ዝነኛው የፈረንሳይ የእግር ኳስ መጽሔት በየዓመቱ ለምርጥ የአውሮፓ እግር ኳስ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች የሚያበረክተው የባልን ድ ኦር ሽልማት ባለፈው ሰኞ ተከናውኗል። ከአስር ዓመታት በላይ በሁለቱ ከዋክብት ሊዮኔል ሜሲና ክርስቲያና ሮናልዶ ፍፁም የበላይነት ተይዞ የቆየው ይህ ሽልማት ወደ አዳዲስ ኮከቦች ፊቱን አዙርዋል።ነገር ግን ዘንድሮም ወደ አፍሪካውያን ወይም ጥቁር ተጫዋቾች ሳይመጣ ቀርቷል።ፈረንሳዊው የሪያል ማድሪድ ኮከብ ካሪም ቤንዜማ ለመጀመሪያ ጊዜ ሽልማቱን ሊወስድ ችሏል።
ሽልማቱ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ አጨቃጫቂ ሆኖ ባያልፍም የቆዳ ቀለማቸው ጥቁር በመሆኑ ብቻ ይህን ታላቅ ሽልማት ማሸነፍ ሲገባቸው ያላሸነፉ ተጫዋቾች ጉዳይ ሁልግዜም አነጋጋሪ ነው። ለአብነት ያህል ያለፈው ዓመት ሽልማት መስፈርቱ ከዘረኝነት የፀዳ ቢሆን ኖሮ የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድንና የቼልሲው ግብ ጠባቂ ኤድዋርድ ሜንዲ የምርጥ ግብ ጠባቂዎችን ሽልማት ማሸነፍ ይገባው እንደነበር በርካቶች በብዙ ማሳያዎች ይከራከራሉ።
ሜንዲ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በውድድር ዓመቱ ከቼልሲ ጋር አሸንፏል፣ የሱፐር ካፕ ዋንጫን አንስቷል፣ በዚህም የአውሮፓ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሽልማትን ማሸነፍ ችሏል። በብዙ ጨዋታዎች ጎል ሳይቆጠርበት በመውጣት ቀዳሚ ነው፣ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግም በብዙ ጨዋታዎች ጎል ሳይቆጠርበት በመውጣት ሁለተኛው ግብ ጠባቂ ነው፣ በቻምፒዮንስ ሊግ ሶስት ጎል ብቻ ተቆጥረውበታል፣ የባሎን ድ ኦርን ሽልማት ያሸነፈው ግን ይህን ሁሉ ስኬት በውድድር ዓመቱ የተጎናጸፈው ሜንዲ ሳይሆን ከጣሊያን ብሔራዊ ቡድን ጋር የአውሮፓ ዋንጫን ያሳካው ዶናሮማ ነው። እውነታው ግን አፍሪካውያን በእግር ኳሱ ዓለም እውቅና የላቸውም፣ አፍሪካውያን ተጫዋቾች ጥቁር በመሆናቸው ብቻ ብዙውን ጊዜ ማግኘት ያለባቸውን ነገር እንደማያገኙ ማሳያ ነው። ይህም በበርካቶች ዘንድ ጥያቄ ማስነሳቱ የተለመደ ነው።
አፍሪካውያን ወይም ጥቁር ተጫዋቾች ይህን ሽልማት እኤአ በ1995 ላይቤሪያዊው ኮከብ ጆርጅ ዊሃ ካሸነፈ ወዲህ ማሸነፍ አለመቻላቸው የሁልጊዜም ጥያቄ ነው። በተለይም አፍሪካውያን ተጫዋቾች ከሌሎች ተጫዋቾች በተሻለ ስኬታማ በነበሩባቸው በርካታ ዓመታት ይህን ሽልማት አለማግኘታቸው በአፍሪካውያን ዘንድ ቁጭት እንደፈጠረ ነው። ለአብነት ያህል በቅርቡ 2019 ላይ ከሊቨርፑል ጋር አስደናቂ የውድድር ዓመት ያሳለፉት ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኔና ግብጻዊው ሞሐመድ ሳላህ ሽልማቱን የማሸነፍ ትልቅ እድል እያላቸውና እየተገባቸው ለሊዮኔል ሜሲ መሰጠቱ በርካቶችን ያበሳጨ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
