ስለ ‹‹ጠላ ቤት›› ሲነሳ በአብዛኞቻችን አዕምሮ ውስጥ ቀድሞ የሚመጣው የሴቶች ልፋትና ውጣውረድ ሊሆን ይችላል። አለፍ ስንል ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚተዳደሩበት የሥራ መስክ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸውን መጠጦች መጠጣት የማይችሉ ሌሎች ደግሞ የሚዝናኑበት እንደሆነ እናስባለን። ሥራውን በጎ ካልሆኑ ገጽታዎቹ ጋር ብቻ የምናስብም አንጠፋም። ለምን ከተባለ በዚህ ስፍራ ሁልጊዜ ስካርና ሁካታ ስላለ ነው። ከዚሁ ስሜት ጋር ተያይዞ ክፉ ቃላቶች ይወጣሉ፤ ጉንተላና ስድብ፣ ከዚህም አልፎ ድብደባና ደም መፋሰስ አይጠፋም። እናም ከኮማሪቷ ድካምና ልፋት በላይ ትዝ የሚለን በቦታው የሚያጋጥሙት ነገሮች ናቸው።
በአብዛኞቻችን ዘንድ አንዲት ጠላ ነጋዴ ይህንን ሥራ ለምን እንደመረጠች የሚረዳ የለም። ኑሮን ለማሸነፍ ዝቅ እንዳለች ከመገንዘብ ይልቅ የበታችነቷን ተቀብላ እንድትኖር ብቻ ይፈርዱባታል። በቻሉት ልክም ጫናውን ያሸክሟታል። አንዳንድ ደንበኞቿ ደግሞ የስድብ ናዳ ያወርዱባታል፤ ያዋርዷታል፣ ባስ ካለም ቡጢ ጡጫውን ያቀምሷታል። እንዲህ ዓይነቶቹን ማንነቶች እንድትለምደው፤ ኀዘናቸውን፣ ንዴታቸውን ባህሪያቸውን ጨምሮ ሁሉን እንድትቋቋመው ይፈረድባታል። አልፈው ተርፈውም ጾታዊ ትንኮሳ ያደርሱባታል።
ሰዎቹ የቀን ገቢ ያላቸው ለፍቶ አዳሪዎች ቢሆኑም እንኳን ታታሪዋን ሴት በብዙ መልኩ ይፈትኗታል። እንዲህ መሆኑ ደግሞ ጠላ ቤቱ በብዙ ጎዶሎዎች መሀል ከጨዋነት መስመር ስቶ እንዲወጣ ያደርገዋል። በአብዛኞቹ ጠላቤቶች እስካሁን የለመድነውና እያስተወልነው የመጣነው እንዲህ ዓይነቱን እውነት ነው።
በጠላ ቤቱ ጎራ የሚሉ አንዳንድ ደንበኞች ውሃ በጠማቸው ጊዜ ለጉሮሯቸው ማርጠቢያ ጠላዋን ተጎንጭተው በዚያው ልክ ስድብና ጡጫቸውን አሳርፈው የሴቷን ሕመም አብዝተው ይወጣሉ። በጠላ ሽያጩ ላይ የምትቆመው ሴት ግን መቼም ቢሆን አምርራ መቀየም አይቻላትም። ምክንያቱም በበዛ ጥረትና ድካም የምትደፍነው ጉሮሮ ይጠብቃታልና። በተለይ ትዳሯን የፈታችና ባሏ የሞተባት ሴት ልጆቿንና ራሷን ለማሳደር ይህ ዓይነቱ ሥራ ዋነኛ አማራጭ ታደርጋለች። በውሎ አጋጣሚዋም የሁሉንም አመል ማረቅና መሸከም ከውዴታ ግዴታዋ ሆኖ አብሯት ይዘልቃል።
ብዙ ጊዜ ሴት ልጅ ሥራ ከበደኝ፣ አቃተኝ እንደማትል ከዕለት ተዕለት አድካሚ ሥራዎቿ መረዳት ይቻላል። እንዲህ ዓይነቷ ባለሙያ በዚህ ሥራ ብዙ ትለፋለች። ጌሾ መውቀጥ፣ ብቅል ማዘጋጀት፣ የጠላ ቂጣ መጋገር የእርሷ ሥራ ነው። ወፍጮ ፍጩልኝ ሳትል፤ ለጌሾ ወቀጣው ወንዶችን ሳትጠራ ሁሉንም በራሷ ታደርገዋለች።
