አዲስ አበባ፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት የሚመሩት የቦርድ አባላት ቋሚ ባለመሆናቸው የአሰራር ክፍተት እንዳለበት በቦርዱ አሰራር ዙሪያ የተካሄደ ጥናት አመለከተ። በሲቪል ሰርቪስ ተደራጅቶ ኮሚሽን መሆን እንዳለበትም ሀሳብ ቀርቧል፡፡
በኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አዋጅ ቁጥር 532/1999ዓ.ም እና ተያያዥነት ያላቸው ሕጎች ላይ በመወያየት ግብዓት ለመሰብሰብ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት በኢንተርኮንቲኔ ንታል ሆቴል ባካሄደው ውይይት ላይ፣ ቦርዱን በሚመሩት 9ኙ አባላት ቋሚ አመራሮች ካለመሆናቸው በተጨማሪ በመካከላቸውም የመጠባበቅና የስልጣን ግጭት የሚፈጠርበት አጋጣሚ እንደነበር ጥናቱ አመላክቷል፡፡በዚህም በአሰራሩ ላይ ከፍተት እንደነበረው ተገልጿል፡፡
የጥናት ማብራሪያውን ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት መምህር ዶክተር ሲሳይ አለማየሁ እንዳስረዱት፣ የቦርድ አባላት በሙያ ብቃታቸው፣ በገለልተኝነት፣ በስነምግባራቸውና ለህገመንግሥት ያላቸው ታማኝነት በሚል መስፈርት እንዲመረጡና እንዲሾሙ ቢደረግም የመመልመያና የሹመት አሰጣጡ መስፈርቱ ጥቅል በመሆኑም ግልጽነት ይጎድለዋል፡፡ በአጠቃላይ የቦርዱ ስልጣንና ተግባር የበጀት ጉዳይ ግልጽ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡
ዶክተር ሲሳይ የነበሩትን ክፍተቶች ለይቶ በቀጣይ የቦርዱ አጠቃላይ ስልጣንና ተግባር ምን መሆን እንዳለበት፣በቦርዱና በጽህፈት ቤቱ መካከል ያለው ግንኙነትና የስልጣን ክፍፍል፣ እንዲሁም ቦርዱ በጀት እንዲኖረው፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች አመላመልና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ለተሳታፊዎች ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ ጋር በማጣቀስ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫኔ ከበደ በሰጡት አስተያየት ዘላቂ የሆነ የምርጫ ስርዓት ለመዘርጋት እንደ አንድ ሲቪል ሰርቪስ ተቋም መደራጀት እና ኮሚሽን መሆን እንዳለበት ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ህብረት ፕሬዚዳንት አቶ ገብሩ በርሄ በበኩላቸው አሁን ያለውን የቦርዱ ግልጽ ያልሆነ አሰራር ለማስቀረትና አሰራሩ ጉልበት እንዲኖረው አደረጃጀቱ በኮሚሽን መሆን እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ አስተያየት ሰጭዎቹ በአሰራሩ ዙሪያ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ መዘጋጀቱንም አድንቀዋል፡፡
የግብዓት መሰብሰቢያ መድረክ ቀጣይነት እንዳለውና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም ውይይት እንደሚካሄድ ከመርሐግብሩ ለመረዳት ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2011
በለምለም መንግስቱ