በወቅታዊ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየናረ የመጣውን የጥቁር ገበያ ለመቆጣጠር ሲባል ከውጭ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ክልከላ ለተደረገባቸው 38 የምርት ዓይነቶች ባንኮች ከጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ኤል.ሲ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) መክፈት እንደማይችሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መግለጹ ይታወቃል።
ተሽከርካሪን ጨምሮ 38 ምርቶች እንዳይገቡ በመወሰኑ፣ ባንኮችም በዚህ ውሳኔ መሠረት ለምርቶቹ የውጭ ምንዛሪ እንዳይፈቅዱ መመሪያ እንዲደርሳቸው መደረጉ ከሰሞኑን ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው። ከተሽከርካሪዎች ሌላ ክልከላ ከተደረገባቸው ምርቶች ውስጥ እንደ ከረሜላ፣ ማስቲካና ጣፋጭ ምግቦች ተጠቃሽ ናቸው። የተለያዩ የፍራፍሬ ጭማቂዎች፣ ሲጋራ፣ ውስኪ፣ ወይንና ሌሎች የአልኮል መጠጦች በዚህ መመሪያ መሠረት ላልተወሰነ ጊዜ እገዳ የተጣለባቸው ናቸው።
የባንኩ ምክትል ገዥና ቺፍ ኢኮኖሚስት አቶ ፈቃዱ ደግፌ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ለእነዚህ ምርቶች ማንኛውም ባንክ ኤል.ሲ መክፈት አይችልም። ይህንን መመሪያ ጥሰው ኤል.ሲ የሚከፍቱ ባንኮች ካሉ ሕግ በመተላለፍ ተጠያቂ የሚሆኑና የሚቀጡ ይሆናል።
የውጭ ምንዛሪ የማይፈቀድላቸው 38 የምርት ዓይነቶች መከልከላቸው ፋይዳው ምን እንደሆነና በጥቁር ገበያ የሚዘረዘረው ዶላርም ከ100 ብር በላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም፤ ከዕርምጃው በኋላ ከ70 ብር በታች የመሆኑ ምስጢር በተደረገው ውሳኔ የመጣ ለውጥ ነውን? ስንል በጉዳዩ ዙሪያ የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግረናል።
የፓን አፍሪካ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ክቡር ገና እንደሚናገሩት፤ በተወሰኑ ምርቶች ላይ የተጣለው የውጭ ምንዛሪ እገዳ እየጨመረ ያለውን የዋጋ ንረት ያረጋጋል። ተተኪ ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ምክንያትም ይሆናል።
ብሔራዊ ባንክ 38 ምርቶች ላይ ላልተወሰነ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ እገዳ መጣሉን ተከትሎ አገር ውስጥ ያሉ የፋብሪካ ባለቤቶች አስፈላጊ ናቸው ብለው የገመቱትን በአገር ውስጥ ለማምረት የሚሞክሩበት አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል ነው ያሉት። እንደእርሳቸው አባባል፤ ድጋፍ ከተሰጠ እና እገዛ ከተደረገ የአገር ውስጥ አምራቹን በማነሳሳት ከውጭ ይገቡ የነበሩና የታገዱ ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ የሚያደርግ ጥሩ ምክንያት ይሆናል። የቅንጦት እቃዎች ዋጋ በየጊዜው የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ላይ ተጽእኖ እያሳደረ በመሆኑ ለእቃዎች ግዢ ይውል የነበረው ገንዘብ ለልማት እና እሴት ጨምረው ለሚወጡ ዕቃዎች የሚውል በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው።
እገዳ እንዲጣልባቸው ከተዘረዘሩት ሚዛን የሚደፉት ተሽከርካሪ እና ከተሽከርካሪ ጋር የተያያዙት ናቸው ያሉት ባለሙያ፣ እነዚህ ቀርተው ገንዘቡን ለመሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች እና ለልማት እንዲውል ማድረጉ ጥሩ እርምጃ ነው ብለዋል። ብሔራዊ ባንክ ከውጭ ይገቡ በነበሩ ምርቶች ላይ የጣለው እገዳ አገሪቱ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ብትሆንም ብዙም አስቸጋሪ ነገር አይፈጠርም ብለዋል።
ብሔራዊ ባንክ ጥቁር ገበያውን ፈቅዶ አያውቅም፤ አሁንም የተወሰዱትን እርምጃዎች አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ ነው። ድርጊቱን የሚፈጽሙት ሕገ ወጦች የማስቆም ጅማሮ መልካም ሲሆን፣ አሁንም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱ እጅግ የሚደገፍ ሀሳብ ነው። ውሳኔውን ተከትሎም በጥቁር ገበያ በሚደረገው ግብይት የአንድ ዶላር ዋጋ ከ100 ብር በላይ ደርሶ የነበረውን በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት በማስተካከል ፖሊሲው ውጤት እያመጣ መሆኑን ያሳያል ሲሉ ባለሙያው ይናገራሉ።
ይሁንና ይህ እስከመቼ ይቀጥላል ለሚለው በሰጡት ምላሽ፤ ‹‹ገና አልታወቀም›› የሚል ምላሽ ያስቀምጣሉ። እንዲያም ሆኖ የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች ግን የተፈለገውን ዓላማ ለማሳካት እንደሚያስችል አሳይቷል ብለዋል። በቂ ምርቶች በብቃት አለመግባታቸው ወይም አለመመረታቸው ግሽበትን እንዲፈጠር አድርጓል። በሰዎች እጅ ብዙ ገንዘብ አለ፤ ነገር ግን ሰው የሚፈልገውን የሚያገኝበት ሁኔታ አለመፈጠሩም አሳሳቢ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
በአጠቃላይ ሲታይ ትልቁ ግሽበት እየመጣ ያለው በምግብ በመሆኑ በተለይ አቅመ ደካማውን የሚጎዳ ነው። ከተማ ውስጥ የሚታየው የቤት ኪራይና ሽያጭ ላይ የሚስተዋለው ዋጋ ከዕለት ወደ ዕለት እየናረ ሄዷል። አንዳንድ አገራት ከተወሰነ ገንዘብ በላይ የሚያወጣ ሽያጭ ካለ ታክሱ በጣም ከፍተኛ ይሆናል። በእኛ አገርም መጠናት ይኖርበታል ብለዋል።
አሁን የተወሰደው እርምጃ በተወሰነ መልኩ የውጭ ምንዛሪ ቢያድንም ምን ያህል? የሚለው ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይገባዋል። ምክንያቱም እገዳ የተጣለባቸው ከአውቶሞቢል ውጪ ሌላው ቢተመን በዓመት ውስጥ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በታች እንጂ ከእዛ በላይ አያወጣም። በርግጥ ይሄ ቀላል ነው ማለት ባይሆንም ሚዛን ደፊ አይደለም ብለዋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዛፉ እየሱስ ወርቅ ዛፉ እንደሚሉት፤ የጦርነት ኢኮኖሚ ውስጥ የሚገኘውን የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ለመታደግ ብሔራዊ ባንክ እየወሰደ ያለው እርምጃ መልካም ነው። በመንግሥት በኩል የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት፤ ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፍቃድ (ፍራንኮ ቫሉታ) በጉምሩክ በኩል በቀጥታ እንዲገቡ የተፈቀደውን ውሳኔ ያለአግባብ ጥቅም ላይ የሚያውሉ አካላት የሚያደርጉት ተግባር ተገቢ አይደለም።
እርሳቸውም እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተናዎች ገጥሟታል። ይህንን ችግር በመገንዘብ መንግሥት እየሠራበት ይገኛል፤ ሆኖም ለመፍትሄው የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። በአገሪቱ ለሚስተዋለው የኢኮኖሚ ችግር ኃላፊነቱን የመንግሥት ብቻ አድርጎ መመልከት ትልቅ ስህተት ነው። መንግሥት፤ ድርጅቶች በአንጻራዊ ሰላም ሁኔታ ሥራቸውን እንዲሠሩ ማድረግ ይገባል። የኑሮ ውድነቱ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን በከፍተኛ ደረጃ ቢያጠቃም፣ የመንግሥትና የግል ዘርፉ ሠራተኞችንም ስለሚጎዳ ለመንግሥት ብቻ ሊተው አይገባም።
አቅርቦትን ከፍ ማድረግ በአንድ ሌሊት የሚሆን ጉዳይ አይደለም ያሉት አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ፣ ጉዳዩ ጊዜ የሚፈጅ፣ ሂደትን አልፎ የሚዘጋጅ ነው ብለዋል። መንግሥት የውጭ በጀቱን ያህል የውስጥ ገቢን ሊሰበስብ ይገባል። በአገር ውስጥ የውጭ ምንዛሬ አቅም ላይ የሚስተዋለውን መመናመን ማስተካከል እንደሚገባውም ይጠቁማሉ።
በሕገወጥ መንገድ የሚካሄዱ የውጭ አገር ምንዛሬ እና ክምችትን፣ የወርቅ ዝውውርና ክምችት፣ የሐሰተኛ የብር ኖቶች ሕትመትን ለመቆጣጠር ሕገወጥ ድርጊቶችን ለመጠቀም ብሔራዊ ባንክ ማበረታቻ አስቀምጧል። ፍራንኮ ቫሉታን በሕገ ወጥ መንገድ ተግባር ላይ በሚያውሉ ግለሰቦች ላይም ማበጀት ይገባል ያሉት አቶ ዛፉ፣ ለሰላም መስፈን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባዋልም ብለዋል።
እንደ እርሳው ገለጻ፤ ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተናዎች ገጥሟታል። ይህንን ችግር በመገንዘብ መንግሥት እየሠራበት ይገኛል፤ ሆኖም ለመፍትሄው የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ወሰን ሰገድ አሰፋ በበኩላቸው፤ አገሪቱ ከሚያስፈልጋት ነገር አንፃር ሲታይ ይታገዱ በተባሉት 38 ምርቶች የምናጣው ዶላር በጣም ብዙ አይሆንም። ይህ ማለት አገር ውስጥ እንዳይገቡ የተከለከሉት ምርቶች ያን ያህል አስፈላጊ የሚባሉ ባለመሆናቸው መሠረታዊ ያልሆኑትን ነጥሎ ማስቀረቱ መልካም ተግባር ሊባል የሚችል ነው። ያን ያህል መሠረታዊ ያልሆኑ የማህበረሰቡ ሕይወት ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ የማያመጡ መሆናቸው ይበል የሚሰኝ ተግባር ሆኖ ሳለ ለዶላር እጥረቱ መፍትሄ ነው።
የቁሳቁስ ከውጪ እንዳይገባ ክልከላ ሲደረግ ቀድመው በአገር ውስጥ ገብተው የነበሩ አሁን ላይ የተከለከሉ ቁሶች የመሸሸግ እጣም ሆነ ዋጋቸው ከፍተኛ መሆኑ አይቀርም። በቀጣይ ወራት ምርቶቹ ወደ ጥቁር ገበያ እና ኮንትሮባንድ ሥርዓት ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበትን ሁኔታም ሊፈጥሩ የሚችሉ መሆኑን ጠቁመዋል።
የክልከላው ዓላማም ምርቱን ከአገር ውስጥ ገበያ በተዘዋዋሪ ማጥፋት ስለሆነ በአጭር ወራት ገበያው ከሸቀጦች ዝርዝር በውዴታ ሳይሆን በግዴታ የተከለከሉ ቁሶችን ጭራሽ ባይሆንም በብዛት ስለሚያስወጣቸው ቅፅበታዊ የዋጋ መጨመሮች በሂደት መስተካከላቸው አይቀርም ብዬ አስባለሁ ብለዋል።
የዶላር እጥረቱን ለመቆጣጠር ዶላር ከሚያሳጡን ነገሮች ይልቅ ዶላር የምናገኝባቸው ነገሮች ላይ ማተኮር ይበልጥ አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣ ደጋፊ መፍትሄ ሀሳብ መወሰድ አለበት ይላሉ።
ይህንን ለማግኘት ደግሞ በኤክሰፖርት አቅምን ማሳደግ፤ የቱሪዝም ሀብትን ለጎብኚዎች ክፍት ከማድረግና ቱሪስቶች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፤ ከውጭ የሚላኩ ገንዘቦች በሕጋዊ መንገድ እንዲሆን በማደረግ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን መጨመር ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ መንግሥት እዚህ ላይ ትኩረት ሊያደረግ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
ሌላው ሕዝቡ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዲኖረው ማድረግ ሕጋዊ መንገዶችን ዜጎች እንዲጠቀሙ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ሲባል የጥቁር ገበያና የሕጋዊ ገበያውን ልዩነት ማጥበብ፤ ለቤተሰቦች የሚላከው ገንዘብ በብር ሲለወጥ ከሚያስፈልገን ዶላር አንፃር በመመልከት ምንዛሪውን መጨመር፤ ዲያስፖራው ማህበረሰብ አገሩ ውስጥ ያለውን ልማት እንዲደግፍ ተአማኒነት ያለው አሠራር መዘርጋት ከሙስና የፀዳች አገር መኖሯን የሚያሳይ ተግባር ሲከናወን ውጭ አገር ያሉ ዜጎቻችን ገንዘብ የማይልኩበት ምክንያት አይኖርም በማለትም ገልጸዋል።
አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው፤ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አስፈላጊ ናቸው የሚባሉ ድርጅቶች ካሉ ግብዓቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ። የገንዘብም ሆነ የብድር ድጋፍ ቢመቻች በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርቱን አሳድገው የገበያውን ዋጋ ሊያስተካክሉት ይችላሉ። በዋናነት ግን በተለይ የግብርና ምርትን ማሳደግ ላይ ብዙ ሊሠራ ይገባል። በአገር ውስጥ ያለው ሀብት መሬት እንደመሆኑ ምርትን ማሳደግ በሚቻልበት መንገድ ጥቅም ላይ በማዋል መሠረታዊ ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል።
ሌላው የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመቀየርና ቁጥጥሩን አጠናክሮ በመቀጠል ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ጦርነቱን በማስቆም የቱሪዝም ሀብቱን ለመጠቀመ የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ መፍጠር ተገቢ ነው በማለት አስረድተዋል። ይህ ሲባል አገሪቱ የሚኖራትን የዶላር ሀብት ለመጨመር የሚያስችሉ መፍትሄዎችን መመልከትም ሌላው አማራጭ መሆኑን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊው ባንክ የውጭ ምንዛሪ ዝውውርን በተመለከተ ገደብ እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችሉ መመሪዎችን ተግባራዊ ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያ አለመሆኑ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ባንኮች በተለያዩ መንገዶች እጃቸው ከሚገባው የውጭ ምንዛሪ 70 በመቶውን ወደ ማዕከላዊ ባንክ እንዲያስተላልፉ ጥር 2 ቀን 2014 ዓ.ም በባንኩ ገዥ ፊርማ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ተግባራዊ እንዲሆን መደረጉ ይታወሳል።
ዓለም አቀፍ የገንዘብ ፈንድ (IMF) በዘንድሮ ትንበያው የቀጣይ ዓመት የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት የሸመታ አቅም አሁን ካለበት 21 ቀን ወደ 18 ቀን ዝቅ ሊል ይችላል ብሏል። በ2014 ኢትዮጵያ ከውጪ የሚያስፈልጋትን ቁሳቁስ በተወሰነ መልኩም ለመሸመት ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዳወጣች ይታወቃል። ስለዚህ በ2022 በግርድፉ ከተሰላ 1 ነጥብ 03 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ምንዛሬ ክምችት በካዝናዋ አላት እንደማለት ነው ሲል አመልክቷል።
ለዚህ መፍትሄው ምሁራኑ እንዳመላከቱት ከክልከላው ይልቅ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበትን አማራጭ በስፋት መመልከት እንዲሁም የቁጥጥር ዘዴውን ማጠናከር፤ እንዲሁም ተኪ ምርቶችን በብዛት ማምረት ነው።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2015