በዚህ ልፋት ድካሟ መሀልም የዚህችን ሴት በረከት የሚሹ ነፍሶች ይጠብቋታል። እሷም ብትሆን ግዴታዋን ሁሉ ትወጣለች። ልጆቿን አሳድጋ ለወግ ማዕረግ ታበቃለች። ተግባሯ በልፋቷ ተሞሽሮ ከማሰሮው ማንቆርቆሪያ ይወርዳል። የቀንድ ዋንጫውን ሞልቶም በመዓዛው እያወደ በጣዕሙ ጥፍጥና ለሌሎች እርካታ ይደርሳል።
ይች ሴት ለድካሟ የማይመጥን ገንዘብ ለቅማ የሌሎችን ደስታ ሞልታ ልጆቿን ካሰበችው ስታደርስ፤ ከብርጭቆው በስተጀርባ ያኖረችውን ውጤት ታገኘዋለች። የብርታቷን ፍሬ ቀምሳ ታጣጥማለች።
የብርታቷን ፍሬ ከሚቀምሱት መካከልም ዛሬ የመረጥናት ብርቱዋ ሴት ወይዘሮ ዝናሽ አየለ አንዷ ናት። ታሪኳ እንደተለመደው ጠላቤት ኮማሪዎች ሳይሆን በራሱ መስመር የተጓዘና ለስኬት ያበቃት ነው። ይህንን ንግድ መተዳደሪያቸው ያደረጉ ሴቶች ዓይነትም አይደለችም። ንግዱን የጀመረችው ለአዕምሮዋ እረፍት ለባህሏ ክብር ለመስጠት ነው። ከዚያም አልፋ የሴቶችን ብርታት ለማሳየት ነው።
እነሱ መክሳት መጥቆራቸውን በፈገግታቸው፤ ጨለማ ችግራቸውን እንደ ሻማ ብርሃን ሆነው የልጆቻቸውን ቀን እንዳንቦገቦጉ ለማሳየት ተግታ ትሠራለች። ብቸኝነታቸውን ከራሳቸው አዋህደው ዓመታትን ቢያሳልፉም ልጆቻቸውን ካሰቡት ላይ እንደሚያደርሱም ሆና ታሳያለች።
ጠላ ከልፋቱ ባሻገር ሌሎች ዓይን ገላጭ ነገሮችም እንዳሉት ምስክር ሆናለች። እንዴት ከተባለ ልፋቱን ከመቀነስና ከቦታው እንዲሁም ከጠጪዎቹ አንጻር በሠራችው ሥራ በማስደመም ነው። ሥራዋን አሀዱ ያለችው በከተማ በመሆኑ የጠላ አዘገጃጀቱ እንደገጠሩ ቢሆንም ልፋቱን ግን በብዙ መልኩ ቀንሳዋለች። በአብዛኛው ለጌሾ ወቀጣና ለብቅል መፍጨቱ ዘመናዊ ወፍጮ ቤትን ስለምትጠቀም ለእሱ የሚወጣውን ጉልበት ወደሌላኛው ሥራ ላይ እንዲያርፍ ታደርጋለች።
ጠላ በማኅበረሰቡ አሉታዊ ምልከታ የተነሳ ከጊዜ ወደጊዜ የነገሥታት መጠጥ ሳይሆን የድሆች እየሆነ በመምጣቱ በተለይ በአዲሱ ትውልድ ቦታ የሚሰጠው እንዳልሆነ ልብ ይሏል፤ ነገር ግን ይህች ልባም ሴት ጠንካራ በመሥራቷና በማሠራቷ አሁን ላይ በከተማው ሰው ዘንድ ሀሳቡ ተቀይሯል።
በቅጽል ስሟ ‹‹ደሸሾ›› እየተባለች የምትጠራውና ጠላ ቤቷን በዚህ ስም ያደረገችው ዝናሽ፤ ከእናቷ በወሰደችው የጠላ ጠመቃ ሙያ እንዲሁም ቤተሰቧ ላይ በምታየው የባህል መጠጦች ፍቅር የተነሳ ሥራውን ስለመጀመሯ ትናገራለች። እንደ ገጠር ሴትነቷ በጠላ ጠመቃ ዙሪያ ያለውን ልፋት ባታውቀውም ክብር ያለው መጠጥ መሆኑን ግን ከቤተሰቦቿ ጋር በኖረችበት ዕድሜ ሁሉ አይታለች። በእነርሱ ቤት በርካቶች እንደሚያደርጉት ለበዓላትና ለሌሎች ድግሶች ባህላዊ መጠጦች ይዘጋጃሉ፤ በቤቱ ጠላ ጠፍቶ አያውቅም። ፍቅርን፣ መተሳሰብን፣ መሰባሰብን፣ ለችግር መፍትሄን መፈለግን ለማምጣት ጠላ ትልቅ ድርሻ አለው። ስለዚህ ልዩ ክብር ሰጥታ እንድትሠራበት ብትሆንም መተዳደሪያዬ ይሆናል ብላ አላሰበችም ነበር። ነገር ግን ከሚሰጣት አስተያየትና ሙገሳ አንጻር ሥራውን ወዳና የተሻለ አድርጋ በመሥራቷ ዛሬ ላይ የገቢ ምንጯ ሆኗል።
