እነ ዘውዴ መታፈሪያ፣ ተሰማ መንግስቴ እና ገብረየስ ገብረማሪያም ደስታ በደስታ ሆነዋል። በተለይ የገብረየስ መሳጭ ንግግር የተሰማን እና የዘውዴን አንጀት እያራሰ እርስ በእርስ በስሜት እያስተሳሰራቸው ይገኛል። ገብረየስ በበኩሉ ተሰማ እና ዘውዴ እርሱን ከማዳመጥ አልፈው ቃላቱን እያመኑበት መስማማታቸውና ቆመው በጭብጨባ መግለፃቸው አየር ላይ እየተንሳፈፈ ያለ እንዲመስለው አደረገ። በዓይኑ እምባ ሞላ።
‹‹ የትግራይ ሕዝብ እኮ ዛሬ ጉልቻ የራቀው አመድ ያጠለቀው የተበደለ ችግር ያንገላታው፤ ድጋፍ ያጣ ነው። ለእዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ የእነ ደብረፂዎን ሴራ እና እብሪት ነው። የትግራይ ሕዝብ ከለውጥ በኋላም ያርስ ነበር፤ ተማሪው ይማር ነበር። ነጋዴው ይነግድ ነበር። ባንክ፣ ቴሌ መብራት ነበረው። ጥጋበኛው ትህነግ ሰሜን ዕዝን ከጀርባወ በመውጋት ጦርነት ጀምሮ ወደ ሌሎች ክልሎች አስፋፋ። ዶሮ ብታልም ጥሬዋን ነውና የትግራይ ሕዝብም የአሸባሪውን ቡድን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሰምቶ እና ተታሎ ‹አሸባሪው ሕወሃትና የፌዴራል መንግስት ጠበኞች ናቸው ፊት አዟዙረዋል፤ ተጣልተዋል› ብሎ በማመን ነገሩን በስፋትና በጥልቀት ሳይመረምር የቅርቡ ላይ ብቻ በማተኮር ተታለለ። ›› በማለት ገብረየስ ስለትግራይ ሕዝብ እያሰበ እንባው ፈሰሰ። ሁሉም ፀጥ ብለው ፈዘዙ። ተሰማ አይዞህ በሚል ስሜት የገብረየስን ጀርባ አሻሽቶ ቸብ ቸብ አደረገው።
ዘውዴም በበኩሉ ለገብረየስ ‹‹አይዞህ ያለፈው አልፏል። ያለውን መቀበል ነው። ወንድም በወንድሙ ላይ አይጨክንም፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። ከዚም ከዚያም ሁሉም ተጎድቷል። ብዙ ኢትዮጵያውያን ሞተዋል። ከሥልጣን በፊት አገርና ሕዝብ ማስቀደም ያቃታቸው በገሃዱ ዓለም ሲቃዡ የኖሩ ትህነጎች ኢትዮጵያ ላይ ፈልተው ኢትዮጵያን ነቀዝ ሆነው ቦርቡረዋታል። በድህነትና በኋላቀርነት በምትማቅቅ አገር ላይ ጦርነት በማወጅ ተጨማሪ ውድቀት እንዲኖር ምክንያት ሆነዋል። ልክ ከ30 ዓመት በፊት ሥልጣን በአጋጣሚ እጃቸው ሲገባ ኢትዮጵያውያንን በጠላትነት እየፈረጁ ሲያስሩ፣ ሲያሰቃይ፣ ሲያሳድዱና ሲገድሉ እንደኖሩት ሁሉ አሁን ደግሞ የትግራይ ሕዝብን ምሽግ አድርገው ተጫወተውበታል።
