ለረዥም ሰዓት መቀመጥ ህይወትን አደጋ ላይ እንደሚጥል ምን ያህል ተገንዝበን ይሆን? አዎ ረዥም ሰዓት መቀመጥ በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ::
የካናዳው ዘ ዋሽንግተን ፖስት ድረ ገጽ አንድን ጥናት መነሻ አድርጐ እንዳስነበበው በቀን ውስጥ ለ11 ሰዓታት የሚቀመጡ ሰዎች የመሞት እድላቸው በ40 በመቶ ከፍ ይላል:: ይህም ከምንሰራው የሥራ ባህሪ ጋር በተያያዘ ሊከሰት የሚችል መሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል::
ብዙ መቀመጥ እንዴት ነው ለጉዳት የሚያጋልጠው?
ዘ ዋሸንግተን ፖስት ያወጣው ፅሁፍ እንዳሰፈረው ለረጅም ሰዓት መቀመጥ እጅግ በርካታ የጤና ችግሮች እንዲከሰቱ ምክንያት ይሆናል:: በዚህም ጡንቻዎቻችን አነስተኛ ስብ ብቻ እንዲያቃጥሉና የደም ዝውውሩ የተፋዘዘ እንዲሆን ያደርጋል:: አሲዳማ ስብ በልባችን ላይ እንዲከማች በማድረግም ለልብ ህመም ያጋልጣል::
የጀርባ አጥንት፣ የዳሌ ጡንቻዎች እንዳይፍታቱ በማድረግ በቀላሉ እንዳንቀሳቀስ ሁሉ ሊዳርገን የሚችልበት እድል ሰፊ ነው::
ለረዥም ሰዓት መቀመጥ በእግር ላይ የተቀላጠፈ የደም ዝውውር እንዳይኖር፣ አጥንቶቻችን ጥንካሬ እንዳይኖራቸው በማድረግ፣ አእምሮ እንዲፈዝ፣ የአንገት ፣ የትከሻና የጀርባ ህመም እንዲከሰት በማድረግ በኩልም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበርክታል::
ተጣጣፊ የጀርባ አጥንት እንዳይኖርና የዲስክ መንሸራተት እንዲከሰትም በማድረግ ረገድ ተጽእኖው በቀላሉ የሚታይ አይደለም::
በመሆኑም ከአምስት እስከ ስምንት ዓመታት ለረዥም ሰዓታት በመቀመጥ ጊዜያቸውን ያሳለፉ ሰዎች በቀን ከአንድ ሰዓት በታች ብቻ ከሚቀመጡ ሰዎች ጋር ሲነፃፀሩ 61 በመቶ የመሞት እድላቸው ሰፋ ያለ ነው::
ለተራዘመ ጊዜ መቀመጥ ወደ ሰውነታችን የገባው ምግብ በተገቢው መንገድ አገልግሎት ላይ እንዳይውል ያደርጋል:: እንቅስቃሴ ሲኖር የሰውነታችን ህዋሳት ምግቡን ለኃይል ምንጭነት እንደሚጠቀሙበት ይሆናል። ረጅም ሰዓት በመቀመጥ ውስጥ ግን እንቅስቃሴ ስለማይኖር በተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች ላይ አላስፈላጊ የሆኑ የስብ ክምችቶች እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል:: ይህም ወደ አላስፈላጊ ክብደት መጨመር ያመራል::
በዚህም ምክንያት የሰውነት ህዋሳት ከምግብ የሚገኙ ስኳር እና ቅባት የመሳሰሉ ንጥረ ነገሮችን እንደ ኃይል ምንጭነት የመጠቀም አቅማቸው እየቀነሰ፤ ሰውነታችን በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን የመቆጣጠር አቅሙን እያጣ፤ የስብ ክምችታችንም በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ይሄዳል:: ስለዚህ ለሁለተኛው አይነት የስኳር ህመምና ለደም ግፊት የመጋለጥ እድላችን ይሰፋል:: የደም መተላለፊያ ቱቦዎቹ እየጠበቡ ሲመጡ ደግሞ የደም ግፊቱ እንደሚከሰት ይሆናል::
አብዝቶ መቀመጥ ለክብደት መጨመር በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ምክንያት ከክብደት መጨመር ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ በርካታ የጤና ችግሮችም መጋለጥ ይኖራል::
ለረዥም ጊዜ ስንቀመጥ ክብደታችን በተወሰኑ የሰውነት ክፍሎቻችን ላይ ብቻ ስለሚያርፍ ያልተስተካከለ የሰውነት ቅርጽ፣ የጀርባና የአከርካሪ አጥንት መጉበጥ፣ የትከሻ መዛነፍ እንደዚሁም የአንገት መጣመም ሊከሰትብን ይችላል::
እነዚህ ሁሉ ችግሮች የሚያሳዩት ብዙ በተቀመጥን ቁጥር የእድሜያችንን ፍፃሜ እያቀረብን መሆኑን ነው:: ስለዚህ ችግሩን ለመቀነስ የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ ይገባል::
በሌላ በኩልም በተለይ በአሁኑ ወቅት በተራዘመ መቀመጥ ምክንያት ሰዎች ለአከርካሪ አጥንት ችግርና ለወገብ ህመም በሰፊው እየተጋለጡ መሆኑ ይነገራል። እነዚህን ሁኔታዎች ለመቀየር ደግሞ አንድ ሰው በሳምንት ያላማቋረጥ ለ 150 ደቂቃዎች ያህል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለበትም ባለሙያዎች እየመከሩ ነው:: በቀን መመገብ ያለብንን 800 ግራም የተመጣጠኑ ምግቦችና አንድ ነጥብ አምስት ሊትር ውሀ መውሰድም መዘንጋት የለበትም::
ሌላው በተለይም በአከርካሪ አጥንታችን ላይ የሚከሰተውን ችግር ለመቀነስ የምንቀመጥበትን ወንበር ምቹ ማድረግ፣ ቀጥ ብሎ መቀመጥ፣ የመሳሳብ ስፖርቶችን ማዘውተር፣ በእግር ጉዞ ማድረግ፣ በስራ ቦታም ቆመንና እየተጓዝን መስራት የምንችላቸው ስራዎች ሲኖሩ መንቀሳቀስ፣ የዮጋ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን ያግዛሉ::
መቀመጥ ይገድላል ብለን ለመነሳታችን ምክንያት የሆነን ደግሞ ባሳለፍነው ሳምንት የተከበረው ዓለም አቀፍ የአከርካሪ አጥንት ቀን ነው። እለቱ “እያንዳንዱ አከርካሪ አጥንት ዋጋ አለው” በሚል መሪ ቃል የተከበረ ሲሆን በተለይም አሁን አሁን በሰዎች ላይ እየተከሰተ ያለው የአከርካሪ አጥንትና የወገብ በሽታ እያሳደረ ያለው ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ችግር ሰፊ ከመሆኑም በላይ ብዙዎች እየተሰቃዩበት ያለ መሆኑን አመላክቷል።
እለቱ መከበር የጀመረው እኤአ በ2008 ሲሆን ዕለቱ በሚከበርበት ጊዜም ሰዎች ስለ አከርካሪ አጥንታቸው ግንዛቤ እንዲኖራቸው እንዲሁም ከአከርካሪ አጥንት ቸግር የሚያድኑት እንዴት ነው? የሚለውን ለማስረዳት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለማስፋት ስለመሆኑም በበዓሉ ላይ ተገልጿል።
