አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያውያን የውጭ ተጽእኖን መቋቋም የሚያስችል የዲፕሎማሲ ስራ በተናበበና በተቀናጀ መንገድ መስራት እንደሚጠበቅባቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በአማራ ክልል በሰላማዊ ሰልፍ ድጋፍ ላደረጉ ዜጎች ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግና እና አርበኛ ነው፡፡ በተለያዩ ዘመናት ለተቃጣበት ጥቃት ሁሉ ያልተበገረ፤ ኢትዮጵያን በጽናት፣ በመስዕዋትነት ክብርና ነጻቷን አስጠብቆ ያጸና ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያም በረጅም ታሪኳ ህልውናዋን እና አድነቷን ያስከበረችው እና እያስከበረች ያለችው ደም በተከፈለበት መስዕዋትነት ነው።
ሉዓላዊነታችን የሚዳፈር፤ የአገራችን ክብር የሚያዋርድ የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላት በመጣ ጊዜ ሁሉ እኛ ኢትዮጵያውያን ሆ! ብለን በአንድነት በመቆም ድል እየተቀዳጀን እና አሸናፊ እየሆነ መምጣታችን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የአሁኑ ትውልድም በተግባር እየሰራው የሚገኝ እውነት ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራና አፋር ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ በማካሄድ ወገኖቻችንን የገደለ፣ አካል ያጎደለ፣ ሀብትና ንብረት የዘረፈና ያወደመ ወንጀለኛ እና አረመኔ ቡድን ነው። ይሁን እንጂ ከመላ ኢትዮጵያውያን ጋር ሁነን ባደረግነው ርብርብ ወረራውን በመቀልበስ ችለናል። አሁንም በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን እና ጥምር ኃይላችን ወያኔ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በጀግንነት ወኔ ተጋድሎ እያደረገ ይገኛል።
ጦርነቱ የውክልና ጦርነት እንጂ ከወያኔ ጋር ብቻ የሚደረግ አይደለም ያሉት ዶክተር ይልቃል፤ የውክልና ጦርነት ለመሆኑ የአማራና የአፋር ሕዝብ ሲጠቃ፣ ሲገደል፣ ሲፈናቀል፣ ሀብትና ንብረቱ ሲዘረፍና ሲወረር ምንም ያልተነፈሱት ምዕራባውያን ኃይሎች ተልካሻ ምክንያት እያቀረቡ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲና የሚዲያ ጫና ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
አንዳንድ ምዕራባውያን እና ታሪካዊ ጠላቶቻችን ለወያኔ እየሰጡት የሚገኘው የገንዘብ፣ የዲፕሎማሲ እና የሚዲያ ድጋፍ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና አንድነት የሚዳፈር በመሆኑ በጽኑ እናወግዘዋለን ብለዋል።
በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለው ጫና፣ ወከባና ዛቻም ዓለምአቀፉን ሕግ፣ መርህና አሰራር የሚቃረን ነው። ከዚህ የተዛባ እና ከዓለም አቀፍ ሕግ ተቃራኒ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ አጥብቀን እንጠይቃለን ሲሉም አሳስበዋል።