መደበቃቸው እና ሕዝብ ውስጥ ተሸሽገው ጦርነት መክፈታቸው በ27 ዓመት በስልጣን ዘመናቸው ከመንግሥታዊ ተቋማት በቢሊዮን የሚቆጠር ሃብትን የመዝረፍ ተግባራቸውን ለማስቀጠል ነበር። ያም አልሆን፤ ካልሆነላቸው ደግሞ ከገደሉትና ከዘረፉት ሕዝብ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ ነበር። ሆኖም እንዳሰቡት አልሆነም። እንደውም ሥራቸው በጥፋት ላይ ጥፋት ሆነ። ያለፈውን ጥፋት ሕግ ፊት ቀርበው ፍርዳቸውን መቀበል ሲገባቸው በበለጠ መልኩ እጃቸው በንፁኃን ደም አጨማለቁት። ከሕግ ለማምለጥ ሲሉ የትግራይ ሕዝብ ውስጥ ተደብቀው ጦርነት ከፈቱ። የአገር አለኝታ የሆነውን መከላከያን አጠቁ።
መንግስት ሕዝብ ከሚያልቅ ሕግ ማስከበር ይዘግይ ሲል፤ በአገር ውስጥ በሌሎች አካባቢዎች ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት እንዲሰፍን የተቻላቸውን ሁሉ ሰሩ። ያም አልሳካ ቢላቸው፤ ሌላ አካል ያወደማቸው ያጠቃቸው የከበባቸው አስመስለው ተበዳይ መስለው የትግራይነትን ጭምብል በማጥለቅ በደም መነገዳቸውን ቀጠሉ። ወረራቸውን አጧጧፉ። የትግራይን ሕዝብ አታለው ከገዛ ወንድሙ ጋር አጋደሉት።›› በማለት ዘውዴ ትህነግ ምን ያህል በትግራይ ሕዝብ እየነገደ እና ከገዛ ወንድሞቹ ጋር እያናከሰው እንደሆነ ገለፀ።
ተሰማ የፌዝ ሳቅ እየሳቀና ፈገግ እያለ፡ ‹‹አሸባሪው ትህነግ መሠረቱ ውሸት ነው። ውሸቱን ለማሳመን የማይቆፍረው ጉድጓድ የለም። ዓላማውን ለማስፈጸም የሚጠቀመውን ውሸት በእውነትን በመተካት ትግራይም ሆነች መላው ኢትዮጵያ የሴረኛው የትሕነግ መጫወቻ እና መፈንጫ እንዳንሆን ጥረት ማድረግ አለብን። መሸወድ የሌለብን አሁን ላይ ትህነግ መሀረብ ዘርግቶ እያለቀሰ ነው። ምንም ነገር ለመፈፀም ጥንካሬ የለውም።
ነገር ግን የትግራይን የድሃ ልጅ እየማገደ የራሱን ቤተሰብ አውሮፖና አሜሪካ አስቀምጦ ዛሬም የትግራይን ሕዝብን መደበቂያ በማድረግ እንደተራ የብረት መሳሪያ እንደባሪያ እየተጠቀመበት ነው። ጥንታዊ የጦርነት ዘይቤ በመከተል በሠው ማዕበል በመዋጋት ሕዝብ እያስጨረሰ ትውልድ እንዲነጥፍ ምክንያት በመሆን ላይ ያገኛል። የተለያዩ የመረጃ ተቋማት እንደሚያሳዩት አሸባሪው ትህነግ ጦርነቱን እንዲገፋበት ከአንድ አገር ሁለት ሚሊዮን ዶላር እንደተበረከተለትና በየ 45 ቀኑም 500 ሺ ዶላር ድጋፍ ሲደርግለት እንደቆየ ምስጢራዊ ሰነዶች እያረጋገጡ ነው።
ይህ ከውጪ ጠላት ጋር አብሮ ኢትዮጵያን ለመጣል እየተጋ ያለ ምስጥ በሕዝብ መሸነፉ እና በድጋሚ ላይነሳ መቀመቅ መውረዱ አይቀርም።›› በማለት የሽብር ቡድኑ አቅም እንደሌለው ሳይወድ በግድ ሽንፈቱን እያረጋገጠ መምጣቱን አይተነዋል። እሱ ግን በኢትዮጵያ ጠላቶች እየታገዘ መሆኑን ተናግሮ በረዥሙ ተነፈሰ።
