የየትኛውም አትሌት ዓላማ እና ህልም በሚወዳደርበት ርቀት በትልልቅ መድረኮች ተሳትፎ ውጤታማ መሆን ነው። አሸናፊነቱ በኦሊምፒክ እና በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አሊያም በሌሎች ቻምፒዮናዎች ሲሆን ደግሞ ከራስ ስም በላይ አገርንም የሚያኮራ በመሆኑ ክብሩ ድርብ ይሆናል። ከሁሉም የሚልቀው ግን የአትሌቱ አሸናፊነት በዓለም ደረጃ እውቅና አግኝቶ የዓመቱ ምርጥ አትሌት ሲሰኝ ነው። ይህ እድል ደግሞ ብዙዎቹ የሚቀዳጁት ሳይሆን እጅግ ጠንካራዎች የሚያሳኩት ነው።
ዓለምን ባስደመሙ ምርጥ አትሌቶቿ የምትታወቀው የሯጮቹ ምድር ኢትዮጵያም በተካፈሉበት ውድድሮች ብቻም ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጥር አንድ የተሰኙ አትሌቶቸ በርካታ ናቸው። እአአ ከ1988 ጀምሮ በየዓመቱ በዓለም አትሌቲክስ አማካኝነት የሚያካሂደውንና በአትሌቲክስ ቤተሰቡ ድምጽ የሚሰጥበትን የዓመቱ ምርጥ አትሌት ሽልማት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ረገድ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ሽልማት አሸናፊ የሆነው ጀግናው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ነው። አትሌቱ አሸናፊ የሆነበት ውድድር ደግሞ እአአ በ1998ቱ ነው። እአአ በ2004 እና 2005 ደግሞ ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በተከታታይ አሸናፊ በመሆን ታሪካዊ አትሌትነቱን አረጋግጧል።
በሴቶች በኩል እአአ በ2007 ምርጥ አትሌት የተባለችው አትሌት መሰረት ደፋር ነበረች። እአአ በ2015 እና 2016 ደግሞ ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና የምርጥ አትሌትነት ምርጫው ኢትዮጵያ ላይ እንዲያርፍ ያደረጉ አትሌቶች ናቸው። ዘግይቶ በተጀመረው የምርጥ ተስፈኛ አትሌቶች ምርጫም ወጣቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ እአአ በ2019 ተሸላሚ ለመሆን ችሎ ነበር። ይሁንና ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸናፊዎች ብቻም ሳይሆን እጩ ውስጥ የመግባት እድላቸው እየተመናመነ ሲሄድ ታይቷል። የዘንድሮው ዓመት (2022) የምርጥ አትሌቶች ዝርዝር ላይም 20 አትሌቶች በእጩነት በሁለቱም ጾታ ቀርበዋል። ይሁንና በዝርዝሮቹ ውስጥ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አልተካተቱም። ይህም አትሌቲክስ መታወቂያዋ ከሆነው ኢትዮጵያ ብዙዎች የሚጠብቁት አይደለም።
እየተገባደደ በሚገኘው የፈረንጆቹ ዓመት ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ የተሻለ ስኬታማ የሚባል ነበር። ምክንያቱ ደግሞ በዓመቱ ከተካሄዱት ታላላቅ ቻምፒዮናዎች ማለትም የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና እንዲሁም በአሜሪካዋ ኦሪጎን የተደረገው የአትሌቲክስ ዓለም ቻምፒዮና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመሪነት በማጠናቀቁ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በርካታ አትሌቶች በዳይመንድ ሊጎች እና ሌሎች የግል ውድድሮች ላይ በመካፈል እንደተለመደው ውጤታማ ዓመት ነበር ያሳለፉት። የዓለም አትሌቲክስ እጩዎቹን ይፉ ሲያደርግም በዓመቱ ዋና ዋና በሚባሉ ውድድሮች ላይ ያስመዘገቡትን ውጤት መሰረት በማድረግ ነው። ታዲያ በእነዚህ ቻምፒዮናዎች ስኬታማ የነበሩት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለምን ሳይካተቱ ቀሩ የሚለው ጥያቄ የበርካቶች ነው።
ለአብነት ያህል በቤልግሬድ በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ከዓለም አንደኛ በመሆን ነበር ያጠናቀቀችው። ከተመዘገቡት የወርቅ ሜዳሊያዎች መካከልም አንድ ሜዳሊያ በአትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ነበር የተገኘው። አትሌቷ ከወራት በኋላ በተካሄደውና ኢትዮጵያ ከዓለም ሁለተኛ በሆነችበት የኦሪጎኑ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ደግሞ በ5ሺ ሜትር የወርቅ እንዲሁም በ1ሺ500 ሜትር የብር ሜዳሊያዎችን ነበር ያጠለቀችው። አትሌቷ በሌቪን እንዲሁም በቤት ውስጥ የቱር ውድድር ድንቅ ብቃቷን ያሳየችበት የዓመቱ ውድድር ነበር። ዳመንድ ሊግ ላይም እስከመጨረሻው መጓዝ የቻለችና ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ሲሰጣት የቆየችም አትሌት ናት። ይሁንና ይህቺ አትሌት ከእጩዎቹ አንዷ ልትሆን አልቻለችም።
ይህ ጉዳይ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይም የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች ምርጫ ዝርዝር ውስጥ የሚካፈሉ አትሌቶች፤ በአትሌቲክስ ማለትም ረጅም፣ መካከለኛ እና አጭር ርቀት የመም፣ የሜዳ ተግባራት እንዲሁም የጎዳና ላይ ሩጫ ላይ የተካፈሉ አትሌቶች ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እየታየ ያለው በእጩነት ከሚቀርቡት አትሌቶች መካከል አብዛኛዎቹ የአጭር እና መካከለኛ ርቀት አትሌቶች እንዲሁም የሜዳ ተግባራት አትሌቶች ናቸው። የረጅም ርቀት የመም አትሌቶች በምርጫው እምብዛም የማይካተቱ ሲሆን፤ ጥቂት የጎዳና ላይ ሯጮች ብቻ በእጩነት ውስጥ እንደሚገቡ በግልጽ የሚታይ ነው። ይህ ደግሞ ምዕራባዊያን ለራሳቸው ከሚሰጡት ስፍራ የተነሳ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ይስማማሉ።
ብርሀን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11 ቀን 2015