ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ትምህርት እንዴት ይዟችኋል? በደንብ እያነበባችሁ ነው አይደል? ከመጀመሪያው ጀምሮ ማንበብን ልምምድ ካደረጋችሁ ውጤታማ ትሆናላችሁ። ስለዚህም ጎበዝ ተማሪ ለመሆን ከፈለጋችሁ ዛሬ የተማራችሁትን ዛሬውኑ አንብቡ።ተጨማሪ ነገሮችን በማከልም አቅማችሁን ማጎልበት አለባችሁ። ልጆች ዛሬ ይዤላችሁ የመጣሁት በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ሚኒስትሪ ተፈታኝ የሆኑትን የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችንና ዝግጅታቸውን ነው።ስለ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ጥቅምም በደንብ ነግረውኛልና ከእነርሱ ተሞክሮ እንደምትወስዱ እምነት አለኝ።
መጀመሪያ ያነጋገርኳት ልጅ ማን መሰለቻችሁ? ደራርቱ ድሪባ ትባላለች።ከላይ እንዳልኳችሁ የዘንድሮ የስምንተኛ ክፍል ተፈታኝ ናት። በትምህርቷ ደግሞ በጣም ጎበዝና ጥንቁቅ ልጅ ነች። በትምህርት ቤቷ ስርዓተ ጾታ ክበብ ውስጥ፤ የጤና ክበብ ውስጥና የሚኒሚዲያ ክበብ ውስጥ ትሳተፋለች። በዚህም በርካታ ለውጦችን በራሷ ላይ አምጥታለች። በተለይ ልዩ ተሰጥኦዋን አውቃ እንድትቀጥልበት ሆናለች።ለዚህም በአብነት ያነሳችልን የቴአትር መስራት አቅሟን ማየቷን ነው።
ልጆች ደራርቱ የስምንተኛ ክፍል ተፈታኝ በመሆኗ ከዚህ ቀደም ሲመቻት እንጂ ጊዜ ወስዳ ሳታጠና የቆየችበትን የአጠናን ዘዴ ቀይራለች።አሁን ዛሬ የተማረችውን ዛሬ እንጂ ለነገ አትተውም። ጎን ለጎን ለፈተና ያግዙኛል ብላ የምታስበውን ታነባለችም።ለዚህ ደግሞ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ድጋፍ እንደሆነላት ታነሳለች። የትምህርቱ ዝግጅቱና የመማር ማስተማሩ ሥራ ብዙ ምቹ ሁኔታን የፈጠረላት እንደሆነም ታምናለች።ከስር ከስር የሚሰጣቸውን ትምህርት ለማጥናት ትሞክራለች።
በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ነገሮች እንደቀለሉም ትናገራለች። ታችኛው ክፍል ድረስ ወርዶ ከማጥናት ገላግሎናል። በዚያ ላይ ለትምህርት ደረጃው የሚመጥን ተደርጎ ስለተዘጋጀ ትምህርቱ ከዚህ ቀደሙ የሚቀል ነው።እናም ስናጠናና ለፈተና ስንዘጋጅ አንቸገርበትም ትላለች። አሁን ገና ትምህርት ከመጀመሩ ጀምሮ አጠናኗን እያስተካከለች በመሆኑም ደስተኛ ሆናለች።
ደራርቱ የእናቷን ህልም ለመኖር እየሰራች ትገኛለች። ይህም እናቷ ጎበዝና የተማረች ብትሆንም ዶክተር የመሆን ህልሟ ጋር በችግር ምክንያት ልትደርስ አልቻለችም።እናም ደራርቱ ይህንን ህልሟን መመለስ ትሻለች።በህክምና ሙያው ተመርቃ ማህበረሰቡን በማገልገል ውስጥ እናቷን ማስደሰት ትፈልጋለች። ለዚህም ገና ከውጥኑ ጠንካራ ተማሪ ለመሆን እየተጋች ነው።
ልጆች ደራርቱ ለእናንተ የምትመክረው ነገር አላት።የመጀመሪያው ትምህርታችሁን ትኩረት አድርጉ የሚለው ነው። በትምህርት ማንኛውንም ነገር መለወጥ ይቻላል። ማንም ሰነፍ ሆኖ አልተፈጠረም።የመጠቀምና የመስራት ጉዳይ ነው ልዩነቶችን የሚያመጣው።እናም በርትታችሁ የምታነቡና ትምህርታችሁን ወደ ተግባር የምትለውጡ ልጆች ከሆናችሁ የማትደርሱበት ነገር አይኖርም። የማትፈቱት ችግርም እንዲሁ ትላለች።