ዘውዴ ከተሰማ ቀጠል አድርጎ ‹‹ ይህንን የኢትዮጵያ ጠላት ‹ጤፍ አጋደለ› ቢለው ‹ገብስ እንዳይሰማ› እንደተባለው የእርሱ መጥፎ አርአያነት ወደ ሌላው እንዳይዛመት ቀጥቅጦ ሕግ ፊት ማቅረብ እና የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። አገር ውስጥ ሲፈፀም የነበረው ግፍ በሙሉ ለማመን ቢያስቸግርም ብዙሃኑ በእርሱ ሴራ በተጠረገ የክፋት መንገድ የተካሔደ ስለመሆኑ አያጠራጥርም። ዜጎች ማንነታቸው እየተለየ ሲጨፈጨፉና የተረፉት ሲፈናቀሉ የነበረው እርሱ ከውጪ ጠላት ጋር በነበረው ትስስር እና ባገኘው ድጋፍ ተመስርቶ እንዲሁም በስልጣን ዘመኑ የነበረ ኔትወርኩን ተጠቅሞ ነበር።
በዛ ጭፍጨፋ፣ በዛ መፈናቀልና ዘረፋ የትግራይ ሕዝብ በምንም መልኩ ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል የለም። እንደውም ከተጠቃሚነቱ ይልቅ ተጎጂነቱ እንደሚያመዝን አያጠራጥርም። በሴራ ፖለቲካ የተካኑ፤ የሚፈልጉትን ዓላማ ለማሳካትና አገር እስከማፍረስ የወጠኑት የአሸባሪው ትህነግ አባላት በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችንና ጭፍጨፋዎች እንዲፈፀሙ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሲጭሩ የነበረው እሳት ወላፈኑ ቢያንስ በስነልቦና ደረጃ የትግራይ ተወላጅን ሲያስጨንቅ ነበር።
እነዚህ በትግራይ ሕዝብ ላይ፣ በአማራ ሕዝብ ላይ፣ በአፋር ሕዝብ ላይ፣ በኦሮሞ ሕዝብ ላይና በሌላውም ሕዝብ ላይ በአጠቃላይ በኢትዮጵያውያን ላይ መከራን እንደዝናብ ያዘነበው የእፉኝት ልጆች የእነርሱ ክህደት ወደሌላው እንዳይጋባ መቀጣጫ እንዲሆኑ እስከጫፍ ድረስ መቀጣት አለባቸው።›› ሲል በምሬት ትህነጎች ሲሰሩ የነበረውንና ክፋታቸውን በመዘርዘር ቅጣት ይገባቸዋል ሲል ደመደመ።
ገብረየስ ተሰማ እስኪናገር አልጠበቀም። ይልቁኑ እርሱም የሚያምንበትን ለመናገር ጉሮሮውን ጠራረገ። ‹‹ በእኔ እምነት ምንጊዜም ቢሆን እውነት ያሸንፋል። ፈጣሪ ከበጎ ሰሪዎች ጎን ነው። ክፉ ሰሪ ቀኑን ይጠብቃል እንጂ የገዛ ሥራው ጠልፎ እንደሚጥለው ማረጋገጫው አሸባሪው ትህነግ ነው። አሁን ‹ገዳይ ሲያረፋፍድ ሟች ይገሰግሳል› ሆኗል። ሕዝብ ተደግፎ በዛው ሕዝብ ላይ መጫወት በራስ ላይ አደጋ መጋበዝ ነው። አሸባሪው ትህነግ እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው። ሕዝብ ተደግፈው በዛው ሕዝብ ላይ መቀለዳቸውን አላቆሙም። አሁንም ድረስ ቁማራቸውን እንደቆመሩ ነው። በነፍስ ላይ ቁማር በመጫወት ሃሳብ ናውዘዋል። ተበላን ብለው አያስቡም። ንብረቱን ጨርሶ ሚስቱን ለቁማር ሲል ለመሸጥ እንደተዘጋጀ ነፈዝ ሱሰኛ አባወራ በደመነፍስ በሱስ ውስጥ ሆነው እየገሰገሱ ነው።›› አለ።
