ሰሞኑን በተለያዩ የኢትዮጵያ እንዲሁም የውጭ አገር ከተሞች ጭምር መንግሥትን በመደገፍ፣ አሸባሪውን ቡድን ሕወሓትንና ምዕራባውያንን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል። እነዚህ ሰልፎች ከ45 ዓመት በፊት በድሬዳዋ የተካሄደን ሰልፍ አስታውሰውናል። በዚህም ለዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ጋዜጣው ያቀረበውን የዚህን ሰልፍ ዘገባ ልናስታውስ ወደናል። በተጨማሪም የመረ ጥናቸው ዘገባዎች ከ55 ዓመት በፊት የወጡ ሲሆን አንዳንዶቹ የሚያሳዝኑ ሌሎቹም ግርምትን የሚፈጥሩ ናቸው።
በድሬዳዋ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሔደ
ድሬዳዋ(ኢ.ዜ.አ.)፡- በምሥራቅ ጦር ግንባር የዘመተው መደበኛው መለዮ ለባሽ፤ ሚሊሺያው ሠራዊትና አባላት ጦረኛው የአድኃሪው የሶማሌ ገዥ መደቦች ወራሪ ወታደሮች በማንበርከክና ቅስም በመስበር ፍጹም ስትራቴጂካዊ የሆነውን የካራማራ ኮረብታና የጅጅጋን ከተማ በማስለቀቁ የተሰማውን ደስታ በመግለጽ የድሬዳዋ ከተማና የአካባቢው ሕዝብ ከትናንት በስቲያ ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ አድርጓል።
በከተማው ውስጥ በሚገኘው የኮካኮላ ፋብሪካ አጠገብ በሚገኘው አደባባይ ላይ በተደረገው በዚሁ የደስታ መግለጫ ሰልፍ ላይ የ፳፫ ቀበሌ የሴቶችና የወጣቶች የገበሬዎች ማህበራት አባሎች የመንግሥት ሠራተኞች የማምረቻና ሰበነክ ወዛደሮች የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽህፈት ቤት አንቂ ጓዶችና ወታደራዊ ካድሬዎች የፖሊስ አባሎች መምህራን ተማሪዎች በጠቅላላው ቁጥሩ ከ፺፭ ሺ የማያንስ ሕዝብ ተካፋይ ሆኗል።
ከጦር ሜዳ ትግሉ ጀርባ በደጀንነት ተሠልፎ ዘማቹ ሠራዊት አብዮታዊውን ጦርነት በአሸናፊነት እንዲወጣ የሞራል የስንቅ እርዳታ የሚያደርገው ይኸው የከተማውና የአካባቢው ሕዝብ በየማኅበሩና በየሙያ አርማ ሥር ተሰልፎ ደስታውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ በተጓዘበት ወቅት ‹‹አሻግሮ ገዳይ በረሃ ያለውን ጠላቱን ዛሬ አመድ አረገው›› በማለት ወኔን የሚቀሰቅሱ መዝሙሮች ሽለላና ፉከራዎች አሰምቷል።
(የካቲት 29 ቀን 1970 የታተመው አዲስ ዘመን )
ዝንጀሮዎች ሰው ገደሉ
ጐፋ (ኢ-ወ-ም) በገሙ ጐፋ ጠቅላይ ግዛት በጐፋ አውራጃ በጐፋ ወረዳ ኰስቲ በተባለው ቀበሌ ሺበሺ ሌንሳ የተባለው የ፲፪ ዓመት ዕድሜ ያለው ልጅ የበቆሎ ሰብል ሲጠብቅ ዝንጀሮዎች በቆሎውን ለመብላት መጥተው ሊያባርራቸው ቢሞክር ተሰብስበው በመያዝ እየጐተቱ የገደሉት መሆኑን የአውራጃው ፖሊስ አስተዳደር በጽሑፍ መግለጣቸውን ዋናው ጸሐፊ አቶ ታደሰ ለገሠ አስታወቁ።
( መስከረም 1 ቀን 1960 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን )
ሰይጣን አርግዣለሁ የሚለው ወህኒ ቤት ገባ
አመያ (ኢ-ዜ-አ-) ቤኩማ ተረፈ፤ ማሞ ዘለቀ፤ አበበ ገሩና ለገሠ መኲሪያ የተባሉ ሰዎች በጨቦና ጉራጌ አውራጃ አመያ ወረዳ ግዛት ውስጥ ሽባ እየመሰሉ በልመና ተግባር ተሠማርተው በመገኘታቸው በእሥራት እንዲቀጡ ተደርጓል።
