በስፔን ከሚካሄዱ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች መካከል የቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው። የዓለም አትሌቲክስ ለዚህ የጎዳና ላይ ውድድር እአአ በ2016 የወርቅ ደረጃ የሰጠው ሲሆን፤ በዓለም ላይ ‹‹ሱፐር ሃፍስ›› ከሚባሉት መሰል ታላላቅ የግማሽ ማራቶን ውድድሮች(ሊዝበን፣ ፕራግ፣ ኮፐንሃገን እና ካርዲፍ የግማሽ ማራቶን ሩጫዎች) ጎን የሚሰለፍም ነው። በዚህም ምክንያት የዓለም የግማሽ ማራቶን ቻምፒዮናን ለማካሄድም ቫሌንሲያ ተመራጭ ሊሆን ችሏል።
በውብና በበርካታ ስነህንጻ ባማረችው ቫሌንሲያ ከተማ የሚካሄደው ይህ ውድድር በታላላቅና ዝነኛ የጎዳና ላይ ሯጮችም ተመራጭ ነው። ተመራጭ የሆነበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ፈጣን ሰአት የሚመዘገብበት ውድድር በመሆኑ ነው። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ በሴቶች የዓለም ግማሽ ማራቶን ክብረወሰን የተመዘገበው በዚህ ውድድር በመሆኑ ነው። ይህም በኢትዮጵያዊቷ ጠንካራ አትሌት ለተሰንበት ግደይ የተመዘገበ ሲሆን፤ አትሌቷ ባለፈው ዓመት ርቀቱን ስታሸንፍ 1:02:52 ሰዓት ማስመዝገቧ ይታወሳል። ኬንያዊው ኪቢዎት ካንዳይ ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት 57፡ 32 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ የአለምን ክብረወሰን መስበር ችሎ ነበር። በዘንድሮው ውድድርም በሁለቱም ጾታዎች ፈጣን ሰዓት እንደሚመዘገብ ይጠበቃል።
የዚህ ዓመቱ የቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶንም በመጪው እሁድ የሚካሄድ ሲሆን፤ እንደተለመደው በርቀቱ ጠንካራ የሆኑና ፈጣን ሰዓት ያላቸው አትሌቶች ተሳታፊዎች ይሆናሉ። ከእነዚህ አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም በሁለቱም ጾታ ተሳታፊዎች መሆናቸው ተረጋግጧል። ይሁንና በወንዶች በኩል የቦታው ባለፈጣን ሰዓት ባለቤቱ ካንዳይ ዘንድሮም የውድድሩ ተሳታፊ መሆኑ እንዲሁም ሌሎች ፈጣን ሰዓት ያላቸው የሃገሩ ልጆችም የሩጫው ተካፋይነታቸውን ማረጋገጣቸው ውድድሩን ከባድ ሊያደርገው እንደሚችል ይጠበቃል።
ጠንካራ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም ከተፎካካሪነት በዘለለ ከፍተኛ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት የተሰጣቸው ሆነዋል። አትሌት ሚልኬሳ መንገሻ በርቀቱ ባለው ፈጣን ሰዓት ቀዳሚው የአሸናፊነት ግምት ከተሰጣቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንዱ ነው። የ22 ዓመቱ ወጣት በዓመቱ በርካታ ውድድሮች ላይ የተሳተፈ ሲሆን፤ በሂውስተን እና ኮፐንሃገን ግማሽ ማራቶኖች ላይም ሮጧል። ባለፈው ወር በተካሄደው የኮፐንሃገን ግማሽ ማራቶን ተወዳድሮም 58:58 የሆነ የግሉን ፈጣን ሰዓት ሊያስመዘግብ ችሏል።
ሌላኛው በመም የረጅም ርቀት ውድድሮች በተለይ የሚታወቀው ኢትዮጵያዊ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻም በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ከሚጠበቁት አትሌቶች መካከል ነው። ዮሚፍ በቅርቡ በጎዳና ላይ ሩጫ አይታይ እንጂ እአአ በ2019 የቫሌንሲያ ማራቶንን በመሮጥ አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው። በወቅቱ የገባበት 59፡05 የሆነ ሰዓት ደግሞ አትሌቱ በርቀቱ ያለው ፈጣን ሰዓት ነው። በመሆኑም አትሌቱ ጠንካራ ተፎካካሪ ብቻም ሳይሆን አሸናፊ የመሆን እድሉ የሰፋ እንደሚሆንም ተገምቷል። ታደሰ ወርቁም በዚህ ውድድር የሚካፈል ኢትዮጵያዊ አትሌት መሆኑ ታውቋል።
በሴቶች በኩል ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ያለፉትን አራት ዓመታት በተከታታይ አሸናፊዎች ነበሩ። ዘንድሮ የውድድሩ ተሳታፊነታቸውን ያረጋገጡ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች እንደተለመደው አሸናፊዎች ሊሆኑ እንደሚችሉም ተገምቷል። ከእነዚህም መካከል ቀዳሚዋ አትሌት ሃዊ ፈይሳ ናት። በኮፐንሃገን፣ ባህሬን እና በቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን በመሮጥ ልምድ ያላት ይህች አትሌት፤ ባለፈው ዓመት በኮፐንሃገን ግማሽ ማራቶን ያስመዘገበችው 1ሰዓት ከ05ደቂቃ ከ41 ሰከንድ የግሏ ፈጣን ሰዓት ነው። ይህ ሰዓት አብረዋት በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉት አትሌቶች በሰከንዶች ብቻ የዘገየ ቢሆንም ጠንካራ የአሸናፊነት ፉክክር እንደምታደርግ ይጠበቃል።
በአምስት ሰከንዶች ብቻ ከሃዊ የዘገየ ሰዓት ያላት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ቦሰና ሙላቴም የዚህ ውድድር ተካፋይ ናት። በዚህ ዓመት የኮፐንሃገን ግማሽ ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀችው ሌላኛዋ አትሌት ጽጌ ገብረሰላማም የቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን ተካፋይ ናት። አትሌት እታገኝ ወርቁም በተመሳሳይ የውድድሩ ተፎካካሪ ይሆናሉ በሚል ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል አንዷ ሆናለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2015