የወያኔን መደገፍ ኢትዮጵያን ማዳከምና ማፍረስ፣ በወረራ ጥቃት በደረሰባቸው ወገኖቻችን ላይ መሳለቅ፣ አሸባሪና በሕዝቦች ላይ ግፍ የፈጸመ ዘረኛ፣ ወንጀለኛ ቡድንን መደገፍ ነው። በመሆኑም የአገራችን ሉዓላዊነት በማስከበር የውስጥ ችግር በውስጥ እንዲፈታ አንዳንድ የምዕራባውያን ኃይሎች ከጣልቃ ገብነት አሰራራችሁ በመቆጠብ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ እንጠይቃለን ብለዋል።
ዶክተር ይልቃል እንደተናገሩት፤ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደተለመደው በጽናት እና በአርበኝነት ስሜት በአንድነት በመቆም የአገራችንን ሉዓላዊነት የምናስከበር ሕዝቦች እንጂ በፍርሃት፣ በተጽዕኖ ነጻነታችንን አሳልፈን ለማንም የማንሰጥ ለመሆኑ የቅኝ ግዛት የአርበኝነት ተጋድሏችን ምስክር ነው። አሁን ለገጠመን የውጭ ተጽዕኖ የማንበገር ለመሆኑ ከጫፍ እስከ ጫፍ የምናሰማው የአንድነት ድምጻችን ማረጋገጫ ነው።
በሌላ በኩል በአንድ አገር ውስጥ የሚፈጠር ችግር በራሱ በአገር ውስጥ ጉዳይ ታይቶ የሚፈታ መሆኑን በውል በመገንዘብ የውጭ ጣልቃገብነት ትክክል አለመሆኑንና ጣልቃ ገብነትን በማውገዝ የአገራችን ሉዓላዊነት እንድናስከብር ከጎናችን በመቆም ያልተቋረጠ ድጋፍ ለሚያደርጉልን ወዳጅ አገሮች፣ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ምስጋና እናቀርባለን ሲሉም ገልጸዋል።
በመሆኑም ሉዓላዊነታችንን ማስከበር የይሁንታ ጉዳይ ሳይሆን ተፈጥሯዊ መብታችን በመሆኑ ሁልጊዜም እንደምናሸንፍ አልጠራጠርም። ሉዓላዊነታችንና አንድነታችን በውጭ ተጽእኖ እንዳይደናቀፍ የውጭ ዲፕሎማሲ ስራችን በሚገባ አውቀንና ለይተን ለመስራት መረባረብ ይገባናል ሲሉም አሳስበዋል።
የሉዓላዊነታችን መገለጫ የሆነውንና ጸረ ሕዝብ በሆኑ ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ፣ የአርበኝነት ስሜት እየጎመራ እንዲሔድ፣ ሉዓላዊነታችንና አንድነታችን እየጠነከረ እንዲሔድ ደሙን እያፈሰሰ፤ አጥንቱን እየከሰከሰ ከሚገኘው ጦር ኃይላችን ጎን በመቆም የተለመደውን ድጋፋችንን እና ደጀንነታችን አጠናክረን እንቀጥል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን የውጭ ጣልቃ ገብነት ተጽዕኖን መቋቋም የምንችለው የውስጥ አንድነታችን የበለጠ በማጠናከር በመሆኑ በውስጥ ያሉ ልዩነቶችን ለጊዜው ወደጎን በመተው እጅ ለእጅ ተያይዘን የውጭ ጣልቃ ገብነትና ተጽእኖን በአርበኝነት ስሜት፤ ተደራጅተንና ተቀናጅተን፣ አንድ ሁነን ተጽእኖውን ለመቋቋም በአንድነት እንድንነሳ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን ጦርነቱን የሚሸከም ኢኮኖሚ ለመገንባት ሁላችንም በተሰለፍንበት ዘርፍ ሁሉ ውጤታማ ሁነን ልማትን እናፋጥን ብለዋል፡፡
በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምኖር ኢትዮጵያውያን በአርበኝነት ስሜት በአንድነት በመነሳት የውጭ ተጽእኖን መቋቋም የሚያስችል የዲፕሎማሲ ስራ በተናበበና በተቀናጀ መንገድ ያለምንም መታከትና መዘናጋት እንስራ በማለት ጥሪ ያቀረቡት ዶክተር ይልቃል፤ የአገራችን ሉዓላዊነትንና አንድነት ለማስከበር በጀግንነት እየተፋለመ ለሚገኘው ጀግናው መከላከያ ሠራዊትና ጥምር ኃይላችን በራሴና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ስም ያለኝን ታላቅ አክብሮት እና ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14 ቀን 25 ዓም