ዓለም አቀፉን የአከርካሪ ቀን አስመልክቶ “ስፓይን ሄልዝ ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያ “ ከተለያዩ ተባባሪ አካላት ጋር ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ እንደተገለጸው ድርጅቱ በተለይም የአከርካሪ አጥንት ጉዳት ላይ ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ የሴቶች ና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ትምህርት ሚኒስቴርን በማሳተፍና ከእነሱም እውቅና በማግኘት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመገኘት ልጆች ስለ አከርካሪ አጥንታቸው ጤንነት ግንዛቤ እንዲኖራቸው በተቻለ መጠንም አከርካሪ አጥንታቸውን የሚንከባከቡበትን መንገድ በመጠቆም እየሰራም ስለመሆኑ የድርጅቱ ተወካይ ወይዘሮ ቢኒያም ግርማ በበዓሉ ላይ ተናግረዋል።
ተማሪዎች ጋር በመሄድ ቀላል የሆኑ ስፖርቶችን እንዲሰሩ አተነፋፈሳቸውን አቀማመጣቸው እንዲከታተሉ የማድረግ ስራ እንሰራለን ያሉት ወይዘሮ ቢኒያም ከመገናኛ ብዙሃን ጋርም በመሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ስለ አከርካሪ አጥንቱ በቂ ግንዛቤን እንዲጨብጥ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም አመላክተዋል።
በአከርካሪ አጥንታቸው ላይ ጫና የሚፈጥር ስራን የሚሰሩ ለምሳሌ መካኒኮች፣ በኮንስትራክሽን ስራ ላይ የሚሰማሩ ሰዎች በቀላሉ የአከርካሪ አጥንታቸው ሊጎዳ ስለሚችልና የእነሱ መጎዳት ደግሞ በቤተሰባቸው አለፍ ሲልም በአገር ለይ የሚያደርሰው ኢኮኖሚያዊ ጫና በቀላሉ የሚታይ ስላይደለ ግንዛቤያቸውን የማስፋት ራሳቸውን የሚጠብቁበትን መንገድ የማመቻቸት ስራም እንሰራለን ይላሉ።
ቀኑን ብቻ በማሰብ መዋል የለብንም ያሉት ወይዘሮ ቢኒያም ድርጅቱም አከርካሪ አጥንት ላይ ሲሰራ እንደመቆየቱ በተያዘው ዓመትም እለቱን ከማሰብ በተጨማሪ “ቀጥ በሉ” በሚል መሪ ቃል የተለያዩ ትምህርቶችን እየሰጠ ነው።
እንደ ወይዘሮ ቢኒያም ገለጻ “ቀጥ በሉ” የሚለው መሪ ቃል የተመረጠው የትኛውም ሰው በያለበት ሆኖ ሲሰማው ወይም ሲያነበው ስለ አቀማመጡ እያደረገ ያለውን ነገር ቆም ብሎ እንዲያስብ አልፎም ስለ አከርካሪ አጥንቶች ግንዛቤ እንዲኖር እንዲሁም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ወዲያው እንዲወስዱ ለማድረግ ነው።
በዘርፉ ረጅም ዓመት የሰሩት ካይሮፕራክተር ዶክተር ሰላም አክሊሉ እንደሚሉትም የአከርካሪ አጥንት የመላው የሰውነታችን ጤንነት ምሰሶ ነው፤ በመሆኑም አንድ ሰው ሙሉ ጤነኛ ነኝ ለማለት የሚችለው መጀመሪያ የአከርካሪ አጥንቶቹ አቀማመጥ ትክክለኛ ሲሆኑ ነው። ይህም ሲባል የአንድ ሰው የነርቭ ስርዓት ያለው ከራስ ቅሉ አንስቶ በህብለ ሰረሰርና በአከርካሪ አጥንት መካከል ስለሚያልፍ የሰውነታችን ጤንነት ሙሉ ሊሆን የሚችለው የአከርካሪ አጥንታችን ደህናና አቀማመጡም ትክክል ሲሆን ነው።
ኢትዮጵያውያን በአከርካሪ አጥንታችን ላይ ያለን ግንዛቤ በጣም አናሳ ነው፤ ድሮ ሲጋራ ማጨስ ገዳይ ነው በሚባልበት መጠን መቀመጥ ይገላል እየተባልን ነው፤ ነገር ግን ይህንን ብዙ ሰው አያውቅም የሚሉት ዶክተር ሰላም ይህ ማለት ደግሞ ሰው ተቀምጦ በሚውልበት ጊዜ ከመቀመጥም በላይ ደግሞ አንገት ደፍቶ ስልክና ኮምፒውተር ላይ ሲቆይ የነርቭ ስርዓቱ ላይ ላቅ ያለ እክልን እያመጣ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፤ እክል ብቻም ሳይሆን ደግሞ የአተነፋፈስ፣ የጨጓራ መፍጨትና የአንጀት ስራ የልብ ምት ድረስ የሚደርስ ችግርን እንደሚያስከትልበትም ማወቅ ያስፈልጋል።
እንደ ዶክተር ሰላም ገለጻ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊያውቀው የሚገባው ነገር ቀኑን ሙሉ ስልክ ላይ አቀርቅሮ መዋል ገዳይ መሆኑን ነው። ይህንን በምሳሌ ባስረዳ “ አንድ ሰው ቀጥ ብሎ በቆመ ወይም በተቀመጠ ሰዓት ጭንቅላቱ ብቻ 6 ኪሎ ግራም አካባቢ ይመዝናል፤ አንገቱን 45 ዲግሪ ባጠፈ መጠን ደግሞ የጭንቅላቱ ክብደት አምስት እጥፍ ይሆናል፤ ይህ ክብደት ደግሞ በአንገቱ እንዲሁም በህብለ ሰረሰሩ ላይ በማረፍ ጫና ይፈጥራል፤ “ በመሆኑም ይህንን ተረድቶ ገዳይ የሆነውን መቀመጥን አለማብዛት መቀመጥ ካስፈለገም ቀጥ ብሎ በመቀመጥ ጤናን መጠበቅና ሞትን መቀነስ እንደሚገባም ያስረዳሉ።
በሌለ በኩልም ችግሩ የተከሰተባቸው አብዛኞቹ ሰዎች ከህመማቸው ጋር ነው የሚቀመጡት የሚሉት ዶክተር ሰላም ምናልባት ከተማ አካባቢ ያሉ ሰዎች ለዚያው ጥቂቱ ግንዛቤው ኖሯቸው ወደ ህክምና ተቋም ሊሄዱ ይችላሉ፤ ነገር ግን ከፍ ያለ የስራ ጫና የሚበዛባቸውና ስለ አከርካሪ አጥንት ጤንነት ግንዛቤ የሌላቸው የገጠር ሰዎች፣ በአነስተኛ መጠን የኮንስትራክሽን ስራ የሚሰሩ ሁሉ ከህመሙ ጋር ሊቀመጥ ይገደዳሉ፤ በመሆኑም የግንዛቤውን ደረጃ ማስፋት የባለሙያዎች እንዲሁም የመገናኛ ብዙሀን ስራ ሊሆን ይገባል ይላሉ።
በጤና ጣቢያዎቻችንና ትልልቅ የህክምና ተቋማት በጣም ብዙ ሰዎችን መርዳት የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት የሚሉት ዶክተር ሰላም ለዚህ ደግሞ በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን ማብቃት ያስፈልጋል፤ በተጨማሪም ልጆቻችንን የሚያስተምሩ የስፖርት መምህራን ትልቅ ግብዓት ናቸው፤ በመሆኑም ልጆችን ሲያስተምሩ የአካላቸውን አቀማመጥ፣ የትከሻቸውን፣ የጀርባቸውን መዛነፍ አለው ወይ የለውም የሚለውን ቢያዩልን በቶሎ መፍትሔ ይገኛል ችግሩንም በዛም ልክ መቀነስ ይቻላል ባይ ናቸው።
“የአከርካሪ አጥንት የጤንነታችን መሰረት መሆኑን እንገንዘብ፤ እቃ ስናነሳ፣ ተሸክመን ስንሄድ፣ መምህራን ልጆች በትምህርት ቤት አቀማመጣቸው ምን መምሰል አለበት? የሚሸከሙት ቦርሳ መጠኑ ምን ያህል ሊሆን ይገባል? የሚለውን እባካችሁ ተከታተሉልን፣ መገናኛ ብዙሃን የተጠናከረ ስራን ስሩልን “ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ 1 ቢሊየን ሰዎች በአከርካሪ አጥንት ችግር ይሰቃያል። ከሌላው ዓለም በይበልጥ አፍሪካ ዝቅ ሲል ደግሞ እንደ እኛ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች አራት እጥፍ ነው ችግሩ የሚታይባቸው።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2015