ቤኩማ ተረፈና ለገሠ መኲሪያ እያንዳንዳቸው በአራት ወራት እሥራት፤ እንደዚሁም የቀሩት ሁለቱ በሦስት ሦስት እሥራት እንዲቀጡ መደረጉን የወረዳው ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ዓለማየሁ አስረድተዋል። ከነዚህ ውስጥ በተለይ ቤኩማ ተረፈ የተባለው ሰው የሦስት ዓመት ሰይጣን አርግዤ ወደ ሐኪም ቤት የምገባበት እርጠቡኝ እያለ በማታለል ሆዱን በጨርቅ ጠቅልሎ በማሠር እየተንፏቀቀ ይለምን ነበር።
አድራጐቱ እውነት ያልመሰላቸው አቶ አንጋሳ ነገራ የተባሉ ሰው በቤኩማ ሆድ ላይ የታሠረውን ጨርቅ ቢፈቱት ስለተጋለጠ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው ፍርዱን እንዲያገኝ አድርገዋል ሲሉ አቶ ዓለማየሁ አረጋገጡ።
ለገሠ መኲሪያ የተባለውም ሰው እጁን በጨርቅ እየጠመጠመ ሽባ በመምሰል ሲለምን የተገኘ መሆኑን የገለጡት ዳኛ የቀሩት በተመሳሳይ አድራጐት መገኘታቸውን አስረድተዋል።
( መስከረም 22 ቀን 1960 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን )
መዛኞች ፻፸፫ ሰዎችን አስቀጡ
የአውራ ጐዳና ባለሥልጣን የክብደትና ልክ መወሰኛ ክፍል ከነሐሴ እስከ ጳጉሜ ፭ ቀን ፲፱፻፶፱ ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ፤ በአምስቱ ዋና በሮች ማለት በደሴ ፤ በሞጆ፤ በጐጃም፤ በነቀምቴና በጅማ መስመሮች በሕዝብና በጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር አድርጓል።
በተደረገውም ቁጥጥር ፮፻፹፭ ባለተሽከርካሪዎች የትራፊክን ሕግ በመተላለፋቸው ተከስሰዋል። ከተከሰሱትም ውስጥ ፩፻፸፫ቱ ፍርድ ቤት ቀርበው ፲፫ ሺህ ፭፻፶፪ ብር ተቀጥተዋል። የቀሩት ፭፻፲፪ ቱ ገና በቀጠሮ ላይ መሆናቸው ተገልጧል።
እንዲሁም ፬፻፲፱ መንገደኞች በቦታ ጥበት ምክንያት በመጉላላታቸው ከላይ የተጠቀሰው ቅጣት በአሽከርካዎች ላይ መወሰኑን ጭምር የባለሥልጣኑ የማስታወቂያ ክፍል አረጋግጦአል።
( መስከረም 12 ቀን 1960 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን )
የታንዛንያ ጠንቋዮች በረዶ
አዝንመው ታሰሩ
ከዳሬሰላም (ሮይተርስ)፡- በታንዛንያ ውስጥ በኪጐማ ቀበሌ የሚኖሩ ጠንቋዮች የቀበሌውን የአየር ጠባይ እንዲቆጣጠሩ በየዓመቱ ድርጐ ይከፈላቸው ነበር።
ነገር ግን ሕዝቡ ድርጐአቸውን ስላስቀረባቸው በረዶ የተቀላቀለበት ኃይለኛ ዝናም አዝንመው እህል እንዲበላሽ በማድረጋቸው ተወንጅለው ታስረዋል።
በምዕራብ ታንዛንያ በኪጐማ ቀበሌ አቅራቢያ በሚገኝ መንደር ውስጥ የሚኖሩ ገበሬዎች በሚኖሩበት ቀበሌ ላይ የውሃ መጥለቅለቅና ድርቀት ቢደርስ ይድረስ ብለው በመቁረጥ የዓመት ድርጐአቸውን አንከፍልም ብለው ነበር። ይህንንም እንዳሉ ወዲያውኑ የቀበሌውን እህል ሊያጠፋ የቻለ በረዶ ጥሏል። ወደፊትም በቀበሌው ላይ ከፍተኛ በረዶ ለማውረድ ዝተዋል።
( የካቲት 17 ቀን 1960 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2015