አፍሪካውያን ተጫዋቾች ከጆርጅ ዊሃ በኋላ ለዚህ ሽልማት አለመብቃታቸው የተለያየ መላምትና ምክንያት ይደረደራል። የቀድሞው ሴኔጋላዊ ኮከብ ፈርዲናንድ ኮሊ በአንድ ወቅት አፍሪካውያን ይህን ሽልማት ማሸነፍ ከማይችሉበት ምክንያት አንዱ ብሔራዊ ቡድኖቻቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ ባለመሆናቸው መሆኑን ጠቅሷል። ይሁን እንጂ ይህ ለብዙዎች አሳማኝ አይደለም። ምክንያቱም ሊዮኔል ሜሲ ከአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ጋር የዓለም ዋንጫን ሳያነሳ ሰባት ሽልማቶችን ጠራርጎ ወስዷል።
ባለፉት በርካታ ዓመታት ከክለቡ ሊቨርፑል ጋር አስደናቂ ጊዜን ያሳለፈው አሁንም ግብፃዊው ኮከብ ሳላህ፣ የባሎን ድ ኦር ሽልማት ከዓለም ዋንጫ ጋር መቆራኘቱን እንዲህ ሲል ይቃወማል ‹‹በአፍሪካ ተጫዋቾች ማሸነፍ የነበረባቸው ብዙ የባሎን ዶር ሽልማቶች አሉ፣ ነገር ግን አልተሸለሙም። ካልተስማማችሁ እባካችሁን በአንድ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ ከ20 በላይ ግቦችን ያስቆጠረና ሊጉን ያሸነፈ አፍሪካዊ ተጫ ዋች እንደነበር ላስታውሳችሁ። እንዲሁም በመጨረሻ አንድ አፍሪካዊ ተጫዋች በቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ያልደረሰበትን አንድ ወቅት ይጥቀሱ። የዓለም ዋንጫን ስለማሸነፍ እየተናገራችሁ ከሆነ ይህ ማለት ባሎን ድ ኦር በየዓመቱ በሚባል ደረጃ በስህተት ተሸልሟል ማለት ነው፣ ምክንያቱም የዚህ ሽልማት አብዛኛዎቹ አሸናፊዎች የዓለም ዋንጫ የላቸውም።››
ታሪካዊው የካሜሩን ኮከብ ሮጀር ሚላም በዚህ ረገድ የተለየ እይታ ወይም አስተያየት አለው። እንደ ሚላ እምነት ሽልማቱን የሚሰጠው ተቋም አፍሪካውያን እንዲያሸንፉ አይፈልግም፣ ሊዮኔል ሜሲ ይህን ሽልማት ደጋግሞ የሚያሸንፍበት መሰረትም ከስፖርታዊ ብቃት ይልቅ ከንግድ ጋር የተቆራኘ ነው። ሚላ ጆርጅ ዊሃ ብቸኛውን ሽልማት ባሸነፈበት ዓመት ሸላሚዎቹ ዊሃ የነበረውን በግልጽ የሚታይ ብቃት መሸሸግ ስለማይችሉ ነገሮች አስገዳጅ ሆነውባቸው ነው ይላል።
አንድ ቀን ግን ነገሮች ተቀይረው አፍሪካውያን ተጫዋቾች ይህን ዝነኛ ሽልማት ደጋግመው እንደ ሚያሸንፉ ሮጀር ሚላ ተስፋ አለው። ‹‹ነገሮች የሚለወጡ ይመስለኛል፣ ግብጻዊው ኮከብ ሳላህ አስደናቂ ነገር እያሳየ ነው፣ ሴኔጋላዊው ማኔ የሚሰራው ድንቅ ነገርም ያልተለመደ ነው፣ ሽልማቱና ሰዎች የመርህ ተገዢ መሆን አለባቸው፣ የባልን ድ ኦር ሽልማት ለአፍሪካ እግር ኳስ የሚጨምረው ነገር አለ›› የሚለው ሚላ የእግር ኳስ ዓለም አቀፋዊ እድገት እንደ አፍሪካ ባሉ አህጉራት እንዲቀጥል ከተፈለገ እግር ኳሱን የሚመሩ አካላት በሃቅ መስራት እንዳለባቸው ይመክራል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም