በገጠር አካባቢ የተወለዱት ህፃናት እያዩ የሚያድጉትና ከፍ ሲሉም የሚሰሩት ስራ ነው እረኝነት። በገጠር ሴትም ሆነ ወንድ እረኝነትን ሳይሞክር እና ቤተሰቡን ከብቶች በመጠበቅ ሳያገለግል የሚያድግ ልጅ አይኖርም። የእረኝነት ስራው የሚሰራው ደግሞ ከአካባቢያቸው ራቅ ባለ የሚጋጥ ሳርና ውሃ ባለበት ቦታ ነውና ከብቶቹን የሚጠብቁት እረኞች ስንቃቸውን ይዘው ከቤታቸው ራቅ ብለው ይሄዳሉ። በዚህ ወቅት ታዲያ የተለያዩ አደጋዎችም ሊያጋጥማቸው ይችላል። ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ። በጎርፍ መወሰድ በዱር እንስሳ መነከስና መበላት እንዲሁም በሰዎች መደባደብ አልፎ ተርፎም አድበቶ ለማጥቃት በመጣ ጠላት የመሞት አደጋዎችን ያስተናግዳሉ።
በዛሬው የ‹‹ዶሴ›› አምዳችን ላስነብብ የፈለኩት ስለ እረኝነት ሳይሆን በእረኝነት ላይ ሆነው በአሰቃቂ ሁኔታ ስለተገደሉ ህጻናትና የፍትህ ውሳኔ ይሆናል።
ጓደኛሞች እረኞች
በጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ ደቦ ቀበሌ ነው የተወለዱት። ሕፃን ዘላለም ጀቦና ነፃነት ገብሬ ይባላሉ። ቤታቸው ጎን ለጎን በመሆኑ የጠበቀ ጉርብትና ካላቸው ቤተሰቦች ነው የተገኙት። ሕፃን ዘላለም ጀቦ ስድስት ዓመቷ ሲሆን ህፃን ነፃነት ገብሬ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረች። እድሜያቸው አቻ በመሆኑ እና የቤተሰቦቻቸው የጠበቀ ጉርብትና ልጆቹ ተዋደው እና ተግባብተው የእህትማማች ያህል አብረው እንዲያደጉ አድርጓቸዋል።
ዘላለም የተወለደች ጊዜ የነፃነት እናት እንደ እናትም እንደ እህትም ሆና ነበር የዘላለምን እናት ያረሰቻት። እርስ በእርስ የሚደጋገፉት ጎረቤታሞች ፍቅር ልጆቹ ላይም ተጋብቶ ሲወጡም ሲገቡም አይለያዩም ነበር። ነፃነት በእድሜ ከፍ ብትልም እረኝነትን የጀመሩት ግን አብረው ነበር። ለእረኝነት ሲወጡ እናቶቻቸው የቋጠሩላቸውን ምግብ ይዘው ከትናንሽ አለንጋቸው ጋር በጎቻቸውን እየነዱ ይውላሉ። ሜዳው ላይ ጨዋታው ቡረቃውን ደስታቸው ወደር የለውም ነበር። በፍቅር የሚጨዋወቱ ህፃናት ከሚኖሩበት አካባቢ ብዙም ርቀው ስለማይሄዱ አደጋ ይደርስብናል ብለው አስበው አያውቁም ነበር። ሁልጊዜ ደስታና ጨዋታ የማይለያቸው እነዚህ ንፁህ ፍጡራን ላይስ ማን ክፉ ይደርስ ይሆናል ብሎ ያስባል? አያድርስ ነው እንጂ!
ጓደኛሞቹ ገበሬዎች
አቶ ጀቦና ጎቼና አቶ ገበሬ ጎየቶ በጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ ደቦ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። የእነዚህ ጓደኛሞች ቤት አጠገብ ለአጠገብ ከመሆኑም ባሻገር ማሳቸውም ኩታ ገጠም በመሆኑ አብረው አርሰው ምርታቸውን አንድ ላይ ነበር የሚያስገቡት። ለገበያ እንኳን ሲወጡ የማይለያዩት ጓደኛሞች አንዱን ያለ አንዱ ማየት ይከብድ ነበር። የጎረቤታሞቹ ጥብቅ ቁርኝት ቤተሰቦቻቸውም አንድ ላይ የሚኖሩ ስለነበሩ አንድን ቤተሰብ ከአንዱ መለየት እጅግ ከባድ ነበር።
እነዚህን ጓደኛሞች አንድ ላይ ሰርተው የተሻለ ምርት በማግኘታቸው የሚቀኑባቸው ብዙዎች ነበሩ። በተለይም የእርሻ መሬታቸው በኩታ ገጠም የተሻለ የምርት ሂደትን በመከተላቸው ከመማር ይልቅ በቅናት መመልከትን ጀመሩ። ይባስ ብለው ዙሪያው ካለው መሬት የተሻለ ሆኖ የታያቸውን የእነዚህን ጠንካራ ገበሬዎች እርሻ ለመቀማት ዳር ዳር ይሉ ገቡ።
የእነሱን የቅናት ሀሳብም ሌሎች ላይ በማጋባት ስምንት የሚሆኑ ግብረ-አበሮችን አደራጁ። የሀሰት መስካሪዎችን አዘጋጁ። ቀጥለውም እናንተ የምታርሱት መሬት የእኛ እርስት ነው በማለት በአካባቢያቸው ባለ ፍርድ ቤት ከሰሷቸው። በህግና በስርዓት የሚመሩት ጓደኛሞቹ ገበሬዎች የይዞታ ማረጋገጫቸውን በማቅረብ መሬቱ የራሳቸው መሆኑን በማረጋገጥ ክርክሩን ረተው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ።
በዚህ እጅግ የተናደዱት መለሰ ሚጁ፣ ማቲዎስ አየለ፣ ገብረመድህን ሚጁ፣ ታምራት (ሸቶ) አሸናፊ፣ ታምራት ተስፋዬ፣ ባህሉ አየለ፣ ኢሳያስ ወርቁና ፍሬአየሁ አየለ በተባሉት ስምንት ሰዎች እነዚህን የሚዋደዱ ጎረቤታሞች የሚተነኩሱበት ነገር በየፊናቸው ማሰላሰል ጀመሩ።
የጥፋት ምክክር
ስምንቱ ለጥፋት የተሰባሰቡት ጓደኛሞች ከእለታት አንድ ቀን ከገበያ ሲመለሱ ክፋትንና ምቀኝነትን በልባቸው እንዳረገዙ አንድ መጠጥ ቤት ተቀመጡ። አንዱ “ቤታቸውን በላያቸው ላይ እናንድደው….” ሲል ሀሳቡን ያቀርባል። ሌላው “እነሱ ጠንካሮች ስለሆኑ መልስው ይተኩታል ሌላ ሀሳብ ….” በማለት ጓደኞቹን በጥያቄ አይን ይመለከታል። ሌለኛው “ለምን ማሳቸው ውስጥ ከብት አንነዳበትም…..?” ሲል ይጠይቃል። “ይህም አይሆንም ጎተራቸውን የሞላውን እህል እየበሉ ሊቆዩ ይችላሉ። ይልቅ ሌላ አንጀታቸውን ድብን የሚያደርግ ሀሳብ አለኝ” በማለት ሌላ ያለውን ሀሳቡን ለጓደኞቹ ያቀርባል።
ይህ ሀሳብ በስምንቱም የጥፋት ልኡካን ተቀባይነት ያገኝና እንዴት ማድረግ እንዳለባቸው ለመመካከር ለሳምንት ቀጠሮ ይዘው ይለያያሉ። ሁሉም ላሰብት እኩይ ተግባር ይጠቅመናል ያሉትን መሳሪያ በድብቅ ማሰናዳት ይቀጥላሉ።
ቀን አያውቁ ህጻናት
ሁለቱ ጓደኛማቾች ህጻናት ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ በጎች በመጠበቅ ላይ ነበሩ። ጓደኞቻቸው ምሳቸውን ለመብላት ወደ ቤታቸው በመመለሳቸው የተነሳ ብቻቸውን ጥላ ስር ቁጭ ብለው ቅልልቦሽ እየተጫወቱ ነበር። ሲሸናነፉ በመንጫጫትና በመሯሯጥ ትንሽ ሲስቁ ይቆዩና ወደ ዛፍ ጥላ ስር ከለል ብለው ጨዋታቸውን ይቀጥላሉ። በስድስት ዓመቷ ሕፃን ዘላለም ጀቦና የሰባት ዓመቷን ነፃነት ገብሬ የተባሉ ሴት ሕፃናት ባላሰቡት ጊዜ ነበር ድንገት ስምንት ጎረቤቶቻቸው ወደእነሱ አቅጣጫ ሲመጡ የተመለከቱት።
ልጆቹ ቀና ብለው አየተው የሚያውቋቸው ሰዎች መሆናቸውን ሲያረጋግጡ ያለምንም ስጋት ወደ ጨዋታቸው ተመለሱ። አሁንም ሰዎቹ ወደእነሱ እየቀረቡ ነው። እነሱ ጋር ለመድረስ ትንሽ ርቀት ሲቀራቸው አራቱ በተለያየ አቅጣጫ ተበታትነው አራቱ ደግሞ ወደእነሱ እየቀረቡ ነበር። ልጆቹ በጨዋታ ልባቸው ጠፍቶ ስለነበር ምንም ተኩረት አልሰጧቸውም። እነዚያ የጥፋት መልዕክተኞች ግን አጠገባቸው እንደደረሱ ልጆቹ ድምፅ ሲያሰሙ ሊያጥፋቸው ይችላሉ ብለው ባዘጋጁት ቁሳቁስ በማፈንና ትንፋሽ በመሳጣት፤ በመቀጠልም በገመድ በማነቅ የህፃናቱን ሕይወት አጠፉ።
ልጆቹን ከገደሉ በኋላም እንደ በግ በየሜዳው ላይ ዘርርው ጥለዋቸው በመሄድ የክፋት ሀሳባቸውን ያጠናቅቃሉ። ያን ጊዜ ምሳቸውን በልተው የሚመለሱት የህፃናቱ ጓደኞች የሆነውን በሙሉ ተመልክተው ኖሮ ልክ ሰዎቹ ከአካባቢው ዞር ሲሉ ጠብቀው እርዳታ ፍለጋ መንደሩን በጩኸት አቀለጡት። ጩኸቱን የሰሙት የአካባቢው ነዋሪዎች በቦታው ሲደርሱ የተመለከቱትን ማመን አቃታቸው። ዳሩ ነፍስ የማያቁ ህፃናት ሕይወት እንዲህ ባለ ሰቅጣጭ ሁኔታ ጠፍቶ መመልከትን ያህል ልብ ሰባሪ ነገር ከወዴት ሊገኝ?።
የህፃናቱ ወላጆች በቦታው ሲደርሱ የተመለከቱትን ማመን አቃቷቸው፤ ሁኔታው ኩፉኛ አስደንጋጭና ፈፅሞ ያልጠረጠሩት ስለነበርም ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ራሳቸውን ሳቱ። የሆነው ሁሉ ሆኖ ሰው ሲረጋጋ እርዳታ የጠየቁትን ህፃናት ስለጉዳዩ በመጠየቅ ጉዳዩን ይዘው ለህግ አካል አቀረቡ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ጉዳዩን እንደሰማ ልጆቹ የተመለከቷቸውን አራት ገዳዮች ለመያዝ ይሰማራል። የልባቸውን ሰረተው ቤታቸው የተከተቱት ጓደኛሞች ከየቤታቸው ተለቅመው ይወጣሉ። ፖሊሶች ባደረጉት ምርመራ አራቱ ሰዎች ብቻ ገዳይ አለመሆናቸውንና ሌሎች ግብረ-አበሮች አብረዋቸው እንደነበሩ ይደርስበታል። እነዚህን ተባባሪ ወንጀለኞች
ለመያዝ ባደርገው ጥረት የማህበረሰቡም ርብርብ ተጨምሮበት በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ለህፃናቱ ሞት ምክንያት የሆነው ቅናት መሆኑን፤ በማይረባ በመሬት ግጭት የተነሳ የህፃናቱ ሕይወት መጥፋቱን ፖሊስ ይናገራል። የአይን ምስክሮችን፤ የህክምና ማስረጃን በመጠቀም የቴክኒክና የታክቲክ ምርመራ ሲያደረጉ ከቆዩ በኋላ ፖሊስ ምርመራውን ጨርሶ ወደ ዓቃቤ ህግ በመላክ ውሳኔውን እየተጠባበቀ ይገኛል።
ውሳኔ
ዓቃቤ-ህግም ፖሊስ አጠናክሮ የላከለትን መረጃና ማስረጃ ተመልክቶ ተጠርጣሪዎቹን በከባድ የግድያ ወንጀል ክስ መሰረተባቸው።
ዓቃቤ ህግ ሐምሌ 6 ቀን 2013 ዓ.ም በጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ ደቦ ቀበሌ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ በጎች በመጠበቅ ላይ በነበሩት በስድስት ዓመቷ ሕፃን ዘላለም ጀቦና የሰባት ዓመቷን ነፃነት ገብሬ የተባሉ ሴት ሕፃናትን በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ በፈጸሙት ግለሰቦች ላይ ከባድ ቅጣት እንዲጣልባቸው ክሱን አቅርቧል።
የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰው መግደል ወንጀል የተከሰሱት ስምንት ግለሰቦች ላይ ውሳኔ ለመስጠት ቀን ቀጥሯል።
ሰው በመግደል ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች ‹‹ድርጊቱን አልፈፀምንም›› በሚል የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡ በመሆኑ፤ ዓቃቤ ህግ ያሰባሰባቸውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች በማቅረብ ተከራክሯል። ተከሳሾችም መከላከያ ማስረጃ በማቅረብ ያሰሙ ቢሆንም፤ በዓቃቤ ህግ የቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹን በተከሰሱበት አንቀፅ ሥር ‹‹ጥፋተኛ ናቸው›› በማለት ብይን ሰጠ።
ግራ ቀኙን ሲያከራክር የቆየው የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል በኢፌዴሪ የወንጀል ህግ ቁ539/1/ሀ/ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉ ተከሳሾችን በሞት እንዲቀጡ ወሰነ፤ ከ4ኛ እስከ 8ኛ ያሉ ተከሳሾችን ደግሞ በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ቁ671/1/ሀ/ እያንዳንዳቸውን የስድስት ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ቢወስንም በቅጣቱ ላይ የግራ ቀኙ የቅጣት አስተያየት አቅርበዋል።
የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ የጣለባቸው መለሰ ሚጁ ፣ማቲዎስ አየለ፣ ገብረመድህን ሚጁ፣ ታምራት (ሸቶ) አሸናፊ፣ ታምራት ተስፋዬ፣ ባህሉ አየለ፣ ኢሳያስ ወርቁና ፍሬአየሁ አየለ በተባሉት ስምንት ተከሳሾች ላይ ነው። ተከሳሾቹ ሐምሌ 6 ቀን 2013 ዓ.ም በጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ ደቦ ቀበሌ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ በጎች በመጠበቅ ላይ በነበሩት በስድስት ዓመቷ ሕፃን ዘላለም ጀቦና የሰባት ዓመቷን ነፃነት ገብሬ የተባሉ ሴት ሕፃናትን በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ በፈጸሙት ግለሰቦች ላይ ነው።
የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥቅምት 4/2015 በዋለው ችሎት በመሰለ ሚጁና በገብረመድህን ሚጁ ላይ እያንዳንዳቸው በ25 ዓመት ማቲዎስ አየለ በ21 ዓመት ከ5ኛ እስከ ስምንተኛ ያሉ ተከሳሾችን ደግሞ በአምስት ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል። መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ተመልሷል፤ ይግባኝም መብት ነው ተብሏል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2015