ኢትዮጵያን በስፖርቱ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካስጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ናቸው። እኚህ ታላቅ ሰው ከጋዜጠኝነት ሙያ ባለፈ በስፖርቱ ዘርፍ የተለያዩ አገልግሎቶችን በማበርከት የኢትዮጵያን ስፖርት ከምስረታው አንስቶ የደገፉ ናቸው። አቶ ፍቅሩ በዓለም አቀፍ የስፖርት ማህበራትም በአማካሪነትና ሌሎች ስራዎች ያገለገሉ ሰው ናቸው። የስፖርት ትምህርት ቤትና ማህደር የነበሩት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ባሳለፍነው ሳምንት በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወቃል። የቀብር ስነስርዓታቸውም ረጅም ዓመታትን በኖሩበት ፈረንሳይ የተፈጸመ ሲሆን፤ በአገራቸው ኢትዮጵያም ስራዎቻቸውን የሚዘክሩ መርሃ ግብሮች ተከናውነዋል።
ከእነዚህ መካከል አንዱ በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ከትናንት በስቲያ ምሽት የተዘጋጀው ዝክረ ፍቅሩ ኪዳኔ ዋነኛው ነው። አቶ ፍቅሩ በተለይ የሚታወቁት በስፖርት ጋዜጠኝነት ሲሆን፤ በጋዜጣ እና በሬዲዮ ስፖርትን በመዘገብም ቀዳሚው ሰው ናቸው። በአማርኛ፣ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎችም ከኢትዮጵያው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እስከ ትልልቆቹ የፈረንሳይ ጋዜጦችና መጽሄቶችም ስፖርታዊ ዘገባዎቻቸውን አስነብበዋል። ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆንም የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርን በመመስረትና በመምራት የማይዘነጋ ሚና አላቸው። ይህንን የሚዘክር መድረክም በሙያ ልጆቻቸው ማህበር የተካሄደ ሲሆን፤ እርሳቸውን የሚያውቁ እንግዶችም በቦታው ተገኝተዋል።
በዝክር መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ካደረጉ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ትውውቃቸውን በማስታወስ ነበር ንግግሩን የጀመረው። ኃይሌ በሲድኒ ኦሊምፒክ ሲያሸንፍ፤ አቶ ፍቅሩ ከዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች ጋር በመሆን በስታዲየም የተገኙ ሲሆን ደስታቸውንም አጠገቡ ሄደው ነበር የገለጹለት። ከዚያን በኋላም ትውውቃቸው ጠንክሮ በተለያዩ ውድድሮች ላይ በቅድሚያ የሚያገኛቸው ሰው ናቸው። እንደ ቤተሰብም ይጠያየቁ ነበር። በቅርቡ የተሰማው ህልፈታቸው አሳዛኝ ቢሆንም በሕይወት ሳሉ ሃውልታቸውን ሰርተው ካለፉ ሰዎች መካከል መሆናቸውን ጀግናው አትሌት ተናግሯል። አቶ ፍቅሩ አፍሪካዊ ሆነው በዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት ውስጥ ነጮችን ማማከራቸውም ምን ያህል ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደሆኑ የሚያሳይ መሆኑንም አብራርቷል።
ሌላኛው በመድረኩ ላይ ትዝታቸውን ያጋሩት የአቶ ፍቅሩ የረጅም ጊዜ ወዳጅ የሆኑትና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል ናቸው። በንግግራቸውም አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ለኢትዮጵያ፣ አፍሪካ እና ዓለም ስፖርት የተፈጠሩ ሰው መሆናቸውን አንስተዋል። ‹‹በዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት ስማቸው የተከበረ የስፖርት ማህደር›› መሆናቸውንና በየትኛውም ዘርፍ የኢትዮጵያ ጠበቃ እንደነበሩም በሃዘን ስሜት ውስጥ ሆነው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ አቶ ፍቅሩ ፈር ቀዳጅ ከሆኑባቸው ጉዳዮች መካል አንዱ የስፖርት ጋዜጠኝነት ሲሆን፤ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርንም በ1960ዓ.ም በመመስረትና በአመራርነትም አገልግለዋል። ኑሯቸውን በፈረንሳይ ካደረጉም በኋላም ማህበሩ በተለያየ ጊዜ አዳዲስ አመራሮችን ቢቀያይርም ከጎኑ በመሆንና፤ ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ለአባላቱ የትኛውንም ሙያዊና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በማማከርና ልምዳቸውን በማካፈል ቆይተዋል። በመሆኑም ማህበሩ ታላቅ ሰው ማጣቱን የማህበሩ ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ነዋይ ይመር ገልጿል። ላበረከቱት አስተዋጽኦም ማህበሩ ከአራት ዓመታት በፊት የሕይወት ዘመን ልዩ ተሸላሚ አድርጓቸው ነበር። በጊዜውም ለጀማሪ የስፖርት ጋዜጠኞች መታሰቢያ ይሆንላቸው ዘንድ መጠየቃቸውንና የትኛውም ባለሙያ ሲፈልጋቸው በቅርበት የሚገኙ ሰው እንደነበሩም አስታውሷል።
አቶ ፍቅሩ የኢትዮጵያውን የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ብቻም ሳይሆን የአፍሪካ እና የዓለም የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ምስረታ ላይም ቀዳሚው ሰው ነበሩ። ይህንን ተከትሎም የማህበራቱ አመራሮች በተንቀሳቃሽ ምስል ሃዘናቸውን ገልጸዋል። አቶ ፍቅሩ የክብር አባል የሆኑበት የዓለም የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ጂያኒ ሜርሎ፤ ማህበሩ አማካሪው የነበሩ ትልቅ ሰውን አጥቷል ብሏል። የአፍሪካ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ሚሼል ኦቢ በበኩሉ፤ በማህበሩ ምስረታ እንዲሁም አቅጣጫዎችን በመስጠት ሚናቸው ከፍተኛ እንደነበር አውስቷል። የጋዜጠኝነትን ፍልስፍና በተግባር ያሳዩ መሆናቸውንም ከስራቸው መረዳት እንደሚቻልም ነው የገለጹት።
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ በመድረኩ ላይ ተገኝተው ሃዘናቸውን ገልጸዋል። በዚህም አቶ ፍቅሩ በኢትዮጵያ ፋና ወጊ ጋዜጠኛ ከመሆናቸው ባሻገር ኢትዮጵያን ያስቀደሙ የስፖርት ዲፕሎማት መሆናቸውንም ነው ያመላከቱት።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2015