ትንሿ ምግብ ቤት
አዲስ አበባ ላይ ባለትዳርና ሁሉ ነገር የሞላላት ብትሆንም መሥራት ግን ትፈልጋለች። ለዚህም ሥራ መምረጥን አትሻም። በቀላሉ እከውነዋለሁ ብላ ያሰበችውን የምግብ ሥራ በቤቷ አስቤዛ ከሠራተኛዋ ጋር በመሆን ጀመረች። የሥራ ቦታዋ ምቹ ካለመሆኑም በላይ ለሥራዋ ከባለቤቷም ፍቃድ አላገኘችም ነበር። ግን ቁጭ ብላ መብላትን አትፈልግምና እንደምንም አሳምናው ደንበኞችን አገኝበታለሁ ባለችበት ላምበረት አካባቢ ሥራውን ጀመረች።
በቀን ሥራ የሚተዳደሩና ሊስትሮዎች ይመገቡልኛል የሚል ግምት ነበራትና ፈጣን ምግቦችን ማዘጋጀት ያዘች። በመጀመሪያው ቀን ግን ያሰበችው ቀርቶ ያላሰበችው ሆነ። አንድ መኪና ጎማው ይበላሽና ሁሉም ተሳፋሪ ቤቷን አጥለቀለቀው። ሁለት ሆነው ያን ሁሉ እንግዳ ማስተናገድ ተሳናቸው። ምንም አልተዘጋጁምና ሜኑ አልነበረም። ስንት እንደሚከፈል አልተወሰነም። የሰጧትን እየተቀበለች ሁሉን አስተናግዳ ጠበል ጸዲቅ በሚመስል መልኩ ሸኘች። በዕለቱ ብዙዎቹ እንዳልከፈሏት ታስታውሳለች።
በዚህ ሁኔታም ከሦስት ወር በላይ ቆየች። ሠርታ መመለሷን እንጂ ትርፍና ኪሳራ አለየችም ነበር። ጥፍጥ ያለ ምግብ አዘጋጅታ በትንሽ ዋጋ ትሸጥና ደስተኛ ሆና ወደቤቷ ትመለሳለች። እንዲህ መሆኑ ደግሞ የቤት ኪራይ ጭምር ከባሏ እንድትጠይቅ አስገደዳት። ሁኔታው ግን ከጊዜ ወደጊዜ ያሳስባት ገባ። ስጋት ያዛት። ነገሮችን መቀየር እንዳለባት በማሰብ ለቤቱ ባይመጥንም የወጥቤት ሠራተኛ ቀጠረች። ምግቡን በሚመጥን ዋጋ ማቅረብ የጀመረችው ከዚህ ጊዜ በኋላ ነበር።
ዋጋው የተመጣጠነ በመሆኑ ከሩቅ ጭምር እየመጡ የሚመገቡ ደንበኞችን አፈራች። ይህ ደግሞ ሥራዋን በትልቁ እንድታስበው አደረጋት። በተለይ የላምበረት መናኸሪያ ሲከፈት ብዙ ደንበኞች ወደእርሷ እንደሚተሙ ገመተች። በሠራተኛም ሆነ በቦታው ሰፋ ብላ መሥራት እንዳለባት አወቀች።
መገናኛ አካባቢ ቋሚ ስፍራዋን አድርጋ የምግቡን ሥራ ማጧጧፍ ቀጠለች። ደንበኞቿ በመብዛታቸው ቦታው ሊችላቸው አልቻለም። በዚያ ላይ ፎቁ ላይ ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ ስለነበሩ ቅሬታ ያቀርቡባት ጀመርና አከራዮቿ አስለቀቋት። እናም ለወራት ሥራዋን አቁማ ቆየች። ተስፋ መቁረጥ ባህሪዋ አይደለምና ዳግመኛ ከቦታው ሳትርቅ ቤት ፈልጋ ሥራውን ጀመረች።
በአዲስ መልኩ የተከራየችው ቤት ብዙዎች የከሠሩበትና ውድ ዋጋ የወጣለት ነው። በቂ ገንዘብ በእጇ ላይ ሳይኖር ለመከራየት ወሰነች። መለኛነቷን ተጠቅማ እቁብ ቀድማ ወሰደች። ቤተሰቤ ከምትለው አንድሰው ገንዘብ ተበድራም የልቧን አደረሰች። ቤቱን በከፈተች በሳምንቱም እቁቧን መክፈል እንደጀመረች አትረሳም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአካባቢው ላይ በስፋት መታወቋ ነበር። እናም ዳግመኛ ደንበኞችን ለማምጣት ሳትቸገርና ሳትከስር ሌላ አማራጭ ሰጥቷት ዛሬ ድረስ ቀጥላለች።
ጠላን በመሀል ከተማ
ከምግቡ ጎን ለጎን በትንሹ ጠላ እየጠመቀች ለደንበኞቿ ትጋብዛለች። ይህ ደግሞ ወደቢዝነስ እንድትቀይረው ይገፋፋት ጀመር። እናም ጎን ለጎን መሥራቱን ያዘች። ከተጠቃሚ ብዛት አንጻር ግን በቦታው መቀጠል አልቻለችም። ምክንያቱም የጠላ ቤት ጨዋታ በቀላሉ የሚገታ አይደለም፤ ሙዚቃና ጭፈራውም እንዲሁ። አሁንም አዲሶቹ አከራዮቿ ይህንን ሊወዱላት አልቻሉም። ቦታውም ቢሆን ጠቧታል። በዚህም ጉዳዩን አስረድታ የሚያከራያትን ሰው ፈለገች።
ዛሬን አመስግና ከማትጠግበው የዋች ሕንፃ ባለቤት ጋር ተገናኘች። ይህኛው አከራይ ባህሉን የሚወድ እንደሆነ በአደረገላት ነገር ያስታውቃል። መጀመሪያ ጠላው እስኪለመድ በሚል የቤት ኪራይ አልተቀበላትም። ሲለመድ ደግሞ በቅናሽ ዋጋ ኪራዩን ተቀበላት። ዝናሽ ይህንን ማበረታቻ ስታይ በተለምዶ ቁመታቸው ዝቅ ባሉ መደቦች ላይ የሚዘወተረውን ጠላ ለዘመናዊ መጠጦች የተዘጋጁ በሚመስሉ መቀመጫዎች ከፍ አድርጋ መሥራቷን ቀጠለች።
እንደተለመደው ጣሳ ሳትሰቅልና ማስታወቂያ ሳትለጥፍም አራተኛ ፎቅ ላይ እንድታስተናግድም ሆነች። ባለሙያዋ ጠጪዎቿን ሳይቀር ቀይራለች። ቦታው የተማረና ባህሉን የሚወድ ጨዋ ሰው የሚታደምበት በመሆኑ ደንበኞቿ ደስተኞች ናቸው። ጠላን በዚህ መልኩ ማግኘት በመቻላቸው እጅጉን ወደውታል።
‹‹ደሸሾ›› በሚል ስያሜ የተሰጠው ምግብ ቤትና ባህላዊ መጠጥ ቤቱ ከ50 በላይ ሠራተኞችን በቋሚነት ቀጥሯል። ባህላዊ መጠጦቹ ጠላ፤ ጠጅና አረቄ ከምግብ ጋር አብረው ይቀርባሉ። ጎን ለጎንም የጽሕፈት መሣሪያዎች መደብር (ስቴሽነሪ) በመክፈት ቋሚ ሠራተኞችን ቀጥራ ታሠራለች። በተለይም የፈጠረችው የሥራ ዕድል የቀን ሠራተኞችን ሲጨምር ከመቶ ሰው በላይ ነው። ይህ ደግሞ በትንሽ ገንዘብ ተነስታ ለብዙዎች ተስፋ የሆነች ሴት ያደርጋታል።
ዝናሽ ጠላ ቂጣውን፣ ብቅሉን፣ አሻሮና ሌሎች ነገሮችን ነጣጥላ በመሥጠት ቋሚ ሠራተኞቹን ታሠራቸዋለች። ሁኔታዎች የሚከብዳቸው መስሎ ከተሰማት ደግሞ የጉልበት ሠራተኛን ትጨምርላቸዋለች። በዚያ ላይ ቀን በቀን የጉልበት ሠራተኛው እህልና መሰል የወፍጮቤት ሥራዎችን እንዲከውኑ ታደርጋለች። ይህ ደግሞ በጊዜና በጥራት ባህላዊ መጠጦቹ እንዲዘጋጁ ያግዛታል።
በእነ ዝናሽ ጠላ ቤት የውጭ መስተንግዶ ‹‹ቴክ አዌ›› የሚባል አሠራር አለ። ለነብሰጡሮች፤ ብቻቸውን መጠጣት ለማይወዱ ሰዎች ቤታቸው ወስደው እንዲጠጡ ዕድሉ ይሰጣቸዋል።
