ ታይቷል።እስከ 10ኛው ኪሎ ሜትር ድረስም አስር የሚሆኑ አትሌቶች 27:51 በሆነ ሰዓት የሸፈኑት ሲሆን፤ ከ13ኛው ኪሎ ሜትር አንስቶ ግን ውድድሩ የነበረበት ሁኔታ መለወጡ ታይቷል። የቀድሞ የርቀቱ ክብረወሰን ባለቤት ኬንያዊው ኪብወት ካንዳይ እና የሃገሩ ልጅ ዳንኤል ማቲኮ እንዲሁም ኢትዮጵዊያኑ ዮሚፍ ቀጄልቻና ታደሰ ወርቁ በመሆን የአሸናፊነት ፉክክር ውስጥ ሊገቡ ችለዋል።እስከ 20ኛው ኪሎ ሜትር ድረስም በመካከላቸው የነበረው ርቀት የ23 ሰከንዶች ብቻ ነበር።
ከፍተኛ ፉክክርና የአሸናፊነት ትንቅንቅ በተደረገበት በዚህ ውድድር ላይም በርቀቱ ታዋቂ የሆነው ኬንዊው አትሌት ኪብዎት ካንዳይ 58:10 በሆነ ሰዓት አሸናፊነቱን አረጋግጧል።አትሌቱ በርቀቱ ሶስተኛውን ፈጣን ሰዓት ሲያስመዘግብ ከሁለት ዓመት በፊት በቦታው የክብረወሰን ባለቤት ሲሆን ከገባበት በአንድ ደቂቃ የዘገየ ነው።ለአሸናፊነት ብርቱ ፉክክር ሲያደርግ የቆየው ኢትዮጵያዊው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ደግሞ በ23 ሰከንዶች ዘግይቶ ሁለተኛ በመሆን አጠናቀል።የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና የሁለት ጊዜ ቻምፒዮኑ ዮሚፍ እአአ በ2019 በቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን ሲሮጥ የገባበት ሰዓት 59ደቂቃ ከ05 ሰከንድ ነበር።በዚህ ውድድርም ከአንድ ደቂቃ በላይ የሆነ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብም የኢትዮጵያን የርቀቱን ክብረወሰን ሊሰብር ችሏል።
ኬንያዊው ዳንኤል ማቲኮ እና ኢትዮጵያዊው አትሌት ታደሰ ወርቁም በተመሳሳይ ጥቂት ሰከንዶችን ብቻ በመዘግየት በ58 ደቂቃ ሶስተኛ እና አራተኛ ሆነው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።ባልተጠበቀ ሁኔታ ሲጀመር ተቀዛቅዞ በፈጠነው በዚህ ውድድር ላይም ስድስት አትሌቶች ከአንድ ሰዓት በታች 21 ኪሎ ሜትሩን መሮጣቸው ታውቋል።
በሴቶች በኩልም በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊያን እና ኬንያዊያን አትሌቶች አሸናፊ ይሆናሉ በሚል የተገመተ ቢሆንም የበላይነቱ ግን ወደ ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ያደላ ነበር።በተያዘው ዓመት የኮፐንሃገን ግማሽ ማራቶን ውድድርን ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያዊቷ ጽጌ ገብረሰላማ ርቀቱን በመምራት ሰፊ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ብታገኝም በአራት ሰከንዶች ብቻ በመበለጧ ሳይሳካላት ቀርቷል።1:05:41 በሆነ ሰዓት በመግባትም ጀርመናዊቷ አትሌት ኮንስታንዜ ክሎስተርሃፈን የዘንድሮው የቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን ውድድር አሸናፊ ልትሆን ችላለች።
ሩጫውን ስትቆጣጠር የቆየችው ጽጌ 1:05:45 በሆነ ሰዓት በመግባትም የግሏን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች።ከጽጌ ጋር በመሆን ጠንካራ ፉክክር ስታደርግ የቆየችውና አስቀድሞ ታሸናፋለች የሚል ከፍተኛ ግምት የተሰጣት አትሌት ሃዊ ፈይሳ ደግሞ የሀገሯን ልጅ በመከተል ሶስተኛ ደረጃን ልትይዝ ችላለች።በቫሌንሲያ፣ ኮፐንሃገን እና ባህሬን ግማሽ ማራቶኖች በመሮጥ ልምድ ያላት ሃዊ ርቀቱን የሮጠችበት ሰዓት 1:06:00 ሆኖ ተመዝግቧል።
በሌላ በኩል በስሎቬኒያ በተካሄደው የሉቢኒያ ማራቶን ኢትዮጵያዊው አትሌት ገብረጻዲቅ አብረሃ አሸናፊ መሆኑ ታውቋል።አትሌቱ ርቀቱን 2:06:09 በሆነ ሰዓት ሲሮጥ፤ አትሌት አብደላ ጎዳና ደግሞ 2:08:54 በሆነ ሰዓት አራተኛ ሆኖ ገብቷል።በሴቶችም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ስራነሽ ይርጋ 2:21:08 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ስትሆን፤ ስንታየሁ ለውጠኝ ደግሞ 2:22:36 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ወጥታለች።በጣሊያኗ ቬነስ በተደረገው ማራቶንም አትሌት ታፈሰ ደለለኝ እና ክብሮም ደስታ ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ሲይዙ፤ በሴቶች ፋንቱ ዘውዱ እና ጠጅቱ ስዩም አምስተኛ እና ስድስተኛ ሆነው ውድደሩን ፈጽመዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2015