ተሰማ በመገረም መንፈስ፤ ‹‹ አንዳንድ ሰው በራሱ በቀላሉ ከችግር ማምለጥ ሲችል ራሱን እና ሌላውንም ችግር ውስጥ በመክተት የባሰ ከችግር የመውጫ መንገዱን የበለጠ ያወሳስበዋል። በራሱ ላይ ይቆልፋል። መውጫ በሚያሳጣ መልኩ በራሱ ላይ ቁልፉን ያጠብቀዋል። ሌሎች ደግሞ ይህ እንዳይፈጠር ከመሞከር ይልቅ አብረው መሳሪያ ይሆናሉ። ከዚያም አብረው ይታሰራሉ። እነርሱም ራሳቸው ላይ በተመሳሳይ መልኩ ይቆልፋሉ። የትህነጎች ላቅ ይላል። ጥቂቶች ቢሆኑም ብዙሃኑ ሕዝብ ላይ ቆልፈዋል።
የአሸባሪው ትህነግ ቡድን ሕዝቡ እንዲሰቃይ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። ህዝቡ በሌላው ኢትዮጵያዊ እንዲጠላ ብዙ ሰርተዋል። በግጭት አድገው ከግጭት ውጪ ማሰብ የተሳናቸው መሆኑን በግልፅ አሳይተዋል። ሰው እያፈሱ ጦርነት ውስጥ መማገድ መደበኛ ሥራቸው ሆኗል። በጦርነቱ ከተገደለው በላይ በትህነግ አፈሣ በማስገደድ የታጠቀውን የራሳቸውን ሠራዊት ሸሽተሃል በሚል ራሳቸው እየረሸኑ በብዙ ሺህ ጨርሷል።›› ሲል የገብረየስን ሃሳብ በመደገፍ ትህነጎች በራሳቸውም ሆነ በተለይ በትግራይ ሕዝብ ላይ ምን ያህል ነገሮችን እንዳወሳሰቡ ለመግለፅ ሞከረ።
ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹ጥንቃቄን ከዕድለ ቢሱ ይማሩታል፤ በእርግጥም ከእነዚህ በደንብ መማር ያስፈልጋል። በአንዱ ላይ የታየው መጥፎ ነገር ለሌላው ትምህርት ይሆናል። በስልጣን ላይ ሆኖ መንደላቀቅ ሕዝብ እስከፈቀደበት ቀን ብቻ ነው። ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ደግሞ ቢያንስ እንደማንኛውም ተራ ሕዝብ ለመኖር ራስን ማዘጋጀት እና ላጠፉት ጥፋትም ሃላፊነት ወስዶ ቅጣትን መቀበል ይሻላል። በእኛ ውብ ባህልም የቅርታም እኮ ነበር። እሱንም ለመቀበል ዝግጁ አይደሉም እንጂ። ከዛ ውጪ ከሕዝብ አመልጣለሁ ብሎ ሴራ መጎንጎንም ሆነ ከውጪ ጠላት ጋር እስከ ማበር የደረሰ የአገር ክህደት መፈፀም፤ ከምንም አያስመልጥም። ይልቁኑ የመኖሪያ እና ምህረት የማግኛ ጊዜን ሙሉ ለሙሉ ማጣት ነው።
ትህነጎች እስከ አሁን ያጠፉት ለመቁጠር ያዳግታል። የኢትዮጵያን ህልውና በመፈታተን እስከሚችሉት ድረስ ሞክረዋል። በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይሰፍን ሰማይ እስከመቧጠጥ ለመድረስ ከአቅማቸው በላይ ተንጠራርተዋል። ነገር ግን አልሆነላቸውም። ይህ ህልማቸው ቅዠት መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ አረጋግጦታል። ገሚሶቹ በዛው በበረሃ ሲሸሹ እንደሞቱት ሁሉ፤ አሁንም ሆነ ወደፊት ቀን ሲደርስ እያንዳንዳቸው የአሸባሪው ትህነግ አባላት የትም ሜዳ እንደሚበተኑ አልጠራጠርም።›› ብሎ በንግግራቸው መሃል ረስተውት የቆዩትን ከተቀዳ የቆየው ድራፍት ተጎነጨ።
ገብረየስ ‹‹በዋናነት እንድትዘነጉት የማልፈልገው ግን›› አለ። ቀጠለና ‹‹ገመድ ቢበጠስ መቀጠል፤ አባይ መስካሪን ወደ ገደል ነው። የትግራይ ሕዝብ ብዙሃኑ በተለይ አሁን ትህነግን ተቀብሎ ሳይሆን አማራጭ አጥቶ ነው። አማራጭ ያጣ ሕዝብ መሆኑን፤ በትህነግ ተገዶ ለጦርነት መሰለፉን፣ ማወቅ ተገቢ ነው። እኔ አሁን የሚያሳስበኝ የትግራይ ሕዝብ ጉዳይ ነው። ትህነጎች የተሸነፉት በሕዝብ ተደግፈው ሕዝብን በሸጡበት ቀን ነው። አሁን ጫፍ ላይ ደርሰዋል። በእርግጥም እነርሱ እንዲሞቱ አይደለም፤ መቀጣጫ እንዲሆኑ ለፍርድ እንዲቀርቡ መንግሥትም ሆነ አገር ወዳድ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ምኞቱ መሆኑ ትክክል እና ተገቢ ነው። እንኳን እንደ አሸባሪው ትህነግ አይነቱን አገር ከጂ ቀርቶ ማንኛውንም የጥፋት ፀባይ ተጠቂ በህግ መቅጣት ተገቢ ነው። ባለ ክፉ ፀባይ አሸባሪው ትህነግን ማስተማር ይገባል።
ነገር ግን ድህነት ያመሳቀላቸው ለግል ሥልጣንና ጥቅማ ጥቅም ሲል አሸባሪው ትህነግ የተጫወተባቸው የትግራይ ተወላጆችን ላይ ጨፌ ተቃጠለ እንደሚል ወሬኛ ያልሆነ የሆነውን በማውራት ከገበታ ከማራቅ ይልቅ ተጠግቶ፤ እነርሱም ከማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለዩ አለመሆናቸውን፤ ሌላው ህዝብ አሸባሪው ትህነግን እንጂ ከትግራይ ህዝብ ጋር ምንም ዓይነት የጠላትነት ስሜት የሌለው ስለመሆኑ መግለፅ ያስፈልጋል። ምክንያቱም አሸባሪው ትህነግ ቢጠፋ እንኳ ዘርቶት የሚሔደው ክፋት እና እስከ አሁንም በትግራይ ሕዝብ አዕምሮ ውስጥ ክፋትን ለማተም ሲል ሲሰራ የነበረው ፕሮፖጋንዳ ቀላል ባለመሆኑ በዚህ ላይ ከወዲሁ ማሰብ ያስፈልጋል።›› አለ።
ዘውዴ ‹‹ ትክክል ነው። ከዚህ በኋላ ሁሉም አንድ ሕዝብ ነው። ለኢትዮጵያ አንዱ ባለቤት እየሆነ ሌላው ባይተዋር የሚሆንበት ጊዜ ያበቃል። ሕዝብ ለዛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ገራገር ነው። እርስ በእርሱ ይቅር ተባብሎ፤ ተጫውቶ ተስማምቶ መኖሩ አይቀርም። ዋናው ነገር ከዚህም በኋላ ማንም ቢሆን ቂምና ተንኮልን በማስወገድ ደግ ሆኖ ቤተሰቡን እና አገሩን መምራት አለበት። የትግራይ ሕዝብማ የት ይሔዳል ያው ወንድማችን ነው። ቀን ሲያልፍ አብረን ተቃቅፈን ማዕድ መጋራታችን አይቀርም። ይህ ቀን ሩቅ እንደማይሆን እርግጠኛ ነኝ።›› ሲል የዕለቱን ጨዋታቸውን አብቅተው። ሁሉም ከመጠጥ ቤቱ ለመውጣት አኮበኮቡ። ዘውዴ ሰውነቱን እያንጠራራ በመጨረሻ ‹‹ የአሸባሪው ትህነግ መዋረጃው ተቃርቧል›› ሲል ተናገረ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2015