ሌላው የመከረችው ነገር እንደ አገር ለተማሪዎች የተሰጠው ነገር እጅግ የሚያስደስት ነው።ቤተሰቦቻችን አርፈው፤ እኛም ሳንጨናነቅ የምገባ ስርዓት ተጀምሮልን እንድንማር ሆነናል። የደንብ ልብስና የትምህርት ቁሳቁስም ተሟልቶልናል። ለእኛ የሚያስፈልገው ደግሞ ይህ ብቻ ነው። ስለዚህ ለቤተሰቦቻችን ደስታ ለአገራችን ውለታ ለመክፈል በጣም ጎበዝ ተማሪና አትራፊ መሆን ይገባናል የሚለው ነው። በተለይም እምቅ ችሎታ ያላቸው ልጆች ይህንን እድል መጠቀምና ለማህበረሰቡም ሆነ ለራሳቸው ሕይወት ለውጥ መስራት እንዳለባቸው ታሳስባለች።
እንደ ደራርቱ ሁላ በካራ አሎ ቅድመ መደበኛና መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የምትማረው ፍሬጽዮን የሺጥላ ስትሆን፤ እርሷም የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ናት። በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የሚጀመረውን የስምንተኛ ክፍል ፈተና ትወስዳለችም።ስለዚህም ገና ከአሁኑ ራሷን ለፈተናው እያዘጋጀች ትገኛለች።በዋናነት ዝግጅቷን እያደረገች ያለችውም ፕሮግራም አውጥታ በማጥናት ነው።ጎን ለጎን ባላት ጊዜ ከተማሪዎች ጋር በመሆን ታነባለች።
አዲሱ የትምህርት ስርዓትን በጣም ወዳዋለች። ምክንያቱም በእርሱ ውስጥ አገሯን ማየት ጀምራለች። ስለውጪው ባህልና ወግ ሳይሆን ስለ አገራችን ማንነትና ምንነት በሚገባ ያሳውቃልና የማታውቀውን ነገር እንድታይ አድርጓታል።በዚያ ላይ በስነምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ፤ ባህላቸውን ያወቁ ዜጎች እንዲፈጠሩ ለማድረግ እንደ አንድ ትምህርት የሚሰጠው ነገር ብዙ ነገሮችን እንደሚቀይር ታስባለች። ከሁሉም በላይ ግን ልዩ ተሰጥኦዋቸውን አውቀው እንዲጓዙና የሥራ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ ስለሚያግዛቸው ደስተኛ አድርጓታል።
ልጆች በእነ ፍሬጽዮን ትምህርት ቤት ልዩ የመማር ማስተማር ሥራ መከናወኑም ለፈተና ዝግጅታቸው እጅጉን እንደሚያግዝ ፍሬጽዮን ትናገራለች።ለአብነት የጠቀሰችውም ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎች በማሰብ የቅዳሜ ትምህርትን ማስጀመሩን ነው።ትምህርቱ ሲሰጥ ከሰኞ እስከ አርብ የተማሩትን የሚከለስበት በመሆኑ ለጥናት ነገሮችን ያቀልላቸዋል። በዚያ ላይ ምን ያህል እውቀት እንደጨበጡ ያረጋግጥላቸዋል።
ሌላው ከትምህርትቤታቸው የወደደችው ነገር ተማሪዎች በህብረትም ሆነ በተናጠል ሳይጨናነቁ እንዲያጠኑና እንዲሰሩ ለማድረግ የተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታን ነው። ይህም ‹‹ የንባብ ፓርክ›› ጉዳይ ሲሆን፤ በአጸድ የተሸፈነና ለማንበብ የሚማርክ እንደሆነ ታነሳለች። ስለዚህም ተማሪዎች የተፈጠረላቸውን መልካም አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመው ውጤታማ መሆን አለባቸውና ይህንን ያድርጉ ስትል ትመክራለች።እኔም ተሞክሯቸው በተለይም ለተፈታኞች ይጠቅማልና ሁኑበት እያልኩ ለዛሬ አበቃሁ። መልካም ሰንበት ይሁንላችሁ !!
ጽጌረዳ ጫንያው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም