በ2008 ዓ.ም. ግንባታውን አንድ ብሎ የጀመረው ብሔራዊ ስቴድየም፣ የመጀመሪያውን የግንባታ ምዕራፍ በ2012 ዓ.ም. ቢያጠናቅቅም፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የምዕራፍ ሁለት ግንባታው በዕቅዱ መሠረት ለማከናወን እንዳልተቻለ ሲነገር መቆየቱ ይታወቃል:: የስቴድየሙ ግንባታ በውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት መቆሙን የሚገልጹ የተለያዩ ዘገባዎች ሰሞኑን በማህበራዊ የትስስር ገጾች ሲዘዋወሩ ታይተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ከእውነት የራቀ መሆኑን አዲስ ዘመን ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች አረጋግጧል።
የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታው ተቀዛቀዘ እንጂ እንዳልቆመ የገለጹት የአዲስ ዘመን ምንጮች፣ ግንባታው በነበረበት ፍጥነት እንዳልቀጠለ ጠቁመዋል። ለዚህ ምክንያት ደግሞ ተቋራጩ የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርግ በመንግስት ደረጃ ንግግር እየተደረገበት በመሆኑ ነው:: ግንባታው ቆሟል የሚባለውም ከተቋራጩ ጋር ውል ሲቋረጥ ብቻ እንደሆነ ታውቋል።
ከአዲስ አበባ ስቴድየም እድሳት ጋር ተያይዞም በተለያዩ ደረጃዎች እድሳቱ እየተከናወነ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ተችሏል። የመጫወቻ ሜዳ እና የተጫዋቾች ማረፊያ፣ የክብር እንግዶችና የተመልካች ንጽህና ቤቶችን የሚመለከተው የመጀመሪያው ደረጃ እድሳት መጠናቀቁ የተጠቆመ ሲሆን፣ ቀጣዩን ስራ ለማስጀመርም ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በሂደት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። ቀሪው የግንባታ ስራ በውል የሚከናወን እንዲሁም በካፍ ስታንዳርድ መሰረት ቁሳቁሶችን ማሟላት ደግሞ በግዢ እንደሚከናወንም ተገልጿል።
ግንባታዎቹን በሚመለከት ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት የት ደርሷል የሚለውን የመገናኛ ብዙሃንን በመጋበዝ ማብራሪያ ይሰጥ ነበር:: ይሁንና በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸውን ተከትሎ ከእውቀት ውጭ እንዲሁም ያለውን ነገር ካለመረዳት አግባብ ያልሆኑ ትችቶች ሲቀርቡ ይስተዋላል:: በመሆኑም ውጤት ለማሳየት በማቀድ መግለጫና ማብራሪያ ሳይሰጥ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል::
በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ እየተገነባ ያለው ስቴድየም 62 ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም አለው። ከስቴድየሙ እግር ኳስ ሜዳ ሳር ማልበስና የመሮጫ ትራክ በስተቀር በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያው ምእራፍ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን ይህም አጠቃላይ የህንፃውን መዋቅር ጨምሮ የስፖርተኞች ማረፊያ፣ ቢሮዎች፣ የጋዜጠኞች ማስተናገጃ ወዘተ ያካትታል።
የመጀመሪያው ምእራፍ የፕሮጀክቱ ሥራ በተወሰነ ጊዜ የዘገየ ሲሆን ለዚህም ምክንያቶቹ ከውጭ የሚገቡ እቃዎች በጊዜው አለመድረስና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ተጠቅሰዋል።
ሁለተኛው ምእራፍ የስቴድየሙ ፕሮጀክት ከሚካተቱት ሥራዎች መካከል የመጫወቻ ሜዳውን ሳር ማልበስ፣ የመሮጫ ትራክ ማንጠፍ፣ የስታዲየሙን ጣሪያ ማልበስና ወንበር መግጠም ይገኙበታል። ከዚህም ሌላ ሰው ሰራሽ ሀይቅ፣ የሄሊኮፍተር ማረፊያ፣ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራ ሌሎች በርካታ ስራዎች ይከናወናሉ ተብሏል። ለመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ከ2.47 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገ ከዚህ ቀደም የተገለጸ ሲሆን፣ ሁለተኛው ምእራፍ የግንባታ ሥራ ከዚህ የበለጠ ወጪ ይጠይቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ስቴድየሙ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮችን ከማስተናገድ በተጨማሪ ሌሎች እንደ አትሌቲክስ አይነት ውድድሮችን ለማስተናገድ ምቹ አጋጣሚን የሚፈጥር ነው። የሁለተኛውን ምዕራፍ ግንባታ በዘጠኝ መቶ ቀናት ለማጠናቀቅ የታሰበ ቢሆንም ከተያዘው ቀን በላይ እንደሚያስፈልግ ተረጋግጧል። ሁለተኛውን ዙር ግንባታ ለማጠናቀቅ ከ 5.5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስወጣ ይጠበቃል።
የአደይ አበባ ስታዲየም ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከ 62,000 በላይ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም እንዳለው ይጠበቃል። ይህ ውብ ስታዲየም ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሎች (ሳውንድ ፕሩፍ የሆነ)፣ 8 ቪ አይ ፒ ክፍሎች፣ 2 ቪ ቪ አይ ፒ ክፍሎች ፣ ከ 1,000 በላይ መፀዳጃ ቤቶች (የወንድ እና የሴት )፣ 10 የሚዲያ ክፍሎች፣ ከ15 በላይ ሬስቶራንቶች (በአንድ ጊዜ ከ2,500 ሰው በላይ ማስተናገድ የሚችሉ) እና 7 ሊፍቶች እንደሚኖሩት ይጠበቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2015