መጀመሪያ አካባቢ ሥራው እስኪለመድና የሚመጣው ሰው በቅጡ እስኪታወቅ ማንኛውም ባህላዊ መጠጥ በብዛት አይዘጋጅም ነበር። የሰዎች ቁጥር ሲበራከትና ደንበኞች የፍላጎታቸውን ማግኘት ሳይችሉ ሲቀሩ ግን ሥራውን አስተካከለች በዚህም በቂ የሆነ መጠጥ አዘጋጅቶ በማቅረብ የለም የሚል ነገር አጠፋች። አሁን በእነርሱ ቤት በየቀኑ ባህላዊ መጠጦች አሉ። በዚህ ደግሞ እየበሉ፤ እየጠጡ ባህላዊ ሙዚቃን እየኮመኮሙ በቤቱ ውስጥ የሚዝናኑ ሰዎችም ቁጥር ተበራክቷል።
ምክር
ችግር የሌለው ሥራ የለምና ሁሉንም በትዕግስት ማሳለፍ ይገባል፤ እኔ በሥራዬ ትልቅ ችግር ሆኖብኝ የነበረው አተላ መድፊያ ነው። ከመጸዳጃ ሲጨምሩት ፍሳሽ አስወጋጆቹ ባዕድ ነገርን አንመጥም በማለት ያስቸግራሉ። አሁን ላይ ‹‹እፎይ›› ያልኩት አተላውን ጭኖ ወደሱሉልታ የሚወስድ ሰው በማግኘታቸው ነው ትላለች።
ዝናሽ ጠላን ወደ ውጭ የመላክ ህልም አላት። ምርቱ አገርን በተለያየ መልኩ ያሳድጋል። የመጀመሪያው ባህልን ማስተዋወቅ ሲሆን ሌላው የእርስ በእርስ ትስስርን ማጠናከር ነው። ከዚህ በተጨማሪም ወደ ውጭ በመላክ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጭም ይሆናል። ሁሉም ባለበት የሚያበረክተው ቁም ነገር አለውና መልካሙን ሁሉ ያድርግ ትላለች።
ዝናሽ «ባህላችንን ማሳደግ ከፈለግን ማንነታችንን አንርሳ፤ ባህል ማለት ዘመኑን የሚዋጅና ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ነው፤ ወደ ኋላ የሚጎትተንን፤ ማንነታችንን የሚያጠለሽብንን ነገር ወደጎን እየተውን የሚያበረታንን ነገር እየያዝን ወደፊት መጓዝ አለብን» ትላለች።
‹‹ሴቶች በብዙ ትግል ውስጥ እያለፉ መልካሙን ወይን እያጠጡ ሲያስጉዟችሁ ጫናዎችን አታሳርፉባቸው›› ለወንዶች ያስተላለፈችው ምክር ነው። በዚህ ውስጥ አልፈው ብዙዎችን ለወግ ማዕረግ ያበቁትን እያሰባችሁ ደግፏቸውም ምክሯ ነው።
ሌላው ማንኛውም ሥራ ልፋት፣ መሰናክል አለው። ‹‹አልችልም›› ካልን ግን አንራመድበትም። ጥገኛ ሆነን ዓመታትን እንድናሳልፍ እንሆናለን። እናም «እኛ ሴቶች ብልሃታችን ከሌላው የተለየ ነውና ሁሉንም በመቻል ስኬትን እስክንጎናጸፍ ድረስ መልፋት ይኖርብናል።
በሥራው ላይ የተሰማራችሁ ሴቶች ዝቅ ያልኩ ነኝ ብላችሁ ራሳችሁን ማሳመን የለባችሁም። ከፍ የሚባለው ከዝቅታ በመነሳት እንደሆነ እመኑ። እኔ ከምንም ተነስቼ ባህላዊ መጠጦች የሚቀርቡበትን ጨምሮ ሁለት ቦታ ምግብ ቤት፤ የጽሕፈት መሣሪያ መሸጫ(ስቴሽነሪ) ከፍቻለሁ። እናም ተስፋችሁን ባላችሁበት ቦታ ላይ ሁሉ አለምልማችሁ ስኬታማ ለመሆን ሥሩ›› የዝናሽ የማሳረጊያ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2015